Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹ወጣቶች ለፖለቲካ ፍጆታ ከሚጠቀሙባቸው አካላት ራሳቸውን መጠበቅ አለባቸው››

‹‹ወጣቶች ለፖለቲካ ፍጆታ ከሚጠቀሙባቸው አካላት ራሳቸውን መጠበቅ አለባቸው››

ቀን:

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ሐሙስ ጥቅምት 8 ቀን 2011 ዓ.ም. በአንድ ሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ በፓርላማ ተገኝተው፣ በሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች መክፈቻ ላይ ፕሬዚዳንቱ ባደረጉት ንግግር ላይ ከፓርላማ አባላት በተነሱ ጥያቄዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አሥር ጥያቄዎች ቀርበውላቸው በዘርፍ በዘርፉ አድርገው መልሰዋቸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልሳቸው ያነሱት አንዱ ጉዳይ በለውጡ እየገጠሙ ያሉ ችግሮችንና የመንግሥት ተቋማትን በሚመለከት ሲሆን፣ በስድስት ወራት ውስጥ ይህን ያህል ጉልህ ለውጥ በዚህ ረገድ መጠበቅ እንደማይቻል አብራርተው፣ ‹‹ያካሄድነው ሬቮሉሽን (አብዮት) አይደለም፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

‹‹በአገራችን በአሁኑ ጊዜ ያለውን የሰላም ጉዳይ መላው የአገራችን ሕዝብ ተረጋግቶ መኖር የሚችልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እንደሚሠራ ተገልጿል፡፡ ይሁንና በየአካባቢው ባሉ የመንግሥት መዋቅሮች ሕዝብ የሚያቀርባቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መፍታት ባለመቻሉ፣ ከቀበሌ ጭምር መፍትሔ ፍለጋ ከሁሉም አቅጣጫዎች ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ወደ ሌሎች የፌዴራል ተቋማት የሚመላለሱ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች አሉና የዚህ መሠረታዊ ምክንያት ምንድነው?›› ተብለው የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የታችኛው የመንግሥት ዕርከን ቀበሌ አካባቢ ተቋማት ፈርሰዋል ደካማ ናቸው መባሉን ተቀብለው፣ ‹‹በምን ቋንቋ መግለጽ እንደሚቻል ቢያስቸግረኝም ታች ቀበሌ ሳይሆን ከላይ ጀምሮ መንግሥት ባቀደው ልክ እያንዳንዱ መሪ ሠርቶ ማስፈጸም ወደሚችልበት ተቋማዊ ብቃት አላደገም፡፡ ከላይ እስከ ታች በስድስት ወራት ውስጥ ጠንካራ ቁመና ያለው ተቋም መፍጠር የሚችል አገር ለመኖሩ እርግጠኛ ባልሆንም፣ እንደዚህ ቀላል ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ ዛሬ ደሃ መሆንና መለመን ባላስፈለገ ነበር፣›› ሲሉም አብራርተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያንዳንዱ ሠራተኛ ሦስት ሰዓት ገደማ ከሥራ ገበታ ላይ እንደሚያባክን ገልጸው፣ በአግባቡ ቢሠራና ኃላፊነት መወጣት ቢቻል ድህነትን ማሸነፍ እንደሚቻልና ለሠራተኛውም የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄዎችን መመለስ እንደሚቻል አብራርተዋል፡፡

በተያያዘ የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኛውንና የመከላከያ ኃይሉ የደመወዝ አነስተኛነት ተጠይቀው የመለሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በቂ ደመወዝ የሚከፈለው አካል እንደሌለና አገሪቱ ካለባት የዕዳ ጫናና ባለፉት ሦስት ዓመታት ባሳለፈችው የብጥብጥ ጊዜ የደመወዝ ጭማሪ ማድረግ እንዳልተቻለ፣ ብሎም አሁን የዋጋ ንረቱ በሁለት አኃዝ እያለ የደመወዝ ማስተካከያ ማድረግ ለሠራተኛው የማይጠቅመውና የዋጋ ግሽበቱንም ሽቅብ የሚገፋው በመሆኑ፣ የዋጋ ግሽበት ወደ ነጠላ አኃዝ እስከሚወርድ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡ በአገር ውስጥ የነበሩትም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች የመንግሥትን መጠባበቂያ በጀት እንደተሻሙና ለሌላ ተግባር ይውል የነበረ ገንዘብ ለተፈናቃዮች መዋሉም፣ የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደነበረው ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ሠራተኞች እንዳለው ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የመከላከያ ሠራዊቱ ደግሞ ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ተርታ የሚመደብ ነው ብለዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት በመሠረታዊነት ለእኩል ሥራ የተለያዩ ክፍያዎች ስላሉ ያንን ማስተካከል የሚያስችል ጥናት መጠናቱን፣ ነገር ግን ተያያዥ የደመወዝ ጭማሪ ጥናትም እንደተካተተበት ተናግረው፣ በጥናቱ የተቀመጠው ዝቅተኛው የደመወዝ ጭማሪ ምክረ ሐሳብ ቢተገበር 37 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚኖረው፣ ከፍተኛው የደመወዝ ጭማሪ ምክረ ሐሳብ ተተግብሮ ቢሆን ደግሞ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ይጠይቅ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

የአስፈጻሚ አካላትን የማስፈጸም አቅም ከፍ ለማድረግም ከፓርላማ ቆይታቸው ማግሥት ለሚኒስትሮችና ለሚኒስትር ዴኤታዎች ሥልጠናዎች እንደሚሰጡ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በቀጣይነትም የማሻሻያ ሥራዎች እንደሚኖሩ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም 20 ሚኒስትር ለመምረጥ ከባድ ፈተና እንደነበርና ሁሉም የራሱን ፍላጎት ለማስጠበቅ እንደሚረባረብ ተናግረው፣ ‹‹እንደምንናገረውና እንደምንተቸው ቀላል አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ባለፉት ስድስት ወራት በተከናወኑ ሥራዎች የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ካለፈው በጀት ዓመት አራተኛ ሩብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ334 በመቶ መጨመሩን አውስተው፣ አሁን ከሞላ ጎደል ተቀባይነት ያለው የውጭ ምንዛሪ ክምችት አገሪቱ ሊኖራት እንደቻለ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ቁጥጥር ሕግ እንደሚዘጋጅና አጠቃቀሙም ቁጥጥር እንደሚደረግበት ያወሱ ሲሆን፣ አገሪቱ ውስጥ ያሉት ሚዲያዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የሚያስችል የቁጥጥር ሥርዓት እንደሚዘረጋም አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ወጣቶችን በተመለከተ ሕግ ለማስከበር በተለያዩ ሥፍራዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች መኖራቸውን በአኃዝ አስደግፈው አስረድተዋል፣ ለሕግ ከቀረቡ 80 በላይ ሰዎች እንዳሉና ከአንድ ሺሕ በላይ ወጣቶች ሥልጠና እንዲወስዱ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ከአጥፊዎች ጋር ተቀላቅለው የታሰሩ ወጣቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመው፣ በዚህ ሁኔታ የተጎዱ ወጣቶች ለለውጡ የከፈሉት መስዋዕትነት አድርገው ቢወሰዱ መልካም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት በአዲስ አበባ ባቀዳቸው ሥራዎች ወጣቱን በስፋት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ወጣቶች ለውጡን የሚደግፉ ብቻ ሳይሆኑ መሪ እንደሆነ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ሆኖም ወጣቶች ተገቢ ባልሆነ መንገድ ለፖለቲካ ፍጆታ ከሚጠቀሙባቸው አካላት ራሳቸውን መጠበቅ አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...