በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በሀገረማርያም ወረዳ በሚገኘው በቱሉፋ ቀበሌ በ100 ሚሊዮን ዶላር ዘመናዊና ግዙፍ የመድኃኒት ፋብሪካ ግንባታ ሥራ ከሰኔ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ይካሄዳል፡፡
የመድኃኒት ፋብሪካውን በባለቤትነት የሚያስገነባው ሂውማንዊል ፋርማሲውትካል ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ነው፡፡ ከአዲስ አበባ 55 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው በቱሉፋ ቀበሌ ሰባት ሔክታር መሬት ላይ ለሚያርፈው ለዚሁ ሕንፃ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ የማስቀመጡ ሥነ ሥርዓት ግንቦት 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ተከናውኗል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር መብራቱ መለሰ የመሠረቱን ድንጋይ ካኖሩ በኋላ፣ በ2010 ዓ.ም. የአገሪቱ የመድኃኒት ገበያ እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ መገመቱን ገልጸዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ 80 ከመቶ የሚሆነው መድኃኒት ከውጭ እንደሚገባ፣ በአገሪቱ ያሉት የመድኃኒት ፋብሪካዎችም እያቀረቡ ያሉት እስከ 20 በመቶ ያለውን ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ታዋቂ የሆነው ይህ ፋብሪካ ወደ ሥራ የገባው የራሱን በጀት ይዞ ሲሆን፣ ግንባታውንም የሚያካሂደው ከባንክ ሳይበደር በራሱ ወጪ ነው፡፡ በኤዥያ፣ በአሜሪካ፣ በአውሮፓና በአፍሪካ በበርካታ አገሮች እየሠራ የሚገኝ ኩባንያም ነው፡፡
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፣ በአገሪቱ የአሥር ዓመት የመድኃኒት ኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ተነድፏል፡፡ ከዚህም ውስጥ የአምስት ዓመቱ ስትራቴጂ ተግባራዊ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም ስትራቴጂ ከተቀመጡት ዋና ዋና ፕሮግራሞች መካከል አንደኛው ኢንቨስትመንትን ከአገር ውስጥና ከውጭ የመሳብ ሥራ ሲሆን፣ ሁለተኛው ፕሮግራም ደግሞ ባለሀብቶችን ለመሳብ የሚያስችል የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በየአካባቢው እንዲስፋፉ ማድረግ ነው፡፡
በዚህም መሠረት አዲስ አበባ ውስጥ ቦሌ ለሚ አካባቢ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ እንደተጀመረ፤ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሐዋሳ ከተማ በመገንባት ላይ ያለው ፓርክ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ተጠናቆ ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ በአማራ ክልል በኮምቦልቻ ከተማ፣ በትግራይ ክልል በመቀሌ ከተማ በዘጠኝ ወራት ውስጥ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ይገነባሉ፡፡
የፕሮጀክቱ ኮንትራክተር የቻይናው ጋንሰን ኢንተርናሽናል ኮንስትራክሽን ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ቫን ጆንግ፣ በአሁኑ ወቅት በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋሉትን ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም ግንባታውን በጥራት አከናውነውና በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ጨርሰው ለማስረከብ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ዋና መሥሪያ ቤቱ ቻይና የሚገኘው የሂውማንዊል ፋርማሲውቲካል ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ኩባንያው በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰፊ ልምድና ተሞክሮ እንዳለው ገልጸው፣ ያለውንም ልምድ ይዞ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣቱ ደስተኛ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
አቶ ንጉሴ ጉቻለ የሀገረማርያም ወረዳ አስተዳዳሪ በወረዳው ውስጥ ትልቅ የኢንቨስትመንት መንደር ለመመሥረት የሚያስችል ዝግጅት በመከናወን ላይ መሆኑን፣ በተለይም የቱሉፋ ቀበሌ ለአዲስ አበባና ለደብረ ብርሃን ከተሞች ቅርብ በመሆኑ የተነሳ ለፋብሪካው መገንባት ተመራጭ እንዳደረገው ገልጸዋል፡፡
በዚህም የተነሳ በዚሁ ቀበሌ የፕሮጀክት ሐሳብ አቅርበውና መሬት ተሰጥቷቸው በሥራ ላይ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ቁጥር ወደ 50 መድረሳቸውን አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡
የፋብሪካው ግንባታ በሦስት ደረጃ የሚካሄድ ሲሆን፣ አጠቃላይ ሥራው ግን በአንድ ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ፋብሪካው ሽሮፕ፣ ክኒን፣ ካፕሱልና መርፌ እንደሚያመርት ታውቋል፡፡