በገነት ዓለሙ
ማክሰኞ ጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የኢፌዴሪ አስፈጻሚው አካል ሥልጣንና ተግባር እንደገና ለመወሰን ተዘጋጅቶ የቀረበውን ረቂቅ ሕግ (አዋጅ) እና በዚህም መሠረት የአዲሱን የካቢኔያቸውን ዕጩዎች ሹመት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበበት የፓርላማ ውሎ፣ አዳዲስ የመነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳዮችን ይዞ መጥቷል፡፡ የሰላም ሚኒስቴር የሚባል አዲስ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መቋቋሙ፣ የኢትዮጵያ ከፍተኛው የአስፈጻሚነትና የአስተዳደሪነት የመንግሥት ሥልጣን ከሃያ ወንበሮቹ መካከል ግማሹን (አሥሩን) በሴት ሚኒስትሮች ማዋቀሩ፣ ከእነዚህም መካከል አሁንም ለመጀመርያ ጊዜ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሚኒስትር፣ የኢትዮጵያ የሰላም ሚኒስትር (የደኅንነት፣ የፖሊስ፣ የወህኒ ቤቶች፣ የኢሚግሬሽን፣ የስደተኞች የመረጃና የኢንተለጀንስ ነገር ሁሉ ያለበት)፣ የትራንስፖርት ሚኒስትር ሴቶች ሆነው የተሾመበት መሆኑ ዋና ዋናዎቹና አንዳንዶቹ ናቸው፡፡ እነዚህን ሁሉ በየልክና መልካቸው፣ እንዲሁም እንዳመጣጣቸው ማነጋገራቸውና ከንግግር በላይ አለመሆናቸው አዲስ ነገር መሆን የለበትም፡፡ ወይም ለምን አዲስ ነገር ሆኖ ንግግር ፈጠረ? መነጋገሪያ ሆነ መባል ያለበት አይመስለኝም፡፡ ለውጥ ማለት ለለውጥ መታገል ማለት እንዲህ ዓይነት በለወጡ ውስጥ አሠላለፍን የሚያበላሹ፣ ኋላቀር ዕይታዎች ደግሞ ሌላ ጊዜ በአረም የማይመለሱ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ከማለባበስ ይልቅ፣ ፍርጥ አድርጎ መነጋገርን የጥበብ መጀመርያ አድርጎ እሱኑ ታጥቆ መረማመድን ይጨምራልና፡፡
በእኔ በኩል ግን ቅድሚያ የሚሰጠው በዕለቱ የተመሰከረ ሌላ መነጋገሪያ ያለ ይመስለኛል፡፡ በዚህ ረገድ ከብዙዎቹ የዕለቱ አነጋጋሪ ጉዳዮች መካከል ከሚከነክኑኝና ከሚያሳስቡኝን ነገሮች መካክል በዕለቱ በቀረበውና በፀደቀው ሕግ ውስጥ፣ በአንቀጽ 34 ለአስፈጻሚው አካል ደግሞ እንደገና የተሰጠው ሥልጣን ነው፡፡ ለአስፈጻሚው አካል ወይም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አሁንም በዚህ የለውጥ ዘመን የተመረቀለት፣ ያፀኑት ሥልጣን ‹‹. . . አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ደንብ በማውጣት፣ ነባር አስፈጻሚ አካል እንዲታጠፍ፣ ከሌላ አስፈጻሚ አካል ጋር እንዲዋሀድ፣ እንዲከፋፈል ወይም ተጠሪነቱ እንዲለወጥ በማድረግ ወይም አዲስ አስፈጻሚ አካል እንዲቋቋም በማድረግ የፌዴራል አስፈጻሚ አካላትን እንደገና የማደራጀት ሥልጣን›› ሰጥቶታል፡፡
አሁን እዚሁ ጽሑፍ ውስጥ ደጋግሜ እንደገለጽኩት፣ ‹‹የፌዴራል አስፈጻሚ አካላትን እንደገና የማደራጀት ሥልጣን›› በአዋጅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት/ለመስተዳድሩ የተሰጠው ገና ዛሬ በዚህ የዶ/ር ዓብይ ዘመን አዋጅ አይደለም፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ እንዲህ ያለ ሥልጣን ለራሱ ለአስፈጻሚው አካል በአዋጅ የተሰጠው ከአሥር ዓመት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ዘመን ከጥቅምት 14 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ በፀና በአዋጅ ቁጥር 603/2001 ነው፡፡
የሚገርመው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህንን ‹‹ . . .የፌዴራል አስፈጻሚ አካላትን እንደገና የማደራጀት ሥልጣን . . . ›› ያገኘው፣ እንደተለመደው የአስፈጻሚ አካላትን በመላ አካቶና አጠቃልሎ እንደገና ለማደራጀት በወጣ ሕግ ሳይሆን፣ ድንገት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽንን፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባደረገው አዋጅ ውስጥ እግረ መንገዱን ድንገት ባደረገው ማሻሻያ ነው፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አንቀጽ 34 እንጂ ምን ችግር አለው? የሚል ጥያቄ መነሳቱ እውነት ነው፡፡ ያን ጊዜም የሚሰማ ጆሮ ስለጠፋ እንደተነሳ ጥያቄ ነው፡፡ ችግር አለው፡፡ ችግሩም ሕገ መንግሥታዊ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ዕውን ዴሞክራሲያዊ ነው? ዕውን ሪፐብሊካዊ ነው? የሚለው ትልቁ ጥያቄ አካል ነው፡፡ ሕዝብ ራሱን በራሱ እያስተዳደረ መሆኑን፣ መንግሥታዊ ሥልጣን ከሕዝብ ሿሚነትና ጠያቂነት ሥር መውደቁን፣ ሕዝብ በተወካዮቹ፣ ተወካዩቹ በአስፈጻሚው ላይ በሕግ መሠረት ‹‹አድራጊ ፈጣሪ›› መሆናቸው፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ አንድ የተደነገገው የኢትዮጵያ መንግሥት ስያሜ በተግባር መዋል ይችላል? ወይስ የውሸትና የለበጣ መለኪያችን ነው? በተለይም በዚህ የለውጥ ጊዜ ውስጥ ሕዝብ ተወካዮችን፣ የሕዝብ ተወካዮች ደግሞ አስፈጻሚውን ይቆጣጠሩታል? ይገሩታል? የሚለው ጥያቄ ዋነኛው የለውጡ መፈክር ነው፡፡ ይህን የምንለው አምስተኛው ፓርላማ ራሱና ተወካዮች በቃላቱ ትክክለኛ ትርጉምና አግባብ፣ እንዲሁም ይህንን አረጋግጣለሁ ብሎ በተደነገገው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 8 ውሳኔ መሠረት 547 መቀመጫዎች ይዘው የተቀመጡት እንደራሴዎቻችን፣ የሕዝብ ፍላጎትና ፈቃድ ከምርጫ ጋር በማይግባባበት አሠራር የተሰባሰቡ መሆናቸውን እያወቅን ነው፡፡ በዚያው ማዕቀፍና ጉድጓድ ውስጥ ግን ተወካዮቻችንና ባለሥልጣኖቻችን በሕግ መሠረት፣ ከራሳቸው ቁጥጥር ውጪ ባልሆነ ሕግ መሠረት መረማመድ ሲያቅታቸው እናያለን፡፡
ለውጡ ከሁሉም በላይ የመጣው ይህንን ያርማል ተብሎ ነው፡፡ ይህንን ለማረምና ለማረቅ ነው፡፡ ከረዥም ጊዜ አንስቶ በተለይም ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በነበሩት ሦስት ዓመታት የትግሉ ዒላማ በጭራሽ ገዥው ቡድን አይደለም ሲባል የቆየው ለአንደበት ወግ ያህል አልነበረም፡፡ ያለ ምክንያትም አይደለም፡፡ ከገዥው ቡድን ውስጥ ተፈልቅቆ የወጣው የዓብይ አህመድ የለውጥ ኃይል እንዳሳየውም ዛሬም በዚሁ ሕገ መንግሥት ሰፊ ማዕቀፍ ውስጥ ለውጥ ማምጣት የማይቻል ነገር አይደለም፡፡ ስለዚህም የትግሉ ዒላማ ገዥው ቡድን ሳይሆን፣ ለብቻዬ ካልገዛሁና የእኔ ሐሳብ አመራሩን ካልያዘ አገር ይጠፋል ማለት ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ እኔ ብቻ ልክ፣ እኔ ብቻ ባለመብት ባይነቱ የተለየ ሐሳብን በሐሳብ ከማሸነፍ ይልቅ በሸር የሚገላገልበት የሕግ አወጣጥና አፈጻጸም መስመር መከተሉ ነው፡፡ ሕግ የማውጣትና ሕግ የማስከበር የመንግሥት ሥራ ተቃውሞ መቆጣጠሪያና ማስተዳደሪያ እስከመሆን ብልሽት ያስከተለውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በተለይም በመንግሥታዊ ሥርዓቱ በአስተሳሰብ፣ በአሠራርና በአደረጃጀት ባህል ላይ የደረሰው ብልሽት በዝምታ እንዲታለፍ መፍቀድ የለውጡን ተጠናዋቾች መጥቀም ነው፡፡
ወደ ተነሳንበት ሕግና ፖለቲካ ዝርዝር ውስጥ እንግባ ከ2001 ዓ.ም. ጥቅምት ወር ጀምሮ ‹‹የፌዴራል አስፈጻሚ አካላትን እንደገና የማደራጀት ሥልጣን››ን በጓሮ በር ነጥቆ የወሰደው አስፈጻሚው አካል፣ ‹‹ይሉኝታ›› የለሽነት የሚጀምረው ይህን ሥልጣን ያገኘው በራሱ ‹‹የኢትዮጵያን ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን›› ሌላ የሥልጣን አካል ባወጣው አዋጅ/ሕግ መሠረት ነው፡፡ ይህም አካል የተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ ከፍተኛ የሥልጣን አካል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ የሕግ አስፈጻሚው አካል የሚባለውና በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 72 መሠረት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ የአስፈጻሚነት ሥልጣን የተሰጠውና ያለው የሥልጣን አካል ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው፡፡ አስፈጻሚው አካል፣ መስተዳድር፣ ካቢኔ፣ ወዘተ የምንለው ይህን የሥልጣን አካል ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 56 መሠረት ይህን የሥልጣን አካል የሚያደራጀው ፓርላማው ነው፡፡ በዚህ መሠረት የፓርላማውና የአስፈጻሚው አካል ግንኙነት የ‹‹ፈጣሪ›› እና የ‹‹ፍጡር›› ዓይነት ነው፡፡ ሕግ የማውጣት፣ አስፈጻሚውን የማቋቋምና የማደራጀት፣ አስፈጻሚውን የመቆጣጠርና አስፈላጊም ሲሆን አስፈጻሚውን እምነት አጣሁብህ ብሎ የመበተን ሥልጣን ያለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ዕውን ዴሞክራሲ ናት? ዕውን ሪፐብሊክ ናት? ብለን ስናመርና ስንጠይቅ ከሌሎች መካከል መንግሥታዊ ሥልጣን በሕዝብ ሿሚነትና ጠያቂነት ውስጥ ነው ወይ? ሕዝብ ተወካዮችን ተወካዮቹ አስፈጻሚውን መቆጣጠር ችለዋል ወይ የምንለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
ተወካዮቻችንን መርጠን የምንልክበት የሥልጣን አካል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ዋናው ሕግ አውጪው አካል ይኼው የተወካዮቻችን ምክር ቤት ነው፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤትም በሕገ መንግሥቱ የተሰጠ ሕግ የማውጣት ሥልጣን አለው፡፡ የዚህ የሥልጣን አካል ሕግ የማውጣት ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 77 ንዑስ ቁጥር 13 መሠረት የተደነገገውን የሚመስል ከታች እንዳያፈስ፣ ከላይ እንዳይተነፍስ ሆኖ የታሰረና የተቋጠረ ነው፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ‹‹የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚሰጠው ሥልጣን መሠረት ደንቦችን ያወጣል››፡፡ ስለዚህም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዝም ብሎ ሕግ አያወጣም፡፡ መጀመርያ ነገር የሚያወጣው የሕግ ዓይነት ‹‹ደንብ›› በመባል የሚታወቀው የሕግ ዓይነትን ብቻ ነው፡፡ አንዳንዴ (በተለይም ባለፉት ሁለት የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታዎች ወቅት እንደታዘብነው) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ‹‹አዋጅ›› የሚባል የሕግ ዓይነት ማውጣት እችላለሁ፣ አወጣሁም ሲል መስማታችን ባይቀርም የመስተዳድሩ ሕግ የማውጣት ሥልጣን ‹‹ደንብ›› በሚባል የሕግ ዓይነት ላይ የተወሰነና የተገደበ ነው፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ የሚባል የሕግ ዓይነት ሲያወጣ ሕገ መንግሥቱን የማክበር ግዴታ አለበት ሲባል አደራው፣ ‹‹ሕገ መንግሥቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር፣ እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም›› በሚለው የሕገ መንግሥቱን የበላይነት በሚደነግገው በአንቀጽ 9 ላይ ብቻ የተተወ አይደለም፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ራሱ ሕግ የማውጣት ሥልጣኑ ያገኘው በውክልና ነው፡፡ ይህንን በውክልና የተገኘ ሥልጣን ከተፈቀደው ውጪ ማዋልም፣ በውክልና አሳልፎ መስጠትም (እንኳን መቸር) አይችልም፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሕግ የማውጣት ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 77(13) ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ የሚባል የሕግ ዓይነት ሲያወጣ ብዙ ጊዜ እንደተለመደውና በተግባርም እንደታየው (በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጡት ያለፉት 27 ዓመታት በነጋሪት ጋዜጣ የታተሙ ደንቦችም እንደሚያሳዩት)፣ ደንብ የማውጣቱ ሥልጣን በአንቀጽ 77(13) ላይ ወይም አንቀጽ 77(13)ን መሠረት ባደረገ የመስተዳድሩ ማቋቋም ሕግ/አዋጅ ላይ ብቻ የተመሠረተ አይደለም፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሕግ ፊት የሚፀና ‹‹ይለፍ›› ይዞ እያሳየና እያውለበለበ በኩራት ሕግ አውጪ መሆን የሚችለው ከአንቀጽ 77(13) በተጨማሪ ሌላ ለጉዳዩ አግባብ ያለው ሁለተኛውን ‹‹ይለፍ›› ማሳየት ሲችል ነው፡፡ የመጀመርያው ቋሚ ወይም የማለዋወጥ ይለፍ በተደጋጋሚ የተጠቀሰው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 77(13) ነው፡፡ ‹‹የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚሰጠው ሥልጣን መሠረት ደንቦችን ያወጣል›› የሚለው፣ ወይም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያወጣውን የአስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር ማቋቋሚያ አዋጅን በምትኩ ወይም በአማራጭ ሊጠቅስ/ዋቢ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ይህ በምትክ ወይም በአማራጭ የሚጠቀሰው የአስፈጻሚን አካል ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ ሕግ አንቀጽ የሚኒስትሮች ምክር ቤትን ሥልጣንና ተግባር በአጠቃላይ የሚገልጸው፣ ብዙ ጊዜም (ኧረ ሁልጊዜም) ‹‹የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፕብሊክ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 77 የተመለከተው›› ነው የሚለው ነው፡፡
ይኼ ቋሚ ‹‹ይለፍ›› ብቻ ግን በቂ አይደለም፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወይም መስተዳድሩ ደንብ የሚባል የሕግ ዓይነት የማውጣት በሕገ መንግሥት የተሰጠ ጠቅላላ ውክልናው፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየነቂስ ጉዳዩ በሚሰጠው ልዩ የውክልና ሥልጣን ላይ ጭምር የተመሠረተ በመሆኑ መስተዳድሩ የሆነ ደንብ ሲያወጣ ይህንን ልዩ ‹‹የውክልና ሥልጣን››ም ማሳየት አለበት፡፡ ነገር መበላሸት የጀመረው ይህ በሕግ የታዘዘና በተግባርም ብዙ ጊዜ (በተለይም መጀመርያ ላይ) ይተገበር የነበረ አሠራር ቀስ በቀስ እየተናደና እየተተወ ሲመጣ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ የማይናቅ ቁጥር ያላቸው በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጡ ደንቦች የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 77(13) ወይም ይህንን አንቀጽ የሚጠቅሰውን የኢፌዴሪ አስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣውን አዋጅ አንቀጽ ብቻ የሚጠቅሱና ተገቢውን ‹‹ይለፍ››ም ያልያዙ ናቸው፡፡ ይህ ትልቅ ግድፈት፣ ስህተትና ጥፋት ሆኖ ቆየ፡፡ ከ1934 ዓ.ም. ወዲህ አገራችን እየለመደችው፣ እያወቀችውና እያዋሀደችው በመጣው ባህል መሠረት እንኳንስ ዋነኞቹ ሕግ አውጪ የመንግሥት የሥልጣን አካላት ተራ መሥሪያ ቤቶች የሚያወጡት፣ ከአዋጅና ከደንብ በታች ያሉ የሕግ ዓይነቶች ገና ሲጀምሩ ‹‹አውጪው ባለሥልጣን›› የሚል ርዕስና መግቢያ የመጀመርያውና የጥበብ መጀመርያቸው ነበር፡፡ አውጪው ባለሥልጣን ይሉና የአውጪውን ባለሥልጣን ስም ብቻ ሳይሆን፣ ይህን የሕግ ዓይነት እንዲያወጡ ሥልጣን የሰጣቸውን አካልና ሕግ ይጠቅሳሉ፡፡ ለፍርድ ቤት የውክልና ሥልጣን እንደማቅረብና ይለፍ እንደማሳየት ማለት ነው፡፡ በሕግ በተለይም ደንብ በማውጣት ሥርዓቱ ውስጥ ሲጎድል፣ እንዳሻውና እንደፈቀደ ሲደረግ የምናየው ዋናው ችግር ይኼው ነው፡፡
በዚህ ብቻ ሳያበቃ የባሰ ነገር ደግሞ የተወካዮች ምክር ቤት ራሱ ባወጣው ሕግ (ማውጣት እችላለሁ ባለው ሕግ) የፌዴራል መንግሥት አስፈጻሚ አካላትን እንደገና የማደራጀት ሥልጣን ለራሱ ለባለ ጉዳዩ ሲሰጥ ነው፡፡ ይህ የሆነው እዚህ አዳላጭ ድጥ ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ የገባነው (ለዚያው በአጠቃላይ ጥናትና የመዋቅር ጥናት ሳይሆን)፣ አንድ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽንን ወደ ሚኒስቴርነት ከፍ ለማድረግ በወጣና እመጫት ሆኖ እንዲገባ በተደረገ ማሻሻያ ሕግ ነው፡፡ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽንን የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባልነትና የሚኒስትርነት ከፍታ ከሰጠው የሕግ ማሻሻያ ጋር አንቀጽ 34 ‹‹የፌዴራል አስፈጻሚ አካላትን እንደገና ስለማደራጀት›› የሚል ድንጋጌ አብሮ ተጭኖ አለፈ፡፡
ይህን በመሰለ ተጠያቂነት በሌለበት፣ ሳይጠየቁ መቅረት ተመርቆ በተቋቋመበት አሠራር ‹‹የሚኒስትሮች ምክር ቤት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ደንብ በማውጣት ነባር አስፈጻሚ አካል እንዲታጠፍ፣ ከሌላ አስፈጻሚ አካል ጋር እንዲዋሀድ፣ እንዲከፋፈል ወይም ተጠሪነቱ እንዲለወጥ በማድረግ ወይም አዲስ አስፈጻሚ አካል እንዲቋቋም በማድረግ፣ የፌዴራል አስፈጻሚ አካላትን እንደገና ለማደራጀት ሥልጣን›› ተሰጠው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲህ ያለ ሥልጣን መስጠት ይችላል ወይ? የሚኒስትሮች ምክር ቤትስ እንዲህ ያለ ሥልጣን ተሰጥቶኛል ማለት ይችላል ወይ? የሕግ የበላይነት እያሉ ነጋ ጠባ ለሚወተውቱን የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሲቀርብ የቆየ አሥር ዓመት ያከበረ/የሞላው ጥያቄ ነው፡፡ ዓብይ አህመድም ዝም ብለው ያሳለፉት፣ ዝም ያሉትና በእሳቸውም ቋንቋ ‹‹የሳቱት›› ዓብይ ግድፈት ነው፡፡
በዚህ ሁኔታ የተፈጠረውና ለድፍን አሥር ዓመት ‹‹መጫወቻ›› ሆኖ የኖረው ይህ ‹‹ሥልጣን›› የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን የአንድ ‹‹ነገር›› መብት አሳልፎ በመስጠት፣ ወይም የአንዱን ሥልጣን ሌላው በማለዋወጥ ትርጉም የለሽ፣ ለውጥ የለሽ፣ ዕርባና ቢስ ተብሎ በሚዘነጋና ቸል በሚባል ‹‹ስህተት›› ተመካኝቶ የሚቀር አይደለም፡፡ ይህን ዝም ማለት በገዛ ራሱ ምክንያት በሕዝብ፣ በተወካዮችና በአስፈጻሚ መካከል ያለውን (ሕገ መንግሥቱ አለኝ የሚለውን) ግንኙነት ይሰውራል፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ እንደ ተወካዮች ምክር ቤት (በአንፃራዊነት) ግልጽ ባልሆነ አሠራር የታክስ ከፋዩንና የመንግሥትን ገንዘብ እንደ ጉድ ያለ ተጠያቂነት የሚቆረጥሙ የውስጥ ለውስጥና የ‹‹ኪስ› መሥሪያ ቤቶች እንደ አሸን ያፈላል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ልምምድ በጎደለው፣ የሕዝብ ዓይንና ጆሮ ድርሽ በማይልበት አሠራር የሚደራጁ መሥሪያ ቤቶች በፋብሪካ መጠን የሚያወጧቸው መመርያዎች በሰው ልጆች ላይ ግዴታ የሚያቋቁሙ፣ በመብት መገልገል ላይ ገደብ የሚያበጅ ሆነው ያርፉታል፡፡ የቋንቋ መብት ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ አግኝቶ ለዚያውም የገዛ ራሱ ‹‹ችግር›› ፈጠረ በሚባልበት አገር እኛ ወይም ዋርድያዎች ከሚውቁት ቋንቋ ውጪ፣ እስረኞች ዘመድ ማነጋገር አይችሉም የሚል ዓይነት ደንብ/መመርያ ለፍርድ ቤት በአቤቱታ ተደጋግሞ ሲቀርብ የምናየውና የማያዳግምም ምላሽ አላገኝ ያለው፣ እንዲህ በየጓዳውና ጎድጓዳው ሕግና ደንብ የማውጣት ‹‹ስድ›› እና ‹‹ልቅ›› ሥልጣን አለኝ ከማለት የተነሳ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ለውጡ መንገድ ያዘ፣ ብሎም ተሳካ ማለት የሚችሉት እንደጀመሩትና እንደለመዱት የድርጅታቸው የኢሕአዴግን ሁሉንም ነገር ማድረግና ሁሉንም ነገር የመሆን የሥልጣን ልክፍትና አባዜ አይቻልም፣ አይደገምም ሲሉና በዚያውም ልክ የሕዝቡን ድጋፍና እንቅስቃሴ ማሸነፍ ሲችሉ ነው፡፡
በእሳቸው የጠቅላይ ሚኒስትርነት ዘመን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተነጋግሮ ካፀደቀው በኋላ ለፓርላማ የቀረበው የመጀመርያቸው የመስተዳድሩ ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ አዋጅ ግን (አዋጅ ቁጥር 1097/2011 ሆኖ የፀደቀው የኢፌዴሪ አስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው በአዲሱ የለውጥ መንግሥት ዘመን የወጣ የመጀመርያው ሙሉ አዋጅ ነው)፣ እነሆ እንደተመለከትነውና የጥንቱን የጠዋቱን የአንቀጽ 34 ሥልጣንን ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ በዚህ በአንድ ቀን ዕይታና ንባብ በፀደቀው አዋጅ መሠረት ዓብይና መንግሥታቸው አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኙት ደንብ እያወጡ የትኛውንም አስፈጻሚ አካል ሊያጥፉ፣ ከሌላ ጋር ሊያዋህዱ፣ ለሁለት ለሦስት እንዲሰነጠቅ ሊያደርጉ ተጠሪነቱን ወይም ሥልጣንና ተግባሩን ሊለውጡ፣ ሊለዋውጡ፣ ወዘተ ይችላሉ ማለት ነው፡፡
በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ የተደረገው ውይይትና ዝግጅት በዚያው በግማሽ ቀን የከሰዓት በፊት የፓርላማው ውሎ የተጠናቀቀ ቢሆንም፣ የአንቀጽ 34 ጉዳይ በአንድ የምክር ቤት አባል መጠየቁና መነሳቱ አልቀረም ነበር፡፡ ድፍንፍንና ችግሩን ይልቁንም ይህን ያህል አስፈላጊ ያደረገውን ምክንያት እንደ መንግሥት ያስረዳና የሚረታ ምክንያት ያቀረበ አስረጂ አልነበረም፡፡ ዓብይም ራሳቸው ጉዳዩን ያለፉት ሳይናገሩ በዝምታ ነው፡፡ ከአሥር ዓመታት ተከታታይ ስህተትና ጥፋት በኋላ እንደገና በዓብይ የለውጥ ዘመን ጭምር እንዲዘልቅ መደረጉን ከሰማሁ ጀምሮ፣ አዕምሮዬን የምሞግተው ይህ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ የዓብይ ፈቃድ በጭራሽ አይደለም እያልኩ ነው፡፡
ዓብይ የአንቀጽ 34ን ሥልጣን ይፈልጋል ማለት ስለማልችል፣ ይህ አንቀጽ ይህን ያህል አፍጥጦ ሲመጣና ዝም ሲባል፣ ዝም ያሉት ችግሩንና ግትልትል ጣጣውን ሳይረዱትና ሳያውቁት ቀርተው እንጂ፣ እያወቁት አይደለም ባይ ነኝ፡፡ የፌዴራል መንግሥት አስፈጻሚ አካላትን የማደራጀት፣ ወዘተ ሥልጣን የፌዴራሉ መንግሥት ሕግ አውጪ አካል እንጂ ይህ አካል ለአስፈጻሚ አካል በውክልና የሚሰጠው ሥልጣን አይደለም፡፡ ደጋግሜ እንደገለጽኩት አገራችን ውስጥ በመንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ በአደረጃጀትም በአሠራር ባህላችንም ውስጥ የደረሰውን ብልሽት ጠፍጥፎ የሠራው፣ እንዲህ ያለ ሥርዓት አልባና ልጓም አልባ የመንግሥት የሥልጣን አካላት የእርስ በርስ ግንኙነት ነው፡፡ ይህ መቅረት አለበት፡፡ በጭራሽ መደገምም፣ መቀጠልም የለበትም፡፡ ሕዝብን አፍራለሁ፣ አከብራለሁ፣ አፍና ተግባሬን አቀራርባለሁ የሚል መንግሥት በመጀመርያ የአደረጃጀት አዋጁ የአንቀጽ 34ን ሥልጣን መርቁልኝ ብሎ አይጀምርም፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡