Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትግቡና ውጤቱ ለየቅል የሆነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ

ግቡና ውጤቱ ለየቅል የሆነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ

ቀን:

እ.ኤ.አ. 1941 ለተወለደባት ስኮትላንድ ከተማ ተጫዋችም አሠልጣኝም በመሆን አገልግሏል፡፡ ከ1986 በኋላ ደግሞ በእምባ ለተለየው ክለብ 26 ዓመታት ከቆየ በኋላ 2013 ላይ በይፋ ከአሠልጣኝነነቱ ተሰናበተ፡፡ የእንግሊዙን ዝነኛ ክለብ ማንችስተር ዩናይትድ ውስጥ በቆየበት ወቅት 38 ዋንጫዎችን ማንሳት ሲችል 13 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ዋንጫዎችን በመሰብሰብም ማንም ያልደፈረውን ታሪክ ማስመዝገብ ችሏል፡፡ ከአሠልጣኝነት መንበሩ ከወረደ በኋላ በማንችስተር እግር ኳስ ክለብ ውስጥ የቦርድ አባል ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡

አሌክሳንድር ቻፕማን ፈርጉሰን በእግር ኳስ ውስጥ ስላሳለፈው የውጣ ውረድ በእንግሊዝ በበርካታ አንባቢዎች የተሸመተው “The Leading” መጽሐፍ ላይ እንዳሰፈረው ከሆነ ‹‹በእግር ኳስ ዘመኔ ትልቅ ስኬት ተጎናጽፌያለሁ ብዬ አላስብም›› ብሎ በቁጭት ይናገራል፡፡

እንደ አሠልጣኙ እምነት ከሆነ በማንችስተር ዩናይትድ ቆይታው ካደረጋቸው 1,500 ጨዋታዎች፣ 895 ማሸነፍ ሲችል፣ በ338 አቻ ወጥቶ በ267 ሽንፈት ቀምሷል፡፡ ዋና አሠልጣኙ ቁጭት ውስጥ የገባው 59.7 በመቶ ብቻ ማሳካት ስለቻለ ነው፡፡

‹‹ዘጠና ደቂቃው እንደተጠናቀቀ ስለቀጣዩ ጨዋታ መጨናነቅ እንጂ፣ ዛሬን አሸንፌያለሁ ብዬ በጊዜያዊ ደስታ መዘናጋት አልፈልግም፤›› በማለት በእግር ኳስ  ማሸነፍ ብቻ ብቸኛ አማራጭ እንደሆነ በመጽሐፉ ውስጥ ይገልጻል፡፡

በዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ ልዩነቱ እየጠበበ በመጣበት በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከነበረበት እያሽቆለቆለ መምጣት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡

ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ እንኳን በተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ አገር አሠልጣኞች ሲመራ እዚህ የደረሰው ብሔራዊ ቡድኑ በተደጋጋሚ ስህተቶቹ መመልከት ችግሩ እየሰፋ መሄዱን አመላካች መሆኑ ይታያል፡፡ እንደ ቀድሞው የማንችስተር ዩናይትድ አሠልጣኝ ከዚያ ስኬት በኋላ ቁጭት ውስጥ መግባት ባሻገር ብልጭ ብሎ በሚጠፋ እንቅስቃሴ የቡድኑ ችግር ተንከባሎ ወደ አፋፍ እንደመጣ ሥጋታቸውን የሚገልጹ አሉ፡፡

የብሔራዊ ቡድኑ ያልተፈቱ ችግሮች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ኳስን ወደ ግብ የመቀየር ችግር ያለባቸው ሲሆን፣ በተቃራኒ ቡድን ደግሞ በተደጋጋሚ የቆሙ ኳሶችን ሲቆጣጠሩባቸው ይስተዋላል፡፡ በተለይ ብሔራዊ ቡድኑ በግንባር ግብ ማስቆጠር ከተሳነው ዘመናት አስቆጥሯል፡፡ ለእነዚህ ሁሉ ችግሮች ተያያዥ መሠረታዊ የሥልጠና ክፍተት እንደሆነ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

የቢቢሲና የካፍ ኦንላይን ስፖርት ተባባሪ ዘጋቢ በሆነው አምና ታደለ አስተያየት ከሆነ በብሔራዊ ቡድኑ የሚስተዋሉት ስህተቶች ከመሠረታዊ የሥልጠና ችግሮች የሚመጡ ናቸው በማለት ያስረዳል፡፡ ‹‹ከክለቦች ጀምሮ የሥልጠና ክፍተት አለ፡፡ ያንን ክፍተት ደግሞ በብሔራዊ ቡድኑ ላይ ሲንፀባረቅ ማስተዋል የተለመደ ሆኗል፤›› በማለት አስተያየቱን ለሪፖርተር ስንዝሯል፡፡

ለዚህም ብቃት ያላቸው አሠልጣኞች ወደ ሙያው መምጣት እንዳለባቸው ያምናል፡፡ የ2019 የካሜሩን አፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታን ውጤትን ተከትሎ የተጫዋቾች ጥራትና ተተኪነት በመመልከት አዲስ ፊት ማየት አለመቻሉና ታዳጊዎችን በአግባቡ አለመጠቀም ችግር መኖሩ ያነሳል፡፡

‹‹አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች በብሔራዊ ቡድን ውስጥ መጫወት ከጀመሩ አሥር ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ ለብሔራዊ ቡድን መጠራት ያልነበረባቸው ተጫዋቾች በዚህ ውድድር ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ ይህ ደግሞ ከሥር ተተኪዎችን እንዳይመጡና ተደጋጋሚ ፊት ለማየት አስገድዷል፤›› በማለት ኦምና ያስረዳል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑም ቢሆን የሊግ ውድድሮችን ከመምራት ባሻገር ቴክኒካል ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ችግሮችን መቅረፍ እንደሚኖርበት ይገልጻል፡፡

በዋሊያዎቹ አሠልጣኝ አብርሃም መብርሃቱ አስተያየት ብሔራዊ ቡድኑ የተስፋ ቡድን ይኖረዋል ማለታቸው ይታወሳል፡፡ በአንፃሩ ግን የተስፋ ቡድን ለማቀፍና በጀት በጅቶ የተለያዩ ቁሳቁስና ውድድሮችን ለቡድኑ ከማዘጋጀት አንፃር ፌዴሬሽኑ ምን ያክል ዝግጁ ነው የሚለው አጠራጣሪ ነው የሚሉ አልታጡም፡፡

በዘመኑ እግር ኳስ ገነው የሚታዩ ክለቦች ወይም ብሔራዊ ቡድኖች መሠረታቸው አካዴሚ እንደሆነ ሀቅ ነው፡፡ በአፍሪካ ደረጃ እንኳን ብሔራዊ ቡድናቸው ለማጠናከር አካዴሚ አቋቁመው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ናይጄሪያ፣ ካሜሩን፣ ግብፅና ቱኒዚያ የመሳሰሉ አገሮች እንኳን ከ20 ዓመት በላይ ማስቆጠራቸው ይነገራል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ምድብ ማጣሪያ ጨዋታ ላይ ኳስን ከግብ ጠባቂ መሥርቶ የመጫወት ዘዴን መከተል ጀምሯል፡፡ በምድቡ ሁለተኛ ጨዋታን በሐዋሳ ከሴሪሊዮን አቻው ሲያደርግ፣ እንዲሁም በምድብ ሦስት የማጣሪያ ጨዋታ ባህር ዳር ላይ ኬንያን ሲገጥም ይኼንን መንገድ ሲከተል ተስተውሏል፡፡ የአጨዋወቱ ዘዴ መልካም ቢሆንም ኢትዮጵያ ግን ከዓመታት በኋላ ዘግይታ መጀመሯ የእግር ኳሱ ደረጃ የቱ ጋ እንዳለ አመላካች ነው፡፡

የክለቦች መሠረታዊ ችግር ብሔራዊ ቡድኑ ላይ የጣለው ጥላ

ፕሪሚየር ሊጉ ሊጀመር ሩብ ክፍለ ዘመን ሊሞላ ጥቂት ዓመታት ቀርተውታል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ የተለያዩ የክልልና የአዲስ አበባ ክለቦች ቢሳተፉም ለዘመናት ከክለቦች ጋር የዘለቀ የሥልጠና ችግር መኖሩ ብሔራዊ ቡድኑ በተተኪ ተጫዋቾች እጥረትና ጥራት ሲመታ መቆየቱ ይገለጻል፡፡

ክለቦች በዓመት በሚሊዮኖች ብር የሚያስፈርማቸው ተጫዋቾች ላይ ትኩረት ከማድረግ ውጪ ሥልጠናና ግባቸውን ለይተው አለማወቃቸው ሲያስተቻቸው ከርሟል፡፡

የተለያዩ የክለብ አሠልጣኞች በሚሊዮኖች የሚያስፈርሙትን ተጫዋች መሀል በገባና ሩጫ እንዲሠራ የሚያደርጉ እንዳሉ ለእግር ኳሱ ቅርብ የሆኑ አካላት ይመሰክራሉ፡፡ ምንም እንኳ እነዚህ ችግሮች ከብቃት ማነስ ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ የሚጠቀሱ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ የአሠልጣኞች ማሠልጠኛ ተቋም አለመኖሩና የበቂ ሥልጠና እጥረት ምክንያት አስፈላጊው ደረጃ ላይ መድረስ እንዳልተቻለ አሠልጣኞች ያብራራሉ፡፡

በኑራ ሂማም በፋና ኤፍኤም 98.1 የሪጎሪ ስፖርት ፕሮግራም አዘጋጅ አስተያየት ከሆነ ሥልጠና ዋነኛ ችግር እንደሆነና የአሠልጣኞች መመዘኛ ምን እንደሆነ ለይቶ ማወቅ ተገቢ እንደሆነ ታምናለች፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ክለቦች በአሠልጣኞች የሚቀጠሩት በልምድና የውጭ አገር እግር ኳስን በማየት ያካበቱትን ልምድ በመንተራስ ነው የምትለው ኑራ የተጫዋቾችን ብቃት በአግባቡ ተመልክቶ በቂ ክትትል ማድረግ መማር ይኖርባቸዋል ትላለች፡፡

በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ተጫዋቾች ከዲሲፒሊን አንፃር ክፍተቶችን ማስተዋል የተለመደ በመሆኑ ከታዳጊ ጀምሮ ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ ታስረዳለች፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑም ቢሆን የተስፋ ቡድን ለማቋቋም የበጀት እጥረት እንዳይኖር የማርኬቲንግ ሥራዎች ላይ ወገቡን ጠበቅ አድርጎ አስፈላጊ ዝግጅት ማድረግ እንደሚኖርበት ይነገራል፡፡

ሊጉን ለክለቦች ሰጥቶና ክለቦች የገንዘብ አቅማቸውን ማፈርጠም እንደሚኖርባቸውም ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

የዘንድሮው የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ከሳምንታት በኋላ ይጀምራል፡፡ ክለቦችም ውድድሩ ላይ ጠንካራ ሆነው ለመገኘት ሚሊዮኖችን በማፍሰስ ከውጭና ከአገር ውስጥ ተጫዋቾችን እያስፈረሙ ይገኛሉ፡፡ በሊጉ የሚሳተፉ ክለቦች ከውጭ ያስፈረሟቸው ተጫዋቾች ቁጥር 40 መድረሱና ከ16 ክለቦች 11ዱ የውጭ አገር ግብ ጠባቂዎችን ማስፈረማቸውም እየተሰማ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...