Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ በቻይናውያን የተገነባው የአፍሪካ ኅብረት ግዙፍ ሕንፃ እጅግ ዘመናዊ፣ ውብና ለከተማይቱ ብሎም ለአገሪቱ ታላቅ እሴት ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት በአዲስ አበባ እንዲፀናና አገሪቱም የአፍሪካውያን መናኸሪያ እንድትሆን የተደረገው ትግል ዋጋ ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ በዓድዋ ጦርነት ነጮች በጥቁሮች ላይ የነበራቸው አመለካከትና የበላይነት እንዲያከትም በማድረጓ ጭምር የተገኘ ውለታ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ይህ ሕንፃ ሲቆም አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን የከፈሉት መስዋዕትነት መታሰቢያ መሆኑን መቼም ቢሆን መርሳት የለብንም፡፡ ቻይናውያኑ ለአፍሪካውያን በስጦታ ያቀረቡት ቢሆንም፣ አፍሪካውያኑ ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ለመውጣት ላደረጉት ትግል የኢትዮጵያ አርዓያነትና ድጋፍ መዘንጋት አይኖርበትም፡፡ ስጦታውን ከአፍሪካውያኑ ወገኖቻችን ጋር እኩል ብንቀበለውም፣ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች አርነት ያደረግነው ተጋድሎም ሊታወስ የግድ ነው፡፡ ይህንን ስንል ግን ራሳችንን በሚገባ እየተመለከትን መሆን አለበት፡፡

ይህ የአፍሪካ ኅብረት ሕንፃ የተገነባበት 50 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ በኢትዮጵያ መንግሥት የተበረከተ ሲሆን፣ አሁን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና መሥርያ ቤትን ይፎካከረዋል የሚባልለት ሕንፃ ያረፈበት ይህ ሥፍራ ደግሞ የራሱ መራር ታሪክ አለው፡፡ ቀድሞ ‹‹ከርቸሌ›› በመባል የሚታወቀው እስር ቤት ‹‹ዓለም በቃኝ›› የሚባል አስፈሪ የማሰሪያ ቦታ ነበረው፡፡ ከደረቅ ወንጀል ጀምሮ የመንግሥት ተቃዋሚ የሚባሉ ፖለቲከኞችና በርካታ የአገሪቱ ዜጎች በከፍተኛ ጥበቃ የሚታጎሩበት እስር ቤት፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በርካታ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በግፍ የተገደሉበት ነበር፡፡ በርካታ የአገሪቱ ወጣቶች በገፍ ታጉረውበት ለነፃነት መታገላቸው ወንጀል ሆኖ የተረሸኑበት እስር ቤት ነበር፡፡ በርካታ የአገሪቱ ዜጎች በተለይ በደርግ ሥርዓት ከፍተኛ ስቃይ የተቀበሉበት ሥፍራ ነበር፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ሳይቀሩ ይህ ሕንፃ በከርቸሌ መቃብር ላይ መገንባቱን ማስተጋባታቸውን አስታውሳለሁ፡፡ ይህ ሕንፃ በአገሪቱ ትልቁ በሚባለው እስር ቤት ፍርስራሽ ላይ መሠራቱን፣ በእዚህ ሞታቸውን የሚጠባበቁ ዜጎች ይታሰሩበት በነበረ ቦታ ላይ ይህ ሕንፃ መገንባቱ ታሪካዊ መሆኑንና ለህልውና የተደረገ ፍሬ መሆኑን ብዙዎችን ያስማማ ነበር፡፡ ይህንን ስንቶቻችን እንገነዘበዋለን?

እንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ ደግሞ ብዙ ነገር እንዳነሳ ይጋብዘኛል፡፡ መራራ ነገሮችን ጣፋጭ ለማድረግ አሁንም ለለውጥ መነሳት የግድ ነው፡፡ በአፍሪካም ሆነ በአገራችን በመጥፎ ፍርስራሾች ላይ መገንባት የሚገባቸው በርካታ መልካም ነገሮች አሉ፡፡ አንዱና ዋነኛው ዴሞክራሲ ነው፡፡ በበርካታ የአፍሪካ አገሮች ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ መሆኑ ተዘንግቶ ቅንጦት እየመሰለ ነው፡፡ ብዙዎቹ መሪዎች ሥልጣን ላይ ሙጭጭ ብለው ዜጎችን አበሳ ያሳያሉ፡፡ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ምርጫ ተካሂዶ የሕዝብ ድምፅ ይወሰን ሲባሉ ጠመንጃ መወልወል ይጀምራሉ፡፡ የዴሞክራሲ ዕጦት እንደ ነቀዝ እየበላን ስለሆነ፣ በአምባገነንነት ፍርስራሽ ላይ ዴሞክራሲ ይገነባ ዘንድ አቤት ማለት ተገቢ ነው፡፡ ከዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ አፈንግጦ ለመኖር መሞከር ዋጋ እንደሚያስከፍል ማጤን ይገባል፡፡

የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች መጣስ አገራችንን ጨምሮ የበርካታ የአፍሪካ አገሮች ዋና መለያ ነው፡፡ አገር የአንድ ፓርቲና የአባላቱ ርስት እስክትመስል ድረስ የሕዝቦች ሰቆቃ በገፍ ታይቷል፡፡ የፍትሕ ያለህ የሚለው የትዬለሌ ነው፡፡ ጉዳይን በአጭር ጊዜ ለማስጨረስ ይቅርና ለአቤቱታዎች ምላሽ የሚሰጥ የለም፡፡ ወገንተኝነት በመብዛቱ ከመሠረታዊ አቅርቦቶች እስከ መሬት ክፍፍል ድረስ አድሎአዊነት ተንሰራፍቷል፡፡ ዜጎች በሕገወጥ መንገድ ይታሰራሉ፣ ይደበደባሉ፣ ንብረታቸውን ይወረሳሉ፡፡ እንባቸውን የሚያብስ ግን የለም፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ አሳፋሪ ተግባር ፍርስራሽ ላይ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ይኖርበታል፡፡ የሰብዓዊ መብት ክብር ሐውልት ሊገነባለት የግድ ይላል፡፡ ይህንን መገንዘብ ካልቻልን አዙሪቱ አይለቀንም፡፡

እንደ ሰደድ እሳት በተስፋፋው ዘረፋና ሌብነት ምክንያት የአገር ሀብት ሲወድምና ድህነት በሰፈነባት አፍሪካ ውስጥ ሙስና ሃይ ባይ ሲያጣ በስፋት እየታየ ነው፡፡ የአኅጉሪቱ ተስፋ የሆነው ወጣቱ ትውልድ በሌብነት ምክንያት ትምህርት፣ ጤና፣ ሥራና ሌሎች ተዛማጅ አገልግሎቶችን ሲያጣ ምርጫው ስደት ሆኗል፡፡ በሌብነት የተነሳ ጥቂት አልጠግብ ባዮች በአሳፋሪ ሁኔታ ሲበለፅጉ ብዙኃኑ እየደኸዩ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የሚልሱትና የሚቀምሱት አጥተው፣ በዘረፋ እስካንገታቸው የተነከሩ ጥቂቶች ግን ለዘር ማንዘራቸው የሚተርፍ ሀብት አካብተዋል፡፡ በሌብነት ፍርስራሽ ላይ ከሙስና የፀዳ ኩሩ አገር መገንባት አለበት፡፡ በችግር በተሞሉ የመልካም ገጽታ ጥላሸቶች ፍርስራሽ ላይ መልካም ነገሮች መገንባት አለባቸው፡፡

ከትልቋ ልጄ ጋር በዚህ ርዕስ ላይ ስንወያይ፣ ‹‹አባቢ ያልገባህ አንድ መሠረታዊ ጉዳይ አለ፤›› አለችኝ፡፡ ብዙዎቻችን የምንስማማበትን ሐሳብ አንስቼ ነበር ሳወያያት የነበርኩት፡፡ እግረ መንገዴን ነፃና ኩሩ ዜጋ ሆና ማደግ እንዳለባትም እያሳሰብኳት ነበር፡፡ ግን ለምን ይሆን አልገባህም የምትለኝ? መልሷ ምን ይሆን እያልኩ፣ ‹‹ምኑ ነው ያልገባኝ?›› ብዬ ጥያቄ አቀረብኩላት፡፡ ሌባ ጣቷን ጭንቅላቷ ላይ አድርጋ፣ ‹‹በመጥፎ ነገሮች ፍርስራሽ ላይ መልካም ነገሮችን ለመገንባት ቀዳሚው ተግባር አዕምሮን መለወጥ ነው፤›› ስትለኝ ጃፓኖች፣ ‹‹ሁሌም ለውጥን በፀጋ መቀበል የሥልጣኔ ምልዕክት ነው፤›› የሚሉትን አስታወሰችኝ፡፡ ያልተለወጠ አዕምሮ ለውጥን መቀበል ያዳግተዋል፡፡

ለውጥ ግን ምሉዕ ሆኖ መቀጠል የሚችለው በማሰር፣ በማስፈራራት፣ ጊዜው የእኔ ነው ብሎ በመደንፋትና ጉራ በመቸርቸር አይደለም፡፡ ይህ ዓይነቱ ጥጋብ በዚህ ዘመን ለማንም አይበጅም፡፡ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት በዚህ ጊዜ ከሚተላለፉ መልዕክቶች የበላይነትንና የበታችነትን ከማንፀባረቅ አልፈው፣ ምን ታመጣላችሁ ዓይነት ዛቻ ድረስ የዘለቁ ትምክህተኞችን እየታዘብን ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በአዲስ አበባ ከተማ ባለቤትነትና ማንነት ጉዳይ የሚሰሙ ድንፋታዎች፣ ከወር በፊት የተደረገውን የጅምላ አፈሳና በስመ ተሃድሶ የተፈጸመው ሕገወጥ ድርጊት የነገውን ክፉ ነገር አመላካች ናቸው፡፡ ትናንት አምባገነኖች ያለፉበትን አጉል መንገድ ለመድገም የሚታትሩ ባለጊዜ ነን ባዮችን እንደገና በሌላ ቅርፅ ማየት ያንገሸግሻል፡፡ ለውጡን የጋራችን አድርገን በመከባበርና በእኩልነት ማከናወን ካልቻልን የአሳሪና የታሳሪ ታሪካችን መደገሙ አይቀርም ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገውን ጉዞ አጨናግፈን የአምባገነኖች መጫወቻ እንሆናለን፡፡ እንኳንስ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫና የዓለም አቀፍ ተቋማት መናኸሪያ ልንሆን፣ እንደ አውሬ እየተበላላን የዓለም መሳቂያ እንሆናለን፡፡ የገባንበት እሰጥ አገባ ያጠፋናልና ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡

(እስጢፋኖስ አንዳርጌ፣ ከመካኒሳ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...