Friday, February 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የተሻሻለው የገቢ ግብር አዋጅ ዝቅተኛ ገቢ የሚያገኘውን ኅብረተሰብ ተጠቃሚ አላደረገም ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የገቢ ግብር አዋጅ ማሻሻያ፣ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ሲገለጽ ቢቆይም፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ያዘጋጀው ረቂቅ የገቢ ግብር ምጣኔ ዝቅተኛ ገቢ የሚያገኘውን የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ አለማድረጉ ተመለከተ፡፡

ግንቦት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ለሕዝብ ይፋ የተደረገው የገቢ ግብር አዋጅ ረቂቅ ማሻሻያ፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ በሰፊው መነጋገሪያ ሆኖ ከመገኘቱ በተጨማሪ፣ የንግድ ሥርዓቱን እንዳያናጋ ሥጋት ፈጥሯል፡፡

የገቢ ግብር አዋጅ ላይ ማሻሻያ እንደሚደረግ ከተገለጸ ወዲህ ግብር የሚከፍለው የኅብረተሰብ ክፍል በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያለው የተሻለ ገቢ እንደሚያገኝ ሲጠብቅ ቆይቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ከሁለት ዓመት በፊት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የገቢ ግብር አዋጁ በሚሻሻልበት ወቅት ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል የሚጠቅም እንደሆነ ገልጸው ነበር፡፡ ነገር ግን ለሪፖርተር ሐሳባቸውን የገለጹ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ከገቢ ግብሩ መቀነስ ይልቅ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት በመሥጋት ላይ ናቸው፡፡

መንግሥት በጥቅሉ በገቢ ግብር ማግኘት የሚችለውን ገቢ በመተው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያጣል፡፡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትሩ አቶ አብዱልአዚዝ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚቀጥለውን ዓመት ረቂቅ በጀት ባቀረቡበት ወቅት የተያዘው በጀት 274.3 ቢሊዮን ብር ከፍተኛ የሚባል ነው፡፡ ይህ በጀት ካለፈው ዓመት በ50 ቢሊዮን ብር ይልቃል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው የገቢ ግብር አዋጅ ተግባራዊ ስለሚሆን ጭምር ነው ብለዋል፡፡

ነገር ግን አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት፣ መንግሥት ከፍተኛ ገቢ የሚያጣ ቢሆንም በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል ቀመር አይደለም፡፡

ለአብነት የሰባት መቶ ብር ደመወዝተኛ ቀደም ሲል የሚከፍለው የገቢ ግብር 57 ብር ከ50 ሳንቲም ነው፡፡ አሁን በተዘጋጀው የአዋጁ ረቂቅ ማሻሻያ፣ ለመንግሥት የሚከፍለው የገቢ ግብር 11 ብር ከ50 ሳንቲም ነው፡፡ ስለዚህ ባለሰባት መቶ ብር ደመወዝተኛ ከቅናሹ የሚያተርፈው 46 ብር ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡፡

የሁለት ሺሕ ብር ደመወዝተኛ፣ ቀደም ሲል የሚከፍለው ግብር 282 ብር ከ50 ሳንቲም ነው፡፡ አሁን በተደረገው ማሻሻያ ረቂቅ መክፈል የሚጠበቅበት 158 ብር ሲሆን፣ ተጠቃሚ የሚሆነው በ124 ብር ከ50 ሳንቲም ነው፡፡

የ3,400 ብር ደመወዝተኛ ቀደም ሲል 615 ብር የገቢ ግብር መክፈል ይጠበቅበታል፡፡ በአዲሱ ረቂቅ አዋጁ 381 ብር ከ75 ሳንቲም ሲሆን፣ የሚያገኘው ጥቅም 233 ብር ከ25 ሳንቲም ነው፡፡

የ6,000 ብር ደመወዝተኛም ቀደም ሲል 1,437 ብር ከ50 ሳንቲም መክፈል ይጠበቅበት ነበር፡፡ በአዲሱ ማሻሻያ ረቂቅ 942 ብር መክፈል የሚጠበቅበት ሲሆን፣ ጥቅሙ 495 ብር ከ50 ሳንቲም ነው፡፡

የአሥር ሺሕ ብር ደመወዝተኛ ደግሞ ቀደም ሲል 2,837 ብር ከ50 ሳንቲም መከፈል ይጠበቅበታል፡፡ አሁን 2054 ብር ከ10 ሳንቲም ዝቅ የተደረገ ሲሆን ልዩነቱ 783 ብር ከ40 ሳንቲም ነው፡፡

ከ10,833 ብር በላይ ደመወዝተኛ የሆኑ መክፈል የሚጠበቅባቸው 35 በመቶ ነው፡፡ ይህ ስሌት እነዚህ ከፍተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ገንዘብ በጥቅሉ 825 ብር ከ05 ሳንቲም ነው፡፡ ረቂቅ አዋጁ ከገቢ ግብር ነፃ ያደረገው ከ585 ብር ድረስ ያሉትን ብቻ ነው፡፡

ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ከገቢ ግብር ቅነሳው ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገምተው የነበረ ቢሆንም፣ ብዙም ለውጥ የሌለው የገቢ ግብር ቅነሳ መደረጉን ይናገራሉ፡፡

እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች እያነሱ የሚገኙት ሥጋት ደግሞ የንግዱ ማኅበረሰብ ይህንን የገቢ ግብር ዝቅተኛ ቅናሽ እንደለውጥ ተመልክቶ በሸቀጦችና በመኖርያ ቤት ኪራይ ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዳያስከትል ነው፡፡

በዚህ ረቂቅ ላይ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ውይይት እንደሚደረግና ከውይይቱ የሚገኝ ግብዓት ታክሎ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ ይጠበቃል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከተቀበለውና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካፀደቀው ከሐምሌ 1  ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተመልክቷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች