የዓባይ ባንክ አክሲዮን ማኅበር ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (አይቲ) ክፍል፣ የአፕሊኬሽንና ኢንፍራስትራክቸር ሥራ አስኪያጅ 440,000 ብር ከተለያዩ ደንበኞች ተቀማጭ ሒሳቦች ላይ ወደራሳቸው በመውሰድ ተጠርጥረው ግንቦት 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተባቸው፡፡
ተጠርጣሪው አቶ በረከት በርሄ፣ በሌላ ሰው ጥቅም ወይም መብት ላይ ጉዳት ለማድረስና ለራሳቸው ጥቅም ለማስገኘት በማሰብ ከባንኩ ደንበኞች ተቀማጭ ገንዘብ ላይ ወጪ በማድረግ፣ ደንበኞቹ ካላቸው ገንዘብ ላይ ወጪ እንዳያደርጉ መቆጣጠር የሚያስችለውን ሲስተም በመቀየር ከጥቅምት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያቶች የተጠቀሰውን ገንዘብ ወጪ ማድረጋቸውን፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የመሠረተው ክስ ያስረዳል፡፡
ሥራ አስኪያጁ በመልቲ ቻናል ፈንድ ትራንስፈር፣ በኤቲኤም፣ በሞባይል ባንኪንግና ሌሎችም የክፍያ መንገዶችን በመጠቀም ድርጊቱን መፈጸማቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ አቶ በረከት፣ ገንዘቡን ወጪ ካደረጉ በኋላ ደንበኛው ካለው ተቀማጭ ላይ ወጪ በማድረጋቸው በቁጠባ ሒሳቡ ላይ የሚታየውን ያልተለመደ የሒሳብ ሚዛን (Over Drown Balance) እና በባንኩ ዋና ቅርንጫፍ ሊታይ የሚችለውን የጥሬ ገንዘብ የሒሳብ ሚዛን ልዩነት ለማስተካከል፣ የሌሎችን ደንበኞችን ሒሳብ ወደፊት በማንቀሳቀስና ወደኋላ በመመለስ በሲስተሙ ሲጠቀሙ መቆየታቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ ሥራ አስኪያጁ፣ የባንኩ ደንበኛ የሆነውን ሳምጌት ጠቅላላ ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት አገልግሎት ጠይቆ ክፍያ የወሰደባቸውን ሁለት ቼኮች በድጋሚ በሕገወጥ መልኩ መጠቀማቸውንና ወደራሳቸው ሒሳብ ገንዘቡን ማሳለፋቸውን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡