Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናለ2009 ዓ.ም. 274.3 ቢሊዮን ብር በጀት ቀረበ

ለ2009 ዓ.ም. 274.3 ቢሊዮን ብር በጀት ቀረበ

ቀን:

         መንገዶች ትምህርትና ዕዳ ክፍያ ትልቁን ድርሻ ይዘዋል

  • ለምህራን የደረጃ ዕድገት አምስት ቢሊዮን ብር ተይዟል
  • ከ2008 በጀት ውስጥ እስካሁን የተሰበሰበው 65 በመቶ ብቻ ነው

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ አቶ አብዱላዚዝ አህመድ የ2009 ዓ.ም. የአገሪቱ አጠቃላይ በጀት 274.3 ቢሊዮን እንዲሆን ዝርዝር የበጀት ረቂቅ አዋጅ ግንቦት 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቀረቡ፡፡

አቶ አብዱላዚዝ ያቀረቡት ረቂቅ የበጀት ሰነድ የ2009 ዓ.ም. አጠቃላይ የአገሪቱ በጀት 274.373 ቢሊዮን ብር ሆኖ መዘጋጀቱን ይህም ከ2008 በጀት በ32.9 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ያሳያል፡፡

ከቀረበው አጠቃላይ በጀት ውስጥ ለመደበኛ ወጪ 68.7 ቢሊዮን ብር፣ ለካፒታል ወጪ 105.7 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ለክልል መንግሥታት ድጋፍ 87.8 ቢሊዮን ብርና ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ  12 ቢሊዮን ብር ተደግፎ ቀርቧል፡፡

ለመደበኛ ወጪ ከተደገፈው 68.7 ቢሊዮን ብር ውስጥ 53.6 በመቶ ወይም 13.9 ቢሊዮን ብሩ የተያዘው ለዕዳ ክፍያ ሲሆን፣ 19 በመቶ የሚሆነው 5 ቢሊዮን ብር ደግሞ ለመምህራን ደረጃ ማሳደጊያ ተደግፎ ቀርቧል፡፡

ለካፒታል ወጪ ከቀረበው 105.7 ቢሊዮን ብር ውስጥ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጣቸው የመንገዶች ግንባታና ጥገና፣ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታና ነባሮቹን ለማጠናከር፣ ለመስኖ ልማትና ግድቦች ይገኙበታል፡፡

በመሆኑም በሁለቱም የወጪ ርዕሶች ማለትም የመደበኛና የካፒታል ወጪዎች በድምሩ 174.5 ቢሊዮን ብር ውስጥ መንገዶች 46.39 ቢሊዮን ብር በመሆን ትልቁን ድርሻ ሲይዝ፣ ትምህርት 39.7 ቢሊዮን ብር፣ ዕዳ ክፍያ 13.93 ቢሊዮን ብርና መከላከያ 11 ቢሊዮን ብር በመሆን ተከታትለዋል፡፡

ከመከላከያ ውጪ የፍትሕና ደኅንነት ተቋማት 5.4 ቢሊዮን ብር፣ የከተማ ልማትና ቤቶች 2.7 ቢሊዮን ብር፣ የገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን አንድ ቢሊዮን ብር ተመድቦላቸዋል፡፡

ለክልል መንግሥታት ከቀረበው 87.8 ቢሊዮን ብር የበጀት ድጋፍ ውስጥ ኦሮሚያ ክልል 28.5 ቢሊዮን ብር፣ አማራ ክልል 20.4 ቢሊዮን ብር፣ የደቡብ ክልል 17.6 ቢሊዮን ብር፣ ለትግራይ ክልል 6.2 ቢሊዮን ብር ተደግፎ ቀርቧል፡፡

አቶ አብዱላዚዝ አህመድ ባደረጉት የበጀት ንግግር (በፓርላማው አሠራር መሠረት) የ2008 የበጀት አፈጻጸምና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን ዳሰዋል፡፡

በ2008 ዓ.ም. ለፀደቀው 241.8 ቢሊዮን ብር ውስጥ ትልቁ የገቢ ምንጭ የአገር ውስጥ ታክስና ታክስ ያልሆኑ የገቢ ዓይነቶች መሆናቸው ይታወቃል፡፡

በመሆኑም የወጪ በጀቱን ለመሸፈን በዘጠኝ ወራት ውስጥ የተሰበሰበው 97.4 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም በዓመት ውስጥ እንደሚሰበሰብ ከታቀደው 65 በመቶ ብቻ ነው፡፡

አቶ አብዱላዚዝ ‹‹ይህ አፈጻጸም ባለፉት ዓመታት ከታየው ያነሰ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ለአጠቃላይ ታክስ ገቢ አሰባሰቡ ማሽቆልቆል በምክንያትነት በተለየ ሁኔታ የተጠቀሰው የተጨማሪ እሴት ታክስ ዝቅተኛ አፈጻጸም ነው፡፡

ሚኒስትሩ ያቀረቡት ሰነድ ከአገር ውስጥ ምርት ተጨማሪ እሴት ታክስ በበጀት ዓመቱ 16.1 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱና በዘጠኝ ወራት ማለትም እስከ መጋቢት 2008 ዓ.ም. ድረስ መሰብሰብ የተቻለው 8.2 ቢሊዮን ብር መሆኑን ያሳያል፡፡ ይህም በበጀት ዓመቱ ሊያልቅ የሦስት ወራት ዕድሜ እየቀሩት መሰብሰብ የተቻለው 51 በመቶ ያህሉን ብቻ እንደሆነ ሰነዱ ያብራራል፡፡

በዘጠኝ ወራት ከአገር ውስጥ ምርት የተጨማሪ እሴት ታክስ የተሰበሰበው ከ2007 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በ23 በመቶ ማሽቆልቆሉን ያሳያል፡፡ በአገር ውስጥ ምርት ተጨማሪ እሴት ታክስ ገቢ ማሽቆልቆል የምርት ሒደት ላይ ችግር መኖሩን የሚያሳይ መሆኑን ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በውጭ አገር የበጀት ድጋፍ 1.07 ቢሊዮን ብር በ2008 ዓ.ም. ይገኛል ተብሎ ከተያዘው ውስጥ በዘጠኝ ወራት ማግኘት የተቻለው 290 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም በ2007 ዓ.ም. ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 2.8 ቢሊዮን ብር 89.9 በመቶ ያንሳል፡፡

ከገቢ አሰባሰብ በተጨማሪ መንግሥትን እንዳሳሰበው ሚኒስትሩ የገለጹት የኤክስፖርት ገበያውና ከዚህ የሚገኘው ገቢ ማሽቆልቆል ነው፡፡

በ2008 በጀት ዓመት በመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት ከወጪ ንግድ 2.04 ቢሊዮን ብር ዶላር የተገኘ ሲሆን፣ በ2007 ዓ.ም. ከተገኘው 2.18 ቢሊዮን ብር በ6.5 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡

‹‹በዘጠኝ ወራቱ ከዕቃዎች ኤክስፖርት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ለዓመቱ ከታቀደው 4 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነፃፀር 51 በመቶ ያህል ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም በሚቀጥሉት ሦስት ወራት የኤክስፖርት አፈጻጸም የተለየ እንቅስቃሴ ካልተደረገ በስተቀር ለዓመቱ የተያዘውን የኤክስፖርት ግብ ለማሳካት አስቸጋሪ እንደሚሆን ከወዲሁ ያመላከተ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይህ ገቢ በማሽቆልቆሉም የአገሪቱ የንግድ ሚዛን ከ16 ቢሊዮን ዶላር በላይ ልዩነት አሳይቷል፡፡

ለ2008 በጀት ዓመት ከፀደቀው 241.3 ቢሊዮን ብር ውስጥ 65.06 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ለመደበኛ በጀት፣ 87.5 ቢሊዮን ብር ደግሞ ለካፒታል በጀት እንዲሁም ለክልል መንግሥታት 76.8 ቢሊዮን ብርና ለዘላቂ ልማቶች ግብ ማጠናከሪያ 12 ቢሊዮን ብር መፅደቁ ይታወሳል፡፡

የበጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ የሦስት ወራት ጊዜ ብቻ በቀረበት በአሁኑ ወቅት የመንግሥት የወጪ አፈጻጸም 145.6 ቢሊዮን ብር ወይም የዓመቱ አጠቃላይ ወጪ 65.7 በመቶ ብቻ ነው፡፡

ለአብነት ለካፒታል ወጪ ከተፈቀደው 87.5 ቢሊዮን ብር ውስጥ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተከፈለው 45.8 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ለመደበኛ ወጪ ከተፈቀደው 65.06 ቢሊዮን ብር ውስጥ በዘጠኝ ወራት የተከፈለው 37.3 በመቶ ብቻ መሆኑን ሰነዱ ያሳያል፡፡

ሰነዱ የዚህን ምክንያት ባይዘረዝርም ከ2007 በጀት ዓመት ከፍተኛ መሆኑን በንጽጽር ያቀርባል፡፡       

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...