Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እልም አለ ባቡሩ!

አገሪቱ በከፍተኛ ዕዳ ካስገነባቻቸው ፕሮጀክቶች አንዱ የአዲስ አበባ ጂቡቲ የምድር ባቡር አገልግሎት ነው፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ኢትዮጵያ ከ3.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ አድርጋለች፡፡ ወጪውም የተሸፈነው ከቻይና መንግሥት በተገኘ ብድር ነው፡፡ አዋጭነቱ ተሰልቶ የተተገበረ ፕሮጀክት ስለመሆኑ አለ አይባልም፡፡

ከአዲስ አበባ ጅቡቲ የሚዘልቀው የምድር ባቡር፣ ኢትዮጵያና ጅቡቲ ባቋቋሙት የጋራ ኩባንያ የሚመራ ድርጅት ነው፡፡ ሁለቱ መንግሥታት በደረሱት ስምምነት መሠረት፣ ኢትዮጵያ 75 በመቶ፣ ጅቡቲ የ25 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ እንዳላቸው  ይታወቃል፡፡ በጥምረት የተተገባው የባቡር መስመር በዋናነት የኢትዮጵያን የወጪና ገቢ ንግድ ለማቀላጠፍ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ታስቦ የተተገበረ ነው፡፡ የኢትዮ ጅቡቲ የምድር ባቡር ፕሮጀክት ‹‹ዕድለኛ ሆኖ›› ሁለት ጊዜ የተመረቀና ለአገልግሎት ዝግጁ ስለመሆኑ ተነግሮለት በምረቃ ሥነ ሥርዓቶች እየተሸሞነሞነ ሥራ መጀመሩ ተደጋግሞ ቢገለጽም፣ በታሰበው ልክ እየሠራ ነው ማለት ግን አይቻልም፡፡

ቀድሞውንም ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሳይጠናቀቅ ተጠናቅቋል ተብሎ በጥድፊያ ሥራ እንዲጀምር የተፈለገበት ምክንያት አሻሚ ቢሆንም፣ በወጉ አገልግሎት ሳይጀምር ለፕሮጀክቱ የዋለውን የብድር ዕዳ መክፈል እንዲጀምር የተገደደ ፕሮጀክት ነው፡፡ የዕዳ አከፋፈሉ ላይ ማራዘሚያ እንዲደረግበት ድርድር የተደረገበት ፕሮጀክት ነው፡፡

የኢትዮ ጅቡቲ የምድር ባቡር በታሰበው ልክ አገልግሎቱን ሊያቀርብ ያልቻለባቸው እውነታዎች ግልጽ ናቸው፡፡ ቀዳሚ ጉዳይ ከሚሰጠው አገልግሎት የሚያገኘው ገቢ በየዓመቱ የሚከፈለውን የዕዳ መጠን ሩቡን እንኳ መሸፈን የማይችል ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡

ኩባንያው ገና ሥራ መጀመሩ ከተገለጸ ማግሥት ጀምሮ፣ የሥራ ሒደቱና አደረጃጀቱ የፕሮጀክቱን አቅም በሚመጥን ደረጃ በቂ ዝግጅት ሳይደረግበት በጥድፊያ የተገባበት ይመስላል፡፡ ከሁሉም በላይ የባቡር አገልግሎቱ ነዳጅ በማመላለስ ረገድ ሊሰጥ የሚችለው አገልግሎት ከፍተኛ ሆኖ ሳለ፣ እስካሁን ድረስ አንድ ሊትር ነዳጅ ማመላለስ አለመቻሉ ሊናጋግር ይገባል፡፡ አገሪቱ የምታስገባውን ነዳጅ በቀላሉ ለማመላለስና ወጪ ቆጣቢና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት ያስችላሉ የተባሉ ነዳጅ ጫኝ ፉርጎዎች ተገዝተው ቢገቡም ያለ አገልግሎት ተቀምጠዋል፡፡ ይህ ለምን ሆነ ለሚለው ጥያቄ አጥጋቢ መልስ የሚሰጥም የለም፡፡ የነዳጅ ማመላለሱ ሥራ ቢጀመር የሚያስገኘው አገራዊ ጠቀሜታ ተሰልቶ ሥራውን ለማስጀመር ይህ ነው የሚባል ጥረት ሲደረግም አይታይም፡፡

የነዳጅ ማመላለሻ ፉርጎዎቹ በአንድ ጊዜ የሚያሱት የነዳጅ መጠን 75 የፈሳሽ ጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች የሚሸከሙትን ያህል መሆኑ ሲታሰብ ያስቆጫል፡፡ እንዲህ ያሉት መሰል ጉዳዮች የኢትዮ ጅቡቲ የምድር ባቡር አገልግሎት ሥራው ሳይጠናቀቅ ለምን ለሥራ ዝግጁ እንደተደረገ ጥያቄ ያጭራል፡፡

በኩባንያው ዕቅድ መሠረት በዓመት ሁለት ቢሊዮን ብር ገቢ እንደሚያስገኝ ታሳቢ ተደርጎ ‹‹ሥራው ጀምሯል›› የተባለ ሲሆን፣ በተለይም የነዳጅ መመላለሻ ፉርጎዎችን ሥራ ማስጀመር ሳይችል በመቅረቱ ምክንያት በዕቅዱ የተቀመጠውን ገቢ እንዴት ሊያሟላ ነው? እንዴትስ ዕዳውን ሊከፍል ነው? አስቧል ብሎ መጠየቁም ተገቢ ይሆናል፡፡

በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዚህን ፕሮጀክት ዕዳ መክፈያ ጊዜ እንዲራዘም ከቻይና መንግሥት ጋር መስማማታቸውን፣ የፕሮጀክቱ ዕዳም ከአጭር ጊዜ የብድር ሥርዓት (ኮሜርሺያል ሎን) ወጥቶ በረጅም ጊዜ በሚከፈለው በኮንሴሽናል የብድር ሥርዓት እንዲስተናገድ ባይደረግ ኖሮ፣ ባለው የሥራ እንቅስቃሴ ዕዳውን እንዴት ሊከፈል እንደሚችል ለማወቅ ይከብዳል፡፡ ምናልባትም የቻይና መንግሥት በዕዳ መያዣነት በሐራጅ መውረሱ አይቀሬ ይሆን ነበር ማለት ነው፡፡ አሁንም ቢሆን በሙሉ አቅሙ እንዲሠራ ርብርብ የማይደረግ ከሆነ፣ ነገም ዕዳውን ለመክፈል ወለም ዘለም ማለቱ አይቀርም፡፡

እዚህ ላይ መንሳት ያለበት ሌላው ነጥብ የባቡር መስመሩን ለማስተዳደር ኃላፊነቱን የተረከቡ የቻይና ኩባንያዎች በዓመት ወደ 60 ሚሊዮን ዶላር እንደሚከፈላቸው ነው፡፡ የባቡር አገልግሎቱ ሥራ ከጀመረ ወዲህ እያገኘ ያለው ገቢ የቻይና ኩባንያዎች በዓመት የሚከፈላቸውን ያህል ገቢ ስለማግኘቱ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ አብዛኛው ገቢ ከነዳጅ ማመላለስና ከጭነት አገልግሎት ይገኛል ተብሎ በመታሰቡ ሲሆን ይህንን ግን እንደሚገባው እየተወጣ አይደለም፡፡ እንኳን ትርፍ ሊያስገኝ ዕዳውን የማይክፍል የብረት ቅጥልጥል መባል የቀረበው ባቡር ሆኗል፡፡ መንገደኞችን ከማጓጓዝ ሥራው የሚያገኘው ገቢም ቢሆን በታቀደው ልክ እንዳልሆነና በሙሉ አቅሙ እንደማይሠራ ልብ ይሏል፡፡ ስለዚህ ቢሊዮኖች ዶላሮች የወጣበት ይህ ፕሮጀክት፣ ውጤታማ አገልግሎት አለመስጠቱ መንግሥትንም ሕዝቡን የከነከናቸው አይመስሉም፡፡

 ሌላው አሳዛኝ ጉዳይ ነዳጅ ለማጓጓዝ የሚያስችለው ዋና ዋና የመሠረተልማት አውታር አሁንም ድረስ አለመጠናቀቁ ነው፡፡ በጅቡቲ ወገን መጠናቀቅ የነበረበት  ሥራ አለመጠናቀቁ ትልቅ ጫና ነው፡፡ ምንም እንኳ ነዳጅ ጫኙ የባቡር መስመር ጂቡቲ ከተማን አልፎ ወደ ጂቡቲ ወደብ መዘርጋቱ ቢታይም፣ እጅግ በጣም ያነሰ ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውና ጭነትና ነዳጅ ከመርከቦች ወደ ባቡር ለማስተላለፍ የሚያችለው ሐዲድ አሁንም ድረስ አለመጠናቀቁን እየሰማን ነው፡፡ ወይ ነዶ ያሰኛል፡፡

ይህ ሁኔታ እያለ ነው ፕሮጀክቱ ከአንዴም ሁለት ጊዜ በአደባባይ የተመረቀው፡፡ አንዴ ሙከራ ላይ ነው፡፡ ሌላ ጊዜ ዓለም አቀፍ ፈተናዎችን እያከወናወነ ነው ሲባል የቆየው የባቡር መሠረተ ልማት የዝናብና የፀሐይ ሲሳይ ሆኖ ይገኛል፡፡

ነዳጅ በባቡር መጥቶ ይከማችበታል የተባለውም ዲፖ በባቡር ይመጣል የተባለውን ነዳጅ ማግኘት አልቻለም፡፡ ይህ ለምን ሆነ? ካልን አሁንም ፕሮጀክቱ ተመረቀ ከመባሉ በፊት ሳይጠናቀቅ ወደ ትግበራ መግባቱን የሚያሳብቅ ነው፡፡ የፕሮጀክቱ አንዳንዶቹ ክፍሎች ቀድመው አልቀው ሲጠባበቁ ቆይተውም ሥራውን መጀመር አልቻሉም፡፡ በቂ ዝግጅትና ክትትል የማይደረግ የአገር ሀብት በዕዳ የባከነበት ብኩን ፕሮጀክት ወደ መሆኑ ተጠግቷል ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም ነዳጅ የማመላለሱ ሥራ በወጉ እንዳይከወን ከኋላ የሚገፋ አካል አለ? ወይስ አሁንም አገልግሎቱን ለማስጀመር የሚያስችል አሠራር መዘርጋት አልተቻለም? መፈተሽ አለበት፡፡ አገር በዕዳ የገነባቸው ፕሮጀክት ለምን በወጉ ወደ ሥራ እንዳልገባ ሊታወቅ ይገባል፡፡ አገልግሎቱን ሳናይ የዕዳ ማራዘሚያ ልመና ውስጥ የገባነው በቅጡ ሠርቶ ይከፍላል በሚል ታሳቢ በመሆኑ ነገርየው መጣራት አለበት፡፡ ትርፍና ኪሳራው በአግባቡ ስለ መሠራቱም ተብራርቶ ሊነገረን ይገባል፡፡ የመንግሥትን ግልጽነት እንሻለን፡፡ እያንዳንዳችን ከነገው ኑሯችን ቀንሰን የከፈልበት ፕሮጀክት በመሆኑ ምን እንደጎደለ፣ ምንስ እንደተበላሸ ሊነገረን ይገባል፡፡ ማወቅም መብታችን ነው፡

የአዲሷ የትራንስፖርት ሚኒስትር፣ የመጀመሪያ ከሚያደርጓቸው ሥራዎች ውስጥ የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር አገልግሎት እንደሚሆን አይጠረጠርም፡፡ በመረጃና ተግባቦት ዘርፍ ካላቸው ልምድ በመነሳት ችግሩን ፈትሸው የደረሱበትን ያሳውቁናል፣ ለችግሩም መፍትሔ ይፈልጋሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት