Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ፍኖተ ካርታ ፋይዳ አለው!

የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ፍኖተ ካርታ ፋይዳ አለው!

ቀን:

የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ፍኖተ ካርታ ፋይዳ አለው!

በሸዋዬ ተስፋዬ

በኢትዮጵያ የተጀመረው የመደመርና የይቅርታ ለውጥ እንቅስቃሴ በአገራችን የፖለቲካ መረጋጋት ለማስፈን፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለማጎልበት፣ እንዲሁም የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ልማት ዕውን ለማድረግ ባሳደረው ተስፋ ምክንያት በአብዛኛው ሕዝብ ተስፋ ያሳደረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም በእነዚህና ሌሎችም ዓብይ መስኮች የሚጠበቅ ስኬትን በዕውን ለማረጋገጥ፣ አስፈላጊ የሆኑ የፖሊሲና የተቋማዊ አሠራር ማሻሻያ ዕርምጃዎችን ማቀድና መተግበር ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው፡፡

ከእነዚህም መካከል የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ዓብይ ተግባር እንደመሆኑ፣ አግባብነት ያላቸው ሕግጋትን በማሻሻል የፖለቲካ ምኅዳሩን አመቺ ለማድረግ የለውጥ አመራሩ በተግባር መጠመዱ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ሆኖም የአገራችን የዴሞክራሲ አፈጻጸም ሥር በሰደዱ ውስብስብ ችግሮች ምክንያት እጅግ በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ፣ በመስኩ ጉልህ መሻሻል ለማሳየት በተነጣጠሉ የሕግ ማሻሻያዎች ከመገደብ ይልቅ የተሟላ የዴሞክራሲ ግንዛቤ ላይ በመመርኮዝ ሁለንተናዊ ማሻሻያዎችን በተቀናጀ መንገድ ለማቀድና ለመከወን የሚያግዝ ፍኖተ ካርታ መንደፍ (በትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ እንደሚካሄደው)፣ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሊያበረክት እንደሚችል ጽሑፉ ከወዲሁ አበክሮ ያስገነዝባል፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ አፈጻጸም ደረጃ ከሌሎች አገሮች ጋር በንፅፅር በማቅረብ በተያዘው ለውጥ እንቅስቃሴ የዴሞክራሲ ሥርዓት በመገንባት፣ ጉልህ ስኬት ለማስመዝገብ የሚያግዝ ፍኖተ ካርታ የሚኖረውን አስተዋፅኦ ለመጠቆም ያለመ ነው፡፡ የጽሑፉ ይዘት በሦስት ክፍል የተዋቀረ ነው፡፡ የመጀመርያው ስለዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብና መመዘኛ የተሟላ ግንዛቤ ማስጨበጥ የሚያስችል አጭር ማብራሪያ ያቀርባል፡፡ ሁለተኛው ክፍል በቅድሚያ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ አፈጻጸም ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ጋር በንፅፅር ያሳያል፡፡ ከዚህ በማያያዝ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ አፈጻጸም በአምስት ዓብይ ዘርፎች ያቀርባል፡፡ በመጨረሻም ሦስተኛው ክፍል በአገራችን ከተጀመረው ለውጥ አንፃር የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ፍኖተ ካርታ የሚኖረውን ፋይዳ፣ እንዲሁም የእነዚህን የትኩረት ጉዳዮች በመጠቆም ያጠቃልላል፡፡

የዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብ

የዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብ ትርጉምና የአገሮች አፈጻጸምን በውል ለመመዘን የሚያስችል በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ መስፈርትን በሚመለከት እስካሁን ድረስ ስምምነት ላይ አልተደረሰም፡፡ በመሆኑም በአካዳሚ ተቋማትና የዴሞክራሲን ሥርዓት ለማስፋፋት በሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች አማካኝነት የደራ ውይይትና ክርክር በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ምክንያት አንዳንዶች ዴሞክራሲን በውል ትርጉም ያልተሰጠው የፖለቲካ ሥርዓት በሚል ይገልጹታል፡፡

ዴሞክራሲንና ነፃነትን አንዳንዶች እንደ ተመሳሳይ ጽንሰ ሐሳብ የሚገነዘቡና የሚገለገሉ ቢሆንም፣ አብዛኞች የተለያየ ትርጉም ያላቸው መሆኑን በአፅንኦት ይገልጻሉ፡፡ ከእዚህ በመነሳት ዴሞክራሲን በተቋማዊ ሥርዓት ነፃነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ መርሆዎችና የአሠራር ዘዴዎች ስብስብ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡

በአብዛኞች ዕይታ የዴሞክራሲ ሥርዓት በዝቅተኛ ደረጃ የሚከተሉት ባህርያትን ያካትታል፡፡ እነዚህም የመንግሥት ሥልጣን በብዙኃን ድምፅ መወሰን፣ ነፃና ፍትሐዊ የፖለቲካ ምርጫ ውድድር መካሄድ፣ የኅዳጣን የኅብረተሰብ ክፍሎች መብቶች መከበርና መሠረታዊ የሆኑ ሰብዓዊ መብቶች መከበር ናቸው፡፡ ከእነዚህም በተጨማሪ የዴሞክራሲ ሥርዓት የሕግ እኩልነት መኖርና የፖለቲካ ሐሳብ ብዝኃነት በዕውን መንፀባረቅን ይሻል፡፡

በአንዳንዶች አስተያየት የዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብ መሆን ወይም ያለመሆን ሁለትዮሽ ኩነትን የሚያመለክት ሲሆን፣ ከዚህ በተቃራኒ የዴሞክራሲ አፈጻጸም መመዘኛ ተከታታይ ሒደትንና የተለያዩ ደረጃዎችን እንደሚያካትት አብዛኞች ይጠቁማሉ፡፡ ለምሳሌ ፍሪደም ሐውስ በሚል የሚጠራው ድርጅት የሚያዘጋጀው የአገሮች የዴሞክራሲ አፈጻጸም ዓመታዊ ዘገባ የፖለቲካ ነፃነት አሥር መለኪያዎችንና የሲቪል ማኅበራት ነፃነት 15 መለኪያዎችን የሚያካትት ሲሆን፣ በእነዚህ ዘርፎች ያለውን አፈጻጸም ከ1 እስከ 7 በሆነ ሚዛን በመለካት ጠበብ ያለ የዴሞክራሲ ሥርዓት መሠረታዊ ባህርይ ላይ ያተኩራል፡፡

ይህ ቀመር የፖለቲካ ሥልጣን በነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ውድድር የሚመሠረትና በሥልጣን ላይ የሚገኝ ፓርቲ በምርጫ ውድድር የብዙኃን (አብላጫ) ድምፅ አሸናፊ ካልሆነ፣ የተረጋጋ የሥልጣን ሽግግር እንዲኖር ፈቃደኛ መሆንን ያመለክታል፡፡ ከእዚህም ሌላ የፖለቲካ ነፃነት፣ የምርጫ ሒደት፣ የፖለቲካ ሐሳብ ብዝኃነት፣ የተወሰኑ የመንግሥት ተግባራት አፈጻጸምን እንዲሁም ጥቂት የተሳትፎ ጉዳዮችን ያካትታል፡፡

ይህም በጠባብና በሰፊ የዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብ መካከል ያለውን ቁልፍ ልዩነት ያንፀባርቃል፡፡ ከዚህ ተቃራኒ ሰፊ የሆነ የዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብ መመዘኛ ለፖለቲካ መብቶችና የሲቪል ማኅበራት ነፃነት የበለጠ ትኩረት ይሰጣል፡፡ ይሁን እንጂ ነፃነት የዴሞክራሲ ሥርዓት አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ቢሆንም በራሱ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ በመሆኑም ለተግባር የሚያግዝ የዴሞክራሲ መመዘኛ የፖለቲካ ተሳትፎና የመንግሥት ተግባር አፈጻጸም ጉዳዮችን በሚፈለገው ደረጃ ማካተት ይሻል፡፡

ዘ ኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒት (The Economist Intelligence Unit) በሚል ስያሜ የሚታወቀው ድርጅት የሚያጠናቅረው የአገሮች ዓመታዊ የዴሞክራሲ ቀመር አምስት ዓብይ ዘርፎች የሚያካትት ሲሆን እነዚህም፣

1) ነፃና ፍትሐዊ የምርጫ ውድድርና የፖለቲካ ብዙኃነት

2) የሲቪል ማኅበራት ነፃነት

3) የመንግሥት ተግባር አፈጻጸም

4) የፖለቲካ ተሳትፎና

5) የዴሞክራሲ ፖለቲካ ባህል ናቸው፡፡ እነዚህ አምስት ዓብይ ዘርፎች እርስ በርሳቸው የተዛመዱ ከመሆኑ በተጨማሪ የተሟላ የዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብን ይገልጻሉ፡፡

ከእዚህ አንፃር ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ ይኼን የሚያስችል የፖለቲካ ነፃነት መኖር አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ የዴሞክራሲ መሠረታዊ መገለጫ ባህርይ ነው፡፡ የሲቪል ማኅበራት በነፃነት መንቀሳቀስ ለሊበራል የዴሞክራሲ ሥርዓት አስፈላጊ ነው፡፡ እንዲሁም የሰብዓዊ መብቶች መከበር በአብዛኞች አገሮች ሕገ መንግሥት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በዓለም አቀፍ ስምምነቶች ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘ ነው፡፡

በመንግሥታት ዕውቅና ከተሰጣቸው መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች መሀል  ሐሳብን በንግግርና በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት በነፃነት መግለጽ፣ የእምነት ነፃነት፣ የመሰብሰብና በማኅበር የመደራጀት ነፃነትና ፍትሐዊ ዳኝነት የማግኘት መብት ዋና ዋናዎች ናቸው፡፡ ከእዚህም ሌላ የዴሞክራሲ ሥርዓት የፖለቲካ ውሳኔዎች ዜጎች በነፃነት በሚሳተፉበት ምርጫ አማካይነት በብዙኃን ድምፅ የሚፀድቅ ሲሆን፣ በአንፃሩ ለግለሰብ ሰብዓዊ መብቶችና ለኅዳጣን መብቶች መከበር ዋስትና ይሰጣል፡፡

አብዛኛው የዴሞክራሲ መመዘኛ በዝቅተኛ ደረጃ አስፈላጊ የሆኑ የመንግሥት ተግባራትን በጥራት መከወንን ያካትታል፡፡ ይኼም በዴሞክራሲ አግባብ የሚተላለፉ ውሳኔዎች በፍፁም ሊተገበሩ የማይችሉ፣ ወይም የማይተገበሩ ከሆነ ዴሞክራሲ ምንም ፋይዳ አይኖረውም ከሚል አስተሳሰብ የሚመነጭ ነው፡፡

በአጠቃላይ የዴሞክራሲ ሥርዓት ከተቋማት አሠራር ድምር ውጤት በላይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የዴሞክራሲ የፖለቲካ ባህል ወሳኝና እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህም የመንግሥት አመራር በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው፣ እንዲሁም የተረጋጋና ዘላቂ የዴሞክራሲ ሒደት እንዲጎለብት ያስችላል፡፡ ከእዚህ አንፃር የዜጎች ዳተኛ ወይም ዳር ተመልካች መሆን፣ ለፖለቲካ ጉዳዮች ፍላጎት ያለ ማሳየትና ተሳትፎ ያለማድረግ፣ ፍፁም ታዛዥ መሆንና ቁጥጥር ሥር መውደቅ ለዴሞክራሲ ሥርዓት የሚመጥን ባህርይ አይደለም፡፡ በዴሞክራሲ አግባብ የሚካሄድ ምርጫ በየጊዜው ሕዝብን በአሸናፊና ተሸናፊ ምድብ የሚከፍል ነው፡፡ ስኬታማ የዴሞክራሲ የፖለቲካ ባህል በሰፈነበት ሁኔታ በምርጫ የተሸነፉ ፓርቲዎችና ደጋፊዎቻቸው፣ የብዙኃኑን ድምፅና ውሳኔ በማክበር የተረጋጋ የሥልጣን ሽግግር እንዲኖር ያስችላሉ፡፡

በዴሞክራሲ ሥርዓት የሕዝብ ተሳትፎ አስፈላጊ በመሆኑ የዜጎች ለፖለቲካ ጉዳዮች ፍላጎት ያለ ማሳየትና በምርጫ ውድድር ድምፅ ያለመስጠት ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ በውክልና ላይ የተመሠረተ የሊበራል ዴሞክራሲ መመዘኛ ይበልጥ ውስንነት ያላቸው የሕዝብ ተሳትፎ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓት የፖለቲካ ፖርቲዎችንና የሲቪል ማኅበራትን ጨምሮ፣ ብዙና የተለያዩ ተቋማትን የሚያካትት ሲሆን ከእነዚህም መሀል መንግሥት አንድ አካል ነው፡፡

ይሁንና ዜጎች ለልዩ ልዩ ፍላጎቶቻቸው ምላሽ ባለማግኘታቸው ምክንያት ያደረባቸውን ቅሬታ ለማንፀባረቅ መብት ያላቸው በመሆኑ፣ በፖለቲካ ጉዳዮች እንዲሳተፉ ግዴታ የለባቸውም፡፡ ሆኖም ጤናማ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲጎለብት ዜጎች በራሳቸው ነፃ ፈቃድ በምርጫ ድምፅ በመስጠት እንዲሳተፉ፣ እንዲሁም ለመንግሥት ሥልጣን እንዲወዳደሩ ያስፈልጋል፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓት በዕውን ሊበለፅግ የሚችለው ዜጎች በራሳቸው ፈቃድ በሕዝብ ውይይትና ክርክር መድረክ በመሳተፍ፣ ተወካዮቻቸውን በመምረጥ፣ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ አባል በመሆን ንቁ ተሳትፎ ሲያደርጉ ብቻ ነው፡፡ ከእዚህ ተቃራኒ የዜጎችን ሰፊና ዘላቂ ተሳትፎ ማረጋገጥ ካልተቻለ፣ ዴሞክራሲ ሊቀጭጭና የጥቂት የተመረጡ ቡድኖች እንቅስቃሴ ብቻ እንዲሆን ይወሰናል፡፡

ዘ ኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒት የሚያጠናቅረው የአገሮች የዴሞክራሲ ቀመር በአምስት ዓብይ ዘርፎች የሚከፈልና በእነዚህ ሥር በሚገኙ 60 መመዘኛዎች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በዚህ ረገድ፣

1) ነፃና ፍትሐዊ የምርጫ ሒደትና የፖለቲካ ብዝኃነት 12

2) የሲቪል ማኅበራት ነፃነት 17

3) የመንግሥት ተግባር አፈጻጸም 14

4) የፖለቲካ ተሳትፎ 9

5) የዴሞክራሲ ፖለቲካ ባህል 8 መመዘኛዎች ይዘዋል፡፡

የአገሮች አጠቃላይ የዴሞክራሲ ቀመር በአምስቱ ዓብይ ዘርፎች በሚካተቱ 60 መለኪያዎች ያለውን አፈጻጸም ከዜሮ እስከ አሥር በሆነ ሚዛን በማስላት በሚጠናቀር አማካይ ውጤት የሚገለጽ ሲሆን፣ በእዚህ መሠረት የእያንዳንዱን አገር አሠላለፍ ከ167 አገሮች በንፅፅር ያቀርባል፡፡ ከእዚህም ሌላ በውጤታቸው መሠረት አገሮችን በአራት አጠቃላይ የዴሞክራሲ ሥርዓት ባህርያት የሚከፍል ሲሆን፣ ውጤታቸው ከስምንት በላይ ምሉዕ ዴሞክራሲ፣ ከስድስት እስከ ስምንት የተጓደለ ዴሞክራሲ፣ ከአራት እስከ ስድስት የተዳቀለ አገዛዝና ከአራት በታች አፋኝ የአገዛዝ ሥርዓት በማለት ይመድባል፡፡ የእነዚህ ምድቦችን መገለጫ ባህርይ የሚከተለው ዝርዝር ያብራራል፡፡

ምሉዕ የዴሞክራሲ ሥርዓት

መሠረታዊ የፖለቲካና የሲቪል ማኅበራት ነፃነት መረጋገጥ፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት የሚያግዝ የዳበረ የፖለቲካ ባህል መኖር፣ የመንግሥት ተግባር አፈጻጸም አጥጋቢ ደረጃ መድረስ፣ የመገናኛ ብዙኃን በነፃነት መንቀሳቀስና የሐሳብ ብዝኃነትን ማንፀባረቅ፣ ብቃት ያለው ሚዛናዊ የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት፣ የፍትሕ ገለልተኛ መሆንና የፍርድ ውሳኔዎች መተግበር፣ እንዲሁም በአጠቃላይ ለዴሞክራሲ አሠራር ጥቂት ችግሮች ብቻ ያሉባቸው አገሮችን ያካትታል፡፡

የተጓደለ የዴሞክራሲ ሥርዓት

 የነፃና ፍትሐዊ ምርጫ መካሄድ፣ በመገናኛ ብዙኃን ነፃ እንቅስቃሴ ጥሰትና ተፅዕኖ መኖር፣ መሠረታዊ የሲቪል ማኅበራት ነፃነት መከበር፣ ነገር ግን መልካም አስተዳደርን በመሳሰሉ ሌሎች የዴሞክራሲ ጉዳዮች ድክመት በጉልህ መታየት፣ የፖለቲካ ባህል ያለመዳበር፣ እንዲሁም ዝቅተኛ የፖለቲካ ተሳትፎ የሚታይባቸው አገሮችን ያመለክታል፡፡

የተዳቀለ የአገዛዝ ሥርዓት  

በመጠነ ሰፊ ጉድለቶች ምክንያት የምርጫዎች ሒደት ነፃና ፍትሐዊ ያለመሆን፣ በፓርቲዎችና በዕጩ ተወዳዳሪዎች ላይ የተለመደ የመንግሥት ተፅዕኖ መኖር፣ ከተጓደለ የዴሞክራሲ ሥርዓት ጋር በንፅፅር ሲታይ በፖለቲካ ባህል በመንግሥት ተግባር አፈጻጸምና በፖለቲካ ተሳትፎ ያለ ድክመት በሚብስ ሁኔታ መታየት፣ የሙስና አሠራር በስፋት መዛመት፣ የሕግ የበላይነት ደካማ ደረጃ መገኘት፣ የሲቪል ማኅበራት እንቅስቃሴ ዝቅተኛ መሆን፣ በጋዜጠኞች ላይ ወከባና ተፅዕኖ በብዛት መታየትና የፍትሕ አካላት ገለልተኛ ያለመሆን የሚታይባቸው አገሮችን ያጠቃልላል፡፡

አፋኝ የአገዛዝ ሥርዓት

የፖለቲካ ብዝኃነት ፍፁም ያለመኖር ወይም በከፍተኛ ደረጃ መገደብ፣ አብዛኞቹ በግልጽ እንደ አምባገነን አገዛዝ የሚፈረጁ መሆን፣ አንዳንድ መደበኛ የዴሞክራሲ ተቋማት በዕውን ቢኖሩም እንኳ በተግባር የሚያሳድሩት ተፅዕኖ አነስተኛ መሆን፣ ምርጫዎች የሚካሄዱ ቢሆንም ሒደታቸው ነፃና ፍትሐዊ ያለመሆን፣ የሲቪል ማኅበራት የነፃነት ጥሰትና አላስፈላጊ ገደብ መኖር፣ መገናኛ ብዙኃን በመንግሥት ሥር መሆንና ለገዥው ሥርዓት መወገን፣ በመንግሥት ላይ የሚሰነዘር ትችትን በጥብቅ ቅድመ ምርመራ አሠራር ማፈንና የፍትሕ አካል ገለልተኛ ያለመሆን የሰፈነባቸው አገሮችን ያመለክታል፡፡

በዚህ ዓይነት እ.ኤ.አ. በ2017 ድርጅቱ ባቀረበው የአገሮች የዴሞክራሲ አፈጻጸም ዘገባ ከ167 አገሮች መሀል 19 አገሮች ምሉዕ ዴሞክራሲ፣ 57 አገሮች የተጓደለ ዴሞክራሲ፣ 39 አገሮች የተዳቀለ አገዛዝና 52 አገሮች አፋኝ የአገዛዝ ሥርዓት እንደሚከተሉ ይገልጻል፡፡ በተመሳሳይ 44 ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገሮች መሀል አንድ አገር (ሞሪሸስ) ምሉዕ ዴሞክራሲ፣ ሰባት አገሮች የተጓደለ ዴሞክራሲ፣ 14 አገሮች የተዳቀለ አገዛዝ፣ እና 22 አገሮች (ኢትዮጵያን ጨምሮ) አፋኝ የአገዛዝ ሥርዓት በሚል እንደሚመደቡ ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ቁመና

ዘ ኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒት እ.ኤ.አ. በ2017 ባዘጋጀው የዓለም አገሮች የዴሞክራሲ አፈጻጸም ዘገባ የኢትዮጵያ ውጤት 3.42 ሲሆን፣ ይህም አገሪቱን በአፋኝ የአገዛዝ ሥርዓት ያስፈርጃታል፡፡ ይህ ውጤት አገራችን ቀደም ባሉት ዓመታት ካሳየችው አፈጻጸም፣ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገሮች አማካይ (4.35) እንዲሁም ከዓለም አገሮች አማካይ (5.48) ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ሆኖ ይታያል፡፡ በእዚህም ኢትዮጵያ ከ167 የዓለም አገሮች 129ኛ፣ እንዲሁም ከሰሃራ በታች ከሚገኙ 44 አገሮች 30ኛ  ተርታ እንድትሠለፍ አድርጓታል፡፡

ሠንጠረዥ አንድ እንደሚያሳየው ከሰሃራ በታች ከሚገኙ 44 የአፍሪካ አገሮች መሀል ሞሪሸስ ከአኅጉሪቱ አንደኛ ከዓለም 16ኛ፣ ኬፕ ቬርዴ ከአኅጉሪቱ ሁለተኛ ከዓለም 23ኛ፣ ቦትስዋና ከአኅጉሪቱ ሦስተኛ ከዓለም 28ኛ፣ ደቡብ አፍሪካ ከአኅጉሪቱ አራተኛ ከዓለም 41ኛ፣ እንዲሁም ጋና ከአኅጉሪቱ አምስተኛ ከዓለም 52ኛ ደረጃ ይዘዋል፡፡

በሌላ በኩል ከሃያ ሁለት ዓመት የያህያ ጃሜህ አፋኝና አምባገነን አገዛዝ በኋላ በተካሄደ ብሔራዊ ምርጫ ጋምቢያ እ.ኤ.አ. በ2016 ከአኅጉሪቱ 36ኛ ከዓለም 143ኛ የነበራትን ደረጃ ከሁሉም አገሮች የላቀ መሻሻል በማሳየት፣ እ.ኤ.አ. በ2017 ከአኅጉሪቱ 21ኛ ከዓለም 113 ደረጃ በመያዝ የዓመቱ ኮከብ በሚል ተሰይማለች፡፡

ሠንጠረዥ 1 የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ አፈጻጸም አማካይና በአምስት ዓብይ ዘርፎች (እ.ኤ.አ. 2017)

 

አገሮች

 

ደረጃ

 

የዴሞክራሲ አፈጻጸም – አማካይና በዘርፍ  (ከ 0 – 10)

ከሰሃራ በታች የአፍሪካ

አገሮች (44)

 

ከዓለም አገሮች

 

(167)

 

አማካይ ቀመር

 

የምርጫ ሒደትና የፖለቲካ ብዝኃነት

 

የመንግሥት ተግባር አፈጻጸም

 

የፖለቲካ ተሳትፎ

የዴሞክራሲ ፖለቲካ ባህል

የሲቪል ማኅበራት ነፃነት

ሞሪሸስ

1

16

8.21

9.17

8.21

5.56

8.75

9.41

ኬፕ ቬርዴ

2

23

7.88

9.17

7.86

6.67

6.88

8.82

ቦትስዋና

3

28

7.81

9.17

7.14

6.11

7.50

9.12

ደቡብ አፍሪካ

4

41

7.24

7.42

7.50

8.33

5.00

7.94

ጋና

5

52

6.69

8.33

7.50

6.67

6.25

6.47

ጋምቢያ

21

113

4.06

4.48

3.93

3.33

5.63

2.94

ኢትዮጵያ

30

129

3.42

0.00

3.57

5.56

5.63

2.35

Source: The Economist Intelligence Unit (EIU), 2017 – Democracy Index: Free Speech Under Attack

ይህ ሠንጠረዥ ከአገሮቹ አማካይ የዴሞክራሲ አፈጻጸም በተጨማሪ በአምስት ዓብይ ዘርፎች ያላቸውን ዝርዝር አፈጻጸም ያሳያል፡፡ ከእዚህ አንፃር የኢትዮጵያ አማካይ አፈጻጸም ከአኅጉሪቱ አማካይ ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ከመሆኑም በላይ፣ በምርጫ ሒደትና የፖለቲካ ብዝኃነት እንዲሁም በሲቪል ማኅበራት ነፃነት ዘርፎች የአገሪቱ አፈጻጸም እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ከእዚህም ሌላ በመንግሥት ተግባር አፈጻጸም፣ የፖለቲካ ተሳትፎ፣ እንዲሁም በዴሞክራሲ የፖለቲካ ባህል ዘርፎች ኢትዮጵያ ያላትን አፈጻጸም በዕውን ለማሻሻል የተጠናከረ ዕርምጃ መውሰድ ያስፈልጋታል፡፡ እዚህ ላይ ቀደም ሲል የተጠቀሰው የጋምቢያ አፈጻጸም በከፍተኛ መጠን መሻሻል በአምስቱም ዓብይ ዘርፎች በተወሰዱ ዕርምጃዎች መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ሠንጠረዥ 2 የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ አፈጻጸም አማካይ (እ.ኤ.አ. 2006 – 2017)

አገሮች

2006

2008

2010

2011

2012

2013

2014

2015

2016

2017

አማካይ

ኢትዮጵያ

4.72

4.52

3.68

3.79

3.72

3.83

3.72

3.83

3.60

3.42

3.88

ጋምቢያ

4.39

4.19

3.38

3.38

3.31

3.31

3.05

2.97

2.91

4.06

3.50

ከሰሃራ በታች አፍሪካ አማካይ

4.24

4.28

4.23

4.32

4.32

4.36

4.34

4.38

4.37

4.35

4.32

የዓለም አማካይ

5.55

5.52

5.46

5.49

5.52

5.53

5.55

5.55

5.52

5.48

5.52

Source: The Economist Intelligence Unit (EIU), 2017 – Democracy Index: Free Speech Under Attack

በሠንጠረዥ 2 የተመለከተው እ.ኤ.አ. ከ2006 እስከ 2017 የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ አፈጻጸም ሲታይ የአገሪቱ አማካይ ውጤት (3.88) ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገሮች አማካይ (4.32) እንዲሁም ከዓለም አገሮች አማካይ (5.52) ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ነው፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በንፅፅር የተሻለና ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገሮች አማካይ የላቀ አፈጻጸም ያሳየችው እ.ኤ.አ. በ2006 እና በ2008 ሲሆን፣ ቀጥሎ ባሉት ተከታታይ ዓመታት የአገሪቱ ውጤት አሽቆልቁሏል፡፡ ይህም ከ1997 ዓ.ም. ብሔራዊ ምርጫ በኋላ መንግሥት በወሰዳቸው ዕርምጃዎች የፖለቲካ ምኅዳሩ እየጠበበ በመምጣቱ ምክንያት እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡

በኢትዮጵያ የለውጥ አመራሩ ሥልጣን ከተቆጣጠረ አንስቶ ከወሰዳቸው ዕርምጃዎች መካከል የፖለቲካ መሪዎችንና ጋዜጠኞችን ከእስር መፍታት፣ የመገናኛ ብዙኃንን በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ መፍቀድ፣ የታገዱ ድረ ገጾች የአገር ውስጥ ሥርጭትን መፍቀድ፣ የዴሞክራሲ ምኅዳርን ለማስፋት የፀረ ሽብር፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና የሲቪል ማኅበራት ሕግጋት ማሻሻያ ጥናት መጀመር፣ በአሜሪካ ከሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን (ዳያስፖራ) ጋር በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማካሄድ፣ በአሸባሪነት የተፈረጁና የትጥቅ ትግል የሚያካሂዱትን ጨምሮ በውጭ አገሮች የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የፖለቲካ አክቲቪስቶች፣ በአገር ውስጥ ሰላማዊ ትግል እንዲሳተፉ ስምምነት ላይ መድረስ ዋና ዋናዎች ናቸው፡፡

እነዚህ ዕርምጃዎች በሚቀጥሉት ዓመታት የአገራችን የዴሞክራሲ አፈጻጸም በማሻሻል ረገድ ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ ይጠበቃል፡፡ ሆኖም በአገራችን ካለው ዝቅተኛ የዴሞክራሲ አፈጻጸም አንፃር ጉልህ መሻሻል በማሳየት ስኬት ላይ ለመድረስ በትምህርትና ሥልጠና መስክ እየተፈጸመ እንደሚገኘው ሁሉ፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ፍኖተ ካርታ በመንደፍ እንቅስቃሴዎችን መምራት አስፈላጊ መሆኑን ጽሑፍ ይጠቁማል፡፡

ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት እንዲሁም በመከናወን ላይ የሚገኙ የሕግ ማሻሻያዎችን ከግንዛቤ በማስገባት፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንቅስቃሴ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ማጤን ያስፈልጋል፡፡ ከእነዚህ መሀል ለመጥቀስ ያህል፣

 • ከመካከለኛ እስከ ረዥም ጊዜ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለመገንባት ከሚያስችል አጠቃላይ ፍኖተ ካርታ ይልቅ የማሻሻያ ዕርምጃዎች ሁለንተናዊ ትኩረት በመጪው ዓመት ሊካሄድ በታቀደው ብሔራዊ ምርጫ ላይ ማነጣጠር፣
 • ከምሉዕ ይልቅ ከቁንፅል የዴሞክራሲ ግንዛቤና በወቅቱ የሚታዩ ችግሮች ላይ በማተኮር ፈጣን ውጤት የሚያስገኝ ውስን የሕግ ማሻሻያ ላይ ማጠንጠን፣
 • በጥድፊያ ተግባራትን ለመከወን በሚኖር ፍላጎት በመገፋፋት በዴሞክራሲ አፈጻጸም የተሻለ ውጤት ካስመዘገቡ አገሮች ልምድና ተሞክሮ ለመቅሰም ያለመደፋፈር፣
 • ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ከባቢያዊ ግጭቶችና በእነዚህም የብዙ ዜጎች ከመኖሪያቸው መፈናቀል ምክንያት የተረጋጋ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለማስፈን አዳጋች መሆን፣
 • በአሁኑ ጊዜ በአገራችን የፍትሕና ቁልፍ የዴሞክራሲ ተቋማት ሁለንተናዊ ቁመና አሳሳቢ መሆንና አብዛኛው ሕዝብ በእነዚህ ተቋማት ላይ ያለው መተማመን ዝቅተኛ መሆን፣
 • የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ፣ የዕቅድ ትግበራን በማሳካት፣ የአገልግሎት አቅርቦትን በማሻሻልና፣ የፕሮጀክቶች አፈጻጸምን በማሳለጥ ያለው የመንግሥት የመከወን አቅም ዝቅተኛ መሆን፣
 • በአሁኑ ወቅት በአገር አቀፍ ምርጫ ለመሳተፍ 22 የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም በክልላዊ ምርጫ ለመሳተፍ 40 ፓርቲዎች የተመዘገቡ ሲሆን፣ የእነዚህ በመርሆዎችና ፖሊሲዎች መሠረት ውህደት በመፈጸም የተጠናከረ የፖሊሲ አማራጭ በማዘጋጀት ገዢውን ፓርቲ ከመገዳደር ይልቅ በተናጠል መንቀሳቀስ፣
 • ከአገሪቱ ሕዝብ 80 ከመቶ ያህል የሚገመተው በገጠር የሚኖር አርሶና አርብቶ አደር እንደመሆኑ መጻፍና ማንበብ የሚችለው ሕዝብ ዝቅተኛ ድርሻ ያለው በመሆኑ ምክንያት በዴሞክራሲ ሒደት የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ፣
 • በማኅበረሰብ ውስጥ በዴሞክራሲ ላይ ያለው የግንዛቤ ጉድለትና በፖለቲካ ጉዳዮች የሕዝብ ተሳትፎ ዝቅተኛ ደረጃ መሆን፣
 • በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ፍኖተ ካርታ ዝግጅት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማኅበራትና የኅብረተሰብ ተሳትፎ እንዲኖር የሚያግዝ የውይይት መድረክ በየጊዜው ማዘጋጀት ያለመቻልና
 • የኤሌክትሮኒክና የኅትመት መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ሽፋን ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መገኘትና በይዘት የሐሳብ ብዙኃነትን በማንፀባረቅ ማነቃቃት ያለመቻል ዋና ዋናዎች ናቸው፡፡

የዴሞክራሲ ግንባታ ፍኖተ ካርታ የትኩረት ጉዳዮች

በአገራችን የተረጋጋና ዘላቂ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለማስፈን አስፈላጊውን ሒደት መከተልና የረዥም ጊዜ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በመስኩ ተጨባጭ ስኬት ለማስመዝገብ የተቀናጀ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ፍኖተ ካርታ መንደፍና በአግባቡ መተግበር ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ጽሑፉ አበክሮ ያስገነዝባል፡፡

በአገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ፍኖተ ካርታ ዝግጅት የሚከተሉት ጉዳዮችን እንዲያካትት ያስፈልጋል፡፡ እነዚህም፣

 • በግልፅ ተለይተው የታወቁ ዓላማዎች፣ ግቦችና የሚጠበቁ ውጤቶች ላይ በመወያየት መግባባት መድረስ፣
 • ከቁንፅል ይልቅ የተሟላ የዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብ ግንዛቤ በመያዝ በአምስት ዓብይ ዘርፎች ሥር በተካተቱ ሥልሳ የአፈጻጸም መለኪያዎች የማሻሻያ ዕርምጃዎችን ደረጃ በደረጃ በአጭር፣ መካከለኛና ረዥም ጊዜ ተግባራዊ ለማድረግ ዕቅድ ማዘጋጀት፣
 • የማሻሻያ ዕርምጃዎች በዝርዝር ተለይተው የታወቁ፣ እርስ በእርሳቸው የተዛመዱ (ያልተነጣጠሉ)፣ የትግበራ ቅደም ተከተል የተነደፈላቸው መሆን፣
 • በዴሞክራሲ አፈጻጸም የላቀ ውጤት ካስመዘገቡ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ልምድና ተሞክሮ መቀመር ጠቃሚ መሆኑ፣
 • ለዴሞክራሲ አሠራር አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ የሚችሉ በአገራችን ልዩ ልዩ አካባቢዎች የሚንፀባረቁ ጠቃሚ ማኅበራዊ እሴቶች፣ ባህልና ልምድ በመፈተሽ ለእነዚህ አመቺ ሁኔታ መፍጠር፣
 • በሚዘጋጀው ፍኖተ ካርታ አጠቃላይ ይዘት፣ በዝርዝር ተግባራትና የአፈጻጸም መርሐ ግብር ከመንግሥት ውጪ ከሆኑ አካላት (የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የአካዳሚ ተቋማትና የሲቪል ማኅበራት) ጋር በመወያየት መግባባት መድረስ፣
 • በተመሳሳይ በሚዘጋጀው ፍኖተ ካርታ አጠቃላይ ይዘት፣ በዝርዝር ተግባራትና የአፈጻጸም መርሐ ግብር ላይ በመገናኛ ብዙኃን ተከታታይ የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ስለዴሞክራሲ ሥርዓት ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲዳብር፣ እንዲሁም የሕዝብ ተሳትፎና የፖለቲካ ባህል እንዲጎለብት ቅስቀሳ ማካሄድ፣
 • በተለምዶ የታወቁና ቁልፍ የዴሞክራሲ ተቋማትን (የምርጫ ቦርድ፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የእንባ ጠባቂ ተቋም፣ የፀረ ሙስናና ሥነ ምግባር ኮሚሽን፣ ወዘተ) በሕግ፣ በአደረጃጀት፣ በጽሕፈት ቤት፣ በአሠራር ሒደት፣ በአመራርና በሰው ኃይል፣ እንዲሁም በፋይናንስና በመገልገያ መሳሪያዎች ማጠናከር፣
 • በዴሞክራሲ ተቋማት በአመራር የሚመደቡ ኃላፊዎች አስፈላጊው የሙያ ብቃት፣ የአመራር ክህሎትና የግል ባህርይና ሰብዕና ያላቸው፣ እንዲሁም ከፖለቲካ ፓርቲ ገለልተኛ እንዲሆኑና ተጠያቂነት እንዲኖርባቸው ማረጋገጥና
 • የፍኖተ ካርታ ትግበራ መርሐ ግብር፣ የስኬት መለኪያዎች፣ ግልጽ የአፈጻጸም ክትትልና የግብረ መልስ ሥርዓት መካተት አስፈላጊ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአገራችን የፖለቲካ ምኅዳርን አመቺ ለማድረግ የለውጥ አመራሩ በሕግ ማሻሻያ እንቅስቃሴዎች መጠመዱ ይታወቃል፡፡ ሆኖም የአገራችን የዴሞክራሲ አፈጻጸም ሥር በሰደዱ ውስብስብ ችግሮች ምክንያት አሳሳቢና ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ፣ በመስኩ ጉልህ መሻሻል እንዲኖር የተነጣጠሉ ውስን የሕግ ማሻሻያ ዕርምጃዎች ላይ ከማትኮር ይልቅ ከተሟላ የዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብ ግንዛቤ በመነሳት፣ ሁለንተናዊ የማሻሻያ ዕርምጃዎችን በተቀናጀ መንገድ ለማቀድና ለመከወን የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ይህ ጽሑፍ አበክሮ ያስገነዝባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...