ሰላም ሰላም! ማንጠግቦሽ መቼ እለት፣ ለ25 ዓመታት ሳትጥል ያስቀመጠቻትን ቅል አውጥታ (ቅሏ ተሰብሮ ኖሮ) ያኖሩት እንቅርት ያገለግላል ይሉሃል ይኼ ነው ብላ ተረተች። እኔ ደግሞ ቅሉ ትቼ እንቅርቱ ገረመኝ። እንቅርትን ማኖር ብሎ ነገር አልገባኝ አለ። ኋላ ባሻዬ ዘንድ ሄጄ እንዴት ያለ ተረት ነው ብላቸው ልጃቸው ቀበል አርጎ በእርቅርት ፈንታ ሌባ ተካበት አለኝ። ስተካው ያኖሩት ሌባ ያገለግላል መጣ። ሌባ ተይዞ ዱላ ጥየቃ ቀርቶ እኮ ሌባን አውሎ ማሳደር ከመቼ ወዲህ እለዋለሁ ከ25 ዓመት ወዲህ አይለኝ መሳለችሁ። ምን አለበት እኔስ ዝም ብል? እሱ የሚከተለውን ሲብራራ ባሻዬ በእኔ አኳኋን ይስቃሉ። እነሆ አገራችን በሦስት ሺሕ ዘመን ያላማጠችውን ካፒታል በምን ተዓምር አምጣ ይመስልሃል በ2015 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ ያሰበችው? ቢለኝ ጭራሽ ዞረብኝ። በሌባ ነው እንዳትለኝ ስለው እነሱም አላላሉም እኔም አልልህም። ግን አካሄዱንና አይተህ አጨራረሱን ስትተነብዬው እንዲያ ነው። አዳሜ ዛሬ አገኘሁ ብሎ በሚሊዮን ሲጫወት ሳይታሰብ፣ የካፒታል አኩሚሌሽን ፅዋ ሲሞላ የታየው እንዳልታየ የነበረው እንዳልነበር ይደረጋል። ሲለኝ ከአንጀቴ ባላምነውም አየር በአየር ለሚጫወቱ ሚሊየነሮች አዘንኩ። እናማ የማንጠግቦሽ ቅልን በተመለከተ የተተረተው የእንቅርት ተረት እንደባሻዬ ልጅ ባሉ ምሁራን ከእንቅርት የዘለለ ነው። ግን እላያችን ላይ ያለ ዕውቀት የሚዘል የሚፈነጨው የበዛው ለምንድነው? ብሎ ለጠየቀ መልሱ ያኖሩት እንቅርት ያገለግላል ነው እሺ። ሁሉም ፅዋው የሚሞላበት ቀን አለ ማለት ነው። ብቻ የደጉም እንባ፣ የክፉውም የግፍ ፅዋ ዋንጫ ሳይሞላ ቀን እንዳይጨልም ወጥሮ መፀለይ ነው። ፀሎት እንደማይወጠር ባውቅም ቃሉን የተጠቀምኩት አገር እንደቆዳ የምትወጠርበት ቀን ስላለ ነው እሺ። ደግሞ አምበርብርም ቃና ላይ አፍጦ እየዋለ አማረኛን መተርጎም ጀመረ እንዳትሉኝ!
በነገራችን ቅድም እንቅርት ስል እንኳን እንቅርት ቅማል ምንድነው ብሎ የጠየቀኝ የዘመኑ ልጅ ስላለ እንቅርትን በተመለከተ ንግግር አዘጋጅቻለሁ። ይኼን ዕድል ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ ብዬ ንግግሬን እንደሚከተለው እጀምራለሁ። መቼም አገሩ የንግግር ነው። ክርክር፣ ንትርክ፣ ምንአባክ ምንአባሽ፣ ውይይት (ውይይት እንኳን፣ እንኳን ባህሉ ታክሲውም ሙዚየም የለም) ግምገማ ወዘተ ንግግር ላይ የተሰኩ ቅርጫፎች ናቸው። እንደሚታወቀው በቀናነት ለአገር ልማትና ዕድገት ሊጠቀሙባቸው የደፈሩ አሁን እንጃ መኖራቸውን። እኔ ታሰሩ ተገደሉ አላልኩም አደራ። በቅፅልና በፈጠራ ሃሜት ከቤት እንዳይወጡ ማድረግ የሚያስችል የንግግር (የወሬም ብትሉት ያስኬዳል) ባህል እያለን ምንስ እስርና ሌላ ሌላ ያስፈልጋል። አንዱ በቀደም አንዱን እየጠቆመ እሱ እኮ እንትን ነው አለ። በኋላ ሳጣራ ለካ በኮሚሽን ተጣልቶት ነው። ይኼው አሁን ኧረ ባክህ አትለኝም? እየተባለ እንትን ነው የተባለው እንትና የሚባል ሰውዬ ወጥቶ መግባት አልቻለም። ኦ ለካ ንግግር እያደረኩ ነው። ግን ለምን ነበር ንግግር ማድረግ የፈለኩት? ከመሪ ሐሳብ ማፈንገጥ እንደሆነ በእኔ አልተጀመረም። እንዴ አህያውን ትቶ ዳውላውን እኮ ያሳደገን ነው ምን ነካችሁ። እና አሁንም ንግግሬን በትግስት እያዳመጣችሁ ስለሆነ አመሰግናለሁ። እንግዲህ ለዘመኑ ልጅ ስለእንቅርት ለማብራራት ነበር አይደል? የአሁኑን ባላውቅም በእኛ ጊዜ እንቅርት የሚከሰተው በአዮዲን እጥረት ምክንያት ነው በሚል ተምረን ነበር። ዛሬ በምን እጥረት እንደሚመጣ እንጃ? ግን የሚገርመኝ ሌላ ሌላው አሳሳቢ ነገር ሁሉ ሞልቶ የተረፈልን ይመስል እንቅርትን ነጥለው ምንጩ የአዮዲን እጥረት ነው ብለው ያስተማሩን አስተማሪዎች አይገርሟችሁም? ተው እበጥ ተው እበጥ፤ ተው እበጥ አንት ሆዴ፣ ጥጋብ መሰለህ ወይ ካንገቴ ማበጤ አለ በአዮዲንም በምግብም እጥረት ጥጋብ ያጠረው ሰው!
እናላችሁ እኔ ደግሞ ሰሞኑን ቻፓ አጠረኝ። በነገራችን ይኼ ጨዋታዬ የንግግሬ አካል አይደለም። ንግግሬ ተቋርጧል። ለምን ተቋረጠ? አላችሁኝ? አሁን እስኪ እዚህ አገር ምን የማይቋረጥ፣ የማይቆራረጥ፣ ተጀምሮ የሚያልቅ ነገር አይታችሁ ነው እንዲህ የምትሉኝ። እኛ ራሳችን እኮ ለውዷ አገራችን የተቋረጡ የተቆራረጡና የሚቆራረጡ በሚል ሦስት ረድፍ የተከፋፈልን ተቆራራጭ ህያው ድርሰቶች ነን። ፓ! ለዚህ አባባሌ መቼም አንድ ሞቅ ያለ ጭጨባ ከስፖንሰርሺፕ ከተገኘ ሃያ ሺ ብር ጋር መገጨት ነበረብኝ። ችግሩ እኮ በላቡ የሚያምን እዛም እዚህም ቢጋጭ አይገጨውም። የሚገጨው ያው ጎዳናውን ያጨናነቁ ታፔላዎች እንደሚነግሯችሁ ፓስወርዱ የገባ ነው። ማን ነበር ሕይወትን እግዜር እንጂ ማይክሮሶፍት እንደፈለሰፈው መቼ አወኩ ብሎ ሲያስቀኝ የዋለው? እውነቱን ነዋ። ፓስወርድ፣ ፓስወርድ ፓስወርድ ይሏችኋል። እኛ ደግሞ አለን እንኳን ፕሮሰሰሩን ፕሮሰስ ለማድረግ አክሰስ ኪይ ልንፈልግ ቴሌቪዥናችንን ማጥፋትና ማብራት በቅጡ አውቀን አልጨረስንም። ዋ ብሎ መቅረት ነው ዘመድ እንዳረዱት አለኝ አንድ ወዳጄ በቀደም መኪናውን አየር በአየር አይኑ እያየ ስልሳ ሺሕ ብር አትርፈው ገዝተው ሲሸጡበት አይቶ። ይኼ መሰለኝ አንደኛው ፓስወርድ። ወደን መሰላችሁ እንዴ መሸት ሲል አዝማሪ ቤት የምንሰባሰበው? አየር በአየር ገንዘብ መቀባበል ቢያቅተን ግጥም ለመቀባበል እኮ ነው። ታዲያስ?! ወደን መሰላችሁ ዘፈኑ፣ ፊልሙ፣ ክላሲካሉ ማታ ማታ እያለ ሲያደርቀን አብረን ሆ የምንለው? ለእነኛ ሳይመሽ ሲነጋ ለእኛ ጨለሞ እየጨለመ ብንቸገር እኮ ነው! ተውኝ ዘንድሮስ!
ታዲያ እንደለመድኩት መርካቶ አካባቢ መቶ ሰላሳ ካሬ መሬት ከእነቤቱ ላሸጥ መንደፋደፍ ያዝኩ። ሻጯ ትልቅ ሴትዮ ናቸው። ገዢዎቹ ደግሞ ከ25 እስከ 28 የሚገመቱ ወጣቶች ናቸው። ሴትዮዋ ሦስት ሚሊዮን ካገኘሁ ይበቃኛል አሉ። ወጣቶቹ በአንድ አፍ ብለው የሚይዙት የሚጨብጡት አጡ። ለካስ በጎን ሰባት ሚሊዮን ብር ሊሸጡት እየተደራዱ ነው። እኔ ይኼን የማውቀው ኋላ ነው። ኋላ ድረስ ምን ወሰደህ ብትሉኝ ኪራይ ሰብሳቢነት እላችኋለሁ። የሆነው እንዲህ ነው። ሴትዮዋ ቦታውና ቤቱን የግል ንብረታቸው መሆኑን የሚያረጋግጥላቸው ሰነድ ጠፋባቸው። እሱን ለማስወጣት ወዲያ ወዲህ ሲሉ አሳዝነውኝ አብሬያቸው ከአንዱ ቢሮ አንዱ መውጣት መግባት ሆነ ሥራዬ። ይገርማችኋል ቢያንስ ዕድሜያቸውን አይቶ የሚራራ ጠፋ። ጭራሽ አንዱ ኑ ብሎ ሰወር ያለ ቦታ ወሰደና አንድ አሥራ አምስት ሺሕ ብር ይስጡኝ እኔ አሁን እጨርስልዎታለሁ ብሏቸው አረፈው። እዚያ በቁማቸው እንደፈረንጅ አገር በረዶ በእርጋታ ተንሳፈው ተቀመጡ። አልደድር አልሟሟ ብለው ተክዘው ቆዩ። ምነው? አመሞዎት ስላቸው እንዲህ ነው እንዲያ ነው ሳይሉ እንባቸው እንደ በአምስት ቁጥር ኳስ ስፋት ተድቦልቡሎ ዱብ ዱብ እያለ አይ አገር፣ እውነት ይኼ አገር ነው? እውነቴ እዚህ ነው ተወልጄ ያደኩት? እውነት እዚህ አፈር ላይ ቆማ ነው እቴቴ ጡቷን ያጠባችኝ? ብለው ኸኸኸ ብለው ተንሰቅስቀው አለቀሱ። እሳቸውን እያረጋጋሁ የእንቅርቱ ተረት ትዝ አለኝ። ይኼም አንዱ እንቅርት ይሆን? ብዬ እኔም ሳልሟሟ ሳልደድር ባለሁበት ቀረሁ። እኔ ምለው፣ እናት አባት ቢሞት ባገር ይለቀሳል፣ እህት ወንድም ቢሞት ባገር ይለቀሳል፣ አገር የሞተ እለት ወዴት ይደረሳል ብለን ዘንድሮም ሳናለቅስ እናለቅስ ይሆን? ነው የእናት የአባቶቻችን እንባ እንባችን ሆኖ አብረን ለአገር ማልቀስ እንጀምራለን? ለነገሩ የመጀመር ጣጣ የለብን እኛ!
ወደ መሰነባበቻችን ነን። የሆዴን በሆዴ ይዤ በኪሴ የምይዘውን ልይዝ ከነገርኳችሁ ደንበኛዬ ጋር የጀመርኩትን ጨራረስኩ። ኋላ መሸት ሲል ወደተለመደችዋ ግሮሰሪ ጎራ ብለን እኔና የባሻዬ ልጅ ጨዋታ ያዝን። በመሃል አንድ አዝማሪ መጣ። ተቀበል ሳይባል ያቀባብለን ጀመር። ከመሃላችን ያልጠበቅነው ሰው ጉድ ያስባለ ግጥም አስገጠመ። ጠጋ ብዬ እንዴት ነው ነገሩ ስለው ሙያው ሐኪም እንደሆነ አጫወተኝ። ሥጋም መንፈስም መፈወስ ትችልበታለህሳ ስለው ወድጄ አይምሰልህ ብሎ የቤቱን የትዳሩን ጣጣ ያጫውተኝ ያዘ። የማመሸው የምጠጣው ወድጄ እንዳይመስልህ። ተጠንቅቃ ታጥቃ ለመጨቃጨቅ የተፈጠረች ሚስት ስላገባሁ ነው ብሎ አይኖቹ እንባ አቀረሩ። ለባሻዬ ቀስ ብዬ የሰውዬውን ታሪክ ሳጫውተው እንኳንም ሐኪም አላረገኝ ብሎ ዝም አለ። ላያስችል አይሰጥም የሚባለውን ገልብጨ እኔ በሰውዬው ቦታ ብሆን አብድ እንደነበር ሳስብ ሊያሳብድ አይሰጥም ብዬ ሐኪም ባለመሆኔ ኮራሁ። እኔ የምለው ለፈውስ ተጠርተን የሰው ሰው ስንፈውስ እየዋልን ምነው ግን የራሳችንን ችግርና ጣጣ መፈወስ የተሳነን በዛን ጎበዝ? ለራሳችን ሳንሆን ለሌላው እየኖርን ለሌላው እያደርን እስከመቼ በመጠጥ ተደብቀን እንዘልቀዋለን ትላላችሁ? ፈውስ ከራስ ይጀምራል ብለን እንለያይ? ይመቻችሁ!