Saturday, September 23, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለተጓተተው የኮይሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግንባታ ብድር እንዲፋጠን ተጠየቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለኮይሻ ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግንባታ ፕሮጀክት የሚያስፈልገው የኃይድሮና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች ግዥ መዘግየት አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ በመሆኑ፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ከቻይና መንግሥት ጋር በመነጋገር በፍጥነት የኮንሴሽናል ብድር እንዲያመቻች ተጠየቀ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ለገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር በጻፉት ደብዳቤ፣ የኮይሻ ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የኤሌክትሮ ሜካኒካልና የኃይድሮ ሜካኒካል ሥራዎች በመዘግየታቸው በሲቪል ምሕንድስና ሥራ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ከመፍጠሩ ባሻገር፣ በአጠቃላይ የፕሮጀክቱ እንቅስቃሴም እንዲዘገይ እያደረገ ስለሆነ ፕሮጀክቱ ለተጨማሪ ወጪና ተጨማሪ የክፍያ ጥያቄ እያስከተለ ነው ብለዋል፡፡

‹‹የተጀመረው የብድር ጥያቄ የኮንሴሽናል ብድር መሥፈርቶችን ያሟላ መሆኑ እንዲረጋገጥና ስምምነቱ የሚፋጠንበት ሁኔታ ተመቻችቶ ውጤቱ ይገለጽልን፤›› ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው በደብዳቤያቸው ጠይቀዋል፡፡

በጊቤና በኦሞ ወንዞች ላይ የሚገነባው አራተኛው ኮይሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ 2,200 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ማመንጨት አቅም የሚኖረው ሲሆን፣ ለግንባታው 2.5 ቢሊዮን ዩሮ ይፈለጋል ተብሏል፡፡

የዚህ ፕሮጀክት ዋና ሥራ ተቋራጭ ሆኖ ውል የገባው የጣሊያኑ ግዙፍ ኩባንያ ሳሊኒ ኢምሪጂሎ ኤስፒኤ ቢሆንም፣ በፋይናንስ ችግር ምክንያት የኤሌክትሮና የኃይድሮ ሜካኒካል ሥራው ከሳሊኒ ተነጥሎ ወጥቷል፡፡

የኤሌክትሮ ሜካኒካልና የኃይድሮ ሜካኒካል ሥራው ከሳሊኒ ጋር ተካሂዶ ከነበረው ስምምነት ተለይቶ ሲወጣ፣ ወደፊት ክርክር እንዳያስነሳ ጥንቃቄ እንዲደረግ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር መመርያ መስጠቱ ታውቋል፡፡

ሳሊኒ ይህንን የኮይሻ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የተረከበው ያለ ጨረታ ቢሆንም፣ የኤሌክትሮ ሜካኒካልና የኃይድሮ ሜካኒካል ሥራዎችን የሚያካሂድ ኩባንያ ለመምረጥ ጨረታ ወጥቶ የኮንሴሽናል ብድር ማምጣት እንችላለን ያሉ ሰባት ኩባንያዎች ተወዳድረው ነበር፡፡

ከሰባቱ ኩባንያዎች ውስጥ በጊቤ ሦስትና በኮይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ውስጥ የተሳተፈው የቻይና ግዙፍ ኩባንያ ዶንግ ፋንግ ኤሌክትሪክ ኢንተርናሽናል ኮርፖሬሽን አሸንፏል፡፡

የኤሌክትሮና የኃይድሮ ሜካኒካል ሥራዎች በአጠቃላይ 460.8 ሚሊዮን ዶላር የሚፈልጉ መሆኑን፣ በቀጣይ በሚኖሩ ድርድሮች ዋጋው ሊቀንስ እንደሚችል በአብርሃም (ዶ/ር) የተጻፈው ደብዳቤ ያመለክታል፡፡

ነገር ግን ይህ ከቻይና የሚገኘው ብድር በኮንሴሽናል ብድር ሥሌት መሆን ስላለበት፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ይህንኑ በፍጥነት እንዲያመቻች ተጠይቋል፡፡

የኮይሻ ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በደቡብ ክልል በዳውሮና በወላይታ ዞኖች፣ እንዲሁም በኮንታ ልዩ ወረዳ መካከል ይገኛል፡፡

የፕሮጀክቱ የሲቪል ምሕንድስና እየተካሄደ ቢሆንም፣ የኤሌክትሮና የኃይድሮ ሜካኒካል ሥራዎች ጎን ለጎን እየተካሄደ ባለመሆናቸው፣ በፕሮጀክቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው ተብሏል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ የኤሌክትሪክ ማመንጫ እምብርት ለመሆን እየሠራች ያለችው ኢትዮጵያ ከውኃ 50 ሺሕ ሜጋ ዋት፣ ከንፋስ 1.3 ሚሊዮን ሜጋ ዋት፣ ከእንፋሎት አሥር ሺሕ ሜጋ ዋትና ከፀሐይ 100 ሺሕ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳላት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ነገር ግን የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በዕቅድ መሠረት እየተጓዙ ስላልሆኑ፣ አሁን በማመንጨት ላይ የሚገኘው 4,260 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ብቻ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች