Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኦሪጅን ውኃ 43 በመቶ ድርሻውን ለአሜሪካ ኩባንያ ሸጠ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኦሪጅን የማዕድን ውኃ 43 በመቶ ድርሻውን ለአሜሪካው ሹልዝ ግሎባል ኢንቨስትመንት መሸጡን አስታወቀ፡፡ ቅዳሜ፣ ግንቦት 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ኦሪጅን የማዕድን ውኃ ዓለምገና በሚገኘው ፋብሪካው ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የኦሪጅን ማዕድን ውኃ ባለቤት ሮቤርቶ ጋብሬየስና የኩባንያውን 43 ከመቶ ድርሻ መግዛቱ የተነገረው የአሜሪካው ሹልዝ ግሎባል ኢንቨስትመንት ሥራ አስኪያጅ ጋብሮዬል ሹልዝ እንዲሁም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የኢኮኖሚና ቢዝነስ ጉዳዮች ዳይሬክተር ወይዘሮ ሒሩት ዘመነ ነበሩ፡፡

አቶ ሮቤርቶ ጋብሬየስ እንደገለጹት፣ ኦሪጅን ውኃን ያቀፈው መሥራች ኩባንያ ኤሌክትሮ ኮሜርሻል ሲሆን፣ በኢትዮጵያውያንና በጣሊያን ዜጎች በተለያዩ መስኮች በመሰማራት የሚታወቅ ኩባንያ ነው፡፡ በ1952 ዓ.ም. በተመሠረተው በዚህ ኩባንያ አማካይነት ግዙፍ የብረታ ብረትና የፕላስቲክ ፋብሪካዎች የገነባና በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ትልልቅ ፎቆችም ባለቤት ነበር፡፡ በርካታ ሠራተኞችን አቅፎ ይንቀሳቀስ ነበር፡፡ ሆኖም ንብረቶቹን በ1967 ዓ.ም. በደርግ መንግሥት ተወርሰዋል፡፡ ኩባንያው ላይ ከባድ ኪሳራ ቢደርስበትም እጁን አጣጥፎ ሳይቀመጥ በአስመጪና ላኪነት ሲሠራ ቆይቶ በቅርቡ በአምራችነት ለመሳተፍ ኦሪጅን የማዕድንና የምግብ ማምረቻ የተባለውን ኩባንያ በ2004 ዓ.ም. ዕውን አድርጓል፡፡ ፋብሪካው በተተከለበት ዓለምገና ከተማ የማዕድን ውኃ የሚያመርት ዘመናዊ ፋብሪካ ሥራ አስጀምሯል፡፡ ይህ ፋብሪካ ትክክለኛውን የማዕድን ውኃ ለማምረትና ለአካባቢ ጥበቃ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ የገለጹት የኩባንያው ኃላፊዎች፣ የዓለም የጤና ድርጅት መስፈርቶችን በማሟላት የታሸገ የማዕድን ውኃ በኢትዮጵያ ከማምረት ባሻገር የጥራት ደረጃ እንዲኖረው ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገናል ይላሉ፡፡ ይህ ጥረት የተደረገው ያለምንም ችግር ኦሪጅን የማዕድን ውኃን ኤክስፖርት ለማድረግ ጭምር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ኦሪጅን የማዕድን ውኃ በአገር ውስጥ ምን ያህል ድርሻ እንዳለውና ምን ያህል የገበያ ድርሻ ለመያዝ እንደሚሠራ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ሮቤርቶ ሲመልሱ፣ ‹‹ፋብሪካው ሲቋቋም ሐሳቡ ኤክስፖርት ለማድረግ ነበር፡፡ አሁን የተፈራረመው የአሜሪካው ኩባንያ በንግዱ ዘርፍ ልምድና ችሎታ ያለው በመሆኑና አገር ውስጥ ያለው ተገቢ ያልሆነ ውድድር ስላስቸገረን በአገር ውስጥ ያለን ድርሻ 20 ከመቶ ቢሆንም፣ እኛ ደረጃውን የጠበቀ ፋብሪካ ገንብተን ትክክለኛ የማዕድን ውኃ ለሕዝብ ለማቅረብ ብዙ ደክመናል፡፡ ግን ይህን እየመለሰልን አይደለም፡፡ ስለዚህ ምርቶችን በሚቀጥሉት አራት ወራት ውስጥ ወደ ጂቡቲ መላክ እንጀምራለን፤›› በማለት አቶ ሮቤርቶ ተናግረዋል፡፡

ወደ ጂቡቲ የተዘረጋው የባቡር መስመርም በፋብሪካው በር የሚያልፍ በመሆኑ  ወደ ውጭ የሚላከው ምርት በትራንስፖርት ችግር ምክንያት ሳይበላሽ ወደ ውጭ ገበያዎች ስለሚደርስ ጥሩ ግብይት ይኖራል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል፡፡ የትራንስፖርት ወጪውም በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል ብለዋል፡፡

ሚስተር ጋብሮዬል ሹልዝ በበኩላቸው፣ ኩባንያቸው በጥራት የሚያምንና ከጠንካራ ድርጅትም ጋር የሚሠራ መሆኑን ገልጸው፣ በተለያዩ ዘርፎች መሰማራቱንና ከእነዚህም ውስጥ በኢትዮጵያ ድርሻ በመግዛት የተቀላቀለው የመጠጡ ዘርፍ ተጠቃሽ ነው ብለዋል፡፡ በእስያና በአፍሪካ ትኩረቱን በማድረግ በተለይ በኢትዮጵያ ብዙ ሚሊዮን ዶላሮችን በማፍሰስ ከፋሚሊ ወተት፣ ከተራራ ቡና፣ ከናሽናል ሲሜንት፣ ከቼራሊያ ብስኩት፣ ከፍሊፐር ትምህርት ቤት፣ ከሳሞዲ የግሉኮስ መያዣ ፕላስቲክ ማምረቻ ጋር እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ አሁን ደግሞ ከኦሪጅን የማዕድን ውኃ ጋር የተፈጥሮ የማዕድን ውኃ ምርትን የበለጠ ለማሳደግ እንሠራለን፡፡ በማለት የገለጹ ሲሆን፣ ‹‹ከዚህ ጠንካራ ድርጅት ጋር አንዴ ተጋብተናል፤ ጋብቻችን ደግሞ ነገ የሚፈርስ ሳይሆን በየቀኑ በጠንካራ ሥራ ዘላቂ እናደርገዋለን፤›› በማለት የተዋሃዱበትን አኳኋን ገልጸውታል፡፡

የኦሪጅን የማዕድን ውኃን ድርሻ ለመግዛት ምን ያህል እንዳወጡ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ በርካታ ሚሊዮን ዶላሮች ከማለት ውጭ ቁጥሩን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ በኢትዮጵያ ምን እንደሚሠሩ ሲጠየቁም፣ የሹልዝ ኩባንያ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኢዮብ ቶዎሊና ‹‹ቀጣዩ ትኩረታችን በሆቴል ቱሪዝምና እንዲሁም በጤና ዘርፍ ሲሆን፣ በዚህ ዘርፍ ከተሰማሩት ጋር እየተነጋገርን ነው፤›› ብለዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች