Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ዓይነት ችግር እንዲፈጠር አንፈልግም››

ሳዓድ ዓሊ ሺሬ (ዶ/ር)፣ የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር

ሳዓድ ዓሊ ሺሬ (ዶ/ር) የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2015 ለዚህ ኃላፊነት በተሾሙ ጊዜ አገሪቱን ያስተዳድር የነበረው መንግሥት ሌላ ነበር፡፡ ይሁንና ባለፈው ዓመት በተደረገ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሁን አገሪቱን የሚመሩት ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ ዓሊ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቦታቸውን ይዘው እንዲቀጥሉ መርጠዋቸዋል፡፡ ሚኒስትር ዓሊ ሺሬ (ዶ/ር) የአገራቸውን ገጽታ በማስተዋወቅ ረገድ ብዙ የሚባልላቸው፣ የዓለም መገናኛ ብዙኃንን በየጊዜው በመጋበዝ ሶማሊላንድ ሰላማዊና የተረጋጋች፣ እምነት የሚጣልባትና ነፃነት የሚገባት አገር ስለመሆኗ ለማሳየት የሚያደርጉትን መፍጨርጨር ሶማሊላንዶች ይመሰክሩላቸዋል፡፡ ምንም እንኳ ሶማሊላንዶች ከሞቃዲሾ ሶማሊያ ‹ወደን ተዋህደን ወደን ተለያይተናል› ቢሉም፣ አሁንም ድረስ ነፃ መንግሥትና አገር ሆነው ዕውቅና ለማግኘት ብዙ መጓዝ ይጠብቃቸዋል፡፡ ይህንን ረጀም ጉዞ የሚያሳጥሩባቸውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ማስተናገድ የጀመሩ ይመስላሉ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከሰሞኑ በአገራቸው በተደረሰው የወደብ ማስፋፊያ የግንባታ ስምምነትን መነሻ በማድረግ፣ የበርበራ ወደብ ለኢትዮጵያና ለሌሎች አገሮች ስለሚኖረው ጠቀሜታ፣ የበርበራ ኮሪደር ልማት፣ ከኢትዮጵያ ጋር ስለሚታሰበው የሁለትዮሽ የንግድ ስምምነት፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ከወደብ ልማት ባሻገር የጦር ሠፈር ግንባታ ለማካሄድ ስምምነት ማድረጓ ስለሚኖረው ተፅዕኖና ሌሎችም ጉዳዮች በሶማሊላንድ ከብርሃኑ ፈቃደ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ሶማሊላንድ በአፍሪካ ቀንድ የምትጫወተውን ኢኮኖሚያዊ ሚና ከጀመረችው የበርበራ ወደብ ማስፋፊያ ግንባታና እንደሚዘረጋ ከሚታሰበው የበርበራ ኮሪደር ልማት አኳያ እንዴት ይገልጹታል?

ዓሊ ሺሬ (ዶ/ር)፡- የበርበራ ወደብ በቀጣናው ስትራቴጂካዊ ቦታ ላይ የሚገኝ ወደብ ነው፡፡ ለአፍሪካ ቀንድ ምሥራቃዊው ክፍል ዋናው የመግቢያ በር ነው ማለት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያን ውሰድ፡፡ የመካከለኛው፣ የምዕራብና የደቡብ ኢትዮጵያ ክፍሎችን ብንመለከት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ያላቸውና አማራጭ ወደቦች ሊያስተናግዷቸው የሚችሉ ናቸው፡፡ ለምዕራቡ የኢትዮጵያ ክፍል የአሰብ ወደብ ዋናው የመግቢያ በር በመሆን ለኢትዮጵያ አማራጭ ወደብ እንደሚሆን ይታሰባል፡፡ የጂቡቲ ወደብም ለመካከለኛው ኢትዮጵያ ክፍል ዋናው የባህር በር ሊሆን ይችላል፡፡ ምሥራቃዊው ክፍል በአብዛኛው በበርበራ ወደብ በኩል ሊስተናገድ የሚችል መሆኑ፣ ከኢትዮጵያ ድንበር ጋር ካለው ቅርበት አኳያ አማራጭነቱ የጎላ ነው፡፡ ይሁንና የበርበራ ወደብ ገና እንደሚፈለገው አልለማም፡፡ በዚህም የኢትዮጵያን ጭነት በተለይም የኮንቴይነር ጭነት ለማስተናገድ ብዙ ይቀረዋል፡፡ ለኮንቴይነር ጭነት ያለው የወደብ አገልግሎት ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ፣ በርበራ ይህንን ፍላጎት የሚያሟላ ወደብ አይደለም፡፡ ይሁንና የተፈረመው የማስፋፊያ ግንባታ ስምምነት አዲስ ዘመን የሚፈነጥቅ ነው፡፡ ወደቡ ተስፋፍቶ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ከሶማሊላንድ ባሻገር ኢትዮጵያን፣ ሶማሊያንና ሌሎችንም ሊያገልግል እንደሚችል ይጠበቃል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ 30 በመቶ የወጪና ገቢ ዕቃዎች በበርበራ ወደብ እንደሚስተናዱ የሚያሳዩ መረጃዎች ነበሩ፡፡ አሁን ግን ኤርትራ የአሰብና የምፅዋ ወደቦችን ለኢትዮጵያ ክፍት በማድረግ የወደብ አግልግሎት ውድድሩን አጠናክራለች፡፡ ይህ በሆነበት ወቅት 30 በመቶ ሲባል የነበረው የጭነት መጠን ወደ በርበራ ወደብ የመሄዱ ጉዳይ እንዴት ይታያል? ይህንን ያህል መጠን ማስተናገዱ ለበርበራ እንደተቀመጠ ይቆያል? ወይስ አዲስ ድርድር ተካሂዷል?

ዓሊ ሺሬ (ዶ/ር)፡- የተጠቀሰው አኃዝ ቀድሞ የተቀመጠው በመጀመሪያው የአምስት ዓመቱ [የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ] ውስጥ ተጠቅሶ ነበር፡፡ በሁለተኛው ውስጥ ግን አልተካተተም፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ማንም ዋስትና የሚሰጥ የለም፡፡ አየህ አብዛኛው የኢትዮጵያ የወጪና የገቢ ዕቃዎች የሚስተናገዱት በግሉ ዘርፍ በኩል ነው፡፡ የግሉ ዘርፍ ደግሞ ዋጋው ቅናሽ ወደሆነለትና አዋጭ ሆኖ ወዳገኘው ነው የሚያዘነብለው፡፡ በመሆኑም አማራጭ አላቸው፡፡ ለአብነት አንድ የኢትዮጵያ ነጋዴ ከቻይና ዕቃ ቢያስመጣ፣ ዕቃውን ወደ ኢትዮጵያ ለማጓጓዝ በርካታ አማራጮች ይኖሩታል፡፡ ዕቃውን በፖርት ሱዳን በኩል አሊያም በአሰብ በኩል እንዲጓጓዝለት ማድረግ ይችላል፡፡ ምናልባትም በጂቡቲ ወደብ አሊያም ደግሞ በበርበራ ወደብ በኩል እንዲገባ የሚያደርግባቸው አማራጮች አሉት፡፡ በመሆኑም የተሻለ ጭነት ለማስተናገድ ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል፡፡ እያንዳንዱ ወደብ ባለው የተወዳዳሪነት አቅምና ልክ መሠረት ጭነት የማስተናገድ ዕድል ያገኛል፡፡ በዚህ ምክንያት የበርበራ ወደብ የአሥር በመቶ ወይም የ30 በመቶ የኢትዮጵያን ጭነት የማስተናገድ ዕድል ስለማግኘቱ፣ ማንም ማረጋገጫ ሊሰጠን አይችልም፡፡ በነፃ ገበያ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ተወዳዳሪነትን ስናሰፍን የሚታይ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- በርበራ ወደብ ለምሥራቃዊው የኢትዮጵያ ክፍል ስለሚኖረው አንፃራዊ ጠቀሜታ አብራርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ፊቱን ከበርበራ እንዳያዞር ሊያደርጉ ስለሚችሉ ሌሎች  ጠቀሜታዎቹ ሊባል የሚችል ነገር ይኖራል?

ዓሊ ሺሬ (ዶ/ር)፡- በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ መንግሥታት እንዲሁም በዲፒ ወርልድ መካከል ስምምነት ተፈራርመናል፡፡ ይህ ስምምነት አሁን የፀና ሲሆን፣ የተለወጠ ምንም ነገር የለም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከስምምነቱ መውጣት ፈልጎ እንደሆነም የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ጉዳይም አላነጋገሩንም፡፡ ይህንን የማደረግ ፍላጎት እንዳላቸው የሚያሳይ ምንም ጠቋሚ ነገር አላየንም፡፡ ተስፋ የምናደርገው ሦስቱም ወገኖች ብቃት ያለው ወደብ በመገንባት፣ መላውን የአፍሪካ ቀንድ ማገለግለግ የሚቻልበትን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሦስቱ ወገኖች በስምምነታቸው መሠረት በምን አግባብ እንደሚሠሩ ዝርዝር ሁኔታውን ቢያስረዱን? ለአብነት ያህል የወደብ ልማት የሚያከናውነውን ኩባንያ ሲመርጡ እንዴት እንደሚወስኑ፣ ወይም ደግሞ የትኛው የየትኛው አካል ተግባር እንደሆነ የሚያሳይ ነገር ቢገልጹልን? እንዲህ ያለውንስ ሥራ የሚወጡት በስምምነታቸው መሠረት ነው ማለት ይቻላል?

ዓሊ ሺሬ (ዶ/ር)፡- ስምምነቱን ስንፈርም በተለይም ከዲፒ ወርልድ ኩባንያ ጋር የተደረገው ለሁለት ተከፍሎ የተደረገ ስምምነት ነው፡፡ አንደኛው የባህር አገልግሎትን የሚመለከተው ሲሆን፣ በስምምነቱ መሠረት ይህ ለሶማሊላንድ መንግሥት የተተወ የሥራ ዘርፍ ነው፡፡ የሶማሊላንድ የወደብ ባለሥልጣን የሚመለለከተው ተግባር ነው፡፡ ዕቃዎችን ማስተናገድን በመተለከተ በስምምነቱ የተጠቀሰው ሁለተኛው ክፍል ሲሆን፣ ይህም ዲፒ ወርልድ በርበራ የተሰኘው የሽርክና ኩባንያ የሚመራው ሥራና ኃላፊነት ነው፡፡ በመሠረታዊነት ሥራው ዕቃዎችን ወደ መርከቦች መጫንና ማራገፍ፣ መርከቦችን ማቆየት፣ መጠገን፣ ኮንቴይነሮችን ማፅዳትና የመሳሰሉትን ተግባራት የሚያካትት ሥራ ነው፡፡ ይህ የኩባንያው ኃላፊነት ነው፡፡ ኩባንያውም የመጣው ለዚህ ሥራ ነው፡፡ የአክሲዮን ድርሻን በተመለከተ ሁላችንም ለዲፒ ወርልድ በርበራ የሽርክና ኩባንያ በማዋጣት እንሳተፋለን፡፡ ይህ ኩባንያም የወደቡን የኦፕሬሽን ሥራዎች ይወጣል ማለት ነው፡፡ ግንባታና ጨረታ ማውጣትን በተመለከተ በስምምነቱም እንደተመለከተው የዲፒ ወርልድ ኃላፊነት በመሆኑ፣ ለበርበራ ወደብ ግንባታ ጨረታ ያወጣል፡፡ በዚህ መሠረት ለወደቡ ማስፋፊያ ግንባታ ጨረታ ወጥቶ፣ እንደሚመስለኝ ከመነሻው ሦስት ወይም አራት ኩባንያዎች ተሳትፈዋል፡፡ በኋላ ላይ አሸናፊው ኩባንያ ተመርጦ ስምምነት ፈርሟል፡፡

ሪፖርተር፡- የበርበራ ኮሪደር ልማት የሚል መግለጫ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ይህ ለመሆኑ  እንዴት የሚካሄድ ነው? የኢትዮጵያ መንግሥት በበርበራ ኮሪደር ልማት ላይ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳለው ይታወቃልና የበርበራ ኮሪደር ልማትን በመተለከተ ዝርዝር መረጃዎችን ቢያካፍሉን?

ዓሊ ሺሬ (ዶ/ር)፡- የበርበራ ኮሪደር ልማት የአፍሪካ ኮሪደር ልማት እንቅስቃሴ አካል ነው፡፡ በአፍሪካ የመሠረተ ልማት ትስስርን የማሻሻልና የማስፋፋት ዕቅድ አለ፡፡ እኛም በምሥራቅ አፍሪካ ኮሪደር ውስጥ የምንገኝ በመሆናችን የዚሁ ኮሪደር ልማት አካል ነን፡፡ የኮሪደር ልማት የወደብ ልማትን፣ የመንገዶች ግንባታን፣ የባቡር መስመሮችንና እንደ ኢነርጂና መሰል ያሉትን ሌሎች መሠረተ ልማቶች ማስፋፋትን የሚያካትት እንቅስቃሴ ነው፡፡ በመሆኑም የኮሪደር ልማቶች ለማካሄድ በመጀመሪያ የበርበራ ወደብን ማስፋፋትና ማልማት ይጠበቅብናል፡፡ በኮሪደር ልማቱ ላይ ተደራድረን በዚሁ መሠረት ዕቃዎችና አገልግሎቶች በምን አግባብ መጓጓዝ እንደሚገባቸው ስምምነት ማድረግ ያስፈልገናል፡፡

ሪፖርተር፡- በበርበራ ኮሪደር ልማት ላይ ሊነግሩን የሚችሉት ሌላ ዝርዝር ጉዳይ ምንድን ነው?

ዓሊ ሺሬ (ዶ/ር)፡- በጉምሩክ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነት አለን፡፡ ይህም እ.ኤ.አ. ከ2004 ጀምሮ የነበረ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የሁለትዮሽ የንግድ ስምምነት ለመፈረም እየሠራን ነው፡፡ የእንግሊዝ መንግሥት የንግድ ካርታ እንዴት እንደምናዘጋጅ፣ የኮሪደር ልማቱን በተመለከተ በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ መካከል ማጎልበት ስለምንችልበት መንገድ ድጋፍ እያደረገልን ነው፡፡ አንዳንድ ስምምነቶችን አድርገናል፡፡ ሌሎችም ወደፊት የሚፈረሙ ይኖራሉ፡፡ 

ሪፖርተር፡- የሁለትዮሽ የንግድ ስምምነቱ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ዕውን ሊደረግ ይችላል?

ዓሊ ሺሬ (ዶ/ር)፡- ተስፋ አለኝ፡፡ ከኢትዮጵያና ከሶማሊላንድ መንግሥታት የተውጣጡ ሁለት የጋራ ኮሚቴዎችን አቋቁመናል፡፡ የሶማሊላንድ ኮሚቴ የስምምነቶቹን ይዘቶች እያዘጋጀ  ይገኛል፡፡ እርግጥ ስምምነቱ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም አንዳንድ ማሻሻያዎች አስፈልገውታል፡፡ ምናልባትም የሁለቱ አገሮች ኮሚቴዎች በመጪው ወር ተገናኝተው እንደሚወያዩ ይጠበቃል፡፡ ይህ እንግዲህ እንደሚከናወን ነው የምጠብቀው፡፡

ሪፖርተር፡- በርበራን ከኢትዮጵያ በኩል ቶጎ ጫሌ ከተሰኘው ድንበር አካባቢ የሚያገናኝ የመንገድ ግንባታ እንደሚካሄድና በመጪው ወር ሥራው እንደሚጀመርም ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ ዓሊ ተናገረዋል፡፡ ይህ እንዴት እንደሚካሄድ ቢገልጹልን?

ዓሊ ሺሬ (ዶ/ር)፡- ከበርበራ ወደ ቶጎ ጫሌ የሚወስደው የመንገድ ግንባታ ይካሄዳል፡፡ የመንገዱን የዲዛይን ሥራ የሚያካሂድ ኩባንያም ተመርጦ ሥራውን ጀምሯል፡፡ መረጃ የማሰባሰብ ሥራቸውን አጠናቀው የመንገዱን የዲዛይን ሥራ ለመጀመር እንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ እንዳለቀ የመንገዱን ግንባታ የሚያካሂድ ኩባንያ ለመምረጥ ጨረታ እናወጣለን፡፡ 

ሪፖርተር፡- እንደሚባለው የ100 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ነው? ወይስ ከዚህም ይልቃል?

ዓሊ ሺሬ (ዶ/ር)፡- እስካሁን ባለው መሠረት ፕሮጀክቱ የተያዘለት የ90 ሚሊዮን ዶላር በጀት ነው፡፡ ምናልባት እንደ ሁኔታው የገንዘቡ መጠን ሊቀንስም ሊጨምርም ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡– ኢትዮጵያ በዚህ ፕሮጀክት ትሳተፋለች? የመንገድ ግንባታውስ የሽርክና ፕሮጀክት ነው ሊባል ይችላል?

ዓሊ ሺሬ (ዶ/ር)፡- እስካሁን ባለው ሁኔታ ለመንገዱ ግንባታ የሚውለውን ገንዘብ የሚያቀርበው የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መንግሥት ነው፡፡ የአውሮፓ ኅብረትም አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተስፋ አለን፡፡ የእንግሊዝ መንግሥትም ለፕሮጀክቱ የድርሻውን እንደሚያበርክት እንጠብቃለን፡፡ ይህ ሁሉ የማይበቃን ከሆነ ግን ኢትዮጵያም አስተዋጽኦ እንድታደርግ መጠየቃችን አይቀርም፡፡

ሪፖርተር፡- የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መንግሥት በበርበራ የሚገነባው ወታደራዊ የጦር ሠፈር ሶማሊላንድን መነጋገሪያ ካደረጉ አሳሳቢ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ የወታደራዊ ሠፈሩ መኖር በቀጣናው አገሮች ወይም በጂኦፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ምንድነው? የጦር ሠፈሩ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ ተፅዕኖ ሊያሳድርበት ይችላል?

ዓሊ ሺሬ (ዶ/ር)፡- የወታደራዊ ሠፈሩ ግንባታ ሚስጢራዊ አይደለም፡፡ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መንግሥት ጋር የ25 ዓመታት የሊዝ ስምምነት ፈርመናል፡፡ በመሆኑም ቀድሞም በሩሲያ፣ በአሜሪካና በሌሎችም አገሮች በተለያዩ ጊዜያት ወታደራዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየውን ሠፈር ነው የሰጠናቸው፡፡ የወታደራዊ ሠፈሩ መኖር በቀጣናው ውስጥ ችግር ይፈጥራል ብለን አናምንም፡፡ አስፈላጊው መረጃ ሁሉ ለሕዝብ ክፍት ነው፡፡ በመሠረቱ ወታደራዊ ሠፈሮች ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ ናቸው፡፡ አንዳንዴም ለዘርፈ ብዙ ጉዳዮች አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡ አንዳንዶቹ ለነፍስ አድንና ለሌሎች ተልዕኮዎች አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው፡፡ ለዚህ ተልዕኮም የባህር ኃይል መርከቦቻቸውን በጦር ሠፈሮቻቸው አካባቢ ያሰማራሉ፡፡ አንዳንዶቹ ወታደራዊ ሠፈሮች ለወታደሮቻቸው ማሳረፊያ እንዲሆኑ ታስበው የሚገነቡ ናቸው፡፡ ለወራት በተለያዩ ግዳጆች ላይ ተሠማርተው የቆዩ ወታደሮቻቸውን ለጥቂት ሳምንታት ዕረፍት እንዲያገኙ ለማድረግ ሲሉ ወታደራዊ ሠፈሮችን የሚመሠርቱ አገሮች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ለሥልጠና ማዕከልነት የሚመሠረቱ ሲሆኑ፣ አንዳንዶቹ ሠፈሮች ደግሞ ለሎጂስቲክስ አገልግሎት ሲባል የሚገነቡ ናቸው፡፡ በመሆኑም ወታደራዊ ሠፈሮች በርካታ ተግባራት ያሏቸው በመሆናቸው፣ እንዲሁ ለጦር መምርያነት ተብለው የሚመሠረቱ አይደሉም፡፡ ወታደራዊ ሠፈሮች በመሆናቸው ብቻ ተዋጊ አውሮፕላኖች ዒላማቸውን ለመምታት የሚገለገሉባቸው አይደሉም፡፡ የወታደራዊ ጦር ሠፈሮች ሚና በዚህ ብቻ የሚገለጽ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በበርበራ የራስዋን የጦር ሠፈር አትገነባም እያሉ ነው?

ዓሊ ሺሬ (ዶ/ር)፡- የራሳቸውንም የጦር ሠፈር መገልገያ ሕንፃዎችማ ይገነባሉ፡፡ ነባሮቹ መገልገያዎች ያረጁና የተጎሳቆሉ ናቸው፡፡ በመሆኑም የራሳቸውን ሕንፃዎች ከመገንባት ባሻገር ወታደሮቻቸውንም ይልካሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር የአውሮፕላን ማረፊያና አነስተኛ ወደብም ይገነባሉ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ሶማሊላንድ የወደብ ማስፋፊያ  ግንባታ በማካሄድና ኢኮኖሚዋን በማሳደግ ላ ተጠምዳለች፡፡ ከዚህ አኳያ በአጣዳፊነት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ምንድነው? ሁሌም እንቅልፍ የሚነሳዎ ጉዳይስ ምንድን ነው? 

ዓሊ ሺሬ (ዶ/ር)፡- ሕዝባችን ከሶማሊያ ጋር ተዋህደን በቆየንባቸው ዓመታት ለጉዳት ተዳርጓል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1981 እስከ 1991 ባለው ጊዜ ውስጥ ረጅም ትግል አካሂደናል፡፡ ነፃነታችንን ለማግኘት ባደረግነው ጥረት ውስጥ አስከፊ ጊዜያትን አሳልፈናል፡፡ ሰላሳ ዓመታት እንዳመለጡን እናስባለን፡፡ በመሆኑም ሌሎች ከደረሱበት በቶሎ መድረስ እንዳለብን ይሰማናል፡፡ ይህ ዋናው ፍላጎታችን ነው፡፡ በጥቅሉ ለመናገር ሕዝባችን ሥራ ፈጣሪ ነው፡፡ ሶማሊላንዶች የኢንተርፕራይዝ አመለካከት አላቸው፡፡ ከምንም ነገር ውስጥ የሆነ አንድ ነገር መሥራት ያውቁበታል፡፡ ይህ መንፈስ በመንግሥት ውስጥም አለ፡፡ እንቅልፍ የሚነሳን ነገር በመጪዎቹ 20 እና 30 ዓመታት ውስጥ አገራችንን እንዴት ብለን በሰላምና በብልፅግና ጎዳና እንድትራመድ እናደርጋታለን የሚለው ጉዳይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ቀጣናው ፖለቲካዊ ጉዳዮች እንመለስ፡፡ ከእስያ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ፣ እንዲሁም ከምዕራቡ ዓለም ኃያላን አገሮች የሚታየው እሽቅድምድም አፍሪካን በተለይም የአፍሪካ ቀንድን የውድድራቸው አውድማ ያደረጉት ይመስላል፡፡ ከዚህ አኳያ በፖለቲካ ገበያው የሚታየውን ውድድር እንዴት በመደራደር ተጠቃሚነታችሁን ልታረጋግጡበት ትችላላችሁ? 

ዓሊ ሺሬ (ዶ/ር)፡- የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በታሪኩ ሁሌም የሁሉም ኃይሎች ፍላጎት መናኸሪያ ሆኖ የቆየ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከሚገኝበት ወሳኝ አቀማመጥ የሚነሳ ነው፡፡ የፍላጎቱ ስበት መነሻው የቀጣናው ስትራቴጂካዊ መሆን ነው፡፡ የስዊዝ ካናል መከፈትን ተከትሎ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ለባህር ትራንስፖርት ወሳኝ መተላለፊያ በመሆን አፍሪካን ከአውሮፓ፣ አፍሪካን ከመካከለኛው ምሥራቅ፣ እንዲሁም ከእስያ የሚያገናኝ በጣም ወሳኝ ቀጣና ነው፡፡ ለምሳሌ ብናይ፣ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ላይ እንግሊዞች ወደ ሶማሊላንድ የመጡት ይህንኑ የባህር መተላለፊያ ለመቆጣጠር ነበር፡፡ ባታሊዮኖቻቸውንና የባህር ኃይላቸውን አስፍረው ነበር፡፡ በቀይ ባህር አጠገብ ወደሚገኘው ወደ በርበራ አካባቢም ዘልቀዋል፡፡ ይህንን ያደረጉበት ምክንያት ጭነቶቻቸው ያለ ችግር በሰላም እንዲጓጓዙ ለማድረግ ብለው ነው፡፡ በስትራቴጂካዊነቱ የተነሳ በርካታ ኃያላን አገሮች በቀይ ባህር አካባቢ ወደሚገኙ አገሮች መምጣታቸውን ተያይዘውታል፡፡ ውድድርን በተመለከተ በተለይም ወታደራዊ ሠፈርና መሰል ጉዳዮችን በተመለከተ እኛ ከማንም ጋር ውድድር እንዳልገጠምን መናገር እፈልጋለሁ፡፡ ይሁንና የሆነ አካል መጥቶ ሲያነጋግረንና ስምምነት እንድናደርግ ሲጠይቀን፣ ለሕዝባችን እስከጠቀመ ድረስ ማስተናገዳችን አይቀሬ ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚታየው ሁኔታ ሶማሊላንድን ምን ያህል ያሳስባታል? በሁለቱ አገሮች መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ለውጦች ሊኖሩ ይችላሉ?

ዓሊ ሺሬ (ዶ/ር)፡- በግንኙነታችን ላይ የተደረገ ምንም ለውጥ የለም ማለት ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን ለውጥ በተመለከተ መናገር የምፈልገው የሚታዩትን ለውጦች የምንደግፋቸው መሆናችንን ነው፡፡ በአገሮች መካከል የሚከሰቱ አለመግባባቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ እንፈልጋለን፡፡ ይህንንም እንደግፋለን፡፡ በአገሮች መካከል የሚደረጉ ኢከኖሚያዊ ትስስሮችንም እንደግፋለን፡፡ የሰብዓዊ መብቶች መከበራቸውንና የመንግሥት ድርጅቶች ለግሉ ዘርፍ ክፍት መደረጋቸውንም እንደግፋለን፡፡ እንዲህ ያሉት ለውጦች ተጠቃሚ የሚያደርጉት ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን፣ እኛንና የተቀረውን የቀጣናውን ሕዝቦች በመሆኑ ለውጦቹን ማየት ብቻም ሳይሆን መደገፍም እንዳለብን ይሰማናል፡፡ እርግጥ ነው ለውጦች ሲመጡ ፈተናዎችም አብረው መምጣታቸው አይቀሬ ነው፡፡ በነበረው ሥርዓት የራሳቸውን ጥቅም የሚያሳድዱ ሰዎች መነካታቸው አይቀርም፡፡ ይህንን ስትቀይር እነዚህ ሰዎች ያገኙ የነበረውን ጥቅም የሚነካ ነገር ማድረግህ ስለማይቀር፣ ከመነሻው ለውጥ በሚኖርበት ጊዜ መንፈራገጭ ይኖራል፡፡ ነገር ግን ለውጡን በሚገባ ማስተናገድ ከተቻለ እንዲህ ያሉ ችግሮችን በቶሎ ማለፍ ይቻላል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ለውጡን በሚገባ ማስኬድና መምራት ካልተቻለ ግን ብዙ ችግሮች ማስከተሉ የማይቀር ነው፡፡ እኛም ሥጋት አለን፡፡ ተስፋችን ሁሉ ነገሮች በቀና መንገድ ይከናወናሉ የሚል በመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ዓይነት ችግር እንዲፈጠር አንፈልግም፡፡ ለምሳሌ ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ ከወጡ፣ ከኢትዮጵያ የሚመጣውን ስደተኛ ልናስተናግድ የምችልበት አቅም የለንም፡፡ ሁሌም ሥጋት ቢኖርም ስደተኞች በከፍተኛ መጠን ቢመጡ ግን ለእኛ በጣም አዳጋች ይሆንብናል፡፡ ከባድ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማስተላልፈው መልዕክት የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ያለበቂ ምክክርና ውይይት እንዳይፀድቅ ነው›› አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም፣  የሕግ ባለሙያ

አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም በዳኝነትና በጥብቅና ሙያ ለረዥም ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከአምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ በሕገ መንግሥትና አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ  ጠበቆች ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ...

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...