Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለዘላቂ የከተማ ልማት የወንዞች ብክለትን መከላከል እንደሚገባ ተገለጸ

ለዘላቂ የከተማ ልማት የወንዞች ብክለትን መከላከል እንደሚገባ ተገለጸ

ቀን:

ለአዲስ አበባ ዘላቂ ልማት ለዘመናት የከተማዋ ችግር ሆኖ የኖረው የወንዞች ብክለትን መከላከል ላይ ሊሠራ እንደሚገባ ከንቲባ ድሪባ ኩማ አስታወቁ፡፡ በዚህ ረገድ እስካሁን በከተማዋ የተሠራው ሥራም በቂ አለመሆኑን አክለዋል፡፡ ከተቆረቆረች ከ128 ዓመታት በላይ ያስቆጠረችው ከተማዋ በተለይ ባለፉት አሥር ዓመታት ፈጣን ዕድገት እያሳየች ትገኛለች፡፡ ዕድገቷ በመሠረተ ልማት ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ዓለም አቀፍ ሚናዋ ጨምሯል፣ በኢንዱስትሪ ልማት ዙሪያም ተመሳሳይ እመርታ አሳይታለች፡፡ ‹‹ይህ ዕድገት ትልቅ ኃላፊነት ጥሎባታል፡፡ ኃላፊነቷን ለመወጣትም በርካታ ሥራዎች ይጠብቋታል፡፡ ከእነዚህም መካከል የወንዞችና የወንዞች ተፋሰስ ላይ የሚጠበቅባት የቤት ሥራ ነው፤›› ብለዋል ከንቲባ ድሪባ፡፡

ይህንን የተናገሩት ቅዳሜ ግንቦት 28 ቀን 2008 ዓ.ም. በደብረ ዘይት የከተማ ወንዞችና የወንዝ ዳርቻ ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣም ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በከተማዋ የሚገኙትን ወንዞች ጥቅም ላይ ማዋል በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ነው፡፡ ፕሮግራሙ የተዘጋጀው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ሲሆን ልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል፡፡

ከተቋቋመ አምስት ወራትን ያስቆጠረው ጽሕፈት ቤቱ የከተማዋን ወንዞች ጥቅም ላይ በማዋል ኅብረተሰቡን ከጐርፍና ከብክለት መከላከልና ለኑሮ ምቹ አካባቢን መፍጠር ላይ አትኩሮ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

‹‹ይህ ካልተሠራ አዲስ አበባ ወደፊት ትልቅ ፈተና ያጋጥማታል፡፡ ስለዚህም በኢንዱስትሪ፣ በመንገድና በሌሎችም የመሠረተ ልማት አውታሮች ላይ ትልልቅ ሥራዎች እንደሚሠራ ሁሉ በወንዞችም ላይ መሥራት ግድ ይላል፤›› የሚሉት ከንቲባው ወንዞችን ከብክለት ለመከላከል በወንዞች ተፋሰስ አካባቢ የአረንጓዴ ልማት ማካሄድና ከአንድ በመቶ በታች የሆነውን የአረንጓዴ ልማት ከፍ ማድረግ ግድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ዋለልኝ ደሳለኝ እንደሚሉት፣ በከተማዋ የሚገኙት ወንዞች የተበከሉ ናቸው፡፡ ይህ በዙሪያቸው ለሚኖሩ ሰዎች ችግር እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ የተቋቋመውም ይህን ችግር መፍታትን በማለም ነው፡፡ ከተቋቋመ ጥቂት ወራትን ቢያስቆጥርም እስካሁን ተቋማዊ ኃይሉን ሲያደራጅ መሰንበቱን፣ በቅርቡም ወደ ሥራው እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

‹‹በቅንጅት የሚሠራ ነው፡፡ ሥራው የበርካታ ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ይፈልጋል፤›› ሲሉ ማኅበረሰቡና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለፕሮጀክቱ ተፈጻሚነት የበኩላቸውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የተቀናጀ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት ባለመኖሩ ከመኖሪያ ቤትና ከየተቋማት የሚወጡ ኬሚካሎች፣ የሽንት ቤት ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ በአቅራቢያ ወደሚገኙ ወንዞች እንደሚገቡ ይታወቃል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ተረፈ ምርትንና ፍሳሽን ለማስወገድ እንዲያመች በሚል ኢንዱስትሪዎች ወንዝ ዳር እንዲገነቡ ይደረግ ነበር፡፡ ይህ ከባቢ አየርን ከመበከሉ ባለፈ ለከተማዋ ጽዳት ጠንቅ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍም ማኅበረሰቡና መሰል ተቋማት በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባ ከንቲባው አሳስበዋል፡፡ ወንዞችና የወንዝ ዳርቻዎችን ከብክለት ለመከላከል መንግሥት ያወጣቸው ደንቦችና ሕጐችም በአግባቡ ሊፈጸሙ እንደሚገባ አክለዋል፡፡ በሕጉ መሠረት በወንዞች ዳርቻ ከ15 እስከ 30 ሜትር ድረስ ባለው ክፍት ቦታ መሥፈር የተከለከለ ነው፡፡

ይሁንና ይህ ከወረቀት ባለፈ ተፈጻሚ ሲሆን አይታይም፡፡ ሰዎች ያለምንም ገደብ በወንዞች ዳርቻ ላይ ሲሰፍሩና ለተለያዩ አደጋዎች ሲጋለጡ ይስተዋላል፡፡ የከተማዋን ወንዞችና የወንዞችን ዳርቻዎች ለማልማት የተነደፈው የአምስት ዓመት ዕቅድን የሚያግዝ ጥናት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው፡፡ ጥናቱ ለስድስት ወራት የሚካሄድ ሲሆን ወንዞቹን ማልማት፣ በሰዎች አሰፋፈርና መሬት አጠቃቀም ዙሪያ ዝርዝር ጉዳዮችን ያካትታል፡፡ ይህም ወንዞቹን ከብክለት ለመከላከልና ከወንዞች የሚገኘውን ጥቅም ለማጣጣም እንደሚረዳ አቶ ዋለልኝ ተናግረዋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...