Tuesday, October 3, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአዲስ አበባ ያጋጠመው የቤንዚን እጥረት ‹‹ሰው ሠራሽ›› እንደሆነ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከመጠባበቂያ ክምችት ወጪ ተደርጎ ችግሩን ለመፍታት ተሞክሯል

በተለያዩ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ ነዳጅ ገበያ፣ ካለፈው ሳምንት ሰኞ ጥቅምት 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ በተለይ በአዲስ አበባ የቤንዚን እጥረት ገጥሞታል፡፡ የተፈጠረውን እጥረት የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ‹‹ሰው ሠራሽ›› በማለት ሲገልጸው፣ የነዳጅ ዘርፍ ዋነኛ ተዋናዮች ደግሞ ቤንዚን ከወደብ ለማንሳት ረዥም ጊዜ በመውሰዱ የተፈጠረ ችግር ነው ብለውታል፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ሐሙስ ጥቅምት 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ከመጠባበቂያ ነዳጅ ክምችት ወጪ አድርጎ ማሠራጨት ጀምሯል፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአገሪቱ የተፈጠረ የነዳጅ አቅርቦት ችግር የለም፡፡ ‹‹ነገር ግን የነዳጅ ሥርጭት ቁጥጥሩ የላላ በመሆኑ ለሰው ሠራሽ እጥረት እየዳረገ ነው፤›› በማለት የገለጹት አቶ ታደሰ፣ ‹‹ነዳጅ ዋነኛ ስትራቴጂካዊ ምርት በመሆኑ የመንግሥት ቁጥጥርና ክትትል ያሻዋል፤›› ብለዋል፡፡

የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት ከውጭ የተለያዩ ሸቀጦች ወደ አገር ይገባሉ፡፡ ለአብነት ስኳር በሚከፋፈልበት ወቅት የሸማች ማኅበራት ቁጥጥር ያደርጋሉ፡፡ ነዳጅ የስኳርን ያህል ቁጥጥር እየተደረገበት ባለመሆኑ፣ በየማደያው ሳይደርስ ጭምር ይሸጣል በማለት አቶ ታደሰ የችግሩን አሳሳቢነት አስረድተዋል፡፡

‹‹ጂቡቲ አንድ ሊትር ቤንዚን 51 ብር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ 18 ብር ነው፤›› ያሉት አቶ ታደሰ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ሳይገባ ጭምር በየቦታው በሕገወጥ መንገድ እየተሸጠ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይህ ችግር የኢትዮጵያ የነዳጅ ማመላለሻ ትራንስፖርት ባለንብረቶች ማኅበር በቅርቡ ባካሄደው ስብሰባ ላይም ተነስቷል፡፡

የማኅበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ፀጋ አሳመረ በወቅቱ እንደገለጹት፣ ነዳጅ ተጭኖ መራገፍ ባለበት ቦታ ሳይደርስ በየመንገዱ እየተሸጠ ነው፡፡ ይህንን ያደረገው አሽከርካሪ ከፈጸመበት ሥራ ወጥቶ ሌላ ቦታ ለመቀጠር የሚያግደው ባለመኖሩ ችግሩ እየከፋ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ታደሰም እንዲሁ ይህ ሕገወጥ ተግባር በዚሁ ከቀጠለ አገሪቱ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ትገባለች በማለት፣ የመንግሥት ተቆጣጣሪ አካላት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ አሳስበዋል፡፡

የግሉ ዘርፍ የነዳጅ ተዋናዮች እንደሚሉት፣ ነዳጅ ለመጫን ጂቡቲ ሆራይዘን ተርሚናል የደረሱ ከባድ ተሽከርካሪዎች በፍጥነት ጭነው እየወጡ አይደለም፡፡

‹‹የእኛ ተሽከርካሪዎች ሰሞኑን ነዳጅ ጭነው ለመውጣት አንድ ሳምንት ፈጅቶባቸዋል፡፡ በዚያው ልክ በጂቡቲ በኩል ያለው መንገድ የተበላሸ በመሆኑ አዲስ አበባ ለመድረስ የራሱን ጊዜ ይወስዳል፤›› ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የነዳጅ ኩባንያ ኃላፊ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የነዳጅ ማመላለሻ ትራንስፖርት ባለንብረቶች ማኅበርና የኢትዮጵያ የነዳጅ አከፋፋይ ድርጅት ባለንብረቶች የነዳጅ ማጓጓዣና ችርቻሮ ዋጋ ታሪፍ ምጣኔ እንዲያድግ በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡

በተለይ የነዳጅ ማመላለሻ ትራንስፖርት ባለንብረቶች ማኅበር የታሪፍ ጥያቄው ካልተመለሰለት፣ ከ15 ቀናት በኋላ ሥራ ማቆም አድማ እንደሚመታ በቅርቡ ባካሄደው ስብሰባ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች