በአንዳርጋቸው አሰግድ
ከ100 በላይ የሚሆኑት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች ሰላም መስፈን እንዳለበት ይስማማሉ፡፡ የሕግ የበላይነት መረጋገጥ እንዳለበት ይስማማሉ፡፡ የዴሞክራሲያዊ ምኅዳር መስፋት እንዳለበት ይስማማሉ፡፡ የ2012 ዓ.ም. ምርጫ ነፃና ፍትሐዊ መሆን እንዳለበት ይስማማሉ፡፡ እንደዚሁም በፀረ ሽብርና በብዙኃን መገናኛ ዘዴዎች አዋጆች፣ በምርጫ ቦርዱ አወቃቀርና ይዘት ላይና በምርጫው ዓይነት ላይ (“ያሸነፈ ሁሉን ይጠቅልል” ወይም አብላጫና ተመጣጣኝ) እየተወያዩ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የ2012 ዓ.ም. ምርጫ ነፃና ፍትሐዊ እንደሚሆን ደጋግመው ቃል ገብተዋል፡፡ ይህ መልካም ነው፡፡
የዴሞክራሲ ምኅዳር መስፋት ጥያቄ በምርጫ ቦርዱና በምርጫው ዓይነት መሻሻል ላይ ብቻ የተወሰነ/የሚወሰን ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ በምርጫ ቦርዱና ዓይነት ላይ ከሚደረገው ውይይት ባላነሰ፣ የምርጫ ፉክክሩ ሜዳ እኩልና ፍትሐዊ (Equal Playing Field) መደረግ አለበት፡፡ ለዚህም በተለይም የፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2008 እና የፋይናንስ ምንጭና የመገናኛ ዘዴዎች አጠቃቀም ሕግጋትና ደንቦች ትኩረት ተሰጥቷቸው ከወዲሁ መሻሻል ይኖርባቸዋል፡፡ ያለፉት አምስት ምርጫዎች በእኩልና በፍትሐዊ ሜዳ ላይ በተካሄዱ ፉክክሮች እንዳልተመሩና እንዳልተካሄዱ ማተቱ፣ የሚታወቀውን መድገም ነው፡፡ ይሁንና በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ መመለሱ፣ ለዴሞክራሲያዊ ምኅዳሩ ተሟልቶ መስፋት ያግዛል፡፡ መጪው ምርጫ በእኩልና በፍትሐዊ የፉክክር ሜዳ ላይ እንዲካሄድ ያስችላል፡፡ ሕጋዊ ቅቡልነትንና ተዓማኒነትን የተጎናፀፈ ውጤት ያስገኛል፡፡
በዚህም አኳያ ከምርጫ ቦርዱና ከምርጫው ዓይነት መሻሻል በተጨማሪ፣ ፓርቲና መንግሥት መለያየት አለባቸው፣ የብዙኃን ድርጅቶች ከመንግሥትና ከፓርቲዎች ነፃ መሆን አለባቸው፣ የፓርቲዎች የፋይናንስ ምንጭ ግልጽና ይፋ መሆን አለበት፡፡ የፓርቲዎች የመገናኛ ዘዴዎች ይዞታና አጠቃቀም በሕግ የተወሰነ መሆን አለበት፡፡ በሚከተሉት ክፍሎች በእነዚህ አራት መሠረታዊ የዴሞክራሲያዊ ምኅዳር መስፋት ጉዳዮች ላይ አጭር ዳሰሳ ለማድረግ እሞክራለሁ፡፡ ለዋቢ የተመረኮዝኩባቸው ጥናቶች በጽሑፉ መጨረሻ ላይ ተዘርዝረዋል፡፡ በቅድሚያ ግን አንድ ማስታወሻ፡፡ የማነሳቸው ጉዳዮች በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ሁኔታ በአንድ ጀምበር የሚጠናቀቁ እንዳልሆኑ አስተውላለሁ፡፡ ሆኖም ኢሕአዴግና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ስለዴሞክራሲያዊ መድረክ መስፋት አስፈላጊነት የሚያሳውቁት የምር ከሆነ፣ የጊዜ ገደብ በተቀመጠላቸው ስትራቴጂያዊ ዕቅድ፣ መርሐ ግብርና የተግባር ዝርዝሮች ላይ ከወዲሁ ለመስማማትና በጋራ ወደ ተግባር ለመተርጎም ከመነሳሳት ላይ ለመድረስ የማይቻልበት ምንም ምክንያት የለም፡፡
ፓርቲና መንግሥት መለያየት አለባቸው
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ምኅዳር የጠበበው አንድም በ1983 ዓ.ም. ሥልጣንን የጨበጠው ኢሕአዴግ በገበያ ኢኮኖሚ ስም የመንግሥት ፓርቲካ ፒታሊዝም አገዛዝን በመገንባቱና በማደርጀቱ ምክንያት ነው፡፡ ይህ የኢሕአዴግ አካሄድ “ማንኛውም ሕጋዊ ሰውነትን ያገኘ ፓርቲ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የንግድና ኢንዱስትሪ ሥራዎችን መሥራት አይችልም፤” የሚለውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ በቀጥታ ይፃረራል (አዋጅ 573/2000 አንቀጽ 51/3)፡፡
ሳራ ቮጋንና መስፍን ገብረ ሚካኤል በ2003 ዓ.ም. ባደረጉት ጥናት የኢሕዴግን ኩባንያዎች በመስክ ለይተው ከነጀርባ ታሪካቸውና አደረጃጀታቸው በሰፊው ያትታሉ (S.Vaughan & M. Gebremichael, April 2011፣ ገጽ 35 እስከ 58)፡፡ የብርሃኑ አበጋዝ ጥናታዊ ጽሑፍ በኢሕአዴግ 65 ኩባንያዎች እንደተያዙ ይዘረዝራል (የሕወሓት ኤፈርት 42፣ የብአዴን ጥረት ዘጠኝ፣ የኦፒዲኦ ቱምሳ (ዲንሾ) አሥር፣ የደኢሕዴን ወንዶ ሁለትና በጋራ ስም የተያዙ ሁለት ሌሎች)፡፡ ኤፈርት በኢትዮጵያ ከሚገኙት ሦስት ትልልቅ ይዞታዎች መካከል ከመንግሥትና ከሼክ አል አሙዲ ሚድሮክ ኩባንያዎች ቀጥሎ ሦስተኛውን ሥፍራ የያዘ ኩባንያ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች በዚህ ላይ “የሰብዓዊ” ድርጅቶች (Para NGOs) ባለቤቶች ናቸው (ብርሃኑ አበጋዝ፣ ሚያዚያ 2003 ዓ.ም. ገጽ 34 እና 66 እስከ 67)፡፡
ሳራ ቮጋንና መስፍን ገብረ ሚካኤል ይህንን ጉዳይ አስመልክተው በትክክል እንዳሉት፣ “(በዚህ ሁኔታ) አስቀድሞ የፖለቲካ ውሳኔ የማይሰጥባቸውን የኢሕአዴግ ኩባንያዎች ስትራቴጂ ለማሰብ አይቻልም” ገጽ 33)፡፡ ‹‹IDEA›› የሚባለው የስዊድን ዓለም አቀፍ ለዴሞክራሲና ለምርጫ ድጋፍ ተቋም ይህንን አስመልክቶ እንዳለውም “የፖለቲካ ፓርቲዎች የማምረቻና የንግድ እንቅስቃሴዎች ተዋናዮች ከሆኑ የጥቅም ግጭቶች ይጨምራሉ፡፡ በፖለቲካና በንግድ ጥቅም መካከል ያለው መስመር ይጠለሻል፤” (IDEA፣ 2014፣ ገጽ 47)፡፡ የፓርቲና የመንግሥት መለያየት በተጨማሪ ደግሞ ግን፣ የሥልጣን ክምችትን (Cumul of Power) መታገድ ይጠይቃል፡፡ በኢሕአዴግ አገዛዝ የፓርቲ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል፡፡ የፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል፡፡ የፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር የክልል ፕሬዚዳንት ይሆናል. . . ወዘተ፡፡ በተመለከቱት ዓይነት ቦታዎች ላይ የሚሾሙ ግለሰቦች በሹመት ዘመናቸው የፓርቲ አባልነታቸውን አሳርፈው ቢሰየሙ፣ የፓርቲና የመንግሥት ልዩነት በተሻለ ጎልቶ እንዲታይ ይጠቅማል፡፡ ባለሥልጣኖች ከመሾማቸው በፊት ያላቸው ንብረት በይፋ ቢገለጽ ደግሞ በሥልጣን መባለግን ይገታል፡፡ ጥቅምት 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ሪፖርተር ጋዜጣ “በብሔራዊ ደኅንነትና በሕግ አስከባሪ የፌዴራል ተቋማት ውስጥ በአመራርነትም ሆነ በአባልነት በማገልገል ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ሊነሱ እንደሚችሉ” ዘግቧል፡፡ መደገፍ ያለበትና በሌሎች ቁልፍ የሥልጣን ደረጃዎችም መቀጠል ያለበት ዕርምጃ ነው፡፡
ኢሕአዴግ ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ የመንግሥት ፓርቲ ካፒታሊዝም አገዛዙን መንግሥታዊ/ልማታዊ ካፒታሊዝም በማለቱ የተለወጠ ነገር አልነበረም፡፡ ወደ ኋላ “ኪራይ ሰብሳቢዎች” በተባሉት ላይ ዘመቻ በመክፈቱም እንደዚሁ፡፡ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች በመስከረም 2011 ዓ.ም. ባካሄዷቸው ተከታታይ ጉበዔዎች አንዳንድ መሪ አባሎቻቸው “በክብር” መሰናበታቸው፣ ወጣትና የተማሩ አባላትን በየደረጃው ማካተታቸውና የመተዳደሪያ ደንቦች መሻሻላቸው መልካም ነው፡፡ ይህ ግን ስለኢሕአዴግ ውስጣዊ የተሃድሶ ጥረት ይናገር እንደሆነ እንጂ፣ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ምኅዳር መስፋት የሚያበረክተው መሠረታዊ አስተዋጽኦ ውስን ነው፡፡
ሙስናን፣ ያላግባብ መበልፀግን፣ የፍትሕ ዕጦትንና ብልሹ አስተዳደርን አንሰራፍቶ ኢሕአዴግ “ኪራይ ሰብሳቢዎች” ያላቸውን (በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ አገላለጽ “ሌቦችን”) የፈለፈለውና ያለፉትን ሦስት ዓመታት ነውጥ የጠራው ዓብይ ጉዳይ፣ በመንግሥታዊ/ልማታዊ ካፒታሊዝም ስም የአንድ የመንግሥት ፓርቲ ካፒታሊዝም ሥርዓተ አገዛዝ መደራጀቱና ተስፋፍቶ መንሰራፋቱ ነው፡፡ በመሆኑም መንግሥት የሚባለው ተቋም የኢሕአዴግ ሁዳድና “ጉልት” (አቶ ለማ መገርሳ) እስኪባል ድረስ በፓርቲ አመራሮች፣ በሲቪልና በሚሊተሪው ቢሮክራሲ፣ በብሔር አስተዋጽኦ ካድሬዎች፣ በጥገኞች፣ በደላሎችና በኮንትሮባንዲስቶች በግላጭ የተጠለፈ ተቋም ሆነ፡፡ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) በታኅሳስ 2010 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ በሰጡት አንድ ቃለ መጠይቅ እንዳብራሩት፣ ‘(ጠላፊዎቹ) በራሱ በኢሕአዴግ ውስጥ ሌላ ያልታወጀ ድርጅት ለመሆን አስከመብቃት ደረሱ፡፡ በፌዴራሉና በክልል መንግሥታት አካሎች ውስጥ ሌላ ያልታወጀ መንግሥት አስከመሆን ዘለቁ’፡፡ አንግሎ ሳክሰኖች ይኼንን ጥልቅ/ጥልቁ መንግሥት (The Deep State) ይሉታል፡፡ የዴሞክራሲ ምኅዳሩ እንዲሰፋ ኢትዮጵያ በጥልቅ/ጥልቁ መንግሥት የምትገዛ አገር መሆኗ ማብቃት ይኖርበታል፡፡ ይህንን ማለት በ27 ዓመታቱ የመንግሥት ፓርቲ ካፒታሊዝም ዘመን ዕድገትና መሻሻል አልተገኝም ማለት አይደለም፡፡ ከእነ ችግሮቻቸው ቢሆንም በርካታ ዕውቅና የሚገባቸው ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ ለውጤቶቹ ዕውቅና አለመስጠትና በጥላቻ ስሜት ማንኳሰስ፣ ከየት እንደሚጀምሩና በምን ላይ ተመሥርተው እንደሚቀጥሉ ለማወቅ ያለመፈለግ ያህል ነው፡፡ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ አገዛዝ ወደ ደርግ፣ ከደርግ ወደ ኢሕአዴግ ከሆነው አንድም ትምህርት ሳይቀስሙ መቀጠል ነው፡፡ የሚቀጥል እንጂ ሁሌም ያለፈውን አውግዞ በአዲስ ለመጀመር የሚግተረተር ለውጥ በኢትዮጵያ ምድር ማብቃት አለበት፡፡
ዕውቅና አለመስጠት ሁለተኛም ለኢትዮጵያ ዕድገትና ብልፅግና በእርግጥ የሚያስፈልገውን የመንግሥታዊ/ልማታዊ ካፒታሊዝም የልማት ጎዳና በደፈናው መቃወም ማለት አይደለም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ የኒዮሊበራሎችን ተረት ተረት ሳያላምጡ መዋጥ ማለት እይደለም፡፡ የኢትዮጵያን ልማት ጉዳይ ከመንግሥት ፓርቲ ካፒታሊዝም መንጋጋ ውስጥ ፈልቅቆ ማውጣትና ኢትዮጵያዊ የሆነን መንግሥታዊ/ልማታዊ ካፒታሊዝም በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ መሠረት ላይ መገንባት ማለት ነው፡፡ መንግሥት ከኢኮኖሚ ተሳትፎ ይውጣ፣ የማምረቻ፣ የማከፋፈያ፣ የአገልግሎት ሰጪና የገንዘብ ድርጅቶች ሁሉ ከመንግሥት ይዞታ ወደ ግል ንብረት ይዛወሩ፡፡ አገሮች ለውጭ ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋይ ፍሳሽና ለውጭ ሸቀጦች ዝርገፋ ያለገደብ ይከፈቱ፣ የብሔራዊ ገንዘብ ዋጋ ይቀነስ፣ ሕጎችና ደንቦች ለግል ባለንብረቶች ትርፍ መጨመር በሚጠቅሙ መንገዶች ይደንገጉ፣ በባለሀብቶች አነስተኛ ቀረጥ ይክፈሉ፣ መንግሥት ለምግብ፣ ለሕክምና፣ ለቤት፣ ለውኃ፣ ለመብራት፣ ለማመላለሻ፣ ለምርምርና ለቴክኖሎጂ ዕድገት. . . የሚያደርገው ድጎማ ይሰረዝ፡፡ ኢኮኖሚ በገበያ ጡንቻ ብቻ ይወሰን፣ የሠራተኛ ደመወዝ ይቀነስ (በገበያ ይወስን)፣ ሠራተኞች በማኅበር ለመደራጀት ያላቸው መብት ይገደብ፣ የሥራ መቆም መብት ይሰረዝ. . . በሚለው የኒዮሊበራሎች “የዕድገት” ጎዳና እያሽቆለቆለ የሄደ እንጂ ያደገና የተመነደገ አንድም የአፍሪካ፣ የእስያና የደቡብ አሜሪካ አገር አልታየም፡፡
ብዙኃን ድርጅቶች ከመንግሥትና ከፓርቲዎች ነፃ መሆን አለባቸው
በኢትዮጵያ የማኅበራዊ ጥናት ፎረም (FSS) ምርምራዊ ጥናት መሠረት፣ ኢትዮጵያ በ2012 (2004) ወደ 120 የተመዘገቡ የብዙኃን ድርጅቶች (የወጣቶች፣ የሴቶች፣ የመምህራን፣ የሠራተኞች፣ የባለሙያዎች. . .) ነበሯት፡፡ ይሁንና “የብዙኃን ድርጅቶቹ ከሲቪክ ማኅበሮች በተለየ አብዛኛውን ጊዜ የሚደራጁት በመንግሥት (በኢሕአዴግ) ድጋፍና ትብብር ነው፡፡ አወቃቀራቸው የመንግሥትን አወቃቀር የሚከተል ነው፡፡ ከሚኒስትሮችና ከመንግሥት (ከኢሕአዴግ) ቢሮዎች ጋር ቅርብ የሥራ ትስስሮች አሏቸው፡፡ ባይፈልጉትም እንኳን እንደ ነፃ አካላይ ሳይሆን የሥራው አስፈጻሚው አድርጎ በሚያያቸው መንግሥት (ኢሕአዴግ) ቁጥጥር ሥር ይወድቃሉ፡፡ የአደረጃጀት ተፈጥሯቸውና አሠራራቸው፣ ስለዚህም የቆሙላቸውን ዓላማዎች በሥራ ከማዋል ያግዳቸዋል፡፡ የራሳቸውን ጥቅምና ሚና ወደ ጎን አድርገው ለመንግሥት (ለኢሕአዴግ) እንዲያሸበርኩ ይገደዳሉ” (FSS & ATOS, March 2012፣ ገጽ 10)፡፡
ተጨማሪ ሀተታ አያሰፈልገውም፡፡ ሲጀመር ለ100 ሚሊዮን ሕዝብ 120 የብዙኃን ድርጅቶች ብቻ መቆጣጠራቸው በራሱ አሳፋሪና አሳሳቢ ነው፡፡ ሁለተኛ የብዙኃን ድርጅቶች ከኋላቸው በርካታ አባላት ያሏቸው ድርጅቶች ብቻ አይደሉም፡፡ በምርጫ ክንዋኔዎች ውስጥ ለምሳሌ በሰፊው ይሳተፋሉ፡፡ ስለዚህም በኢሕአዴግ መንግሥት ከሚደገፉትና ከሚያስተባብሩት የኢትዮጵያ ብዙኃን ድርጅቶች ገለልተኝነትንና ፍትሐዊነትን ለመጠበቅ አይቻልም፡፡ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ምኅዳር እንዲሰፋ፣ ብዙኃን ድርጅቶች ከመንግሥትና ከፓርቲዎች ነፃ መሆን አለባቸው፡፡ ነገር ግን ብዙኃን ድርጅቶች የሚባሉት ብቻ ሳይሆኑ፣ ከትግራይ ባዕታዎች እስከ አንድ ለአምስቶቹ ድረስ ያሉት ድርጅቶችም ከመንግሥትና ከፓርቲዎች ነፃ መሆን አለባቸው፡፡
የፓርቲዎች የፋይናንስ ምንጭ ግልጽና ይፋ መሆን አለበት
አዋጅ 573/2008 አንቀጽ 52/1 ሀ እስከ በ በግልጽ እንደዘረዘረው፣ “ከውጭ ዜጎች፣ ከውጭ መንግሥታትና ከውጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከበጎ አድራጎትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከሕገ መንግሥቱ ውጪ ሥልጣን ለመያዝ ከተደራጀ ቡድን ወይም ሰው፣ ከሽብርተኛ ድርጅቶች፣ ካልታወቀ ምንጭ፣ ከሃይማኖት ድርጅቶችና የሕግ እስረኞች ሥጦታ ወይም የገንዘብ ድጋፍ መቀበል በጥብቅ የተከለከለ ነው”፡፡ ፓርቲዎች ገንዘብና ሥጦታ መቀበል የሚችሉት “ከአባልነት መዋጮ፣ ቦርዱ አጥንቶ በሚያስቀምጠው ጣሪያ መሠረት በኢትዮጵያውያን ግለሰቦችና ኩባንያዎች የሚደረግ ሥጦታ ወይም ዕርዳታ ከመንግሥት ከሚሰጠው ድጋፍና ዕርዳታና ቀጣይነት በሌለው የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ነው” (አንቀጽ 51 1 እና 2)፡፡ የተጠቀሱት አንቀጾች ባለፉት ዓመታት በውል ተከብረው ነበር ለማለት አይቻልም፡፡ ለ1997 ዓ.ም. የተወዳደሩት የፖለቲካ ድርጅቶች ለምሳሌ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከተገኘው የ515,150 ዶላር ድጋፍ ውስጥ ሕወሓት 88,750፣ ቅንጅት 71,000፣ ኅብረት 47,500፣ ኦሮሞ ፌዴራሊስት ንቅናቄ 34,150፣ ነፃ ተወደዳሪዎች 141,200 እናም ሌሎች ትንንሽ ፓርቲዎች በድምሩ 132,300 ዶላር ተቀብለዋል (ዶ/ር ወንድወሰን ተሾመ፣ 2009/2001፣ገጽ 409)፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲዎች በአዋጁ መሠረት ከመንግሥት የተደረገላቸው ድጋፍ እንደሌለ ያሳውቃሉ፡፡ በሌላ በኩል ከሌሎች ምንጮች (ከአባል መዋጮ፣ ከወዳጅ፣ ከባለሀብት፣ ከዳያስፖራና ሌሎች) ስላገኙት ድጋፍና ሥጦታ በግልጽና በይፋ ያሳወቁበት መረጃ የለም፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ፓርቲዎቹም ሆኑ ደጋፊዎቹ የኢሕአዴግን ምላሽ ይፈሩ ስለነበር የደረሳቸው ድጋፍ በግልጽና በይፋ እንዲታወቅ አይፈልጉም፡፡ ለጋሹም እንዲታወቅበት አይፈልግም፡፡ የመንግሥት ምላሽ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን በሚያፍንበት የፖለቲካ ድባብ ውስጥ፣ ስለሰፊ ዴሞክራሲ ቀርቶ ስለ ጭላንጭሉ መናገር እንደማይቻል ማተቱ ትርፍ ነው፡፡ በሌላ በኩል የውጭ ድጋፍ በምርጫዎች ውጤት ላይ ሊኖረው የሚችለው አሉታዊ ጫና በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ዶ/ር ወንደሰን በተጠቀሰው ጥናታቸው እንደሚሉት ለምሳሌ፣ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ “የዳያስፖራ ለጋሽ” ከተባለው መካከል “ከፊሉ ከኢንጂነር ኃይሉ ሻውልና ከፊሉ ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋራ በመወገናቸው አሉታዊ ሚና ተጫውተዋል” (ገጽ 407)፡፡ ሌሎች እንዲያውም፣ የወቅቱ የተፎካካሪ ድርጅቶች ከምክር ቤት የመግባት/አለመግባት ጥያቄ የተወሰነው በዳያስፖራው “ለጋሾች” ነው ይላሉ፡፡ ዛሬ ረገብ ብለው ከዶ/ር ዓብይ ጀርባ የተሠለፉት የዳያስፖራ “ለጋሾች” የነገ ሥፍራና ሚና ወደፊት ይታያል፡፡ እኩልና ፍትሐዊ የፉክክር ሜዳ የፓርቲዎች የፋይናንስና የዓይነት ሥጦታ ምንጭ በሕግ የተደነገገ፣ ኦዲት የሚደረግና በይፋ የሚገለጽ መሆኑን ይጠይቃል፡፡ የፓርቲዎች ገቢ/ወጪ ግልጽና ይፋ መደረጋቸውን በሕግ መደንገግ፣ በተግባር መተርጎምና ይፋ መደረግ ይጠይቃል፡፡ እንዲሁም እንደ ፓርቲ ሊኖራቸውና ላይኖራቸው የሚችሉት የማምረቻና የማከፋፋያ ድርጅቶችና የዜና ማሠራጫ ዘዴዎች ንብረት በሕግ ተለይተው የተወሰኑ መሆናቸውን ይጠይቃል፡፡
የፓርቲዎች የመገናኛ ዘዴዎች ይዞታና አጠቃቀም በሕግ የተወሰነ መሆን አለበት
ሕገ መንግሥቱ “ማንኛውም ሰው ያለ ምንም (የመንግሥት) ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለጽ ነፃነት አለው”፣ “ይህ ነፃነት በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ ወሰን ሳይደረግበት የመቀበልና የማሠራጨት ነፃነቶችን ያካትታል” ይላል (አንቀጽ 29፣ 1 እና 2)፡፡ የኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ በበኩሉ፣ “በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉትን የብዙኃን መገናኛ ማለትም ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥንና ጋዜጦች የዕጩ ደጋፊ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶችና የኅብረተሰብ ክፍሎችን ያለ አድልኦ የመጠቀም መብት አላቸው” ይላል (አዋጅ 532/1999 አንቀፅ 1)፡፡ ሕጎቹ በተግባር እንዳልዋሉ በማተት ቀለም ማባከን አያስፈልግም፡፡ የኢትዮጵያ ጠበቆች ማኅበር በጉዳዩ ላይ ቀኑን ሙሉ ውሎበት ያቀረበውን ትንተናና ምክረ ሐሳቦች መመልከቱ ይበቃል (Ethiopian Lawyers Associatio፣ May 2, 2015)፡፡
አንድ የ1995 ዓ.ም. የሜዳ ጥናት ግኝት እንዳመለከተው፣ “ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የመንግሥት የብዙኃን መገናኛዎችን በእኩል ይጠቀማሉ ወይ?” ለሚለው ጥያቄ በአዎንታዊ የመለሱት ተጠያቂዎች 8.8 በመቶ ብቻ ነበሩ፡፡ በ2000 ዓ.ም. በድጋሚ ለተካሄደ ሌላ የሜዳ ጥናት ጥያቄውን በአዎንታዊ የመለሱት 30.7 በመቶ ነበሩ፡፡ የተቀሩት 69.3 ከመቶ በከፊል እንደሚስማሙና ጨርሶ እንደማይስማሙ ያስታወቁ ነበሩ (AIM-DG፣ December 2012፣ ገጽ 112)፡፡ በ2000 ዓ.ም. 30.7 በመቶ ያህሉ በአዎንታዊ መመለሳቸው፣ ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ የነበረውን በነፃ የመናገር ፍርኃት ድባብ የሚያንፀባርቅ እንጂ፣ ተጠያቂዎቹ በነፃ የሰጡት አመለካከት እንደነበር ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፡፡ የመንግሥት የብዙኃን መገናኛ ዘዴዎች ኢሕአዴግና አባል ድርጅቶቹ እንደ ግል ንብረታቸው የሚገለገሉባቸው መሣሪያዎቻቸው እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ኢሕአዴግ በተጨማሪም በቀጥታና በተዘዋዋሪ የገነባቸው የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ድርጅቶች በአገር አቀፍና በክልሎች ደረጃዎች አሉት፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወዲህ ከእነ ጭራሹ ደግሞ አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶችና “አክቲቪስት” የሚባሉ ተዋናዮች የቴሌቪዥን ጣቢያዎቻቸውን እንዲተክሉ እየተፈቀደ ነው፡፡ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጣቢያዎቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ እንዲያስገቡ ይፈቀድላቸዋል የተባሉት ድርጅቶች፣ በእነ ማን የገንዘብና የቴክኒክ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ድጋፍ እንደሚንቀሳቀሱ በግልጽ አይታወቅም፡፡ ይህም ሆኖ ፈቃዱ በሥራ ላይ ከዋለ የትኛውም “አክቲቪስት” እና የፖለቲካ ድርጅት “መብት” ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ ይህም የድኅረ 2010 ዓ.ም. ኢሕአዴግን የእኩልና የፍትሐዊ የፉክክር ሜዳ ጥሰት፣ በሌላ የኢሕአዴግ የእኩልና የፍትሐዊ ፉክክር ሜዳ ጥሰት “ለማረም” የመወሰን ያህል ይሆናል፡፡ በዚህ የሚከፈተውን የውዥንብር ድባብ ለማሰብና ለመገመት ነብይ መሆን አያስፈልግም፡፡
በዴሞክራሲያዊ አገሮች የፖለቲካ ድርጅቶችና ተዋናዮች እንኳን የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ድርጅቶች ባለቤት ሊሆኑ ቀርቶ፣ አክሲዮኖቻቸውንም እንዲገዙ አይፈቀድም፡፡ አሁን አሁን ድረ ገጽ፣ ፌስቡክና ትዊተር መተከላቸው ይህንን መሠረታዊ የዴሞክራሲ አቋም አይሽረውም፡፡ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ የተለየ ወይም የላቀ ለማስመሰል የሚያነሳሳ አንድም አስገዳጅ ምክንያት የለም፡፡ በሲቪክና በዴሞክራሲ ባህል አኳያ የሚገኙበትን ነባራዊ ሁኔታ በውል ማጤኑ የተሻለው ነው፡፡ በመስከረም መጀመርያ ለሪፖርተር ጋዜጣ ባቀረብኩት ጽሑፍ እንዳመለከትኩት፣ “የዴሞክራሲያዊ መድረኮች መስፋት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ተዋናዮች የሚዲያ አጠቃቀም ሕግና ደንብ መኖርን ይጠይቃል፡፡ ፓርቲዎች በፌዴራልም ሆነ በክልሎች የብዙኃን መገናኛዎች ውስጥ እጆቻቸውን እንዳያስገቡ ይጠይቃል፡፡ ይህ መሠረታዊ የዴሞክራሲ ሥርዓት ጉዳይ ሥርዓት ሳይዝ በፊት የሚወሰድ ማንኛውም ዕርምጃ፣ በዴሞክራሲ መድረኮች መስፋት ስም ዴሞክራሲን ራሱን መፃረር ይሆናል፡፡ ለዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ፉክክር የሚያስፈልገውን እኩልና ፍትሐዊ ሜዳ አጣሞ መገንባት ይሆናል፤” (“በይቅርታ መሻገርና በፍቅር መደመር”፣ ሪፖርተር፣ መስከረም 13 ቀን 2011 ዓ.ም.)፡፡
ማጠቃለያ
የ1966 ዓ.ም. አብዮት አንደኛው ወቅታዊ ምክንያት በወሎና በትግራይ በገባው አሰቃቂ ችጋር በሺሕ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ማለቃቸውና መፈናቀላቸው ነበር፡፡ በ2011 ዓ.ም. ኢትዮጵያ በሦስት ሚሊዮን የተፈናቀሉ ሕዝቦቿ የዓለም ተፈናቃዮችን “ክብረ ወሰን” የበጠሰች አገር ሆናለች፡፡ የ1960’ዎቹ ትግል ለመሬትና ለዴሞክራሲ ነበር፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት በተካሄደው የመሬት ወረራ ኢትዮጵያ የሁለተኛው ዙር “የመሬት ለአራሹ” ትግል እንዳታይ ያሠጋል፡፡ ከ1960’ዎቹ ጀምሮ ለዴሞክራሲ በተደረገው ትግል በብዙ ሺሕ ሕይወት ተቀጥፏል፡፡ በብዙ ሺሕ በእስር ተንገላተዋል፡፡ ብዙ ሺሕ ተሰደዋል፡፡ የብዙ ሺሕ ቤት ፈርሷል፡፡
“ዴሞክራሲ አሁኑኑ” የሚለው የ1960’ዎቹ ጥሪ በ2011 ዓ.ም. ለሁለተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር እየተስተጋባ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ለሁለተኛ ጊዜ ደረታቸውን እየሰጡለት ነው፡፡ የ1960’ዎቹ ትግል አንደኛው ጥሪ “ሥራ ለሥራ አጦች” ነበር፡፡ በ2011 ዓ.ም. ኢትዮጵያ “ሥራ ለሥራ አጦች” ጥያቄ፣ ከከተሞች አልፎ ገጠሮቿንና ብዙ ሺሕ ወጣቶችን ለአሰቃቂ ስደትና ለተለያዩ የሱስ ባርነት ዳረገ፡፡ በተግባር ሊተረጎም የሚችል ስትራቴጂካዊ (Realistic) መልስ በአስቸኳይ ያስፈልጋል፡፡ በእኔ አረዳድ ኢትዮጵያ ምናልባትም እንደ 1930’ዎቹ የአሜሪካኑ ሩዝቬልት አዲስ ውል ራሱን የቻለና በቢሮክራሲ ያልተተበተበ ሥራ ፈጣሪ የወጣቶች የቁጠባና የብድር ተቋማት የሚያስፈልጓት አዋሳኝ ምዕራፍ ላይ ናት፡፡ ታሪክ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለስንተኛ ጊዜ ፈገግ ብላ፣ ኢትዮጵያን ለዴሞክራሲ ጎህ መቅደድ የተቃረበች አገር አስመስሏታል፡፡ 2012 ዓ.ም. የ1997 ዓ.ም. ድጋሚ እንዳይሆን የፉክክር ሜዳውን በውል ማነፅ፣ መገንባትና መደልደል ያስፈልጋል፡፡ የ2011 ዓ.ም. ፓርቲዎች አነሰ ቢባል በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ዳር ድንበሯ መከበር፣ በሰላምና ፀጥታ ዓብይነት፣ በሕግ የበላይነት መረጋገጥ፣ በሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ በብሔሮቿ እኩልነት አንድነቷን ባጎለበተች ኢትዮጵያ ማበብ፣ በዴሞክራሲ ምኅዳሩ መስፋት፣ በፍትሐዊ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ተቋዳሽነት መደራጀት፣ በቀጣናዋና በዓለም መድረኮች የተከበረችና የኮራች ኢትዮጵያ ዜጋ በመሆን ይስማማሉ፡፡
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቅድሚያ በእነዚህ ብሔራዊ/አገራዊ የጋራ ስትራቴጂካዊ ጥቅሞች ላይ ተስማምተው አማራጮቻቸውን እንደየፖለቲካ ቤተሰባቸው እያቀረቡ በሰላማዊ መንገዶች የማይፎካከሩበት አንድም ምክንያት የለም፡፡ የ2011 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የታሪክ ፈገግታ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች የአዲሲቱና የዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ መሐንዲሶች እንዲሆኑ የጋበዘ ነው፡፡ ፈገግታዋን የማክሰም መብት የላቸውም፡፡ አንድ ጓደኛዬ እንዳለው የ1997 ዓ.ም. ምርጫ የከሸፈው አንድም፣ ሥልጣኑን ለመልቀቅ የተዘጋጀ ገዥ ፓርቲ ስላልነበረና ሌላም ሥልጣንን ለመረከብ የተዘጋጁ ፓርቲዎች ስላነበሩ ነበር፡፡ የ1997 ዓ.ም. ድጋሚ መሆን የለበትም፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡