‹‹ሰዎች እንዲያስታውሱኝ የምፈልገው የዓለም ከባድ ሚዛን ሻምፒዮና እንደሆነ ጥቁር ሰው ነው፡፡ ሳቂታ፣ ሰውን ሁሉ በትክክለኛ መንገድ ያስተናገደና ማንንም የማይንቅ ሰው ሆኜ መታወስ እፈልጋለሁ፡፡ የእኔ የምላቸው ሰዎችን መርዳት የምችለውን ያህል በገንዘብም ይሁን በነፃነት፣ በእኩልነትና በፍትሐዊነት ትግላቸው የረዳሁ ሰው እንደሆንኩ እንድታወስም እሻለሁ፡፡ የእኔ የምላቸውን ሰዎች ያከበርኩ፣ ክብራቸውን ያልነካሁ፣ ክቡሩን ኤሊያህ መሐመድ በመስማትና በእስልምና እምነት አንድነትን ለመፍጠር የሞከርኩ ሰው ሆኜ ብታወስ እመርጣለሁ፡፡ በዚህ ሁሉ ለመታወስ መጠየቄ ብዙ ከሆነ፣ ለሕዝቦቹ አሸናፊና አስተማሪ እንደሆነ ታላቅ ቦክሰኛ ብታወስም መልካም ነው፡፡ ምን ያህል ግሩም እንደነበርኩ ሰዎች ቢዘነጉም የምከፋ አይመስለኝም፡፡››
ዓርብ ግንቦት 26 ቀን 2008 ዓ.ም. በ74 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ጥቁር አሜሪካዊው ዝነኛው ቦክሰኛ መሐመድ አሊ ከአንድ መጽሔት ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ‹‹ሰዎች እንዴትና በምን መልኩ እንዲያስታውሱህ ትፈልጋለህ?›› የሚል ጥያቄ ቀርቦለት የመለሰው መልስ ነው፡፡ መሐመድ አሊ የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ተወዳጅ፣ እጅግ ታዋቂና አነጋጋሪ ስፖርተኛ ከመሆኑ ባሻገር በጥቁር ሕዝቦች ሰብአዊ መብት ንቅናቄ አቀንቃኝነቱ ይታወቅ ነበር፡፡ የቀድሞው የዓለም ከባድ ሚዛን ቦክስ ሻምፒዮኑ መሐመድ አሊ (በቀድሞው መጠርያው ካስየስ ክሌይ) ሥርዓተ ቀብር ዓርብ ሰኔ 3 ቀን 2008 ዓ.ም. እንደሚፈጸም ታውቋል፡፡