Monday, May 29, 2023

ትጥቅ የመፍታት አተካራና የመንግሥት ተገዳዳሪነት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ሐሙስ ጥቅምት 8 ቀን 2011 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮችና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ላይ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ባሰሙት ንግግር ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በፓርላማ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ለተጠየቋቸው አሥር ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ ካነሷቸው ነጥቦች አንዱ በአንድ አገር ውስጥ በቡድን የመታጠቅ መብት ያለው መንግሥት ብቻ ነው የሚለው ነበር፡፡

በአንድ ሳምንት ውስጥ ለሁለት ቀናት ማክሰኞና ሐሙስ በፓርላማ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ምንም እንኳን በፓርላማ አባላት በጥያቄነት ባይነሳላቸውም፣ የታጠቁ ወታደሮች ምንም በጎ ዓላማ ለሌለው ተግባር በቤተ መንግሥት መገኘታቸውንና በወቅቱም እሳቸው ጥበብ በተሞላበት ሁኔታ ማርገባቸውን አውስተው ነበር፡፡

መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ወታደሮቹ አዲስ አበባ ዙሪያ የነበራቸውን ግዳጅ ጨርሰው ወደ መጡባቸው ካምፖች እየተመለሱ ሳለ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ባሉባቸው ችግሮች ዙሪያ ሊያነጋግሩ መሄዳቸውን በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ሞቱማ መቃሳም ለሪፖርተር ይህንኑ የተናገሩ ሲሆን፣ የኮማንዶዎቹ ዓላማ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማግኘትና እንደ ማንኛውም የአገሪቱ ዜጋ ከእሳቸው ጋር ተወያይተው ችግራቸውን ማሳወቅ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፈገግታና በእርጋታ በሰጡት መግለጫም ይኼንኑ ተናግረው ነበር፡፡

ይሁንና የወቅቱን የመግለጫ ገጽታቸውን አስመልክተው በፓርላማ ለአንድ ሰዓት ከ15 ደቂቃ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ያ አመጣጥ ኢሕገ መንግሥታዊና አደገኛ ብቻ ሳይሆን፣ ሆን ተብሎ ሪፎርሙን ለማጨናገፍ ነው (ኢንቴንሽኑ ሪፎርሙን አቦርት ለማድረግ ነው)፡፡ ምንም ዓይነት ቅን ዓላማ (ጄኒዩን ኢንቴንሽን) የለውም፤›› ያሉ ሲሆን፣ ‹‹ከፑሻፑ በስተቀር ባልተለመደ ሁኔታ በከፍተኛ መዝናናትና መሳቅ ነበር ኢንተርቪው የሰጠሁት የዚያን ቀን፣ ውስጤ ድብን እርር እያለ ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ምንም እንኳን ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ እንደሆነ ባለሙያዎች የሚስማሙበት፣ ነገር ግን ፓርላማው ሳያነሳው ያለፈው ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወታደሮቹን በሚመለከት ለመንግሥት ሚዲያዎች የሰጡት መግለጫ ከቀረቡላቸውና እሳቸውም አለሳልሰው ከመለሷቸው ጥያቄዎች አንዱ የታጠቁ ኃይሎች በአገር ውስጥ መኖራቸውን፣ የተወሰኑት ደግሞ ትጥቅ ለመፍታት ፈቃደኛ አለመሆናቸው ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ የኦነግ መሪ አቶ ዳውድ ኢብሳ ከዋልታ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ትጥቅ የመፍታት ሐሳብ እንደ ሌላቸው ማስታወቃቸውን አስታከው እንዳስታወቁት፣ ‹‹ኦነግ ትጥቅ አልፈታም ይላል ብዬ አላስብም፡፡ ምናልባት የአፍ ወለምታ እንዳይሆን መልሶ ማጣራት ያስፈልጋል፡፡ ትጥቅ ለማንኛውም የተፎካካሪ ፓርቲ አያስፈልገውም፡፡ የሚያስፈልገው ትጥቅ የሐሳብ ትጥቅ ነው፡፡ የተደራጀ ስትራቴጂ፣ የተደራጀ ፖሊሲ፣ የተደራጀ ሐሳብ፣ አሁን ሥራ ላይ ያለውን መሞገት የሚያስችል ምክንያታዊ የሆነ ሳይንሳዊ መሞገቻ አቅም ነው የሚያስፈልገው እንጂ ክላሽ አያስፈልም፡፡ ማንን ለመምታት? እኛ እኮ ጥሪ ያደረግነው ፋሽኑ አለፈበት አንገዳደል ብለን ነው፡፡ ስለዚህ ማንም ወደ ኢትዮጵያ የገባ ኃይል ትጥቅ ያልፈታም የለም፡፡ በሚዲያ እንዳያችሁት ሁሉም ሲገባ እኮ ባንዲራ እያውለበለበ ነው የገባው አይደል እንዴ? ትጥቅ ይዞ የገባ ተቃዋሚ ወይም ተፎካካሪ ፓርቲ አልነበረም፣ አሁንም የለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ሕገወጥ ትጥቅ በጣም ብዙ ነው እንደምታውቁት፡፡ በየከተማው በየገጠሩ በሕገወጥ መንገድ የሚገቡ መሣሪያዎች አሉ፡፡ ይኼንን ከውጭ የመጣ ወይም ያለ ሰው ይዞት ሊሆን ይችላል፡፡ በምናወጣው ሕግ ትጥቅ መፍታት ያስፈልጋል፡፡ ትጥቅ የማያስፈልግበት ዋናው ምክንያት ኦነግ ማንን ነው የሚገድለው? ደምሂት ማንን ነው የሚገድለው? ግንቦት ሰባት ማንን ነው የሚገድለው? እኛስ ብንሆን ማንን ነው የምንገድለው? አቅም ካለን፣ ሀብት ካለን ሰብሰብ አድርገን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት መጠበቅ እንጂ እርስ በርስ መገዳደል አያስፈልግም በሚል እሳቤ ነው፡፡ እና ከመጀመርያው ጀምሮ ጥሪው ግልጽ ነው፣ አሁንም እየሆነ ያለው በዚያ አግባብ ነው፡፡ ብዙም የሚያሠጋ ነገር የለም፤›› ብለው ነበር፡፡

ይሁንና ይኼንን በሚመለከት ጥናት ያከናወኑና በሥራቸውም ከዚህ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ባለሙያዎችና በውትድርና ውስጥ ረዥም ጊዜ ያሳለፉ ከፍተኛ መኰንኖች፣ የእንዲህ ዓይነት ክስተቶች ዋነኛ ምክንያቶች መንግሥት ይኼንን አስቦ አስቀድሞ ያደረገው ቅድመ ዝግጅት አለመኖሩና የታጠቁ ኃይሎች ወደ አገር ቤት ሲገቡ ከመንግሥት ጋር የፈጸሙት ስምምነት ግልጽነት ማጣት እንደሆኑ ያወሳሉ፡፡

በውጭ አገር በተቃዋሚነት ከነበሩና የትጥቅ ትግልን እንደ አንድ አማራጭ የትግል ሥልት አድርገው ከቆዩና በኋላም በመንግሥት በተደረገ ጥሪ ወደ አገር ውስጥ ከተመለሱ ቡድኖች መካከል የአርበኞች ግንቦት ሰባትና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ እንዲሁም፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) የሚገኙበት ሲሆን፣ እነዚህ ቡድኖች የሽብርተኝነት ፍረጃቸው በፓርላማው ከተነሳላቸው በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው፣ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወታደሮቻቸውን ይዘው ገብተዋል፡፡ ይሁንና እስካሁን ድረስ የእነዚህ ወታደሮች ዕጣ ፈንታን በተመለከተ የተደረገው ስምምነት ግልጽ አለመሆን የትጥቅ ፍታ አልፈታም አተካራ ፈጥሯል የሚሉ አሉ፡፡

የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ የነበሩት ሜጄር ጄኔራል አበበ ተክለ ኃይማኖት ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ‹‹የተደረገው ስምምነት ኦነግ ይገባል ከማለት የዘለለ ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ በዛላምበሳ የገቡት ወታደሮች ትጥቅ አልያዙም ነበር፡፡ ግን ከገቡ በኋላ ራሳቸውን እንደገና አስታጥቀው ነው? ወይስ እንዴት ሊታጠቁ ቻሉ? የሚለው በራሱ አይታወቅም፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ሆኖም ታጣቂው ቡድን ጠንካራ ጡንቻ ሲኖረው ምንም ዓይነት ከሆነ ስምምነቱን የማፍረስ ፍላጎት ሊኖረው ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

እንደ ጄኔራል አበበ ምልከታ፣ በእንደህ ዓይነት ሁኔታዎች የሚደረጉ ስምምነቶች ሁለት ገጽታዎች ይኖራቸዋል፡፡ የመጀመርያው በመንግሥት በሚወጣ የምሕረት አዋጅ መሠረት ሁሉም ስምምነት ፈጽመው ወደ አገር ቤት የሚገቡ ሲሆን፣ በምሕረት አዋጁ ላይ ዝርዝር ሁኔታዎች ይቀመጣሉ፡፡ ሌላው ደግሞ አሁን ተደረጉ እየተባሉ እንዳሉት ዓይነት ስምምነቶች አማካይነት የሚደረግ ሲሆን፣ በዚህም አካሄድ በሚፈረመው ስምምነት ላይ ምን ምን ተግባራት እንደሚከናወኑና የታጠቁ አካላት ዕጣ ፈንታ በዝርዝር ይቀመጣል ይላሉ፡፡

‹‹ነገር ግን የታጠቀ ኃይል ሊኖረው የሚችለው መንግሥት ብቻ ነው፤›› ሲሉም ያስረዳሉ፡፡

ከኦነግም ሆነ ከሌሎች የታጠቁ ኃይሎች ጋር የተደረጉ ስምምነቶች ይዘት ምን እንደሆነ እስካሁን አልተገለጸም፡፡ በኤርትራ አቶ ዳውድ ኢብሳን፣ አቶ ኢብሳ ነገዎንና ሌሎችን ጨምሮ ከኦነግ አመራሮች ጋር የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ከተወያዩ በኋላ፣ በሦስት ጉዳዮች ላይ እንደተስማሙ የኤርትራ የኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር አቶ የማነ ገብረ መስቀል በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረው ነበር፡፡ አንደኛው ጉዳይ ጥላቻን ማስወገድ ሲሆን፣ ሁለተኛውና ሦስተኛው ደግሞ ኦነግ በኢትዮጵያ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲያደርግና ስምምነቱን ለማስፈጸምም የጋራ ኮሚቴ ማቋቋም ናቸው፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ በማስታወቅ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡ በዘርፉ የረዥም ጊዜ ልምድና ሙያ ያላቸው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ባለሙያ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በተመሳሳይ ትጥቅ እንዳይፈቱ ወይም እምቢ እንዲሉ የሚያደርጓቸው ማበረታቻዎች ሊኖሩ ይችላሉም ባይ ናቸው፡፡ እነዚህ ወታደሮች ትግልን የገቢ ምንጫቸው ስላደረጉት አማራጭ የገቢ ምንጭ ካልተመቻቸ በዚያው ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ያወሳሉ፡፡ በተጨማሪም ባለፉት ሦስት ዓመታት በነበረው አገራዊ አድካሚ የሰላም ማስከበር ሥራ ምክንያት፣ አሁን መንግሥት ያለበት ሁኔታ የራሱ የሆነውን ኃይል የመጠቀም መብት ለማስጠበቅ ደካማ ደረጃ ላይ በመሆኑም ሌላው ምክንያት ሊሆን ይችላል ባይ ናቸው፡፡

‹‹ያም ሆነ ይህ የዘመናዊ መንግሥትነት መገለጫ በመሆኑ የኃይል አጠቃቀም የብቸኝነት መብቱ ላይ በፍጹም መደራደር የለበትም፤›› ሲሉ ያሰምራሉ፡፡

መንግሥት የሚታጠቀው ከሕዝብ በታክስ ከሚሰበሰብ ገንዘብ በመሆኑ በዋናነት ሰላምን፣ ደኅንነትንና ሕግን ለማስጠበቅ በማለም የሚጠቀመው መብቱ ነው የሚሉት ባለሙያው፣ በዚህ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የትጥቅ ትግል ፋሽኑ ያለፈበትና በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ በጣም አናሳ ተቀባይነት ያለው እንቅስቃሴ ስለሆነ ስኬት የሚያመጣ ተግባር አይደለም ሲሉም ይሞግታሉ፡፡ የኢሕአዴግ ጦር ከደርግ ጋር በነበረው ትግል ወቅት ምንም ዓይነት ዓለም አቀፋዊም ሆነ አገራዊ ምቹ ሁኔታ አልነበረም ይላሉ፡፡ ስለዚህም አዋጩ የጨዋታው ሕግ ዴሞክራሲ መሆኑን ተቀብሎ መኖር ነው ሲሉም ያስገነዝባሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይም በፓርላማ ሐሙስ ጥቅምት 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ባደረጉት ንግግር ኃይል መጠቀም የመንግሥት ብቻ መብት እንደሆነ ገልጸው፣ ‹‹ኃይል የመጠቀም ብቸኛ ሥልጣን ያለው መንግሥት ነው፡፡ ግለሰቦችና ቡድኖች ይህ የመንግሥት ሥልጣን በሕግና በዘመናዊ መንግሥት አሠራር አልተፈቀደላቸውም፡፡ ሥልጣን ወስደው ራሳቸው ፍርድ የሚሰጡ ከሆነ ፍትሕ ይዛነፋል ብለው፤›› ነበር፡፡

ይሁንና አሁን የኢትዮጵያ ደኅንነት ተቋማት ከተቋምነት ይልቅ በግለሰቦች ላይ የተንተራሰ ማንነት ስላላቸው፣ ባለፉት ጊዜያት በአገሪቱ በነበሩ ችግሮች ምክንያት በድካም ላይ ድካም ተጭኖት የቆየው የፀጥታ መዋቅር ዛሬ የትጥቅ መፍታትም ሆነ ከማኅበረሰቡ ግር እንዲቀላቀሉ ለማድረግ ከባድ እንደሚሆንበት ባለሙያው ምልከታቸውን ያካፍላሉ፡፡

የታጠቁ ኃይሎች በኢትዮጵያ ካሁን በፊት

ኢትዮጵያ ከሁን በፊት የትጥቅ ማስፈታት፣ ከማኅበረሰቡ ጋር መቀላቀል ወይም ካለው ወታደራዊ መዋቅር ጋር የማዋሀድ ሥራ ሁለት ጊዜ አከናውናለች፡፡ የመጀመርያው ኢሕአዴግ የትጥቅ ትግሉን ባሸነፈ ማግሥት የነበረውን ተዋጊ በሙሉ አገሪቱ ይዛ የመቆየት አቅም ስላልነበራት፣ ወታደሮቹ ወደ አገር ቤት እንዲመለሱና እንዲያርሱ፣ የተሻለ ወታደራዊ ብቃት የነበራቸው ደግሞ ከተመረጡ የቀድሞው መንግሥት ብቃት ያላቸው ወታደሮች ጋር ተዋህደው እንዲቀጥሉ፣ ከበፊቱም በአጭር ጊዜ ሥልጠና የገቡት ተመልሰው ወደ ማኅበረሰቡ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡

በወቅቱ ኮሚሽን ተቋቁሞ ከደርግ ወደ ሠራዊቱ የሚገቡትን እንዲመለምልና እንዲገቡ ያደረገ ሲሆን፣ የኦነግ ወታደሮች ደግሞ ለብቻቸው በካምፕ እንዲቀመጡ ተደርጎ ነበር፡፡ የ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት እስከሚፀድቅ ድረስ፡፡

በወቅቱ ኢትዮጵያ 350 ሺሕ ወታደሮችን ከሠራዊቱ ያወጣች ሲሆን፣ ይህም ‹መልታይ ካንትሪ ዲሞቢላይዜሽን ኤንድ ሪኢንቲግሬሽን ፕሮግራም› በሚባልና በዘጠኝ አፍሪካዊ አገሮች በሚንቀሳቀስ ተቋም የተደገፈ ነበር፡፡

ይሁንና የሁለተኛው ማለትም ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኋላ የተፈጸመው ተመሳሳይ ድርጊት፣ በባለሙያዎች እጅግ አስደናቂ የተባለ ነበር፡፡ ከ1991 እስከ 1994 ዓ.ም. ባሉት ሦስት ዓመታት ብቻ 148,000 ወታደሮችና 17,000 የቆሰሉ ወታደሮች ትጥቅ ፈትተው ከኅብረተሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ተደርጓል፡፡ ይህም በገንዘብና ገንዘብ ነክ ባልሆኑ ድጋፎች የተከናወነ ሲሆን፣ በመከላከያ ሚኒስቴርና በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ትብብር የተፈጸመ ነበር፡፡ ለዚህ የሚሆን 174 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ በመንግሥት 3.1 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነበር የተሸፈነው፡፡ ቀሪው 170 ሚሊዮን ዶላር በዓለም ባንክ በዓለም አቀፍ የልማት አጋርነት (አይዲኤ) በብድር የቀረበ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ የትጥቅ ማስፈታት ከማኅበረሰብ ጋር መቀላቀልና ከመከላከያ ኃይል ጋር ማዋሀድን በሚመለከት ጥናታዊ ጽሑፍ የጻፉት አቶ ሙሉጌታ ገብረ ሕይወት  በጽሑፋቸው እንዳሰፈሩት፣ ከኢትዮጵያ ተሞክሮ አምስት ትምህርቶችን መውሰድ ይቻላል ይላሉ፡፡

የመጀመርያው ውጤታማ የሆነ የትጥቅ ማስፈታት፣ ከማኅበረሰብ ጋር መቀላቀልና ከመከላከያ ኃይል ጋር ማዋሀድ የሚከናወነው አሳታፊ በሆነ የፖለቲካ ሒደት መሆኑ ነው፡፡ ከጦርነት ወደ ሰላም የሚደረግ ጉዞ እጅግ ወሳኝ እንደሆነና ተቀባይነትንና የደኅንነት ፕሮግራሞችን ለመወሰን ይረዳል ይላሉ፡

ሁለተኛው ለሁሉም የመንግሥት ተግባራት ሰላምና መረጋጋት ቁልፉ መሪ ሐሳብ መሆን እንዳለበት ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ በፈቃደኝነት የተመሠረተ ሲሆን ብቻ ውጤታማ እንደሚሆን ነው፡፡ በአራተኛ ደረጃ የዓላማና የግብ ግልጽነት ሲኖር እንደሆነ፣ በአምስተኛ ደረጃም የውጭ ድጋፍ ውጤታማ የሚሆነው ተግባራዊ በሚያደርገው አገር የፕሮጀክት ባለቤትነት ያለውን ፕሮግራም ሲደግፍ ብቻ እንደሆነ ነው፡፡

ትጥቅ የመፍታት ሒደቶች

የታጠቁ ኃይሎችን በሚመለከት ሦስት አሠራሮች እንዳሉ ባለሙያዎቹም ሆኑ በዘርፉ የተለያዩ በዓም አቀፍ ደረጃ የተጻፉ ጽሑፎች ያስረዳሉ፡፡ እነዚህም ትጥቅ ማስፈታት፣ ወደ ማኅበረሰብ መቀላቀልና ካለው የፀጥታ መዋቅር ጋር እንዲቀላቀሉ ማድረግ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን በዘርፉ በኢትዮጵያ የቀድሞ ተሞክሮዎች ቢኖሩም፣  እነሱን ቀምሮ ለመጠቀም እምብዛም ጥረት እየተደረገ እንዳልሆነ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት ባለሙያ ያስረዳሉ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ አማካይነት ለዚህ ተግባር ያለመ ተቋም እየተቋቋመ ቢሆንም፣ ካሁን ቀደም የነበረውን ልምድ ሙሉ በሙሉ እንደረሳውና እንደ አዲስ ጥረት እያደረገ እንዳለ ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡

‹‹እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ በአገር ውስጥ ያለውን ዕውቀት ከግምት ያስገባ አይደለም፤›› ሲሉም ይወቅሳሉ፡፡

ከመንግሥት በተጨማሪም ለግንቦት ሰባት ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ግንቦት ሰባት ለራሱ ወታደሮች ማቋቋሚያና ለተባሉት ተግባራት ማስፈጻሚያ የሚረዳውን መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት እያቋቋመ ነው፡፡ ይህ ተቋም የግንቦት ሰባት ወታደሮች ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የሚያግዝ ሲሆን፣ በሒደቱም የገንዘብና ሌሎች ድጋፎችን የሚያደርግ እንደሆነ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን መንግሥት በሚወስደው ዕርምጃ እነዚህን አካላት ሲያደራጅ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባው ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡ በተለይ አሁን በሠራዊቱ ውስጥ ያለውን ወታደራዊ ሞራል በማይጎዳ መንገድ መከናወን አለበትና፡፡

‹‹ለምሳሌ የሚከፈላቸው ገንዘብ በ800 ብር በብርድና በሐሩር ድንበር የሚጠብቀውን ወታደር የሚያስከፋና ሞራሉን የሚነካ መሆን የለበትም፤›› ይላሉ፡፡

የሚቀላቀሉም ወታደሮች ቢኖሩ ከፍተኛ የኦሪዬንቴሽን (የአስተሳሰብ) ልዩነት ስላለ፣ ጠንካራ ሥልጠናና የኢንዶክትሪኔሽን ሥራ መከናወን አለበት ይላሉ፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሙያ ብቃቱና በሥነ ምግባሩ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚመሠገን በመሆኑና በሰላም ማስከበር ቀዳሚ ጥሪ የሚደርሰው ሠራዊት በመሆኑ፣ የሚቀላቀሉትን በጥብቅ ዲሲፕሊን ማሠልጠን እንደሚያስፈልግ ባለሙያው ያሳስባሉ፡፡ ነገር ግን አሠራሩ ፈቃደኝነትንም መዘንጋት የለበትም ይላሉ፡፡

እንደ ባለሙያው እሳቤ ካሁን ቀደም በሠራዊቱ ውስጥ የነበሩ ነገር ግን ሸሽተው የሄዱ አካላት እሴት መጨመር የሚችሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በደንብ የተጤነ አሠራር መሆን አለበት በማለት ያክላሉ፡፡

ይሁንና በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ አገር ውስጥ ገብተው ሳለ ትጥቅ ላለመፍታት የሚንገራግሩ ኃይሎችን በሚመለከት፣ መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎችና ዕርምጃዎች እንዳሉ ጄኔራል አበበ ያስደራሉ፡፡

‹‹የመጀመርያው መፍትሔ ፖለቲካዊ ነው፡፡ በተደረገው ስምምነት መሠረት ድርድር ማድረግ ነው፤›› የሚሉት ጄኔራል አበበ፣ ሁለተኛው ደግሞ እዚያ አካባቢ ያለውን ሕዝብ ማሳመንና ትጥቁን አልፈታም ያለውን አካል በሚቀበለው አካባቢ የተሻለ ተቀባይነት ለማግኘት መጣር ነው ይላሉ፡፡

ከዚህ ሌላ በሠራዊቱ (በታጣቂዎቹ) ላይ ፕሮፓጋንዳ መሥራትና ማሳመን አስፈላጊ ነው ሲሉም ይጠቁማሉ፡፡ በዚህ ሒደት ሕዝብ በደለኛውን እንዲያውቅ ማድረግ እንደሚያስፈልግና ማስተካከል ያለበት አካል እንዲያስተካክል ማድረግ ነው ይላሉ፡፡

‹‹የመጨረሻ የሚሆነው ግን ወታደራዊ ዕርምጃ ነው፡፡ ነገር ግን የዚህ ዋጋው እጅግ ከፍተኛ ነው የሚሆነው፡፡ ከወጪ አንፃር ሳይሆን በሕዝብ መካከል ተቀላቅለው ስለሚገኙ በንፁኃን ዜጎች ላይ ከሚደርሰው ጉዳት አንፃር፡፡ ይሁንና ቆይቶ ሕዝቡን ለማሳመን ጥረት ማድረግ አስፈላጊ ነው፤›› ይላሉ፡፡

ወደፊት እንዳይደገም የሚደረጉ ጥንቃቄዎች

ምንም እንኳን በትጥቅ ትግል መንግሥትን ለመጣል የሚታገሉ የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው ኃይሎች ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተመናመነ ቢሆንም፣ የተወሰኑ የአፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የትጥቅ ትግልን አማራጭ መፍትሔ አድርገው የሚታገሉ የፖለቲካ ኃይሎችን አቅፈዋል፡፡

አሁን ኢትዮጵያን በውጭ ሆኖ የሚወጋ ታጣቂ ኃይል ባይኖርም፣ ለወደፊት እንዳይፈጠሩና አገሪቱ ወደ ኋላ እንዳትመለስ መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎች እንዳሉ ባሙያዎች ያሳስባሉ፡፡

የመጀመርያውና ዋነኛው የጨዋታው ሕግ በግልጽ ተቀምጦ ከዴሞክራሲ ውጪ አማራጭ እንደሌለ ማስመር ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

‹‹እነዚህ ሰዎች ዴሞክራሲን አያውቁም፡፡ አማራጭ ማቅረብ ላይ እነሱም ደካማ ስለሆኑ ጠንክረው መሥራት አለባቸው፡፡ መንግሥትም ቆፍጠን ያለ አቋም መያዝ አለበት፤›› ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት ባለሙያ ያስረዳሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይም በመግለጫቸው፣ ‹‹እናነጋግራቸዋለን፣ ኦነጎችንም ሌሎችንም እናነጋግራቸዋለን፡፡ ተቀራርበን እንሠራለን፣ ሌላ አገር የለንም፡፡ አንድ አገር ነው ያለን፡፡ አገር ማፍረስ አያስፈልግም፡፡ ተቀራርቦ ተወያይቶ መገንባት ነው፡፡ ብዙ የሶሻል ሚዲያውን ዘመቻ ማቆም ያስፈልጋል፡፡ ኦነግም ይሁን፣ ግንቦት ሰባትም ይሁን፣ እኔም ልሁን የአገር መከላከያም ይሁን በሕግና በሕግ ብቻ ይሠራል፡፡ ከሕግ በላይ የሚሆን ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር የለበትም፡፡ ማንም ቢሆን፤›› ብለው፣ ‹‹አንድ አገር፣ አንድ መንግሥት፣ አንድ አርሚ ነው ያለን፡፡ ይህን ማጠናከር ለሁሉም ዙጎች የተፈቀደ ነው፡፡ ሁሉም በር ለሁሉም ዜጋ የተፈቀደ ነው፣ ግን በሕግ አግባብ ብቻ፡፡ ይኼንን እያሰብን እንሄዳለንና አንዳንዱን ዘመቻ ያው ረገብ አድርጎ ማየት ጥሩ ይሆናል፡፡ ተመካክረን እንፈታዋለን በቅርቡ ስለምንገናኝ፡፡ እሱ አያሳስብም አትጨነቁ፤›› ሲሉም አረጋግተዋል፡፡

ሥጋቶች

ሠራዊቱን የሚቀላቀሉ የታጠቁ ኃይሎች ለሚታገሉለት ድርጅትና ዓላማ ከፍተኛ ታማኝነት ስላላቸው፣ በአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ውስጥም ሆነ በክልል ፖሊስ ኃይል ውስጥ ቢቀላቀሉ በዚያው አስተሳሰብና ሥነ ልቦና ሊቀጥሉ ይችላሉ የሚል አስተሳሰብ ያላቸው አሉ፡፡ ይህ ከሆነም በሚገቡበት የፀጥታ መዋቅር ውጤታማ መሆን ላይቻላቸው ይችላል ሲሉም መላምት የሚያስቀምጡ አሉ፡፡

እንደ ጄኔራል አበበ አተያይ ግን፣ ይህ ሥጋት እምብዛም አሳሳቢ አይደለም፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት አንዱ ችግር ሊፈጥር የሚችለው ታጣቂዎቹም ሆኑ የአገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች እኩል ቢሆኑ ነበር፡፡ ነገር ግን የኦነግ ሠራዊት ትንሽ በመሆኑና ተበታትኖ ስለሚቀላቀል ይህ ብዙም አሥጊ አይደለም ይላሉ፡፡

‹‹ተመርጠውና ተመልምለው ነው የሚገቡት፣ አዛዦችም ጭምር፡፡ ከዚያም ወደ ሥልጠና ገብተው የሠራዊቱን አሠራርና ሕገ ደንብ እንዲያውቁ ነው የሚደረጉት፡፡ ምልመላውም የሚከናወነው በሠራዊት ምልመላ መሥፈርቶች ነው፤›› ሲሉ ጄኔራል አበበ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹በነበረው የዕዝ ሰንሰለት ስለሚገቡም ይህ አያሠጋም፤›› በማለት ያክላሉ፡፡

ሌላው በሥጋትነት የሚነሳው የበጀት ጉዳይ ነው፡፡ ለእነዚህ ኃይሎች ማቋቋሚያ የሚወጣው በጀት ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችልና የአገሪቱን አቅም ሊፈትን የሚችል እንደሆነም የሚጠቁሙ አሉ፡፡

ነገር ግን ስማቸው ያልተጠቀሰው ባለሙያ፣ ‹‹ትጥቅ ፈትተው ወደ ካምፕ የገቡት አምስት ሺሕ ገደማ በመሆናቸው የበጀቱ ጉዳይ ብዙም አሳሳቢ አይደለም፡፡ እስከ ስምንት ሚሊዮን ሕዝብ በዓመት የሰብዓዊ ዕርዳታ በሚደረግበት አገር ይህ ጭማሪ ብዙም የሚባል አይደለም፤›› ይላሉ፡፡

ይልቁንስ ከበጀቱ ይልቅ በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በሚከናወነው ሥራ የቀድሞውን ተሞክሮ ማገናዘብ እንደሚስፈልግና አሁን ያለውን ሠራዊት ሞራል ማሰብ ዋነኛ ጉዳዮች እንደሆኑ ያስረዳሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -