Friday, March 24, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

መረጃው ሕዝባዊ አጀንዳ ይሁን

በወልደአማኑኤል ጉዲሶ

ከሃያ አምስት ዓመታት በፊት በአገራችን የተከሰተውን የመንግሥት ለውጥ ተከትለው ለአንባቢያን ከቀረቡና እስከ ዛሬ ህያው ሆነው ከቀጠሉ የግል ጋዜጦች መካከል ሪፖርተር  አንዱ ነው፡፡ የበርካታ አንባቢያንን የመረጃ ፍላጎት በተወሰነ መልኩም ቢሆን የሚያረካ ጋዜጣ ነው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ በጠንካራ የመረጃ ምንጭነት አሊያም በአንባቢያን ፍላጎት ተነባቢ እየሆነ ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት ከአንባቢያን ዕይታ ሳይሰወር እስከ ዛሬ ዘልቋል፡፡ እየወደቀ የተነሳባቸው ጊዜያት ሊኖሩ እንደሚችሉ ማሰብ የሚቻል ቢሆንም፣ ከሌሎች የግል ጋዜጦች በተሻለ ሁኔታ በተነባቢነቱ ቀጥሏል፤ ወደፊትም ሚዛናዊነቱን በጠበቁ መረጃዎቹ እንዲዘልቅ ምኞቴ ነው፡፡

እንደ አንድ ቋሚ የጋዜጣው አንባቢ ብቻ ሳልሆን እንደ ጋዜጠኛም ከያንዳንዱ ዕትም (መረጃ ነውና) የሚፈልገውን ርዕስ እያማረጥኩ አነባለሁ፡፡ እንዲያነቡ ለምፈልጋቸው ጓደኞቼም እስቲ ይህችን ርዕስ አንብቡና እንወያይበትም እላለሁ፡፡ በአጭሩ ከእንወያይበት አልፎ እንከራከርበት ወደሚያሰኙ ደረጃዎች የምንዘልቅበት አጋጣሚዎች እንደነበሩም ለማስታወስ ነው፡፡

ወደ ዋናው ቁምነገር ልመለስና በሁለት ብዙም ባልተራራቁ ዕትሞቻችሁ በራሴ ዕይታ ወቅታዊ ብቻ ሳይሆን አንገብጋቢ ነው ብዬ በማምነው ርዕሰ ጉዳይ ላይ አጫጭር መጣጥፎችን አስነብባችኋል፡፡ እነዚህም ርዕሰ ጉዳዮች በጋዜጣው ላይ የወጡት እሑድ ሚያዝያ 30 ቀን 2008 እና ረቡዕ ግንቦት 3 ቀን 2008 ዓ.ም. ሲሆኑ፣ ለመጀመርያው ዕትም በኢሜል አድራሻ  አስተያየት ሰጥቼ ምላሽም አግኝቻለሁና አመሰግናለሁ፡፡ በሁለተኛውና ረቡዕ ግንቦት 3 ቀን 2008 ዓ.ም. ለንባብ በበቃው  “ስለጫት የሚንጸባረቁ ጽሑፎች ንግግር የሚጋብዙ አይደሉም” በሚለው ርዕስ ላይ ግን ትንሽ ከዚያ ሰፋ ያለ አስተያየት ለአንባቢያን ማጋራት እፈልጋለሁና ከመሰላችሁ ለንባብ አብቁት፡፡

ከርዕሱ ብጀምር “ስለጫት የሚንጸባረቁ ጽሑፎች ንግግር የሚጋብዙ አይደሉም” ይላል፡፡ ከምላሽ ሰጪ አስተያየት የተቀነጨበ ርዕስ መሆኑ ባይዘነጋኝም፣ ርዕሱ አንባቢያንን ለንግግር እንዲጋብዝ (በእኔ ዕይታ ውይይት ብል ይሻለኛል) ማድረግ የማን ተልዕኮ ነው? ርዕሰ ጉዳዩን ሕዝባዊ አጀንዳ ማድረግም ከማንም በላይ የጋዜጠኛው ወይም የዝግጅት ክፍሉ መሆኑን መዘንጋት የሚገባ አይመስለኝም፡፡ አንድን ወቅታዊ አጀንዳ ለአንባቢ ጫፍ አስይዞ ብቻ ሳይሆን አስተያየት ለመስጠት ፍላጎትና አቅም ላለው ዜጋ ሁሉ በመጻፍ እንዲሳተፍ የማድረግ መብት አላችሁ፡፡ ይኼ በሕገ መንግሥትም ሆነ በፕሬስ ሕግ በግልጽ የተፈቀደ ጉዳይ ነው፡፡ ርዕሰ ጉዳዩን ሕዝባዊ አጀንዳ ማድረግ ለእናንተ ብቻ የተሰጠ ተግባር ባይሆንም፣ የሚመለከታቸው ሁሉ በጉዳዩ ዙሪያ ትኩረት ሰጥተው እንዲወያዩ ማድረግ ወይም የማድረግ ግንባር ቀደም ኃላፊነት ካለባቸው ሕትመት ሚዲያዎች እናንተም ተጠቃሾች ናችሁ፡፡

በፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ መዘጋጀቱ በተገለጸው መድረክ ላይ ከአሥራ አምስት በላይ የጫትን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚዊና ባህላዊ ተፅዕኖዎች የሚዳስሱ ርዕሶች መቅረባቸው ቢገለጽም፣ በእኔ ዕይታ ጥናታዊ ጽሑፎቹ እንደ ቀድሞው ሁሉ በመደርደሪያ እንዲቀመጡ ከማድረግ ባለፈ ፋይዳው ምን እንደሆነ አልገባኝም፡፡ አልተብራራም፣ ለተሳትፎም የሚጋብዝ አይደለም፡፡  “ወጣትና ልማት” በሚል ርዕስ ለበርካታ ጊዜያት መድረኮች መዘጋጀታቸውን የሚያመለክተው ይኸው ርዕስ በጣም አጓጊ፣ ወቅታዊና አስተማሪነቱ ገዝፎ የሚታይ ሆኖ እያለ በውስጡ የተካተቱ ጭብጦች ግን መረጃውን ወደ ኅብረተሰቡ ለማስራጨት ውሱንነቶች (ፍርሃት ወይም ሥጋት ልበል ይሆን?) የተስተዋሉበት ይመስለኛል፡፡ በሌላ አነጋገር የአምራቾችን ወይም የቃሚዎችን ትችት ገና በሩቁ አጉልቶ የተመለከተ ነው ልበል ይሆን!

ለጋዜጣው ምላሽ የሰጡት ሁለቱ ምሁራን ጫት በአገር አቀፍ ደረጃ እያደረሰ ያለውን ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ባህላዊ ቀውስ በአግባቡ ተረድተው በሚመለከታቸው አከባቢ ሁሉ ተገቢውን ተፅዕኖ ማሳደር የሚያስችል ጥናት መጀመራቸው የሚያበረታታ ሆኖ እያለ መረጃውን በበቂ ሁኔታ ለመስጠት ያሉባቸው ተግዳሮቶች ምን እንደሆኑ ከመግለጽም የተቆጠቡ ይመስለኛል፡፡ በመድረኩ በትክክልም ለወጣቶች የወደፊት ሕይወት መታሰቡም ሆነ አጀንዳው ጊዜ የማይሰጠው መሆኑ ለምን ጎልቶ አልታየም? ወጣቱ ሲባል ሁሉንም ወጣት በጅምላ ለመጨፍጨፍ ሳይሆን በውስን የማምረት ሥራና በተለይም ደግሞ በበርካታ ሁለተኛ ደረጃና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎች እኮ በቀላሉ መወጣት በማይችሉት የሥነ ልቦና ቀውስ ውስጥ ናቸው፡፡ ይኼንን እውነታ እያየንና እያስተዋልን ዝም ብለን የምናልፍ ከሆነ የጋራ ግዴታችንን ተወጣን ልንል አንችልም፡፡ ለእነዚህም ወጣቶች በወጣቶች ዙሪያ በታጠረ መድረክ ብቻ ሳይሆን አጀንዳው የሁሉም ኅብረተሰብ ሆኖ ሊደረስላቸው የሚገባ ይመስለኛል፡፡ ይኼ መረጃ ደግሞ ሊደርስላቸው የሚገባው በመድረኮች ጥናታዊ ጽሑፎችን በማዘጋጀትና ውጤቱንም በመደርደሪያዎች ሰቅሎ በማስቀመጥ ሳይሆን ከመንግሥትም ሆነ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሠራርን ፈጥኖ በመፍጠር ወደ ተግባር ሲገባ ነው፡፡

መድረክ ማዘጋጀትም ሆነ ጥናታዊ ጽሑፎችን አቅርቦ ይህንኑ መደርደሪያ ላይ ማስቀመጥ ከተጀመረ እኮ ረጅም ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ መነሻ አገሩ ኢትዮጵያ እንደሆነች በታሪክ የሚነገረውና የአገራችን ሀብት የሆነው ጫት ብዙ የዓለም አገሮችን አዳርሷል፡፡ በብዙ አገሮች ከበጎ ጎኑ በላይ አሉታዊ ጎኑ አመዝኖ  ባለመታየቱም ጫትን ካልቃሙ መንቀሳቀስ የማይችሉ ትውልዶች እንዲፈጠሩ አድርጓል፡፡ “ከራስ በላይ” እንዲሉ ከቤተሰባዊ፣ ከማኅበራዊና ከአካባቢያዊ ሕይወት ወዘተ. በላይ የራስን ሕይወት የሚያስበልጡ ዜጎች ተፈጥረዋል ማለት አያስደፍርም ይሆን?! ዘልቆ የገባበትን እንኳን ባይሆን የሚቀጥለውን ትውልድ እውነቱን ተናግረን እንታደግ ካልን ጫት ትውልድ እያበላሸ ነው ብለን መጮህ ያለብን ጊዜ አሁን መሰለኝ፡፡ ስለ ጉዳቱ ትውልዱ ራሱ ማስተዋል እንዳለበት ግንዛቤ የማስጨበጥ ጊዜው ሌላ ጊዜ ሳይሆን አሁን ይመስለኛል፡፡

የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በጫት ዙሪያ የሚቀርቡ ጽሑፎች አወዛጋቢና አከራካሪ ስለመሆናቸው ጥርጣሬ የለውም፡፡ ተክሉ ቀውስ ስለ ማድረሱ የሚስማሙ አካላት እንዳሉ ሁሉ በአዎንታዊ ጎኑ አጥብቀው ጠቃሚ ነው ብለው የሚከራከሩ ሰዎች ስለመኖራቸውም በተጨባጭ ያውቃል፡፡ በባህላዊ ዕምነትም ሆነ በሌላ የበለጠ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ወደተባሉት አካባቢዎችና ታዋቂ ግለሰቦችም ድረስ ሄዶ “ራሳቸው ቃሚዎች ስለሆኑ ከእነርሱ ምንም አትጠብቅ” ተብሎ የተመለሰበት የቅርብ ጊዜ አጋጣሚ ትዝ ይለዋል፡፡ ‹‹ወጣትና ጫት›› በሚል ርዕስ በ2007 ዓ.ም. ለንባብ ባበቃው አነስተኛ መጽሐፍ መነሻ በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎችን አገላብጧል፣ በርካታ ታዋቂ ግለሰቦችን አነጋግሯል፣ የተለያዩ ሃይማኖት አባቶችንም አማክሯል፣ የአዕምሮ ሕክምና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን መረጃ አካትቷል፣ የበርካታ ሰዎችን ትምህርታዊ ናቸው ብሎ ያመነባቸውን አባባሎች ተጠቅሟል፡፡ ምንጭ በመጥቀስም የመንግሥትን አቋም አስነብቧል፡፡ በእነዚህ ሒደቶች ሁሉ ጫት ‹‹በአዎንታዊ›› መልኩ ጎላ ብሎ የሚገለጸው የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል የሚለው ፋይዳ ነው፡፡ ቁሳዊ ሀብትና ሰብዓዊ ሀብት የማይነጣጠሉ ቢሆኑም፣ እኔ በግሌ እንደሚገባኝ ለሰብዓዊ ሀብት ቅድሚያ ሊሰጥ የሚገባ ይመስለኛል፡፡ ቁሳዊ ሀብትን የሚያመነጨው ሰብዓዊ ሀብት ይመስለኛል፡፡ ከሰብዓዊ ሀብት ደግሞ አዕምሮ ወይም ሥነ ልቦና ትልቁ ቁምነገር ነውና ይኼንን ቁመና ላለማበላሸት ትልቅና ተከታታይ ትኩረት ይሻል፡፡

ስለ ውጭ ምንዛሪ አጉልተን የምናስብ ከሆነ ሰውን የመሰለ ታላቅ ፍጡር ያለ ጫት ከዋለ መለስተኛ አብዮት ሊያስነሳ የሚችልባቸው አካባቢዎችና አገሮች ማስተዋል ወይም መጥቀስ አይቻልምን? በጫት የተነሳ ውጤታማ ሥራ መሥራት ያልተቻለባቸው አጋጣሚዎች የሉምን? አርሶ አደሩ ጫት ካልቃመ እርሻ የማይታረስባቸው አካባቢዎች አይስተዋሉም ወይ? ተማሪው በጫት ካልተነቃቃ ደብተር የማያነሳባቸው ትምህርት ቤቶች የሉምን? ቀደም ሲል እንኳን መትከልና መቃም በስም የማያውቁ ዛሬ ጉንጫቸውን አሳብጠውና ያለሥራ የጫት ሱስ ምርኮኛ ሆነው የምናያቸው ወጣቶች የሌሉበት አካባቢ የለም ብሎ መደምደም ወደሚያስችል ደረጃ እየደረስን ስለመሆኑ እየተጠራጠርን ይሆን? እነዚህን ነባራዊ ሁኔታዎች ለምን አሳንሰን እናያቸዋለን!! አሳንሰን ያየነውን ያህል ገዝፎ የሚመጣ ችግር ከፊታችን መደቀኑን ባንዘነጋ ሚናችን ከፍ ያለና የዜግነት ግዴታ እየተወጣን ስለመሆናችን ባንዘነጋስ!

ጫት የፎረሙ አጀንዳ ከሆነ አራት ዓመታት እንደሆነው የሚገልጸው የሪፖርተር ጽሑፍ መረጃዎቹ መድረክ ላይ የሚደረደሩ ጥናታዊ ጽሑፎች ሳይሆኑ ወደ ሕዝብ ወርደው የመንግሥትና የሕዝብ አጀንዳ እንዲሆኑ መጣር ይገባል ባይ ነኝ፡፡ ይኼንን ስል ያለምንም መነሻ አይደለም፡፡ በረጅም ርቀት እንሰማቸውና እናያቸው የነበሩ አደንዛዥ ዕጾች ወደ አገራችን ዘልቀው ሲገቡ በአውሮፕላን ጣቢያዎች ስለመያዛቸው በየጊዜው እየሰማን ነው፡፡ እነዚህኑ ዕጾች ተጠቃሚዎች ስለመሆናቸው የምናስተውላቸው ግለሰቦችና አካላትም በየአካባቢው እያስተዋልን ነው፡፡ እንዲያውም እንደ ሌሎች የዕጾቹ አምራች አገሮች በዶላር የናጠጡ ቱጃሮች በአገራችን ስለመኖራቸው የተሟላ መረጃ በይፋ አይውጣ እንጂ እነዚህኑ ዕጾች ማዘዋወር የዕለት ከዕለት ገቢያቸው ያደረጉ ስላለመኖራው ምን ያህል እርግጠኞች ነን፡፡ እስቲ ወደ አማኑኤል የአዕምሮ ሕሙማን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አንድ ቀን ጎራ ብለው ይቃኙ፡፡ ከብዙ መንስዔዎች መካከል ጫትና የዚህን ያህል በአገራችን ጎልቶ የማይገለጹት አደንዛዥ ዕጾች አስተዋጾአቸው ምን ያህል እንደሆነ ተረድተው ይመለሳሉ፡፡ ያኔ የችግሩ መጠን ወዴትና በምን ያህል ፍጥነት እየተጓዘ እንዳለ መረጃ ያገኛሉ ባይ ነኝ፡፡

በጋዜጣው ላይ ጫት ማኅበራዊና ሃይማኖታዊ እሴት ስለመሆኑም በቃለ ምልልሱ ተገልጿልና ከላይ የተገለጸውን አነስተኛ ጽሑፍ ሳዘጋጅ ያነጋገርኳቸው በተለይም የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ በሳል አባቶችና የሃይማኖቱ ልሂቃን የሃይማኖቱ ተጠቃሽ እሴት ስለመሆኑ በትክክል እንደማይቀበሉና በዘልማድ ባህል እየሆነ መምጣቱን አጫውተውኛል፡፡ ጽሑፉ (መንግሥት በፍጥነት ዕርምጃ ይወስዳል ተብሎ እንደማይጠበቅ ይገልጻል፡፡ እኔ ግን የተቃጠለው የተቃጠለ ቢሆንም አሁንም ሳይቃጠል በቅጠል እላለሁ፡፡ መድረኩ ራዕያችን ከሱስ የፀዳ አምራች ኅብረተሰብ ማየት ነው እያለ ይህንኑ ራዕይ ለማሳካት ቆርጦና ወስኖ የገባበት አጀንዳ ስለመሆኑ አጠራጠረኝ፡፡ ጽሑፉ እንደሚለው የሒደቱ መጀመር ብቻውን እንደ ስኬት ሊታይ አይችልም፡፡ ወደ ግብ ቆርጦ መንደርደርን ይጠይቃል፡፡ እንደዚያም ሲል በሒደት ተግዳሮቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ዘንግቼ አይደለም፡፡ አማራጭ የገቢ ምንጮችን በጥናት አስደግፎ ትልቅ የአድቮከሲ ሥራ የሚጠይቁና ወደ ኅብረተሰቡ ይዞ መቅረብን የሚጠይቅ አጀንዳ ነው፡፡ ስለሆነም መረጃው የኅብረተሰቡ አጀንዳ ይሁን፡፡ ይኼ ካልሆነ ነገ በቀላሉ ወደማንወጣት የኋልዮሽ እንራመድና መመለሻ መንገድና መውጫ መሰላል እናጣለን፡፡ እንደማናጣ ግን እርግጠኛ ነኝ፡፡ በየመን የከርሰ ምድርና ገፀ ምድር ውኃ በአብዛኛው የሚያልቀው እኮ በጫት መስኖ ውኃ ምክንያት ነው፡፡ በዓለማያ ኃይቅም ተመሳሳይ አደጋ ደርሷል፡፡ ወደ መፍትሔው ደፍረን ከገባንበት ግን  አጀንዳው የሁሉም ይሆናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

 

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles