Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ይድረስ ለሪፖርተርኮንዶም እንደ ቢራ

ኮንዶም እንደ ቢራ

ቀን:

ሰሞኑን እንደ ወትሮው በቴሌቪዥን በሰፊው ሲራገብ የምናየው የቢራ ማስታወቂያ አይደለም፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ በዝቶ የምናየው የኮንዶም  ማስታወቂያ ነው፡፡ ታዳጊ ልጆችና ሕፃናት ቴሌቪዥን በሚያዩበት ሰዓት የሚታዩ፣ በወሲብ ቀስቃሽ ቃላትና ምሥሎች የተሞሉ የኮንዶም ማስታወቂያዎች እየታዩ ነው፡፡ በሕዝብና በግል ሚዲያዎች ላይ የሚተላለፉ ባህልንና የተመልካችን ሥነ ልቦና ከግምት ያላስገቡ ማስታወቂያዎች፣ በተለያየ መልኩ ማኅበረሰቡን የሚጎዱ ናቸው፡፡

በምዕራብ አገሮች ኮንዶምን በመገናኛ ብዙኃን ማስተዋወቅ የብዙ አከራካሪና ተቃራኒ ሐሳቦች ምንጭ ነው፡፡ በአንድ ጎኑ የኮንዶም ማስታወቂያ የኅብረተሰብን ሃይማኖታዊ እሴቶችና ባህላዊ ወጎች ስለሚቃረን መተላለፍ የለበትም የሚሉ አሉ፡፡  በሌላ ጎኑ ኮንዶም ኤችአይቪ ኤድስንና ሌሎች በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችን እንዲሁም እርግዝናን በመከላከል ኅብረተሰቡን ይጠቅማል የሚሉ አሉ፡፡ ስለሆነም ማስታወቂያው በብዙኃን መገናኛ ቢተላለፍ ችግር የለውም የሚል ሐሳብ ይነሳል፡፡ አኩሪ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶች ባላት አገራችን የትኛው እንደሚሻለን መገመት አይከብድም፡፡

አንድ ወዳጄ ይህን ታሪክ ነገረኝ፡፡ አንድ መነኩሴ አዲስ አበባ ውስጥ በመኪና ሲጓዙ በትልቅ ቢልቦርድ ላይ የተሳለውን የኮንዶም ማስታወቂያ በመገረም እያዩ፣ ‹እንዲያው አሁን ይህ ነገር እውነት ቢያስፈልገን እግዚአብሔር ከነከረጢቱ አይፈጥረንም ነበር?› ብለው ራሳቸውን በሐዘን እየነቀነቁ ይጠይቃሉ፡፡ በጊዜው ታሪኩን ስሰማ ስቄ ነበር፡፡ በኋላ ላይ ግን ይህ ማስታወቂያ ምን ያህል ከአገራችን እምነት፣ ባህልና ወግ ጋር እንደሚቃረን እንዳሰላስል አድርጎኛል፡፡

- Advertisement -

ሌላ ትዝብት ላካፍላችሁ፡፡ የዛሬ 10 ዓመት ገደማ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ሳለሁ፣ ስለኤችአይቪ ኤድስ መከላከል ሲነገር ሦስቱ የ‹‹መ›› ሕጎች ሳይነሱ አይቀሩም ነበር፡፡ አሁን ግን መታቀብና መወሰን የተረሱ የ‹‹መ›› ሕጎች ሆነዋል፡፡ ቤተ እምነቶችም ሥራቸውን ረስተው የተኙ ይመስላሉ፡፡ ተማሪ እያለን ስድስት ኪሎ ዋና ግቢ ፊትለፊት የተሰቀለ አንድ ትልቅ ቢልቦርድ ላይ ሦስት ወጣቶች ወደ ሦስቱ የ‹‹መ›› ሕጎች ቀስት ለመወርወር ሲያልሙ ይታያል፡፡ ተመሳሳይ የማስታወቂያ ቢልቦርዶች በዚያን ጊዜ በየቦታው ይታዩ ነበር፡፡ አሁን ግን በየአደባባዩ የሞላው የኮንዶም ማስታወቂያ ብቻ ነው፡፡

ኮንዶምን ማስተዋወቁ መቅረት አይችልም ከተባለ፣ በሽታ መከላከያ መሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባ ነበር፡፡ ሰሞኑን በየቴሌቪዥኑና በየሬዲዮው የምንሰማው የኮንዶም ማስታወቂያ ግን የወሲብ ፊልም ትሬለር እንጂ የኮንዶም ማስታወቂያ አይመስሉም፡፡

ከግብረ ገብነት አንፃር ካየን በእርግጥ ‹‹ኮንዶም  ተጠቀሙ›› የሚል ማስታወቂያ ሦስት ነገሮችን ይጠቁማል፡፡ አንደኛው ከጋብቻ በፊት ራስህን መቆጠብ አትችልም፣ ስለዚህ በሽታ እንዳይዝህ ወይም ላልታቀደ እርግዝና እንዳትጋለጥ ኮንዶም ተጠቀም የሚል መልዕክት ይሰጣል፡፡ ሁለተኛው ካገባህ ደግሞ በስሜት ስለምትመራ ለጋብቻህ ታማኝ መሆን አትችልም ስለዚህ ኮንዶም ተጠቀም የሚል መልዕክት ይሰጣል፡፡ ሦስተኛው ወሲብ እንደምግብና እንደ ውኃ ሁሌ ስለሚያስፈልግህ አድርገው የሚል መልዕክት ይሰጣል፡፡ ‹‹ኮንዶምን ሁሌና በትክክል መጠቀም›› የሚለው ማስታወቂያ ይህን እሳቤ ይገልጻል፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ‹‹ኮንዶምን ሁሌና በትክክል መጠቀም›› የሚለው ሐረግ የተወረሰው ከታይዋን የኤችአይቪ ኤድስ መከላከያ ዘመቻ ፕሮግራም ነው፡፡ በአጠቃላይ እንዲህ ዓይነት የኮንዶም ማስታወቂያ ባህል የሰው ልጅ የወሲብ ጥሙን በፈለገ መንገድ ማርካት አለበት ከሚለው የተሳሳተ ፍልስፍና ይመነጫል፡፡ ይህ ደግሞ በእምነትም በወግም ከኢትዮጵያውያን ጋር አይመሳሰልም፡፡

በቅርቡ አንድ ጥናት በኢትዮጵያ ውስጥ የኤችአይቪ ሥርጭት መልሶ እያገረሸ እንዳለ ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ የሚያሳየው በሽታውን ከሥር መሠረቱ ሊፈታ የሚችል የአመለካከት ለውጥ አልወጣም ማለት ነው፡፡ ከባህላቸውና እምነታቸው ጋር የሚሄደውን መታቀብና መቆጠብን እንደ ዋና የኤችአይቪ መከላከያ ዘዴ የወሰዱ አገሮች፣ ኤችአይቪ ኤድስን በእጅጉ መቀነስ ችለዋል፡፡ ለምሳሌ በኡጋንዳ፣ ከበርካታ ዓመታት በፊት 15 በመቶ አካባቢ የነበረው የኤችአይቪ ሥርጭት፣ መታቀብና መቆጠብ ዘዴዎች ላይ አትኩራ ዜጎቿን በማስተማሯ በሚያስገርም ውጤት ሥርጭቱን ወደ ሦስት በመቶ ልትቀንስ ችላለች፡፡ ፍሊፕንስም ተመሳሳይ ፖሊሲ ተከትላ የበሽታውን ሥርጭት በትልቁ መግታት ችላለች፡፡

በኢትዮጵያ ሁለቱ የ‹‹መ›› ሕጎች መታቀብና መቆጠብ ጠፍተው ትኩረቱ እንዴት ‹‹መጠቀም›› ላይ ብቻ ሆነ ብሎ ለሚጠይቅ ሰው መልሱ ቀላል ነው፡፡  እርሱም ‹‹የገንዘብ ትርፍ›› ነው፡፡ ኮንዶም አምራች ኩባንያዎች በቢሊዮን የሚቆጠሩ ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ  ላይ ስለኢትዮጵያ አንድ ጽሑፍ አንብቤ ደነቀኝ፡፡ ጸሐፊው በኢትዮጵያ ያለው የኮንዶም ገበያ ስላደገና ሕዝቡ ጥቅሙን ስለተረዳ ዋጋው መጨመር አለበት ብሎ ይከራከራል፡፡ ከዚህ ጽሑፍ የገባኝ ነገር ቢኖር የእነዚህ ኩባንያዎች ዓላማ ዞሮ ዞሮ እኛን ከበሽታ መከላከል ሳይሆን፣ ትርፋቸውን ማሳደግ ነው፡፡ በዚህ የትርፍ ግብግብ ውስጥ የማስታወቂያ ሥነ ምግባር ብዙ ባልተረዱ ሚዲያዎቻችን ምክንያት ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻችን እየተሸረሸሩ ናቸው፡፡

ከሁሉም በላይ አሳሳቢው ጉዳይ እንዲህ ዓይነት ወሲብ ነክ ፀባዮችን የሚያበረታቱ የኮንዶም አስተዋዋቂዎች ቴሌቪዥን ለሚያዩና ሬዲዮ ለሚሰሙ ሕፃናትና ታዳጊዎች አዕምሮ አለማሰባቸው ነው፡፡ ማስታወቂያቸውም ብዙን ጊዜ ቤተሰቦች በጋራ ተቀምጠው ቴሌቪዥን በሚያዩበት ሰዓት የሚተላለፉ መሆኑ ያሳዝናል፡፡ ከማስታወቂያ ሥነ ምግባር ውስጥ አንዱ አስተዋዋቂዎች የሚያስተዋውቁትን ነገር ከተመልካቾች ባህሪ፣ ዕድሜና ሥነ ልቦናዊ ዝግጅት አንፃር ምን ዓይነት ተፅዕኖ ማሳደር እንደሚችል አመዛዝኖ መወሰን ነው፡፡

ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ እንዲህ ዓይነት ማስታወቂያዎች ሕፃናትና ታዳጊ ወጣቶች ኮንዶም መጠቀም ‹‹ትክክለኛ ልማድ ነው›› የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ እንዲያዳብሩ ያደርጋቸዋል፡፡ በዕድሜያቸው አላስፈላጊ ለሆኑ ወሲብ ነክ ምሥሎችና ቃላት ያጋልጣቸዋል፡፡ ኃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻቸውን እንዲዘነጉና የዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ትርፍ ሩጫ ሰለባዎች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ በረዥም ጊዜ ውስጥ የኅብረተሰብ መሠረት የሆነው የቤተሰብ ተቋምና አገርን ይጎዳል፡፡ ስለሆነም የብዙኃን መገናኛዎቻችን ይህን ተረድተው በተቻላቸው መጠን ሕፃናትንና ወጣቶችን ካላስፈላጊ ተፅዕኖ የመከላከል ኃላፊነት መወጣት አለባቸው፡፡

(ከጋዜጠኛ ጌታቸው ታምሩ፣ በኢሜል የተላከ)

* * *

ይድረስ ለፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው

የምንገኝበት ወቅት፣ ኢትዮጵያውያኖች በተለይም የፖለቲካ መሪዎች ልባችሁን ከጥላቻ፣ ከእልህና ከቂም በቀል አፅድታችሁ፣ በሰከነ መንፈስ አርቃችሁ ልታስቡበት የሚገባችሁ ጊዜ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያና የሕዝቦቿ መፃኢ ዕድል በአብዛኛው በእናንተ እጅ ወይም በእናንተ አስተሳሰብ ላይ ወድቋል፡፡ በአገራችን ውስጥ በሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም ድርጅቶች መካከል (ገዥውን ጨምሮ) ሁለት በጣም የተለያዩ አስተሳሰቦችንና አካሄዶችን እመለከታለሁ፡፡ አንደኛው ፍቅርን፣ ይቅርታን፣ ሰላምንና አንድነትን (አንድ ዓይነትነት አይደለም) መሠረቱና መመሪያው ያደረገ ሲሆን፣ ሁለተኛው ጥላቻን፣ ቂም በቀልን፣ ዘረኝነትን (ብሔርተኝነትንና መለያየትን) መሠረት ያደረገ ነው ማለት ይቻላል፡፡

እውነት እላችኋለሁ ሁለተኛው አስተሳሰብና አካሄድ ለማንም የማይበጅና የኢትዮጵያን ሕዝቦች ሁሉ ከአሁን በፊት በአገራችን ታይቶ ወደማይታወቅ አስከፊ የመከራ አዘቅት ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡ ውጤቱም የእርስ በርስ ግጭት፣ ጦርነት፣ ድህነት፣ ረሃብና አገር አልባነትን ማስከተል ይሆናል፡፡

የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ የፈጣሪ፣ ፍጡር ተራ ሰው ነኝ፡፡ የሰዎች ሁሉ አባት የሆነው የአዳም ወይም የአደም ዝርያ ነኝ፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ስለተወለድሁም መለያዬ ወይም ማንነቴ ኢትዮጵያዊ ነው ማለት በቂዬ ነው፡፡ ሆኖም ግን ከላይ የተመለከተውን ሁለተኛውን የፖለቲካ መንገድ የምታራምዱ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው እኔ ከየትኛው የኢትዮጵያ ብሔረሰብ እንደተወለድኩ ማወቅ ከፈለጋችሁ አባቴ ከኦሮሞ እናቴ ደግሞ ከአማራ ናቸው፡፡

ነገር ግን ይህ ለእኔ ምንም ማለት አይደለም፡፡ እዚህ ላይ መጥቀሱ አስፈላጊ መስሎ ስለታየኝ ነው እንጂ፣ ይኼንን ማሰቡም ሆነ ማውራቱ ምንም ስሜት አይሰጠኝም፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እንደ እኔ ከሁለት የተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች እንደተለወዱ እገምታለሁ፡፡

ሁለተኛውን የፖለቲካ አቋም የምታራምዱ መሪዎችና ተከታዮቻቸው ቆም ብላችሁ፣ በሰከነ መንፈስ አርቃችሁ፣ በሰፊው አስቡ፡፡ ለምን ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፡፡ ምናልባት ‹የእኔ ብሔር ወይም ብሔረሰብ ባለፉት ሥርዓቶች ተበድሏል› ብላችሁ የምታስቡ ካላችሁ፣ እውነት  እላችኋለሁ የያዛችሁት የፖለቲካ አቋም እንወክለዋለን ለምትሉት ብሔር ወይም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ፈጽሞ የማይበጅ ነው፡፡ መፍትሔው ቂም በቀል ሳይሆን፣ ይቅር ባይነት፣ ጥላቻ ሳይሆን ፍቅር፣ መጠላለፍ ሳይሆን መተባበር፣ መለያየት ሳይሆን፣ አንድነት ነው፡፡ የማንዴላን መንገድ መከተል ነው፡፡

በነገራችን ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ‹‹አንድነት›› የሚለው ቃል ሆን ተብሎም ይሁን ባለማወቅ የተሳሳተ ትርጉም ሲሰጠው ይስተዋላል፡፡ ‹‹አንድነት ወይም በአንድነት መኖር›› ማለት በአንድ አገር ውስጥ ሁሉም ዜጋ እኩል የዜግነት መብት ኖሮት ተባብሮ፣ አገሩን በጋራ እያለማ ተዋዶ፣ መኖር ማለት እንጂ፣ ተጨፍልቆ አንድ ዓይነት መሆን ማለት አይደለም፡፡

 ማንም ብሔር ወይም ብሔረሰብ የራሱን መናገር፣ ባህሉን መኖርና መንከባከብ የራሱ ሰብዓዊ መብት እንጂ ማንም ሊቸረው ወይም ሊነፍገው የሚችል ስጦታ አይደለም፡፡ አርቆና አስፍቶ ባለማሰብ በሕዝቦች መካከል ጥላቻን፣ ቂም በቀልን፣ ዘረኝነትንና መለያየትን በመስበክ ትውልድን በተሳሳተ መንገድ በመምራት፣ አገርንና ሕዝቦቿን ወደማይወጡት የመከራ አዘቅት አትውሰዱ፡፡ ይልቁንም በላቀና በጠለቀ አስተሳሰብ ጥላቻን ሳይሆን ፍቅርን፣ ቂም በቀልን ሳይሆን ይቅርታን፣ መለያየትን ሳይሆን አንድነትን በመከተል ሕዝቦች በሰላም፣ በፍቅር፣ በእኩልነት የሚኖሩባት ያልተከፋፈለች፣ የማናፍርባት፣ የተከበረችና የበለፀገች አገር እንገንባ፡፡

ሕይወት አጭር ናት፡፡ የጤነኛ ሰው አማካይ ዘመን ከ70 እስከ 80 ዓመት ቢሆን ነው፡፡ ሁላችንም እናልፋለን፡፡ ስናልፍ ሁሉንም ቁሳዊ ሀብታችን ይቀራል፡፡ ከመቃብራችን በላይ የሚቀረው በሕይወት ሳለን የሠራነው ተግባርና ስማችን ብቻ ነው፡፡ መልካም ስም ከመቃብር በላይ ይውላልና)፡፡ እኩይ አስባችሁና እኩይ ሠርታችሁ ሲወቀስና ሲወገዝ የሚኖር ስም ትታችሁ የተረገመች ነፍስ ይዛችሁ አትለፉ፡፡

ይልቁንም ትልቅ አስባችሁ ለሕዝባችሁ መልካሙን ሠርታችሁ በሕይወት ስትኖሩ የህሊና እርካታና ሰላም አግኝታችሁ ለትውልድ ታላቅ አገርን አስረክቡ፡፡ ስማችሁን በዘላለማዊ  ክብርና ምሥጋና ማኅደር በማጻፍ፣ ትውልድ እንዲዘክረው አድርጋችሁ እለፉ፡፡ ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ፡፡

(ያሬድ በላይ፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...