ቀልጣፋና ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጥ ከተፈለገ ከሁሉም ሐኪሞች መሀከል ሻል ያለ አቅም ያላቸው በሜዲካል ዳይሬክተርነትና በኮሌጅ አመራር ላይ መቀመጥ እንደሚኖርባቸው፣ ነገር ግን ይህ እየሆነ አለመሆኑን የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ ፕሮቮስት ዶ/ር ዘሪሁን አበበ፣ ሕክምና ኮሌጁ ለአራተኛ ጊዜ በልዩ ልዩ የሕክምና ሙያ ያሠለጠናቸውን 57 ዕጩ ሐኪሞች ግንቦት 26 ቀን 2008 ዓ.ም. በመጀመርያ ዲግሪ ባስመረቀበት ሥነ ሥርዓት ላይ አስታወቁ፡፡
ዶ/ር ዘሪሁን እንደገለጹት፣ አገሪቷ በጀመረችው የሆስፒታሎች ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ከሚያጋጥሙት ችግሮች መካከል አንዱና ዋነኛው አቅም ያላቸው ሐኪሞች በሜዲካል ዳይሬክተርነት አለመቀመጣቸው ወይም ዲን አለመሆናቸው ነው፡፡ አሁን ባለው የጤና ፖሊሲ መሠረት፣ በጣም ጎበዝ ወይም አቅም ያለው ሐኪም የንቅለ ተከላ (ትራንስፕላንት) ቀዶ ሕክምና፣ የልብ ሐኪም፣ አለበለዚያም የማህፀን ሐኪም ወዘተ ይሆናል እንጂ ወደ አመራር አይመጣም፡፡ ይህ ደግሞ ብዙ ችግሮችን ያስከትላል፡፡
ስለሆነም የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥባቸውን ተቋማት የተሻለ የሥራ አካባቢ ለማድረግ፣ ከውጭ አገር ባለሙያ ማምጣትም ሆነ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መጠበቅም ሳያስፈልግ፣ የሕክምና ባለሙያዎች በራሳቸው ተነሳሽነት መሥራት እንዳለባቸው ዶ/ር ዘሪሁን አስረድተዋል፡፡
እንደ ዶ/ር ዘሪሁን ገለጻ፣ የሕክምና ኮሌጁ ከተቋቋመ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በሦስት ባች አስመርቆ ባለሙያዎቹም በልዩ ልዩ የሕክምና ተቋማት ተመድበው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡
ኮሌጁ የተቋቋመው በማደግ ላይ ካሉት (ጋምቤላ፣ ኢትዮጵያ ሶማሌ፣ አፋርና ቤንሻንጉል ጉሙዝ) ክልሎች ተማሪዎችን እየተቀበለ በሕክምና ሙያ ለማሠልጠንና የክልሎቹን የሕክምና አገልግሎት እጥረት ለመቅረፍ ታስቦ ነበር፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን ከተቋቋመበት ዓላማ በተጨማሪ የማስተማሩን ሥራ በስፋትና በጥሩ ሁኔታ እንደቀጠለበት አስረድተዋል፡፡
በአዲሱ መርሐ ግብር ግን ከመላው አገሪቱ ኮሌጁ የሚያዘጋጀውን የመግቢያ ፈተና ተወዳድረው ያለፉ ተማሪዎችን ብቻ እየተቀበለ ማስተማር እንደጀመረ፣ ይህ አካሄድ በአገሪቱ ቁንጮ የተባሉ ሐኪሞችን ለማፍራት እንደሚያስችል ዶ/ር ዘሪሁን ተናግረዋል፡፡
በካፒታል ሆቴል የስብሰባ አዳራሽ በተከናወነው ሥነ ሥርዓት ላይ ከተመረቁት ዕጩ ሐኪሞች መካከል 42 ወንዶች ሲሆኑ፣ የቀሩት 15ቱ ደግሞ ሴቶች ናቸው፡፡ ከአጠቃላይ ዕጩ ሐኪሞች ውስጥ አንድ አራተኛው ወይም 28 በመቶ ያህሉ በማደግ ላይ ካሉት ክልሎች የመጡ ናቸው፡፡
እጅግ ከፍተኛ በሆነ ማዕረግ ሁለት፣ በከፍተኛ ማዕረግ ሰባት፣ በማዕረግ 13 ዕጩ ሐኪሞች የተመረቁ ሲሆን፣ ለተመራቂዎቹ ዲግሪና በትምህርታቸው ብልጫ ያመጡ ደግሞ ልዩ ልዩ ሽልማቶችን ከኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ገመቺስ ማሞ ተቀብለዋል፡፡