Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊብዙዎች ያልተረዱት ሕመም

ብዙዎች ያልተረዱት ሕመም

ቀን:

በድካም የዛለ አካላቸውን ሻወር ወስደው ዘና ሊያደርጉት መታጠቢያ ክፍላቸው ገቡ፡፡ የክፍሉን በርም ቆልፈው መታጠብ ጀመሩ፡፡ አንድ ሁለቴም ሳሙና የቀቡትን ገላቸውን መለቃለቃቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ድንገት ግን ራሳቸውን ስተው ወደቁ፡፡ በሩን ዘግተውት ስለነበር ሲወድቁ ድምፅ ሰምቶ የደረሰላቸው አልነበረም፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ ራሳቸውን ቢያውቁም፣ በቀላሉ ሊነሱ አልቻሉም፡፡ አንገታቸው ዞሮ በመፀዳጃ ሲንኩ ጀርባ ገብቷል፡፡ ‹‹መተንፈስ አልቻልኩም፡፡ ለሞት የተቃረብኩ ነበር የመሰለኝ፡፡ በሩን ዘግቼ ስለነበረም ማንም ሊረዳኝ አልቻለም፡፡ እንደምንም አንገቴን አቅንቼና ከወደቁበት ተነስቼ በሩን ከፈትኩ፡፡ ልጄ በሩ ጋር  ሆኖ ሲጨነቅ ያስተዋልኩት ያኔ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሕይወቴን ሊያሳጡኝ የሚችሉ ብዙ ገጠመኞች አሉኝ፤›› በማለት ወ/ሮ እናት የእውነቱ በልጅነታቸው በተጠናወታቸው የሚጥል በሽታ ምን ያህል እንደሚሰቃዩ ይናገራሉ፡፡

ከሚጥል በሽታ ጋር አብረው መኖር ከጀመሩ 30 ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ ‹‹በሽታው ድንገት የሚነሳ በመሆኑ በጣም አደገኛ ነው፤›› የሚሉት ወይዘሮዋ፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች በመውደቃቸው በተደጋጋሚ ጊዜ ለከፍተኛ አደጋ ተጋልጠዋል፡፡ ለ14 ጊዜያት ያህልም ከባድ ቀዶ ሕክምና ማድረጋቸውን ይናገራሉ፡፡ ‹‹መንገድ  ሳቋርጥ ብዙ ጊዜ ወድቄያለሁ፡፡ በአንድ ወቅት ባህር ማዶ እያለሁም መኪና እየነዳሁ ሳለው ድንገት ራሴን ስቼ ከመኪና ጋር ተጋጭቼም ነበር፤›› ሲሉ ድንገት የሚነሳባቸው ሕመም ለሞት ሊዳርጉ ለሚችሉ አደጋዎች አጋልጧቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

የወ/ሮ እናት ገጠመኝ በርካታ የሚጥል በሽታ ያለባቸው ሕሙማኖች ገጠመኝም ነው፡፡ ሁኔታዎች እንዳሁኑ ባልተሻሻሉባቸው ዘመናት ደግሞ የሚጥል በሽታ ያለባቸው ሰዎች ዛሬ ከሚደርስባቸው በተለየ መልኩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ይገጥማቸው እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ከከርስቶስ ልደት በፊት የነበረው የንጉሥ ሐሙራቢ ሕግ በዓለም ላይ የመጀመርያው የተጻፈ ሕግ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ዓይን ያጠፋ ዓይኑ ይጥፋ በሚል መርሕ የተዘጋጀው ሕጉ አንዳንድ ፈገግ የሚያሰኙ ድንጋጌዎችን አካትቷል፡፡ ከእነዚህም መካከል የሚጥል በሽታ (ኢፕሊፕሲ) ተጠቂዎችን በተመለከተ የሰፈረው አንቀጽ አንዱ ነው፡፡

በሕጉ መሠረት አንድ የሚጥል በሽታ ያለበት ሰው ትዳር መመሥረት፣ በማንኛውም የሕግ ጉዳዮች ፍርድ ቤት ምስክር ሆኖ መቅረብ አይችልም፡፡ እንዲሁም የሚጥል በሽታ ያለበትን ባሪያ ለመግዛትና ለመሸጥ የተደረገ ውል አይፀናም፡፡

ሕጉ በዘመኑ የነበሩ የሚጥል በሽታ የነበረባቸው ሰዎች ምን ያህል ከማኅበራዊ ሕይወት እንደሚገለሉ ያሳያል፡፡ በባሪያ ንግድ አለመካተታቸውም እንደ ማንኛውም ዜጋ ሠርቶ ማደር እንደማይችሉ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው፡፡ ሕጉ የሚጥል በሽታ ያለባቸውን ሰዎች ከማንኛቸውም ማኅበራዊ ክዋኔም ያገለለ ነበር፡፡

ስለበሽታው ባለው የተዛባ አመለካከት የተነሳ በሕመምተኞቹ ላይ የሚደረገው ኢፍትሐዊ ተፅዕኖ በዛኔዋ ሜሶፖታሚያ ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ በአብዛኛው የዓለም ክፍል በስፋት የሚስተዋለው የግንዛቤ ችግር ዛሬም ድረስ ታማሚዎቹ የሰይጣን መንፈስ እንዳለባቸው ተደርጎ እንዲታሰብ አድርጓል፡፡ የነኩት ነገር ሁሉ ይረክሳል፣ እንዲሁም በሽታው በቀላሉ በትንፋሽ ይተላለፋል በሚል ሥጋት ከአምልኮ ሥፍራ እንዳይገኙ፣ ከሰዎች ጋር እንዳይቀላቀሉና እንዳይነጋገሩ ጭምር ሲወገዙም ለዘመናት ኖረዋል፡፡

በወቅቱ በሽታው ያለባቸውን ሰዎች በአስማትና በሌሎች መንፈሳዊ አገልግሎቶች ለመፈወስ የተደረገው ጥረት ከሙከራ ባለፈ ለውጥ አለማሳየቱ፣ ተመራማሪዎችን መንፈሳዊውን ሕክምና ወደ ጎን ብለው ሌላ ዓይነት ሕክምና እንዲያፈላልጉ አድርጓቸዋል፡፡

በሽታው እርኩስ መንፈስ እንዳልሆነና መዳን የሚችል የጤና ችግር መሆኑም ተረዱ፡፡ መጀመርያ ላይ ስለሕመሙ አፈጣጠርና መገለጫ ያቀረቡት መላምት ትክክለኛ ባይሆንም ታማሚዎች የእርኩስ መንፈስ ሰለባ ናቸው የሚለውን አስተሳሰብ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ለመቀየር ተችሏል፡፡ የሚደርስባቸውን ማግለልና መድሎም አርግቧል፡፡ ሆኖም የሚጥል ሕመም ያለበት ልጅ ያላቸው ሰዎች አጋጣሚውን እንደውርደትና እንደእግዜር ቁጣ በመቁጠር ጉዳዩን በሚስጥር መያዝ ይመርጡ ነበር፡፡ ሕመሙ ያለባቸው ልጆችም ከሌላው የቤተሰቡ አካል ተነጥለው ራቅ ባሉ ስፍራዎች ተደብቀው እንዲቆዩ ይደረጋል፡፡ በዩናይትድ ኪንግደሙ ንጉሥ ጆርጅ አምስተኛ ልጅ በሆነው ልዑል ጆን የደረሰው መገለልም በወቅቱ የነበረውን የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ያንፀባርቃል፡፡

ለቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ የነበረው ልዑል ጆን የሚጥል በሽታ የጀመረው ገና በለጋነቱ ነበር፡፡ ከንጉሡ ልጆች መካከል በጨዋነቱና በቀልጣፋነቱ የሚታወቀው ጆን፣ በአንድ ወቅት ያልተለመዱ ነገሮችን ማሳየት ጀመረ፡፡ ድንገት ተነስቶ ይንቀጠቀጣል ወዲያውም ራሱን ስቶ ይወድቃል፡፡ በሁኔታው የተደናገጡት ቤተሰቦቹ አስፈላጊውን እንክብካቤ አላደረጉለትም፣ ወደ ሕክምናም አልወሰዱትም፡፡ በሕዝቡ ዘንድ የገቡትን ማንነት እንዳያጎድፉ በሚል ነገሩን በሚስጥር በመያዝ ጆንን ከቤተሰቡ ነጥለው ራቅ ወዳለ አካባቢ እንዲኖር አደረጉት፡፡ ልዑሉ በዚህ ሁኔታ ጥቂት ዓመታት ከቆየ በኋላ ሕይወቱ አለፈ፡፡

በሽታው ትክክለኛው መድኃኒት እስኪገኝለት ድረስ በርካቶች በዚህ መልኩ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ነገሮች መልካቸውን ቀይረዋል፡፡ በሽታውን በመድኃኒት መቆጠጠርና መፈወስ ተችሏል፡፡ ታማሚዎችን የማግለል ሁኔታው በተለይ ባደጉትና በሠለጠኑት አገሮች እየቀረ ነው፡፡ ብዙዎቹ ታማሚዎችም ሕክምናቸውን እየተከታተሉ ከማኅበረሰቡ ተቀላቅለው እየሠሩና እየኖሩም ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያም ሕመሙን በሕክምና የሚቆጣጠሩ ሕክምና ቢኖርም፣ ኅብረተሰቡ ካለው የግንዛቤ ችግር ጋር ተያይዞ ሕሙማን በሕክምና በቅጡ መድረስ አልተቻለም፡፡ ለውጥ ቢኖርም አዲስ አበባን ጨምሮ በአገሪቱ በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች አሁንም ችግሮቹ በስፋት ይስተዋላሉ፡፡

ወ/ሮ እናት በተዘዋወሩባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ያልተገቡ ድርጊቶች ሲፈጸሙ አስተውለዋል፡፡ በአንድ የአገሪቱ ገጠራማ አካባቢ ነው፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ስለሚጥል በሽታ ያላቸው ግንዛቤ ጥንት ከነበረው የተለየ አይደለም፡፡ በሽታው ከሰው ወደ ሰው እንደሚተላለፍና ሕመምተኞቹም እርኩስ መንፈስ የተጠናወታቸው ተደርገው ይታሰባሉ፡፡ የሚጥል ሕመም ያለባቸው ሰዎች ከሌላው ተለይተው በአንድ ጨለማ ክፍል ውስጥ እንዲኖሩ ይደረጋል፡፡ ከሌላው ሰው ጋር መቀላቀልም ሆነ መነጋገር የማይታሰብ ነው፡፡ ምግብን ጨምሮ ሌሎች የሚያስፈልጋቸው ነገሮች በተዘጋጀ ትንሽ ቀዳዳ ይወረውሩላቸዋል፡፡ መፀዳጃ ቤት መሄድ የሚፈቀድላቸው ሌሊት ሰው ሳያያቸው መሆን አለበት፡፡ ቀርቦ የሚያናግራቸው የለም፡፡ ሁሉም በሩቁ ይሸሻቸዋል፡፡ አደገኛ አወዳደቅ እየወደቁ ለከፋ ችግር ይዳረጋሉ፡፡

ካለው የግንዛቤ ችግር የተነሳ፣ ሕመሙ ከአምልኮ ጋር የተያየዘ እንደሆነና ከሰው ሰው በትንፋሽና በንክኪ እንደሚተላለፍ የሚያምኑም አሉ፡፡ አንድ ሰው ድንገት መንገድ ላይ ወድቆ አረፋ ሲደፍቀውና ሲያንቀጠቅጠው ሲያዩ የሚሄዱበትን መንገድ የሚቀይሩ ማየቱም የተለመደ ነው፡፡ አንዳንዶች የወደቁትን ለመርዳት በማሰብ ክብሪት ለኩሰው ከወደቀው ሰው አፍንጫ በማስጠጋትና ጭሱን በማሽተት ከወደቀበት እንዲነሳ ለማድረግ ሲጥሩ ይስተዋላል፡፡ አንዳንድ ቤተሰቦች ደግሞ የሚጥል በሽታ ያለበት ልጃቸውን በር ዘግተው ያስቀምጣሉ፡፡  

ጥቂት የማይባሉ በጉልበት ሥራ ላይ ሳሉ ድንገት በሚያጋጥማቸው ሕመም ጉድጓድ ውስጥ ወድቀው፣ ከሕንፃው ተወርውረው ሕይወታቸውን የሚያጡ፣ ምግብ በሚያበስሉበት እሳት ላይ ወድቀው ለቃጠሎ የተዳረጉ እናቶችም አሉ፡፡ ችግሩን የከፋ የሚያደርገው ደግሞ ሕመምተኞች የሚደርስላቸው ሳይኖር እሳትና ሌሎች አደገኛ ነገሮች ላይ  ወድቀው ለከባድ ቃጠሎና ለአካል ጉዳት ብሎም ለሞት መዳረጋቸው ነው፡፡ የሰዎች ዕርዳታ የሚያገኙትም ቢሆኑ የሚደረግላቸው ዕርዳታ በዕውቀት ላይ ያልተመሠረተ በመሆኑ ከጉዳት አያመልጡም፡፡  

ልጃቸውን ወደ ሕክምና ወስደው፣ ለቁም ነገር ያበቁም አሉ፡፡ መድኃኒታቸውን በአግባቡ እየወሰዱ ትምህርታቸውን ጨርሰው በተለያዩ የሥራ መስኮች የተሰማሩ፣ ትዳር መሥርተው ቤተሰብ ያፈሩም ይገኛሉ፡፡

የ33 ዓመቷ ወይዘሪት መንበረ ጌራወርቅ የሚጥል በሽታ እንዳለባት የታወቀው በሰባት ዓመቷ ነበር፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ራሷን ስታ የወደቀችውም ጥርሷን ስትነቅል ነበር፡፡ ሁኔታውን ከጥርሷ መነቀል ሕመም ጋር ያያዙት ወላጆቿም ከወደቀችበት አንስተው አልጋ ላይ እንድትተኛ አደረጓት እንጂ ለሕክምና ወደ ሆስፒታል አልወሰዷትም፡፡ ከዚያ በኋላ ግን በየተወሰነ ጊዜ ይጥላት ጀመር፡፡

‹‹ብዙ ጊዜ ምሽት ላይ ነው የሚጀምረኝ የምትለው፤›› መንበረ፣ ከቤት ውጭ ሆና አሟት እንደማያውቅ ትናገራለች፡፡ ይህም አደገኛ ቦታ ላይ ወድቃ ለጉዳት እንዳትዳረግ ረድቷታል፡፡ ሕክምና መከታተል ከጀመረች 15 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ተገቢውን ሕክምና ከማግኘቷ በፊት ግን ብዙ ተቸግራ ነበር፡፡

‹‹ልጅ ሆኜ ለሕክምና ወደ አንድ ሆስፒታል ሄጄ ነበር፡፡ የመረመረኝ ዶክተር የሰጠኝ መድኃኒት ለዕጢ የሚሆን ነበር፡፡ መድኃኒቱንም ለሁለት ዓመታት ወሰድኩኝ፡፡ ነገር ግን ሕመሙ በመቀነስ ፈንታ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲደጋገምብኝ አደረገ፡፡ ከዚያም ሌላ ባለሙያ ዓይቶኝ ሕመሜ የሚጥል በሽታ መሆኑን ነገረኝ፡፡ መድኃኒትም አዘዘልኝ፤ ብዙ መሻሻሎችም አሳየሁ፤›› ስትል ተገቢውን ሕክምና ለማግኘት ያለውን ውጣ ውረድ ታስታውሳለች፡፡ የታዘዘላት መድኃኒትም ቢሆን ዋጋው በእሷ አቅም የማይቻል ነው፡፡ አገር ውስጥ ስለማይገኝም በየጊዜው 100 ዶላር እየተከፈለ የሚመጣላት ከባህር ማዶ እንደሆነና ገንዘቡን የሚከፍሉትም ወላጆቿና እህቶቿ መሆናቸውን ትናገራለች፡፡

ሕመሙ ያለባቸው ሰዎች ራሳቸውን ስተው በሚወድቁበት ወቅት ሰዎች የተለያዩ ነገሮች ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ ብዙ ጊዜም ከስቃዩ ለመገላገል በሚል ሐሳብ ወደ አፍንጫቸው አስጠግተው ክብሪት ሲጭሩ ይታያል፡፡ ነገር ግን ይህ ታማሚውን ከመርዳት ይልቅ በውስጡ የሚገኘውን ጥቂት ኦክስጅን እንዲያልቅና ሕይወቱን እንዲያጣ የሚያደርግ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ አንዳንድ ሰዎች ሕመሙ ሲጀምራቸው ምላሳቸውን ይነክሳሉ፡፡ በዙሪያቸው የሚገኙ ሰዎችም ከስቃይ እንደሚገላግሏቸው ምላሳቸውን ለማላቀቅ ይሞክራሉ፡፡ ይህንንም ለማድረግም ኃይል ይጠቀማሉ፡፡ ይኽም በሕመምተኛው ላይ ተጨማሪ ጉዳት ያደርሳል ሲሉ የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

መንበረ በምትወድቅበት ጊዜ ምላሷን ትነክሳለች፡፡ ሁኔታዋ የሚያሳዝናቸው ወላጅ እናቷ በተቻላቸው ሁሉ ሊረዷት ይሞክራሉ፡፡ ብዙ ጊዜም ምላሷን ለማላቀቅ ይጥራሉ፡፡ በቀላሉ ስለማይሳካላቸውም ኃይል ይጠቀማሉ፡፡ አፏ ውስጥ ማንኪያ በማስገባት ጥርሷን ለማላቀቅ ይታገላሉ፡፡ መንበረ ራሷን ስታ ከተኛችበት ስትነቃ ጥርሷን ለማላቀቅ የተደረገው ሙከራ ሌላ ሕመም ይሆንባታል፡፡ ይህም ምግብ ከመመገብ፣ ከማውራት ያግዳታል፡፡ ሕመሙም ከሳምንት ለበለጠ ጊዜ ሊቆይባት ይችላል፡፡

የሚጥል በሽታ በተለያዩ ምክንያቶች ይከሰታል፡፡ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ የሚፈጠርም አለ፡፡ በሕፃናት ላይ የሚፈጠረው በወሊድ ጊዜ በመታፈን፣ ጭንቅላታቸው ላይ በሚደርስ ጉዳት ነው፡፡ አልፎ አልፎ በማሕፀን ውስጥ እንዳሉ በሚጥል በሽታ የሚጠቁም አሉ፡፡ በአዋቂዎች ላይ ደግሞ በተለያዩ ኢንፌክሽኖች በማጅራት ገትር፣ በተለያዩ አደጋዎች፣ በመውደቅ፣ ጭንቅላት ላይ በመመታት ይከሰታሉ፡፡

ዕድሜ እየገፋ በሚሄድበት ጊዜ በተለይ ደግሞ ከአንጎል የሚነሳ የካንሰር ሕመም ለሚጥል በሽታ መንስኤ ይሆናል፡፡ ስትሮክ፣ ስኳርና ደም ግፊትም ይጠቀሳሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ሳይንስ መምህር እንዲሁም የነርቭና የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስቱ ዶ/ር አብነት ታፈሰ እንደሚሉት፣ በሽታው በሁለት ይከፈላል፡፡ የመጀመርያው ሁለቱንም የአንጎል ክፍል እንቅስቃሴ በማዛባት ራስን አስቶ የሚጥል እና የማይጥል፣ ነገር ግን ራስንና አካባቢን ለማወቅ የሚያዳግት ሁኔታ ውስጥ የሚከተው ነው፡፡ ሌላው በአንዱ የአንጎል ክፍል ችግር በማድረስ የተዛባ ስሜቶች የሚፈጥረው ነው፡፡ ታማሚው የራሱ ያልሆኑ ነገሮች የራሱ እንደሆኑ አድርጎ እንዲሰማው፣ የተለዩ ሕልሞች እንዲያይ፣ የሚያውቃቸውን ነገሮች እንዲረሳና ግራ እንዲጋባ የማድረግና ሌሎች የስሜት ለውጦች የሚያስከትለው ነው፡፡

‹‹ኤፕሊፕሲ ስሙ አንድ ይሁን እንጂ የተለያዩ የአንጎል ክፍሎችን የሚያውኩ ችግሮች መጠሪያ ነው፡፡ በማበረሰቡ ዘንድ የሚታወቀው ራስን አስቶ የሚጥለው ነው፡፡ ነገር ግን ራስን ስቶ መውደቅና መንቀጥቀጥ ከዚያ ውስጥ አንዱ ነው፤›› የሚሉት ዶ/ር አብነት፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ስለሕመሙ ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆን ሕመሙን ከባድ እንዳደረገው ይናገራሉ፡፡

‹‹ብዙዎቹ ሰይጣን ነው፣ ልክፍት ነው፣ መድኃኒት ተደርጎበት ነው፡፡ ስለሚሉ ወደ ሕክምና መስጫ ቦታ አይሄዱም ይህም በሽታው ሕክምና ሳያገኝ እንዲጠነክር ያደርገዋል፤›› ይላሉ፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ በአገሪቱ ውስጥ ለበሽታው የሚያስፈልጉ ሁሉም ዓይነት መድኃኒቶች ባይኖሩም የተወሰኑት ግን አሉ፡፡ ሕክምናውን መስጠት የሚችሉ በቂ ባለሙያዎችም ይገኛሉ፡፡ የተሻለ ሕክምና መስጠት እንዲችሉም ለሕክምና ባለሙያዎች ወደፊት ሥልጠና ለመስጠት መታቀዱን ዶክተሩ ይናገራሉ፡፡

ይሁንና ባለው የግንዛቤ ችግር በሽታው በሕክምና እንደሚድን የሚያውቁ ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡ በአገሪቱ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ታማሚዎች እንዳሉ ይነገራል፡፡ ከነዚህ ውስጥ 95 በመቶ የሚሆኑት ወደ ሕክምና መስጫ ቦታዎች አይሄዱም፡፡ ሕክምናውን ለማግኘት ከሚጥሩ ጥቂቶቹ መካከልም የመድኃኒቱ ተደራሽነት እምብዛም በመሆኑ እንደ መንበረ ያሉ ብዙዎች ይቸገራሉ፡፡

የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በመሥራት ሕሙማን ወደ ሕክምና መስጫ ቦታዎች እንዲሄዱ ለማድረግ የሚሠራው ኬር ኤፕሊፕሲ የተባለው ተቋም ከወዲሁ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡ የድርጅቱ መሥራች ወ/ሮ እናት ሲሆኑ፣ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሕመሙ ዙሪያ ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ ያተኮረ የእግር ጉዞ አዘጋጅተው ነበር፡፡

‹‹ኬር ኤፕሊፕስ የተቋቋመው በአገሪቱ ለሚገኙ አንድ ሚሊዮን ለሚሆኑ ታማሚዎች ድምፅ ለመሆን ነው፤›› የሚሉት ወይዘሮዋ፣ ተመሳሳይ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ስለበሽታው ያለውን ብዥታ ለማጥራትና ብዙዎች ሕክምና እንዲያገኙ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

በፕሮግራሙ ከተገኙት እንግዶች መካከል የጤና ጥበቃ ሚኒስትር የሚንስትሩ አማካሪ ዶ/ር ተድላ ወልደ ጊዮርጊስ ይገኙበታል፡፡ ሕክምናውን ተደራሽ ከማድረግ አንፃር መንግሥት በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ሪፖርተር አነጋግሯቸው ነበር፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ሕክምናውን ከአዕምሮ ሕክምና ጋር እንዲካተት በማድረግ፣ በየክልሉ በሚገኙ በ160 የሕክምና ቦታዎች ሕክምናው መስጠት ተጀምሯል፡፡ በየሕክምና መስጫ ቦታው የሚገኙ ባለሙያዎችም ሕክምናውን ለመስጠት የሚያስችላቸውን ሥልጠና አግኝተዋል፡፡ እንዲሁም መድኃኒቱ ሳይቋረጥ በየተቋማቱ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ ነገር ግን አሁንም ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች አሉ፡፡ በሕመሙ ዙሪያ ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆን ችግሩን ውስብስብ አድርጎታል፡፡ ለዚህም በቂ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ሊሠሩ ይገባል፡፡ ‹‹ለወደፊትም በትምህርት ውስጥ ተካትቶ ተማሪዎች ግንዛቤ እንዲያገኙ ማስቻል ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...