Friday, April 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት ለማዳበሪያ መግዣ የሚውል የ80 ሚሊዮን ብር ዕርዳታ አገኘ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በተያዘው በጀት ዓመት መንግሥት ከአንድ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ያላነሰ የማዳበሪያ ግዥ እንደሚፈጽም ሲጠበቅ፣ ለማዳበሪያ ግዥ የሚውል 80 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ዕርዳታ ከጃፓን መንግሥት ማግኘቱ ታውቋል፡፡

የጃፓን መንግሥት የሰጠው ዕርዳታ የአንድ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ግዥ አካል ሲሆን፣ ዕርዳታውም በጃፓን አምባሳደርና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ተፈርሟል፡፡ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ካዙሂሮ ሱዙኪ ከገንብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አህመድ ሺዴ ጋር ባደረጉት ስምምነት መሠረት፣ ግዥውን የግብርና ግብዓቶች አቅራቢ ድርጅት ይፈጽማል፡፡ የጃፓን መንግሥት ባለፉት ዓመታት ለማዳበሪያ ግዥ ብቻ በማለት የሰጠው የገንዘብ ድጋፍ 160 ሚሊዮን ብር እንደሚገመት የኤምባሲው መረጃ ይጠቁማል፡፡

በሌላ በኩል ግንቦት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. በተካሔደ ሥነ ሥርዓት፣ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራምን ጨምሮ ሌሎች ተቋማትም ድጋፍ የሚያደርጉለት የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ሥልጠና ማዕከል፣ በጃፓን መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ አማካይነት ለአራተኛ ጊዜ ያዘጋጀውን ግጭትን በመከላከል ላይ ያተኮረ ሥልጠና ይፋ አድርጓል፡፡

ግንቦት 29 ቀን የተጀመረው ሥልጠና ለአሥር ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን ከኢትዮጵያውያን ባሻገር ተቋሙ፣ ከጂቡቲ፣ ከታንዛንያ፣ ከቡሩንዲ፣ ከኡጋንዳ፣ ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከኬንያ እንዲሁም ከሩዋንዳ ለተውጣጡ የሰላም ማስከበር ልዑካን አራተኛውን ዙር ሥልጠና መስጠት ጀምሯል፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ የልቀት ማዕከል መሆኑ የተነገረለት ይህ ተቋም፣ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካይነት እየተሳተፈችባቸው ባሉ የሰላም ማስከበር ተግባራት ውስጥ ጉልህ ሚና አለው፡፡

አምባሳደር ሱዙኪ አራተኛው ዙር ሥልጠና ሲጀመር እንዳመለከቱት፣ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በዓለም የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ውስጥ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰላም አስከባሪዎችን በማዋጣት ላይ ትገኛለች፡፡ በሰው ኃይል ልማት እንዲሁም በግጭት መከላከል መስክ በዚህ ዓመትም በዓለም በአንደኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጣትን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ የምትገኝ አገር ልትሆን መብቃቷ ተነግሯል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2011 የተመሠረተው የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ሥልጠና ማዕከል፣ የሥርዓተ ትምህርተ ዝግጅትን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ከጃፓን መንግሥት ድግፋ በማግኘት ላይ ይገኛል፡፡

ከስድስት ኪሎ ወደ ሽሮ ሜዳ በሚስደው መንገድ ከአሜሪካ ኤምባሲ አጠገብ የሚገኘው ይህ ማዕከል፣ በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሳይኛና በአረብኛ ቋንቋዎች የሰላም ማስከበር ሥልጠናዎችን የሚሰጥ ነው፡፡ 242 ተሳታፊዎችን ማስተናገድ የሚችል ዋና ስብሰባ አዳራሽ ሲኖረው፣ 60 ያህል ሰዎችን የሚያስተናግድ አነስተኛ የስብሰባ ክፍልም ተገንብቶለታል፡፡

ጃፓን በአፍሪካ የሰላም ማስከበርና ግጭትን የመከላከል ተግባራት ላይ የምታደርገው ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱን አምባሳደር ሱዙኪ ጠቁመዋል፡፡

ከሃይማኖትና ጎሳዎች ባሻገር በወጣቶችና በሴቶች፣ በፀጥታና በወታደራዊ ተቋማት አካባቢ ሥልጠና በመስጠት የተሳሳቱና ለግብረ ሽብር መነሻ የሆኑ የጽንፈኛነት አስተምህሮዎችን የመከላከል ተግባራት ላይ በማተኮር በሶማሊያ አዲስ የሥልጠና ፕሮግራም የጀመረው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) የጃፓንን ድጋፍ ማግኘት መጀመሩ አይዘነጋም፡፡ ለዚህ ፕሮግራም ድጋፍ ለማድረግ ብቻም ሳይሆን ለኢጋድ በቀጥታ ድጋፍ ስትሰጥ የመጀመሪያዋ የሆነው ጃፓን፣ ለሥልጠናው እንዲያግዝ በማለት 775 ሺሕ ዶላር ለግሳለች፡፡ በመጋቢት 2008 ዓ.ም. ለአንድ ዓመት ለሚቆይ ሥልጠና ገንዘቡ እንዲውል ጃፓን መስማማቷንና ዕርዳታውን መለገሷን፣ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ካዙሂሮ ሱዙኪ ገልጸዋል፡፡

አልሸባብ በቀጣናው ትልቅ ሥጋት መሆኑን የገለጹት የኢጋድ ዋና ጸሐፊ አምባሳደር ማህቡብ ማሊም፣ በቅርቡ ከጃፓን መንግሥት ጋር በተደረገ የዕርዳታ ስምምነት ላይ እንዳሉት፣ ከዚህ ቀደም በአፍሪካ ኅብረት ወይም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኩል ለኢጋድ ስትሰጥ የነበረው ድጋፍ አሁን በቀጥታ መምጣቱ እንዳስደሰታቸው ተናግረው፣ ከአልሸባብ ነፃ የወጡ የሶማሊያ አካባቢዎች ላይ ፀረ ግብረ ሽብርና ጽንፈኝነት ሥልጠናዎች እንደሚሰጡ አስታውቀዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች