Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

በሕግ አምላክፓርላማውን ፓርላማ ለማድረግ የሚቀሩ ሕግጋትና ተግባራት

ፓርላማውን ፓርላማ ለማድረግ የሚቀሩ ሕግጋትና ተግባራት

ቀን:

በውብሸት ሙላት

ክፍል ሁለት

ይህ ጽሑፍ ባለፈው ሳምንት በዚሁ ጋዜጣ፣ በዚሁ ዓምድ ከወጣው የቀጠለ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ራሱን ችሎም የቆመም ነው፡፡ የባለፈው ላይ የተንጠለጠለ አይደለም ለማለት ነው፡፡ የፓርላማ አባልነት ከባድ ኃላፊነት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ቀላልና ኃላፊነቱን የረሳ ወይም የዘነጋ እንዲሆን አይደለም የፓርላማ  የመኖር ምክንያቱ፡፡ ሕግ አስፈጻሚውን ሥርዓት ይዞ አገር እንዲያስተዳድር ማድረግ ነው ዋና ኃላፊነቱ፡፡ ይህንን ኃላፊነቱን ለመወጣት ሕግ ያወጣል፡፡ በሕጉ መሠረት አስፈጻሚውን ሥራውን እያከናወነ መሆኑንም ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል፡፡

- Advertisement -

የፓርላማ አባላት የሚሆኑ ሰዎች ስለሕግ ማውጣትና በሕግ ስለሚደነገገው ጉዳይ ዕውቀት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የሕዝቡን ፍላጎት በማጥናት ወደ ተሻለ ኑሮ የሚወስዱ ሕግጋትን ማወጣት የሚያስችል ዕውቀት እንዲኖራቸው ይጠበቃል፡፡ በመሆኑም በልምድ እና/ወይም በትምህርት የተሻሉ ሰዎች ናቸው የፓርላማ አባል መሆን ያለባቸው ማለት ነው፡፡ የአገራችንን የፓርላማ አባልነት ታሪክ ስንዳስስ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ትንሽ ዘግይቶም ቢሆን የሕግ መምሪያም ይሁን መወሰኛ ምክር ቤት አባላት ቢያንስ ማንበብና መጻፍ መቻል ግዴታ ነበር፡፡ እንደውም ፈተና ይሰጥ ነበር፡፡ በወቅቱ ከነበረው ሕዝብ አንፃር በትምህርት የተሻሉ ሆነው መገኘት ነበረባቸው፡፡ በተለይ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ  (የአሁኑ አዲስ አበባ) ዩኒቨርሲቲ ከተከፈተ በኋላ በርካታ የፓርላማ አባላትም በማታው ክፍለ ጊዜ በዲፕሎማም በድግሪም ይማሩ ነበር፡፡ የሕግ ትምህርት የሚማሩት ደግሞ ብዙ ነበር፡፡ የተማሩ አባላት እየበዙ ሲሄዱ በሳምንት አንድ ቀን ብቻ ይሰበሰብ የነበረው ፓርላማ ወደ ሦሰት ቀን ከፍ አደረጉት፡፡ በመቀጠልም በሳምንት አምስት ቀናት (ከሰኞ እስከ ዓርብ) ሆነ፡፡

ደርግ ሥልጣን ሲይዝ የፓርላማም ፋይዳውም ቀረ፡፡ በ1980 ዓ.ም. ሥራ የጀመረው ብሔራዊ ሸንጎም (ፓርላማ) በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ነበር ስብሰባው፡፡ ለዚያም አፈ ጉባዔው ያው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ነበር፡፡ የፓርላማን ጥንተ ተፈጥሮ የሚያሟላ አልነበረም ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ለነገሩ የሶሻሊስታዊ አገሮች ፓርላማ ልክ በደርግ እንደነበረው ተመሳሳይ ናቸው፡፡ አገሪቱ ከምትከተለው ርዕዮተ ዓለም ነጥሎ መገምገም አይቻልም፡፡ ወደ ዘመነ ኢሕአዴግ ስንመጣ በእርግጥ የትምህርት ሁኔታ ለፓርላማ አባልነት መሥፈርት አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ፓርላማ በባህሪው (ቃሉም እንደሚያመለክተው) የመወያያ መድረክ ነው፡፡ ቃሉ የመነጨው “Parler” ከሚለው የፈረንሳይኛ ቃል ሲሆን የሚያመለክተውም መናገርን መወያየትን ነው፡፡ በመሆኑም የፓርላማ አባላት የወከሉትን ሕዝብ በሚመለከት መወያየትን መነጋገርን ይጠይቃል፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሊወያዩ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡ ከሚወያዩባቸው አጀንዳዎች ውስጥ በሕግ የሚወጡት መኖራቸው አይካድም፡፡ ይህ ከሆነ ስለሕግ አወጣጥም ስለይዘቱም ሊያውቁ ግድ ይላል፡፡ እስኪ የሕግ አወጣጥና የማርቀቅ ሒደት ከሚጠይቃቸው መሥፈርቶች ውስጥ የተወሰኑት እያነሳን የፓርላማችንን ሁኔታ እንመለከተው፡፡

የፌደራልም ይሁን የክልል ፓርላማ የሚያወጧቸው ሕግጋት ‘አዋጅ (Proclamation) በመባል ይታወቃሉ፡፡ የሚኒስትሮች ወይም የክልል ካቢኔ የሚያወጧቸው ደግሞ ‘ደንብ’ (Regulation) በመባል ይጠራሉ፡፡ እያንዳንዱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ወይም ቢሮ ወይም ተመሳሳይ ሥልጣን ያለው መሥሪያ ቤት የሚያወጣቸው ደግሞ ‘መመርያ’ (Directive) ይባላሉ፡፡ በዚህ መልክ የሚወጡ ሕግጋት በነጋሪት ጋዜጣ መታተም እንዳለባቸው ስለሕግ አወጣጥ የሚደነግጉት የፌዴራልም የክልልም አዋጆች ይገልጻሉ፡፡ ይሁን እንጂ በመመርያ የሚወጡት በነጋሪት ጋዜጣ እየታተሙ አይደለም፡፡ መመርያዎች በብዛት የሚገኙት መመርያውን ያወጣው መሥሪያ ቤት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ቢበዛ ከዚያ መሥሪያ ቤት ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያላቸው ተቋማት ዘንድና ድረ ገጽ ያላቸው ከሆኑ በድረ ገጻቸው ላይ ሊገኙ ይችላሉ፡፡ ይባስ ብሎ የፌዴራል መንግሥቱ ተቋማት ሆነውና የሥራ ቋንቋንው አማርኛ ሆኖ ሳለ በእንግሊዝኛ ብቻ መመርያ የሚያወጡ አሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ብሔራዊ ባንክ  ተጠቃሽ ነው፡፡

የክልልም ይሁን የፌዴራሉ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማንኛውም ሕግ በነጋሪት ጋዜጣ መታተም አለበት የሚለውን ሕግ ባይከበርም፣ እነሱም እየተከታተሉ ቁጥጥር እያደረጉ አይደለም ማለት ይቻላል፡፡ በመሆኑም የሕግ አውጭ ምክር ቤቶቻችን አንድ ድንጋጌ ሕግ ለመባል በጋዜጣ ታትሞ ለሕዝብ ይፋ መሆን እንዳለበት የደነገጉትን እየተፈጸመ ስለመሆኑ ባለመቆጣጠር ኃላፊነታቸውን እየተወጡ አይደለም ማለት እንችላለን፡፡ ወደ ዋናው የሕግ መዋቅር ጉዳያችን ስንመለስ በአዋጅ፣ በደንብም ወይም በመመርያ የሚወጣ ሕግ ሲዘጋጅ ስያሜ፣ ቁጥር፣ የወጣበትና ተፈጻሚ የሚሆንበት ቀን፣ መግቢያ፣ ሕጉን ለማውጣት መሠረት የሆነው የሕግ መሠረት፣ ትርጉም የሚሰጥበት ክፍል፣ ሕጉ ተፈጻሚ የሚሆንበት ወሰንና የማይፈጽምባቸው፣ መሠረታዊ (Substantive) እና የሥነ ሥርዓት ድንጋጌዎች፣ የቅጣት ድንጋጌዎች ብሎም የተሻሩ/የተሻሻሉ ሕግጋትን ያካትታል፡፡ እነዚህ ብቻ ናቸው ማለትም አይደለም፡፡ ሁሉም ጉዳዮች በማናቸውም አዋጅ፣ደንብና መመርያ ውስጥ መካተት አለባቸው ማለትም አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ሕግ ሲወጣ የሚኖረውን መዋቅር በአግባቡ ሳይረዱ በትክክል ለኅብረተሰቡ የሚጠቅሙ ሕግጋትን ማውጣት አዳጋች ሊሆን እንደሚችል መገመት ቀላል ነው፡፡ ለአብነት መግቢያ (Preamble) የሚባለውን የአዋጅ ክፍል እንውሰድ፡፡ ደንብና መመርያም እንዲሁ መግቢያ ይኖራቸዋል፡፡ ለአሁኑ ግን በአዋጅ መልክ የሚወጡትን ብቻ እንመልከት፡፡

መግቢያ ላይ ከሚካተቱት ነጥቦች ዋናው ለሕጉ መውጣት ምክንያት የሆነው ፖሊሲ ነው፡፡ ሕጉ የወጣበት የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና የባህላዊ ወዘተ. ፖሊሲያዊ ዳራ የሚገለጸው በአዋጁ መግቢያ ላይ ነው፡፡ የሚወጣው ሕግ ሊያሳካቸው የሚፈልጋቸው ግቦችም እንዲሁ በመግቢው ላይ መገለጽ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከሕገ መንግሥቱ መግቢያ በመጥቀስ ጉዳዩን በምሳሌ እንመልከት፡፡ የሕገ መንግሥቱ መግቢያ “እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች በአገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገታችን እንዲፋጠን. . . “በማለት ይጀምራል፡፡  ሕገ መንግሥቱ ማሳካት የሚፈልጋቸው ግቦች መሆናቸው ነው፡፡

ሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተካተቱት ድንጋጌዎችም ይሁኑ እሱን ተከትለው የሚወጡ ሌሎች ሕግጋት የመጨረሻ ግባቸው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንላቸው፣ ዘላቂና ቀጣይነት ያለው የዴሞክራሲ ሥርዓት መገንባት የሚያስችል፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ብልጽግና ማምጣት የሚችል መሆን ይኖርባቸዋል፡፡  በሕገ መንግሥቱ የሰፈሩ ዝርዝር ድንጋጌዎች ከላይ ተገለጹት ግቦች ለማሳካት የሚረዱ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ እነዚህ ግቦች እንዴት እንደተቀረፁም እነዚህን ተግባራዊ ለማድረግም ምን መደረግ እንዳለበት ጥቅል የፖሊሲ አቅጣጫ እዚሁ መግቢያው ላይ ተገልጿል፡፡ የራሳችንን ዕድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመንና በነፃ ፍላጎታችን. . . በማለት እንዴት እነዚህ ግቦች እንደተቀረፁ ይገልጻል፡፡

ከላይ በተገለጸው መንገድ ተለይተው የወጡት ግቦች ሲሳኩ የሚፈጥሩትን ውጤት (አገር) በዚሁ በሕገ መንግሥቱ መግቢያ በመጀመርያው መግቢያዊ አንቀጽ (Preambular Statement) ላይ አስቀምጧል፡፡ ይኸውም በሕግ የበላይነት የሚመራ በነፃ ፈቃድ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አገር እነዚህ ባህሪያትን ማንፀባረቅ የምትችል እንድትሆን ነው ሕገ መንግሥቱ የሚፈልገው፡፡ ሌላ ምሳሌ አዋጅ ቁጥር 1051/2009፣ የቡና ግብይትና ቁጥጥር አዋጅን እንመልከት፡፡ ይህ አዋጅ በጥቅሉ 25 አንቀጾችን ይዟል፡፡ በ33 ገጽ ነው የተዘጋጀው፡፡ መግቢያውን እንዲህ ይላል፡፡ “በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ በጥሬውና እሴት የተጨመረበት የቡና ምርት በጥራትና በከፍተኛ መጠን፣ ቀጣይነት ባለውና የምርት ዱካውን በጠበቀ ሁኔታ ለማቅረብ የሚያስችል የቡና ግብይትና የጥራት ቁጥጥር ሁኔታ መዘርጋት በማስፈለጉ የቡና ግብይትን ዘመናዊነት፣ ሕጋዊነትና ፍትሐዊነት በማሻሻል የቡና አምራቾችና የቡና ግብይት ተዋንያን የአገሪቱን ተጠቃሚነት በላቀ ደረጃ ማሳደግ የሚያስችል የተለያየ የግብይት ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ. . .” አዋጁ ወጥቷል፡፡  ይህ አዋጅ እነዚህን ግቦች በማስቀመጥ ነው 25 አንቀጽ የያዘ ድንጋጌ ያበጀው፡፡ የሁሉም ድንጋጌ መዳረሻ ደግሞ መግቢያው ላይ ተቀምጧል፡፡ የቡና ምርትን ጥራቱና መጠኑ እንዲጨምር ማስቻል፣ ጥራቱም ሆነ መጠኑ ሳይቆራረጥ የሚቀጥል እንዲሆን የሚያደርግ ሥልት መዘርጋት፣ የቡና ምርቱን ከመነሻው ጀምሮ ሌላ አገር ደርሶ እስኪሸጥ ድረስ ዱካውን ማወቅ የሚቻልበትን ስልት መቀየስ፣ የግብይት ሥርዓቱ በሕግ ከተቀመጠው አሠራር ውልፍት የማይል፣ ዘመናዊና ፍትሐዊ ማድረግ ብሎም የአገሪቱን ተጠቃሚነት ከፍ ማድረግ ነው፡፡

ከሕገ መንግሥቱና ከቡና ግብይትና የጥራት ቁጥጥር አዋጁ መግቢያ ላይ የተገለጹት ጥቅል የፖሊሲ አቅጣጫዎች ናቸው ማለት እንችላለን፡፡ እንኳንስ መግቢያው ላይ ይቀርና በዝርዝር ድንጋጌዎቹም የተገለጹት እንዲሁ በጥቅሉ ነው፡፡ እንዴት ተግባራዊ መሆን እንዳለባቸው የአሠራርና አፈጻጸም ሥርዓት መዘርጋት የሚጠበቅበት የሕግ አስፈጻሚው ነው፡፡ ስለሆነም በአዋጅ መግቢያ ብቻ ሳይሆን በውስጡ የሚገለጹትን አንቀጾች ከጥልቅ ጥናት የሚመነጩ፣ ከተለያዩ አማራጮች መካከል ከነባራዊ ሁኔታው ጋር የተጣጣሙና የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ፓርላማ ጥልቅ የፖሊሲ ጥናት ዕውቀት እንዲኖራቸው ይጠበቃል፡፡ እነዚህን ፖለሲዎች ነው አስገዳጅ እንዲሆኑ የሕግ ቅርፅ የሚያስይዟቸው፡፡ የሚፈጸሙበትን ሥልትና ሥርዓት ደግሞ አስፈጻሚው እንዲያዘጋጅ ይጠበቅበታል፡፡ በሌላ አነጋገር ተግባራዊ ያደርጋል ማለት ነው፡፡

በዚህ ረገድ የፓርላማን ሚና እንደማንኛውም የፖሊሲ አውጭ ተቋም  የሚከተለው የእሳት እራትና የጉጉት ምክክር ይገልጸዋል፡፡ ተረቱ እንዲህ ነው፡፡ ክረምቱ እየጠና በመሄዱ የብርዱ መጨመርም ያሳሰባት አንዲት የእሳት እራት አንድ አዛውንት ብልኃተኛ ጉጉትን እንዲህ ስትል ትጠይቃለች፡፡ “እሜቴ ጉጉት ክረምቱ እየበረታ ነው፡፡ ብርዱም እየጨመረ ነው፡፡ በዚህ ብርድ ይህንን ክረምት እንዴት መውጣት እንደምችል እስኪ እባክዎትን መፍትሔ ይጠቁሙኝ?” ትላለች፡፡ ጥበበኛዋ ጉጉትም “ደግሞ ይኼ ቀላል አይደል እንደ፡፡ በቃ ራስሽን ወደ ንብ መቀየር ነው፤” በማለት የመፍትሔ ሐሳብ ለእሳት እራቷ ይነገራታል፡፡ የእሳት እራት ግራ ገባት፡፡ “እንዴት አድርጌ ራሴን ወደ ንብ ልቀይር የምትችለው?›› ትላለች፡፡ ጥበበኛዋ ጉጉትም “ይህን ሂጂና ፈጻሚዎችን ጠይቂ፡፡ እኔ ፖሊሲ ወይም ሕግ አመንጪ እንጂ ፈጻሚ አይደለሁም፤” አለቻት፡፡

ከጉጉቷና የእሳት እራቷ ጭውውታዊ ተረት የምንረዳው ፖሊሲና ሕግ የሚያመነጩ በፖሊሲና በሕግ መልክ ለሕዝባና ለአገር የተሻለ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን ማመንጨት የሚችሉ ሰዎች እንደሚያስፈልጉት ነው፡፡ ፖሊሲውንና ሕጉን የሚያስፈጽም ቴክኒካዊ ዕውቀትና ችሎታ ያለው ሰው ደግሞ በአስፈጻሚው ውስጥ መካተት እንዳለበትም ጭምር ያሳያል፡፡ እንግዲህ የአገራችን ምክር ቤቶች ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትልልቅ ሐሳቦችን በማመንጨት የሕግ ቅርፅ በመስጠት ለአስፈጻሚው ሲሰጡና አፈጻጸማቸውንም ሲቆጣጠሩ አይስተዋሉም፡፡ በተቃራኒው ፖሊሲውንም፣ የሕግ ረቂቁንም አስፈጻሚው አካል (የሚኒስትሮች ምክር ቤት) አዘጋጅቶ ለፓርላማው በማቅረብ ማስፀደቅ የተለመደ ነው፡፡ ይህንን በቀላሉ ለማስረዳት ባሳለፍነው ሳምንት የፀደቀውን አዋጅ መመልከቱ በቂ አስረጂ ነው፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ራሱን እንዴት ማደራጀት እንዳለበት ወስኖ፣ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶችንና በሥራቸው ሊሆኑ የሚገባቸውን ተጠሪ ተቋማት ከእንደገና በማዋቀር ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማው አቅርቦ ወዲያኑ በማስፀደቅ ወዲያኑ ተሿሚ ሚኒስትሮችን አስፀድቋል፡፡ መሆን የነበረበት ግን ፓርላማውን አዲስ አወቃቀር አጥንቶ ያወጣቸው ሕግጋት የበለጠ እንዴት ሊፈጸሙ የሚችሉበትን አሠራር በሕግ ይፋ ማድረግ ነበር፡፡ ይህ ባይሆን እንኳን ቀድሞ የተቋቋሙት ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች የሚፈርሱበትን ምክንያት ለመቀበልና አዲስ ለማቋቋም ሰፋ ያለ ጥናት ካደረጉ በኋላ ነው በአስፈጻሚው የተዘጋጀውን ረቂቅ ሕግ ማጽደቅ ያለበት፡፡

የበለጠ ለማስረዳት አዲሱ የአስፈጻሚውን አካል ከእንደገና ለማዋቀር በምክንያትነት ከቀረቡት ውስጥ ጠንካራ ተቋም መገንባት አንዱ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ‘የሰላም ሚኒስቴር’ በሚባለው ሥር ከተካተቱት መካከል አንዱ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ይገኝበታል፡፡ ይህ ተቋም ከብዙ አገር ልምድ እንደምንረዳው ራሱን የቻለ ነገር ግን ኃላፊው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም ለፕሬዚዳንቱ ተጠሪ ይሆናል እንጂ ለሌላ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አይሆንም፡፡ ይህ ዓይነቱ አወቃቀር ከአገር ደኅንነት አኳያ በፓርላው ምንም ጥያቄ ሳይቀርብበት ፀድቋል፡፡ የብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ ተቋምን እንደ አንድ ነጠላ ምሳሌ ነው ያቀረብነው፡፡ ውይይት የሚፈልጉ በርካታ አስረጂዎችን መንቀስ ይቻላል፡፡ ቁምነገሩ ያለው ፓርላማው ለተፈጠረበት ወይም ለተቋቋመበት ዓይነተኛ ግብ መሥራት አለበት፡፡ የቀረበለት ረቀቂ ሕግ ላይ ፀድቋል እያሉ በነጋሪት ጋዜጣ ማውጣት ከበቂ በታች ነው፡፡

ይህን ክፍል ለማጠቃለል ፓርላማው የተቋቋመበትን ዓላማ ለመወጣት ጥረት ማድረግ አለበት፡፡ ከሚፈለገው ቁመና ላይ ባይደርስ እንኳን አባላቱ ያቅማቸውን ያህል መሞከር አለባቸው፡፡

“ባትዋጋ እንኳን በል እንገፍ እንገፍ

የአባትህ ጋሻ ትኋኑ ይርገፍ” እንዲል ሆ ባይ፡፡

ቢያንስ እንደ ፓርላማ እንገፍ እንገፍ ማለት ይጠበቅባቸዋል ለማለት ነው፡፡ በአዋጅ መልክ ድንጋጌ የሚሆኑ ሐሳቦችን፣ የፖሊሲ አማራጮችን፣ ወደ ሕግነት የሚቀየሩ ፖሊሲዎቹንም ጭምር ጠንቅቆ ማወቅ ከፓርላማ አባላት የሚጠበቅ ነው፡፡  ይሁን እንጂ እስካሁን ባለው ልማድ አዲስ ረቂቅም፣ ማሻሻያም መሻሪያም አዋጅ አቅራቢው አስፈጻሚው ነው፡፡ ፓርላማው በገቢር ፓርላማ ለመሆን ብዙ ነገር እንደሚቀረው ለማሳየት ነው፡፡  በሕግ አወጣጥ ረገድ ከፓርላማ የሚጠበቁ ሌሎች ኃላፊነቶችን በሌላ ክፍል  እንመለስበታለን፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...