Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የኢጋድ ነጋዴ ሴቶች ማኅበር መቀመጫ አዲስ አበባ መሆን ከተማዋን የቀጣናው የንግድ ማዕከል ለማድረግ ይረዳናል››

ወ/ሮ እንግዳዬ እሸቴ፣ የኢትዮጵያና የኢጋድ ነጋዴ ሴቶች ማኅበራት ፕሬዚዳንት

የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማኅበር የተቋቋመው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ በዘጠኝ ክልሎችና በሁለት ከተሞች አስተዳደር ውስጥ የሚገኙ 13 ማኅበራትን እንዲሁም የአካል ጉዳተኛ ነጋዴ ሴቶችና የሴት ላኪ ነጋዴ ሴቶች ማኅበርን በማቀፍም ነው የተቋቋመው፡፡ ማኅበሩ፣ የማኅበሩ አባል ያልሆኑትን ጨምሮ ማንኛዋም ነጋዴ ሴት ያለባትን ችግር ለመፍታት ይሠራል፡፡ በተለይ በክልሎች ባሉ ቅርንጫፎች፣ ሴት ነጋዴዎች ንግድ ጀማሪና ሳይሳካላቸው ቀርተው ከንግዱ እንዳይወጡ የመምራት ክህሎት ሥልጠና ይሰጣል፡፡ በሥሩ ያሉት ማኅበራት ደግፎ በመያዝ፣ ወደ መካከለኛ ያደጉ ሴት ነጋዴዎች ምርታቸው ሳይነሳ ቀርቶ ችግር ላይ እንዳይወድቁ፣ በየማኅበሮቻቸው በኩል ሥልጠና እንዲያገኙም ያግዛል፡፡ የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማኅበር ዓላማው ሁሉም ነጋዴ ተያይዞ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክትበትን ሁኔታ ማመቻቸትና ችግሮች የሚፈቱበትን መንገድ ማፈላለግ ነው፡፡ ከጉሊት ነጋዴ ጀምሮ እስከ ላኪዎች ባሉ እርከኖች የቅብብሎሽ መስመር እንዲዘረጋ የማስተባበር ሥራም እየሠራ ይገኛል፡፡ በሴት ነጋዴዎች በኩል ያሉ ችግሮች በብዛት የሚፈቱት በመንግሥት አካላት ስለሆነ፣ ከእነሱ ጋርም አብረው ይሠራሉ፡፡ የፋይናንስ ችግር ላለባቸው ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በማስተሳሰርና በግብር ነክ ችግሮች ዙሪያም ይሠራሉ፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ማኅበሩ የኢጋድ ሴቶች ማኅበር እንዲመሠረትና ጽሕፈት ቤቱም አዲስ አበባ እንዲሆን ከመንግሥት ጋር በመሆን ሚና ተጫውቷል፡፡ ወ/ሮ እንግዳዬ እሸቴ የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማኅበርና በቅርቡ የተቋቋመው የኢጋድ ነጋዴ ሴቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- የኢጋድ ነጋዴ ሴቶች ማኅበር ሰሞኑን ተመሥርቷል፡፡ ሒደቱ ምን ይመስል ነበር?

ወ/ሮ እንግዳዬ፡- የኢጋድ በይነ መንግሥታት የልማት ጽንሰ ሐሳብ ሴቶችንም ይመለከታል፡፡ በመሆኑም እ.ኤ.አ. በ2012 የመጀመርያውን ስብሰባ በኢጋድ አስተናጋጅነት ሱዳን ካርቱም ላይ አድርገናል፡፡ ሁለተኛውን ስብሰባ ኡጋንዳ ላይ በ2014፣ ሦስተኛውን ደግሞ በ2015 መግቢያ ላይ ኬንያ አካሂደናል፡፡ በሦስቱ ስብሰባዎች ላይ መሠረታዊ ሆኖ የተነሳው በኢጋድ አባል አገሮች የሚገኙ ነጋዴ ሴቶችንና የነጋዴ ሴቶች ማኅበራትን የሚያስተሳስር መደላድል (ፕላትፎርም) ይቋቋም የሚል ነበር፡፡ ፕላትፎርም ለማቋቋም ሰባቱም አባል አገሮች ተስማሙ፡፡ ሶማሊላንድም እንደ አንድ ክልል ሆና ተቀላቅላ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ የተካሄደው የአውሮፓ ኅብረት ለኢጋድ በሰጠው ፈንድ ነው፡፡ የእያንዳንዳችንን አገር የንግድ ሕግ በመመርመር በተለይ በምሥራቅ አፍሪካ ያለውን የንግድ ትስስር ለማጠናከርና የሴቶችን አቅም ለማጎልበት ታስቦ የተደረገ ነው፡፡ አራተኛውን ስብሰባ ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ ኃላፊነቱን ወስጄ ነው ከሦስተኛው ስብሰባ የተመለስኩት፡፡ ሐሳቡን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቀረብን፡፡ ሚኒስቴሩ ቀድመን የተሰበሰብናቸውን አጀንዳዎች እንደማስረጃ በመያዝ ፈቃድ ሰጠን፡፡ ከጎናችን በመቆምም በጋራ ሆነን የኢጋድ ነጋዴ ሴቶች ማኅበርን ለመመሥረት ቻልን፡፡

ሪፖርተር፡- ጽሕፈት ቤቱ አዲስ አበባ እንዲሆን የማኅበራችሁ ሚና ምን ነበር?

ወ/ሮ እንግዳዬ፡- ኢትዮጵያ የኢጋድ ሊቀመንበር ናት፡፡ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ደግሞ የኢጋድ ቢዝነስ ፎረም አላቸው፡፡ ጽሕፈት ቤቱም ኡጋንዳ ነው፡፡ በእኛ በኩል የኢጋድ ነጋዴ ሴቶች ማኅበር አቋቁመናል፡፡ የተቋቋመው በኢጋድ ሐሳብ አመንጪነትና ፍላጎት ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ ጽሕፈት ቤቱም አዲስ አበባ ላይ ሆኗል፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያ ያሏት የተመቻቸ የድንበር የንግድ ሕጎች በአጠቃላይም መልካም የንግድ ፖሊሲዎች መኖራቸው ትልቁን ሚና ተጫውቷል፡፡ የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማኅበርም ተነሳሽነቱን በኃላፊነት ወስዶ ነው ጽሕፈት ቤቱን አዲስ አበባ ያደረግነው፡፡ ጥሩ ፖሊሲ ካለ አገሮችም፣ አህጉርም ማደግ ይችላሉ፡፡ አሁን ላይ ምሥራቁን ክፍል ብንይዝም ሲስፋፋ መላ አፍሪካን እናጠቃልላለን ብለን እናስባለን፡፡

ሪፖርተር፡- የኢጋድ ነጋዴ ሴቶች ማኅበር መመሥረት ለኢትዮጵያ እንዲሁም ለአባል አገሮች ነጋዴ ሴቶች ያለውን ጠቀሜታ ቢያብራሩልን?

ወ/ሮ እንግዳዬ፡- አገሪቷ ካላት 51 በመቶ የሴቶች ቁጥር 35 በመቶ ያህሉ ከጉልት ጀምሮ እስከ ትልቅ ንግድ የተሰማሩ ናቸው፡፡ የእኛ ምርቶች በአብዛኛው ወደ ጓዳ የሚገቡና የሚባክኑ ናቸው፡፡ አሁን ግን እንደ አገርም እንደ ማኅበርም፣  እጅ ለእጅ ተያይዞ ምርት በሚፈለግበት ቦታ ላይ፣ አዲስ በተመሠረተው የኢጋድ ማኅበር አማካይነት ወደ ውጭ ለመላክና ከውጭ ልምድና ቴክኖሎጂን ለመለዋወጥ እንችላለን፡፡ ያለንን አካፍለን የሌለንን ለማምጣት መንገድ ይሆነናል፡፡ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓና ከእስያ በተለያዩ የቴክኖሎጂ ሽግግሮች ተጠቃሚ እየሆነች፣ ዕድገትም እያስመዘገበች ነው፡፡ ይህንን ተጠቅመን ሴቶች ገበያ ተኮር ወደሆኑ ምርቶች እንዲገቡና የአገርና የራሳቸውን ኢኮኖሚ እንዲያሳድጉ ዕድል ይፈጥራል፡፡ የጽሕፈት ቤቱ አዲስ አበባ መሆንም በምሥራቅ አፍሪካ አዲስ አበባን ዋና የንግድ ቀጣና ለማድረግ ይጠቅመናል፡፡ የሌሎቹን አባል አገሮች ነጋዴ ሴቶችም በየአባል አገሮቹ በሚያደርጉት የንግድ ልውውጥ ድርብ ታክስ ያስቀርላቸዋል፡፡ በዚህም ሴቶቹ ተጠቅመው የየአገራቸውን ኢኮኖሚ ያሳድጋሉ፡፡ ኢጋድ አባል አገሮቹ እርስ በርስ እንዲተሳሰሩ ከሚያደርጋቸው ስምምነቶች በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያ በድንበር አካባቢዎች እያደረገች ያለችው የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ለድንበር አካባቢ ንግዱም መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ በ2017 ዓ.ም. ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ለማሰለፍ መንግሥት እያከናወነ ያለውን ተግባር ሴት ነጋዴዎችም በማገዝ ዕቅዱን ዕውን ማድረግ፣ የበለጠ ውጤት ለማምጣትና አገራችንንና አህጉራችንን ለማሳደግ እንችላለን፡፡ ምሥራቅ አፍሪካ ለሌሎቹም የአፍሪካ ክፍሎች ትልቅ ምሳሌ መሆን እንድትችል እየተንቀሳቀስን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ህልማችሁን ለማሳካት ከጎናችሁ የሚያግዛችሁ ማነው?

ወ/ሮ እንግዳዬ፡- ዓላማችንን ለማሳካት ከኬንያ፣ ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከጂቡቲ፣ ከኡጋንዳ፣ ከሶማሊያና ከአገራችን ያሉት ጠንካራ ዕውቀቱና አቅሙ ያላቸው ወገኖች በመያዝ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ በተማሩትና ዕውቀቱ ባላቸው በመጠቀምም የዕድገት አድማሳችንን እናሰፋለን ብለን አስበናል፡፡

ሪፖርተር፡- በየአገራቸው ያሉ ሴት ነጋዴዎች በራሳቸው ጥምረት ፈጥረው ከሚሠሩት በተጨማሪ ከአባል አገሮቹ ሴት ነጋዴዎች ጋር በመጣመር የተሻለ የንግድ ድርጅት የሚፈጥሩበትን መንገድ የኢጋድ ማኅበር ያመቻቻል?

ወ/ሮ እንግዳዬ፡- አጎዋ ከቀረጥ ነፃ የንግድ ዕድል ሰጥቷል፡፡ ይህ ቢሆንም አሜሪካ የምትፈልገውን ምርቶች ለማቅረብ አንዱ ችግር የአቅርቦት ወይም የምርት ማነስ ነው፡፡ የኢጋድ ነጋዴ ሴቶች መመሥረት አንዱ ምክንያትም፣ እርስ በርስ ተጠናክረንና አንድ ላይ ሆነን በየግል ደረጃ የሚገጥመንን የአቅርቦት ማነስ ችግር በጋራ ሆነን ለመስበር ነው፡፡ ከአባል አገሮቹ ነጋዴዎች ጋር በመጣመር በአጎዋ በሚፈቀደው ከቀረጥ ነፃ ገበያ ተሳታፊ እንሆናለን፣ እናቀርባለን ብለን እናምናለን፡፡ ይህ ማለት የበለጠ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል፡፡ አፍሪካ ላይ ያለው ምርት አብዛኛው የተፈጥሮ በመሆኑና ተፈላጊም ስለሆነ ያለንን ዕድል በተቻለ መጠን አጠናክረን ገበያውን ለማስኬድ ማኅበራችን ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡   

ሪፖርተር፡- አብዛኞቹ ምርቶች ወደ ጓዳ የሚገቡና የሚባክኑ ናቸው ብለዋል፡፡ በአነስተኛና ጥቃቅን የተሰማሩት ሴቶች ደግሞ አብዛኛው ምርቶቻቸው ለአገር ውስጥ ፍጆታ ከሚሆኑ ምግቦች የዘለሉ አይደሉም፡፡ ሴቶች ምን ዓይነት ምርት ይዘው ወደ ኢጋድ አባል አገሮች ንግድ ሊቀላቀሉ ይችላሉ? ሴቶቻችን የሚያመርቱትና በአባል አገሮቹ መካከል ያለው የባህል ልዩነትንስ እንዴት ታስታርቁታላችሁ?

ወ/ሮ እንግዳዬ፡- ባህላችንን ከንግድ አቅርቦታችን ጋር እንዴት አጣጥመን እንሠራለን? በሚለው የኢጋድ ነጋዴ ሴቶች ማኅበርን በመሠረትን ማግሥት ከአባል አገሮች ተወካዮች ጋር አዲስ አበባ ላይ ጉብኝት አድርገን ተወያይተን ነበር፡፡ በዚህም መሠረት እያንዳንዱ አባል አገር በየአገራቸው ሊቀርብ ስለሚፈልጉት ምርት ጽፈው ወደ ጽሕፈት ቤቱ እንዲልኩ ተስማምተናል፡፡ ሲልኩልን በፍላጎቱ መሠረት በየክልሉ ላሉ አባላት ጭምር ልከን ከጥራት፣ ከብዛትና ከተመጣጣኝ ዋጋ አንፃር ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ እናደርጋለን፡፡ ለዚህም ሙያዊ ድጋፍ እንዲሰጡንና የገበያ ጥናት እንዲያደርጉልን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጠይቀናል፡፡ ማኅበሩን ከመመሥረት፣ መቀመጫውን በአዲስ አበባ ከማድረግና ቢሮ ከማግኘት ባለፈም አባሎቻችን ተጠቃሚ የሚሆኑበትን የገበያ ቅኝት በሰፊው መታየት አለበት፡፡ በኡጋንዳ ሦስተኛውን ስብሰባ ካደረግን ጀምሮ በኢትዮጵያ ሴት ነጋዴዎች ማኅበር በኩል በየትኛው ዘርፍ ብንሰማራ ያወጣናል በሚለው ዙሪያም እየሠራን ነው፡፡ ምግብ ማምረት ላይ ብቻ የተሰማሩ ሴቶችም ወደ ጎጆ ኢንዱስትሪው ገብተው በብዛት እንዲያመርቱ ማስቻል አለብን፡፡ ከቴክኒክና ሙያ ተማሪዎች ጋር መገናኘትም ግድ ይለናል፡፡ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋርም እንዲሁ፡፡ በተለይ ከዩኒቨርሲቲዎቻችን ጋር ግንኙነት እየፈጠርን ነው፡፡ ሴቶቻችን ለምን እንደሚፈለገው ማደግ አቃታቸው? ችግሮቻቸውና መፍትሔዎቻቸው ምንድናቸው? በሚለው ላይ እንዲያግዙንም እንፈልጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- በአንድ ምርት ውስጥ የምርት ሰንሰለት መፈጠር ተያይዞ ለማደግ ይረዳል፡፡ በሴት ነጋዴዎች በኩል ይህን ለማምጣት ምን እየሠራችሁ ነው?

ወ/ሮ እንግዳዬ፡- በአገራችን ግለኝነት እየበዛ የሄደ ይመስለኛል፡፡ በተለይ በንግዱ ዘርፍ ኔትወርክ የመፍጠር ሁኔታ አናሳ ነው፡፡ አንድ የቆዳ ኮት ሲሠራ ገበር፣ ቁልፍ፣ ዘለበትና የተለያዩ ግብዓቶችን ይዞ መስፋትና መገጣጠም ይፈልጋል፡፡ በአገራችን በብዛት የተለመደው አንድ የቆዳ ኮት አቅራቢ ሁሉንም ራሱ አሟልቶ ሲያቀርብ ነው፡፡ ሆኖም አንዱ ቆዳውን ቢሰፋ፣ አንዱ ገበር ቢያስገባ፣ አንዱ ቁልፍ፣ አንዱ ዘለበትና ያለቀውን ደግሞ አንዱ ቢሸጥ ተያይዞ ማትረፍና ማደግ ይቻላል፡፡ ሆኖም ይህ አልተለመደም፡፡ እኛም ለሴት ነጋዴዎቻችን ይህንን አላስተማርንም፡፡ ይህ ለእኛ ትልቅ የቤት ሥራ ነው፡፡ በእንጀራ ማቅረብም ሆነ በሌሎች ንግዶች ከመጀመርያ እስከ መጨረሻ ያሉ የምርት ሒደቶችን በሰንሰለት ብንሠራ አትራፊ እንሆናለን፡፡ ግሎባላይዜሽን ልጓም የሌለው ፈረስ በሆነበት በአሁኑ ወቅት አንድን ንግድ ብቻዬን ይዤ እወጣዋለሁ ማለት አያስኬድም፡፡ እርስ በርሳችን ሰንሰለት ወይም ትስስር መፍጠር አለብን፡፡ በኢትዮጵያው ማኅበራችን በኩልም በየክልሉ ያሉ ማኅበራት በሰንሰለታማ የንግድ ሥርዓት እንዲሳተፉ እንሠራለን፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥትም ሆነ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲረዱን እንፈልጋለን፡፡  

ሪፖርተር፡- ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?

ወ/ሮ እንግዳዬ፡- ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ግንኙነት ፈጥረናል፡፡ ባላቸው የማኅበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም እንዲደግፉን እየሠራን ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከሐዋሳ፣ ከጅግጅጋ፣ ባህር ዳርና ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመናል፡፡ ሴት ነጋዴዎች መሠረታዊ ችግራቸው ምንድን ነው? የትምህርት፣ ያለማወቅ፣ የመረጃና የሌሎችም ከሆነ እንዴት ፈትተን ተጠቃሚ እንደምንሆን ካሉት ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር በማዛመድ ሊያግዙን እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁር የተሠራ  ጥናት፣ የኢትዮጵያ ሴት ነጋዴዎች ችግር በኢጋድ አባል አገሮች ውስጥ ካሉት ጋርም ተመሳሳይ እንደሆነ አሳይቷል፡፡ ተመሳሳይ ችግራችንን ከዩኒቨርሲቲዎቻችንና ከምሁራን ማኅበር ጋር በጋራ ሠርተን ለውጥ እናመጣለን ብለን እናምናለን፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ አሶሲዬሽንን ጨምሮ ምሁራንም በሐሳብና በዕውቀት ሊረዱን፣ ሊደግፉንና ሊያሳድጉን ይገባል፡፡ የኢጋድ ነጋዴ ሴቶች ማኅበር አዲስ አበባ ላይ ቢቋቋምም ካልሠራንበት፣ ምሁራንም ካልተሳተፉበት ዋጋ የለውም፡፡

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ሥጋቶች

ዘ ኮንቨርሴሽን ላይ ‹‹What Next for Ethiopia and its...

‹‹ወልቃይት የአማራ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያም እስትንፋስ ነው›› አቶ ዓብዩ በለው፣ የልሳነ ግፉአን ድርጅት ፕሬዚዳንት

ለወልቃይት የአማራ ማንነት መከበር የሚታገለው የልሳነ ግፉአን ድርጅት ፕሬዚዳንት...