Friday, May 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የልዩ ሕዝብ ማመላለሻዎች ታሪፍ አወሳሰን ወደ መንግሥት ሊዞር ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ዘርፍ በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ወይም በአገር አቋራጭ ርቀት አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ተሽከርካሪዎች በቀን ከ80 ሺሕ በላይ ተጓዦችን እንደሚያስተናግዱ ይነገራል፡፡

እነዚህ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በዓመት ወደ 30 ሚሊዮን የሚጠጉ ተጓጓዦችን ከአንዱ የአገሪቱ ክፍል ወደ ሌላኛው እንደሚያጓጉዙም የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን መረጃ ያመለክታል፡፡ እንደየተሽከርካሪዎቹ ይዘትና የብቃት ደረጃ ተመዝነው ከአንድ እስከ ሦስት ደረጃ ወጥቶላቸው አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች፣ በተለያዩ ማኅበራት አማካይነት ተደራጅተው በሚወጣላቸው የስምሪት ፕሮግራም መሠረት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ የሕዝብ ማመላለሻዎች የአገልግሎት ታሪፍ ሲወሰን የቆየውም በመንግሥት ነው፡፡

በማኅበራት ተደራጅተው በሚፈቀድላቸው መስመርና መንግሥት ባወጣው ታሪፍ መሠረት አገልግሎት እንዲሰጡ ከሚገደዱት የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ውጭ ግን በልዩ ፈቃድ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ የረዥም ርቀት የትራንስፖርት ድርጅቶችም ተፈጥረዋል፡፡

በልዩ የትራንስፖርት አገልግሎት መደብ በተለየ ፈቃድ የሕዝብ ማመላለስ አገልግሎት የሚሰጡ የትራንስፖርት ድርጅቶች ቁጥር በአሁኑ ወቅት ስድስት ደርሷል፡፡ ይህ አሠራር ከተጀመረም ሰባት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡

በልዩ ፈቃድ ሥራ የጀመሩት ድርጅቶች ግን እንደ ሌሎች የሕዝብ ማመላለሻዎች ለአገልግሎታቸው የሚያስከፍሉት ዋጋ በመንግሥት የሚወሰን አልነበረም፡፡ ስምሪታቸውም ቢሆን በመንግሥት ወይም በማኅበራት የሚደለደል ሳይሆን፣ ያዋጣናል በሚሉት መስመር እንዲሠሩ ሲፈቀድላቸው ቆይቷል፡፡

ፈቃድ የሚወስዱት ለልዩ አገልግሎታቸው የተቀመጠውን መሥፈርት ማሟላታቸው ሲረጋገጥ በመሆኑ፣ ልዩ የትራንስፖርት አገልግሎት ፈቃድ የሚሰጠው ድርጅት ለአገልግሎት የሚያቀርባቸው ተሽከርካሪዎች ዘመናዊ መሆን አንዱ መሥፈርት ነው፡፡ በልዩ ፈቃድ አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያሰማሯቸው አውቶቡሶች ዘመናዊ (ሌግዥሪ) የሚባለውን ደረጃ መያዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለአብነት ተሽከርካሪዎቹ በእያንዳንዱ መቀመጫ አቅራቢ የአየር ማቀዝቀዣ መግጠም ይጠበቅባቸዋል፡፡ የወንበር አቀማመጡ ስፋትም ከሌሎች ተሽከርካሪዎች የተለየና ተሳፋሪውን እንደ ልብ የሚያላውስ መሆን ይኖርበታል፡፡

በልዩ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች የሚያሰማሯቸው አውቶቡሶች ለተሳፋሪዎች ምግብና መጠጥ የማቅረብ ግዴታ ያለባቸው ሲሆን፣ እያንዳንዱ አውቶቡስ ፍሪጅ፣ መፀዳጃ ቤት፣ ቴሌቪዥንና ቪዲዮ ማጫወቻ ሊኖረው ይገባል፡፡ በእያንዳንዱ ወንበር መመገቢያ ጠረጴዛና የመሳሰሉትን ማሟላት እንደ መሥፈርት ከተቀመጡት ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ፈቃዱ የሚሰጠውም የዘመናዊ ተሽከርካሪዎች መገለጫ የሆኑትን ሌሎች የተቀመጡትን መሥፈርቶች ሲያሟላ ነው፡፡

የተቀመጠውን መሥፍርት የሚያሟላ አንድ አውቶብስ ለመግዛት አሁን ባለው የገበያ ዋጋ ከ3.8 ሚሊዮን ብር በላይ ይጠይቃል፡፡ ለአንድ አውቶብስ እስከ 800 ሺሕ ብር ቀረጥ እንደሚከፈል ይነገራል፡፡ ለዚህም ነው እነዚህ ልዩ የትራንስፖርት ዘርፍ ፈቃድ የወሰዱ ድርጅቶች በተለየ ታሪፍ እንዲሠሩ፤ ስምሪትም እንዳይመለከታቸው የተደረገው፡፡ በአሁኑ ወቅተ ግን ላለፉት ሰባት ዓመታት ሲሠሩበት የነበረውን አግባብ ሊለውጥ የሚችል ክስተት እየተፈጠረ ነው፡፡ ይህም ልዩ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በራሳቸው ፈቃድ የሚወሰኑትን ታሪፍ የሚያስቀር ነው፡፡ ልዩ የትራንስፖርት አገልግሎት የተሰጣቸው ስድስቱ የትራንስፖርት ድርጅቶች በራሳቸው የሚያወጡት ታሪፍ ቀርቶ ለአገልግሎታቸው የሚጠይቁት ታሪፍ በመንግሥት ለመወሰን ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ ይህ አካሄድ ግን በዘርፉ የተሰማሩትን ድርጅቶች ያስደሰተ አይመስልም፡፡ መንግሥት የልዩ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችን ታሪፍ መወሰን የፈለገው፣ ድርጅቶቹ በራሳቸው እያወጡ ያሉት ታሪፍ ተጋኗል ከሚል መነሻ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ድርጅቶቹ ግን ለአገልግሎቱ ካዋሉት ኢንቨስትመንትና ወጪ አንፃር የሚጠይቁት ታሪፍ የተጋነነ አለመሆኑን በተለያየ መንገድ እየገለጹ ነው፡፡

‹‹ከፍተኛ መዋለ ነዋይ በማፍሰስ የሚገዙና በተሻለ አገልገሎት ወደ ሥራ የገቡ ተሽከርካሪዎችን ይዞ መንግሥት በሚያወጣው ታሪፍ መሥራት ቢዝነሱን ለማስቀጠል እንቅፋት ይሆናል፤›› የሚሉ አስተያየቶችም ተሰንዝረዋል፡፡ በዘርፉ ለመሠማራት ፍላጐት ያላቸውን ሌሎች ኩባንያዎችን ሊገድብ እንደሚችልም ያነጋገርናቸው የልዩ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡

እስካሁን በልዩ የትራንስፖርት መደብ ተሰማርተው ልዩ ፈቃድ የተሰጣቸው አምስቱ ድርጅቶች በጠቅላላ ከ90 በላይ አውቶብሶችን በማስገባት ረዣዥም ርቀት ባላቸው መስመሮች ላይ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

ከትራንስፖርት ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ልዩ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ ፈቃድ ተሰጥቷቸው እየሠሩ ከሚገኙ ድርጅቶች ውስጥ ቀዳሚው ሰላም ባስ አክሲዮን ማኅበር ነው፡፡ ለልዩ የትራንስፖርት አገልግሎት መጀመርም ጥናት በማስጠናት ጭምር አዲስ አሠራር እንዲፈጠር ማድረጉ ይገለጻል፡፡ ፈቃዱንም በመውሰድ የመጀመሪያ ሲሆን፣ በ71 አውቶብሶች በመታገዝ በመሥራት ላይ የሚገኝ ነው፡፡

በልዩ ፈቃዱ 20 ዓመታትን ካስቆጠረው ሰላም ባስ አክሲዮን ማኅበር ሌላ ተመሳሳይ ፈቃድ የወሰዱት አምስቱ የትራንስፖርት ድርጅቶች ስካይ ባስ፣ ኢትዮ ባስ፣ ሊማሊሞ ባስ፣ ጐልደን ባስና ዓባይ ባስ ናቸው፡፡

የትራንስፖርት ድርጅቶቹ ያዋጣናል ያሉት የትራንስፖርት ታሪፍ ከሌሎች የሕዝብ ማመላለሻ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ከሚያስከፍሉት ክፍያ ጋር ሲነፃፀር ልዩነት እንዳለው ይታመናል፡፡ በተለይ በረዣዥም ርቀት ባላቸው ጉዞዎች በልዩ ትራንስፖርት አገልግሎት ፈቃድ የወሰዱት ድርጅቶች ሌሎች አውቶብሶች የሚያስከፍሉት ክፍያ ጋር ሲነፃፀር ከ100 ብር በላይ ብልጫ አለው፡፡ መንግሥትም ታሪፍ ልወስን ይገባኛል ያለው ከዚህ ልዩነት የተነሳ እንደሆነ ይነገራል፡፡

ለእነዚህ ድርጅቶች መንግሥት ታሪፍ ሊያወጣ አይገባውም የሚሉ ወገኖች ግን ከሌሎች ጋር ሲነፃፀር ታሪፋችሁ ብዙ ነው ተብሎ ሊገለጽ አይገባም ይላሉ፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ድርጅቶች ያወጡት ወጪና የአገልግሎት ወጪያቸው ከፍተኛ በመሆኑ በራሳቸው ታሪፍ መንቀሳቀሳቸው ግድ በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ የመንገደኞችን ምቾት ለመጠበቅ 61 ተሳፋሪዎችን መያዝ የሚችለው አውቶብሳቸውን 51 ተሳፋሪዎች ብቻ እንዲይዝ በማድረግ ማገልገላቸውም ሊታሰብ እንደሚገባ ያመለክታሉ፡፡ ተገልጋዩም ቢሆንም በምርጫ የሚጠቀምባቸው ስለሆነ አለ የሚባለው የዋጋ ግነት የሚታይበት አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡

መንግሥት ግን ታሪፍ ወደ መወሰን የሚገባ ስለመሆኑ በይፋ ገልጿል፡፡ መንግሥት ታሪፋቸውን ለመወሰን ያለውን ፍላጐት ተከትሎም ድርጅቶቹ በአሁኑ ወቅት ሥራ ላይ እያዋሉ ያሉትን ታሪፋቸውንና ወጪና ገቢያቸውን የሚያመለክት መረጃ እንዲያቀርቡለት ጠይቋል፡፡ ሆኖም የታሪፍ ውሳኔውን በተመለከተ ከድርጅቶቹ ጋር ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አገልግሎት ሰጪዎቹም ይህንን መድረክ እየጠበቁ ነው፡፡

አምስቱም ድርጅቶች የሚጠይቁት ክፍያ በራሳቸው የሚወሰን ሲሆን፣ የአምስቱም የትራንስፖርት ድርጅቶች ለተመሳሳይ ርቀት ያስቀመጡት ታሪፍ የተለያየ መሆኑን ያሳያል፡፡

ወቅታዊውን የድርጅቶቹ ታሪፍ እንደሚያሳየውም ለምሳሌ ሰላም ባስ ከአዲስ አበባ መቀሌ 485 ብር ያስከፍላል፡፡ ወደ ባህር ዳር ለመጓዝ ደግሞ 350 ብር ይጠይቃል፡፡ በሰላም ባስ ወደ ድሬዳዋ ለመጓዝ ከተፈለገ ታሪፉ 300 ብር ነው፡፡

በስካይ ባስ ደግሞ ወደ መቀሌ ለመጓዝ ዋጋው 460 ብር ነው፡፡ ለድሬዳዋ ጉዞ 293 ብር ያስከፍላል፡፡ ከአዲስ አበባ ባህር ዳር ደግሞ 340 ብር ይጠይቃል፡፡ ለኢትዮ ባስ ወደ ድሬዳዋ መጓዝ ከተፈለገ ደግሞ የሚጠየቀው ክፍያ 300 ብር ነው፡፡ የጐልደን ባስ የአዲስ አበባ ባህር ዳር የጉዞ ዋጋ 320 ብር ነው፡፡

የትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ ፈቃድ የወሰዱት እነዚህ ድርጅቶች በመንግሥት ውጥን መሠረት እንደ ሌሎቹ መደበኛ ማመላለሻ የሕዝብ ማመላለሻዎች ታሪፋቸው በመንግሥት የሚወሰን ከሆነ፣ ችግር ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ የሚል ሥጋት አለ፡፡ የትራንስፖርት ባለሥልጣን ባወጣው ታሪፍ አንደኛ ደረጃ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ታሪፍ በአስፓልት መንገድ ከሆነ 0.30 ሳንቲም በጠጠር መንገድ ከሆነ ደግሞ 0.37 ሳንቲም ነው፡፡

ደረጃ ሁለቶች ደግሞ በኪሎ ሜትር መጠየቅ ያለባቸው ታሪፍ በአስፓልት መንገድ 28 ሳንቲም በጠጠር መንገድ 34 ሳንቲም አካባቢ ነው፡፡ በደረጃ ሦስት የተመደቡ ተሽከርካሪዎች ሊያስከፍሉ ይገባል ተብሎ የተቀጠው ዋጋ በአስፓልት መንገድ ከሆነ በኪሎ ሜትር 26 ሳንቲም ለጠጠር ደግሞ 31 ሳንቲም ነው፡፡

የልዩ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ዋጋ ግን አማካይ በኪሎ ሜትር ከ55 ሳንቲም በላይ ይደርሳል፡፡

በተለያዩ ወቅቶች የቀረቡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ደግሞ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ብቃትና የጥራት ደረጃ ዝቅተኛ መሆኑ ነው፡፡ አነጋጋሪ ሊሆን የሚገባውም ታሪፉ ብቻ ሳይሆን የተሽከርካሪዎች ብቃት እንደሆነ በመጥቀስ የሚከራከሩ አሉ፡፡  

በኢትዮጵያ ውስጥ አገልግሎት ላይ ያሉ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ብቃት ብዙ ችግሮች ያሉባቸው ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል፡፡ የአገሪቱን የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችን ይዘት ብቃትና የአገልግሎት አሰጣጥ የተመለከትና በቅርቡ ቀርቦ የነበረ ዳሰሳ ጽሑፍ አብዛኛዎቹ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች በእርጅና የጐሰቁሉ ናቸው፡፡

‹‹ኢትዮጵያ በዓለም ላይ እስካሁን የተመረቱ ተሽከርካሪዎች ሙዚየም ናት ቢባል ከሃቅ የራቀ አይደለም፤›› በማለት የሚተቹም አልታጡም፡፡

እጅጉን ያረጁና አሁንም ድረስ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች የሚገኙባትና በርካታ ሰዎች በእነዚህ ተሽከርካሪዎች ለአደጋ የተጋለጡባት አገር ስለመሆኑም ይኸው በቅርቡ ለውይይት ቀርቦ የነበረው ጥናት ያመለክታል፡፡       

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች