የትምህርት ቤቱ ሕንፃዎች ለጊብሰን ዩዝ አካዳሚ ተከራይተዋል
‹‹ጠቅላላ ጉባዔው ያስተላለፈው ውሳኔ የለም››
የትምህርት ቤቱ ቦርድና ጉባዔ ሰብሳቢ
የነገው ሰው ትምህርት ቤት አክሲዮን ማኅበር ጠቅላላ ጉባዔ ኅዳር 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ያሳተፈውን ውሳኔ በመጣስ ቦርዱ ዕርምጃ እየወሰደ ነው በሚል ባለድርሻዎች ተቃውሞ አቀረቡ፡፡ የቦርዱ አባላት ምልዓተ ጉባዔው ባለመሟላቱ የተወሰነ የለም ብለዋል፡፡
ከ18 ዓመታት በፊት በ1990 ዓ.ም. በ101 ባለድርሻዎች የተመሠረተው የነገው ሰው አክሲዮን ማኅበር ‹‹ጥራት፣ ጥልቀትና ምጥቀት ያለው የሚሰጥበት፣ የትምህርት ንግድ ሥራ ማካሄጃ፤›› የሚል ዓላማ ይዞ የተነሳ ቢሆንም ትርፋማ አለመሆኑን ተከትሎ፣ ባለድርሻዎቹ ሕንፃዎቹንና ንብረቶቹን ማከራየት ወይም መሸጥ የሚል መደምደሚያ ውሳኔ ላይ መድረሳቸው ተገልጿል፡፡ በመሆኑም የነገው ሰው ትምህርት ቤት አክሲዮን ማኅበር ጠቅላላ ጉባዔ ኅዳር 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ባደረገው አምስተኛ ድንገተኛ ስብሰባ፣ ባለአክሲዮኖቹ ባቀረቧቸው አማራጮች ላይ ለመወሰን የተፈለገ ቢሆንም በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት 2/3ኛ ድምፅ ማግኘት ባለመቻሉ ‹‹አክሲዮን ማኅበሩ ባለበት፣ በተቋቋመበትና በተሻሻለው ዓላማ መሠረት ሥራውን እንዲቀጥል ወስነናል፤›› በሚል ጉባዔው ውሳኔውን ያፀደቀ ቢሆንም፣ ቦርዱ ውሳኔውን በመጣስና ከባለአክሲዮኖቹና ከጠቅላላ ጉባዔው ዕውቅና ውጭ የትምህርት ቤቱን ሕንፃና መጠቀሚያ መሣሪያዎቹን ‹‹ጊብሰን ዩዝ አካዳሚ›› ለሚባል ድርጅት ለአሥር ዓመታት ማከራየቱን ባለድርሻዎቹ ተቃውመዋል፡፡
ኅዳር 25 ቀን 2008 ዓ.ም. አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ መደረጉን ያረጋገጡት የነገው ሰው ትምህርት ቤት አክሲዮን ማኅበር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አምደ ሚካኤል ተክሌ፣ ‹‹በወቅቱ ትምህርት ቤቱ ወይም አክሲዮን ማኅበሩ ባለበት፣ በተቋቋመበትና በተሻሻለው ዓላማ መሠረት ሥራውን ይቀጥል፤›› የሚል የተወሰነ ውሳኔ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ በዕለቱ አምስተኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ የተደረገው የአክሲዮን ማኅበሩን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ተመካክሮ ለመወሰን፣ የማኅበሩን የአንድ አክሲዮን ዋጋ ለመወሰንና የማኅበሩን መመሥረቻ ጽሑፍ አንዳንድ አንቀጾችን ለማሻሻልና ለመወሰን እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የጉባዔው 2/3ኛ ድምፅ ሊሟላ ባለመቻሉ ውይይቱም አለመደረጉን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የማኅበሩ ዳይሬክተሮች ቦርድ በመተዳደሪያ ደንቡ የመሸጥ፣ የመለወጥና የማከራየት ሥልጣን ስላለው ላለፉት 20 ዓመታት ያለምንም ትርፍ ሲንቀሳቀስ የነበረውን ማኅበር ለሁሉም ባለድርሻ ጠቃሚ በሆነ መልኩ ማከራየቱን አቶ አምደሚካኤል ገልጸዋል፡፡ ቦርዱ ትምህርት ቤቱን ለጊብሰን ዩዝ አካዳሚ ከሐምሌ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለአሥር ዓመታት ማከራየቱን የገለጹት አቶ አምደ ሚካኤል፣ እያንዳንዱ ባለድርሻ ለአምስት ዓመታት 30 በመቶ የትርፍ ድርሻ እንደሚያገኝና በቀጣይ አምስት ዓመታት ደግሞ እየጨመረ እንደሚሄድ ገልጸዋል፡፡ አብዛኛው ባለድርሻ ቦርዱ በሠራው ሥራ እጅግ በጣም የተደሰተ መሆኑን ለቦርዱም እየገለጸ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ ጥቂት ከአራት የማይበልጡ የሚሆኑ ባለድርሻዎች ግን መቃወማቸውን አስረድተዋል፡፡ ትምህርት ቤቱን ያከራዩትም በወር 300,000 ብር መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡
የአቶ አምደ ሚካኤልን ሐሳብ የሚቃወሙ ባለድርሻዎች ደግሞ ‹‹የጠቅላላ ጉባዔው ውሳኔ ተጥሷል፤›› ይላሉ፡፡ በማንኛውም የአክሲዮን ማኅበሩ ጉዳይ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠት ኃላፊነት የጠቅላላ ጉባዔው መሆኑን የሚገልጹት ባለድርሻዎቹ፣ ቦርዱ በማን ፍቃድና በምን ሁኔታ የጉባዔውን ውሳኔ ጥሶ ማከራየት እንደቻለ ግራ መጋባታቸውን ተናግረዋል፡፡ ኅዳር 25 ቀን 2008 ዓ.ም. የተካሄደው የባለአክሲዮኖች አምስተኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔ ቃለ ጉባዔ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ተወካይ በተገኙበት የተካሄደና ስለትክክለኛነቱም በጽሕፈት ቤቱ ማኅተም ተረጋግጦ እያለ፣ ቦርዱ ይኽንን ሁሉ በማለፍ የፈጸመው ተግባር አግባብ ባለመሆኑ ከማኅበሩ ጠቅላላ ጉባዔ ውጭ የተደረገው የኪራይ ውል ባስቸኳይ እንዲፈርስ ጠይቀዋል፡፡
ባለድርሻዎቹ ለአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ፣ ለቦሌ ክፍለ ከተማ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ጽሕፈት ቤት፣ ለሰነዶችና ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤትና ለፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በደብዳቤ እንዳሳወቁት፣ ቦርዱ ከጊብሰን ዩዝ አካዳሚ ጋር ያደረገው የኪራይ ውል ሕገወጥ ከባለድርሻዎቹ ተደብቆ በሚስጥር የተደረገ በመሆኑ ክትትል ተደርጎበት ውሉ እንዲቋረጥና የሕዝብን ንብረት ከብክነት በመከላከል በኅብረት ሠርቶ በኅብረት ለማደግ መጥፎ ምሳሌ እንዳይሆን እንዲስተካከል ጠይቀዋል፡፡
አክሲዮን ማኅበሩ ከ500 በላይ አባላትና የተከፈለ 34,970,500 ብር ካፒታል ሲኖረው፣ 33,952 አክሲዮኖችን የሸጠ ማኅበር መሆኑንም አክለዋል፡፡ ቦርዱ የጉባዔውን ውሳኔ ወደ ጎን በመተውና ሕገወጥ ተግባር መሆኑንም እያወቀ ‹‹የመተዳደሪያ ደንቡ በሰጠኝ ሥልጣን መሠረት፤›› በማለት ሙሉ የትምህርት አገልግሎት መስጫ ሕንፃዎችንና ግቢውን ሚያዝያ 3 ቀን 2008 ዓ.ም. በተደረገ ውል ለጊብሰን ዩዝ አካዳሚ ማከራየቱ ሕገወጥና የወደፊት የባለድርሻዎችን ሀብትም ችግር ላይ የሚጥል በመሆኑ ውሉ እንዲቋረጥ ደጋግመው ጠይቀዋል፡፡
በ6,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያለን ትምህርት ቤት በ300 ሺሕ ብር ያለጨረታ ለአንድ ድርጅት ማከራየት ተገቢ አለመሆኑን ባለድርሻዎቹ ተናግረው፣ በግልጽ ጨረታ ቢከራይ የተሻለ ዋጋ ከመከራየቱም በተጨማሪ ባለድርሻውም አውቆት ፍላጎት መኖር አለመኖሩም በዚያም ይረጋገጥ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ እንዴት እንደተከራየና ውሉ እንደተፈጸመ በቀጣይ በሕግ የሚኬድበት ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ባለድርሻዎቹ፣ ተከራዩ ድርጅት ግን ቦርዱ ሕግ ጥሶ እንዳከራየው ከወዲሁ ተገንዝቦ ውሉን እንዲያፈርስ ጠይቀዋል፡፡