Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየሽብር ጥቃት ያጠላበት የዘንድሮው የአውሮፓ እግር ኳስ ጨዋታ

የሽብር ጥቃት ያጠላበት የዘንድሮው የአውሮፓ እግር ኳስ ጨዋታ

ቀን:

ከነገ ወዲያ በፈረንሣይ በሚጀመረው እ.ኤ.አ. የ2016ቱ የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ፣ የሽብር ጥቃት ሊፈጸም ይችላል በሚል አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ አገሮች ሥጋታቸውን ሲገልጹ ከርመዋል፡፡

ፈረንሣይ በበኩሏ የሽብር ጥቃትን ለመከላከል ሙሉ ለሙሉ ዝግጅቷን እንዳጠናቀቀችና ጨዋታውም በሰላም እንደሚከናወን መናገር ከጀመረች ከራርማለች፡፡ የሽብር ጥቃት ቢከሰት ወይም ከመከሰቱ በፊት እንዴት መቋቋም ይቻላል? በሚለው ዙሪያ የደኅንነት ክፍሏ በሲሙሌተር በመታገዝ ጭምር ከ20 ያላነሱ ሽብር ላይ ያጠነጠኑ ሥልጠናዎችን አካሂዳለች፡፡ ጨዋታው ዓርብ ሰኔ 3 ቀን 2008 ዓ.ም. የሚጀመር ሲሆን፣ ዕለቱ ከመድረሱ አራት ቀናት አስቀድሞ፣ ፈረንሣይን በሽብር ጥቃት ሊያናጋ የነበረ የ25 ዓመት ፈረንሣዊ በፖላንድ ድንበር በዩክሬን የደኅንነት ኃይሎች ከነመሣሪያዎቹ በቁጥጥር ሥር መዋሉ በይፋ መገለጹ፣ ቀድሞውንም የነበረውን ሥጋት አጠናክሮታል፡፡

ኢንዲፔንደንት እንደዘገበው፣ ፈረንሣዊው ግሪጎሪ ሙታክስ፣ የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ ጨዋታ በፈረንሣይ በሚካሄድበት ወቅት 15 የሽብር ጥቃቶችን ለመፈጸም አቅዶ ሲንቀሳቀስ በቁጥጥር ሥር የዋለው ከአሥር ቀናት በፊት ቢሆንም በሚዲያ የተገለጸው ግን ከቀናት በፊት ነው፡፡

በዩክሬንና በፖላንድ ድንበር በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሲውል 5,000 ጥይቶች፣ ሁለት ፀረ ታንክ ላውንቸር፣ 125 ኪሎ ግራም የሚመዝን ቲኤንቲ ፈንጂዎች፣ 100 ማፈንጃ መሣሪያዎችና 20 የፊት መሸፈኛ ጭምብሎች ይዞ ነበር፡፡

በዜጋቸውና በአገራቸው ላይ ሽብር የሚፈጽሙ ሰዎች መበራከት ትልቁ ሥጋት እንደሆነ የፈረንሣይ የደኅንነት ክፍል ባስታወቀ ሰሞን በቁጥጥር ሥር የዋለው ፈረንሣዊ የሽብር ተጠርጣሪ፣ በፈረንሣይ ሰሜን ምሥራቅ ክፍል ነዋሪ ሲሆን፣ ጭፍን በሆነ የአገር ወዳድነት አመለካከት የተማረከ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ለሚስተር ሙታክስ ፈረንሣይ ለፈረንሣውያን ተወላጆች ብቻ የተሰጠች ምድር ናት፡፡ ስደተኞችም ሆኑ የእስልምና እምነት ተከታዮች በምድረ ፈረንሣይ መኖር የለባቸውም የሚል አመለካከትም አለው፡፡

መንግሥት እየተከተለ ያለውን የስደተኞች ፖሊሲ ለመቃወም ይህ አመለካከቱ፣ በገዛ አገሩ የሽብር ጥቃት  እንዲነሳሳ አድርጎታል፡፡

እንደሮይተርስ ዘገባ፣ የሙታክስ ዕቅድ የአይሁድንና የእስልምና ቤተ አምልኮዎችን፣ የፖሊስ ተቋማትን፣ ከእግር ኳስ ጨዋታው ጋር ተያይዞ አገልግሎት የሚሰጡና የመንግሥት አስተዳደር ሕንፃዎችን፣ ዋና ዋና መንገዶችና በተለያዩ የፈረንሣይ ግዛቶች የሚገኙ ድልድዮችን የሽብር ጥቃት ሰለባ ማድረግ ይገኝበታል፡፡

የዩክሬን የደኅንነት ክፍል ኃላፊ ቫሲል ግሬይዛክ፣ ሙታክስ ይህንን ዓይነት ሰፊ የሽብር ጥቃት ብቻውን ለመፈጸም አይችልም፡፡ በሥሩ ብዙ ሰዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ ክትትል ማድረግ ተገቢ ነው ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

ሚስተር ሙታክስ ከዚህ ቀደም የወንጀል ሪከርድ ያልተመዘገበበትና በሚኖርበት አካባቢ ያሉ ሰዎችም መልካምነቱን የመሰከሩለት ቢሆንም፣ ፖሊስ በመኖሪያ ቤቱ ባደረገው ፍተሻ ፈንጂ ለመሥራት የሚያስችሉ ኬሚካሎች፣ የናዚ ምልክት ያለባቸው ካኔቴራዎችና አምስት የፊት መሸፈኛ ጭምብሎች ተገኝተዋል፡፡

የፈረንሣይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይም የፈረንሣይ ዜጋ የሆነው ሚስተር ሙታክስ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ሲያረጋግጡ፣ በቁጥጥር ሥር በመዋሉም የአውሮፓ እግር ኳስ ጨዋታ በሚጀመርበት ዋዜማና በጨዋታ ሒደት ውስጥ ሊያከናውን የነበረውን 15 የሽብር ጥቃቶች ማክሸፍ ተችሏል፡፡

የአውሮፓ የደኅንነት አባላት ባለፈው ኅዳር በፈረንሣይ ፓሪስ 130፣ በቤልጂየም ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያና በብራስልስ 32 ሰዎችን የገደለውን የሽብር ጥቃት ተከትሎ፣ በአውሮፓ ከፍተኛ የደኅንነት ቁጥጥር እያደረጉ መሆኑን የሮይተርስ ዘገባ ያሳያል፡፡

የአሜሪካ የደኅንነት ባለሥልጣናት፣ በፈረንሳይ 2016ቱ የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ በሚጀመርበት ዕለት የሽብር ጥቃት ሊሰነዘር ይችላል ሲሉ ያስታወቁት ቀደም ብለው ነው፡፡ ፈረንሣይ የአሜሪካን ትንበያ ባትቀበለውም፣ የሽብር ጥቃት ሳይከሰት እንዴት ማምከን እንደሚቻል ያካተቱ ሥልጠናዎችን ጨምሮ ለደኅንነት ክፍሏ ሥልጠና ሰጥታለች፡፡ በጨዋታው ወቅት ምንም ኮሽታ ሳይሰማ እንዲጠናቀቅም 90 ሺሕ የደኅንነት ሰዎችን አሰማርታለች፡፡

ጨዋታው በፓሪስና በሌሎች ስምንት ከተሞች በሚገኙ ስታዲየሞች ለአንድ ወር ያህል ይካሄዳል፡፡ በዚህ ወቅት የሽብር ጥቃት ይሰነዘራል የሚል ሥጋር ከያቅጣጫው እየጎረፈ ቢሆንም፣ የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ፍራንስዋ ኦላንዴ፣ የሽብር ጥቃት በአገሪቱ የሚካሄደውን የአውሮፓ እግር ኳስ ጨዋታ አያደናቅፈውም ብለዋል፡፡

በዩክሬን የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር የዋለው ሙታክስ፣ ወደ ዩክሬን ያቀናው አምና ነበር፡፡ ወደ ምሥራቅ ዩክሬን አቅንቶም በዩክሬን የበጎ ፈቃድ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ አካሄዶችን ሞክሯል፡፡

የዩክሬን ወታደሮች በሩሲያ ከሚደገፉት ዩክሬናውያን ጋር ከ2014 ጀምሮ ግጭት ላይ ሲሆኑ፣ ፈረንሣዊው ከየትኛው ወገን እንደነበረ ለጊዜው አልታወቀም፡፡

አሜሪካ በአውሮፓ እግር ኳስ ጨዋታ ወቅት በፈረንሣይ የሽብር ጥቃት ይፈጸማል የሚል ጥቆማ ብታደርስም፣ ፈረንሣይ እስካሁን ምንም ዓይነት የሽብር ጥቃት ሊያደርስ የሚችል ቡድንም ሆነ መሣሪያ በደኅንነት ክፍሏ አለማግኘቷን አስታውቃለች፡፡ የዩክሬንና ፖላንድ ድንበር የተያዘው ፈረንሣዊም ባለበት በዩክሬን የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡

ፈረንሣይ በአክራሪዎች የሽብር ጥቃት ሊደርስባት እንደሚችል ብትገነዘብም፣ አሁን ላይ ምንም ሥጋት እንደሌለ የሊዮን ፖሊስ ተጠሪ ተናግረዋል፡፡

አሜሪካ ግን ጨዋታዎቹ በሚካሄዱባቸው የፈረንሣይ ስቴዲየሞች፣ በአውሮፓ በሚገኙ ሁሉም አገሮች ደጋፊ በሚዝናኑባቸውና ጨዋዎቹ በሚተላለፉባቸው መዝናኛ ሥፍራዎች የሽብር ሰለባ ሊሆኑ ይችላሉ ስትል አስጠንቅቃለች፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...