ብራዚል በሪዮ ከተማ የምታስተናግደው የሪዮ ኦሊምፒክ ውድድር በብራዚልም በኢትዮጵያም የየራሳቸውን ትኩሳት አስነስተዋል፡፡ ብራዚል ከፖለቲካው ባሻገር ያጠላባት የዚካ ቫይረስ በኦሊምፒክ ዝግጅቱ ላይ ጽልመትን አሳድሯል፡፡ ይህንኑ ተከትሎም አንሳተፍም የሚሉ አገሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ሥጋት ተፈጥሯል፡፡ ከ10,000 በላይ ስፖርተኞች ግን ለሪዮ ኦሊምፒክ ይጠበቃሉ፡፡ በአንፃሩ ከኢትዮጵያ የሚወጡ ጽንፍ የያዙ አቋሞች በአንድ በኩል ወቅታዊ አቋም በሌላ በኩል ደግሞ ዕውቅናን ከብቃት ጋር መነሻ ያደረጉ ናቸው፡፡
አንጋፋዎቹ አትሌቶች ብቃቱም ብርታቱም ስላለን መሳተፍ አለብን የሚለውን አቋማቸውን አጠናክረዋል፡፡ ፌዴሬሽኑ በበኩሉ በምከተለው አሠራርና መስፈርት ያሟሉትን መርጫለሁ ሲል ይከራከራል፡፡ ጎራ በለየው እንኪያ ስላንቲያ ጥቂት ሳምንታት የቀሩት የሪዮ ኦሊምፒክ ውድድር ላይ እየተካሄደ ስላለው ዝግጅትና እንቅስቃሴ ጆሮ የተሰጠው አይመስልም፡፡ ሁለቱም ወገኖች አገሪቱ ከፊት ለፊቷ ለሚጠብቃት የሪዮ ኦሊምፒክ ተሳትፎ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው የሚናገሩ በርካቶች ናቸው፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ለውድድሩ እየተደረገ ስላለው ዝግጅት ከመስማማት ይልቅ ጥቂት ጊዜ በቀረው ውድድር ላይ የሚደመጠው የሽኩቻ ሞገድ እያየለ መምጣቱ የአደባባይ ሚስጥር ሆኗል፡፡
እንደ አገርና ሕዝብ አትሌቲክሱ ትርጉም ኖሮት እንዲቀጥል ሁለቱን አካላት የሚያስማማ አቋም ያለም አይመስልም፡፡ ይህም ሆኖ አሁን ተፈጥረዋል ወይም ደግሞ እየተፈጠሩ ነው ስለተባሉት ችግሮች መፍትሔ ከተሰጠ መልካም፣ ካልሆነ ግን በይደር አቆይቶ ከሪዮ መልስ መነታረክና መወቃቀስ እንደሚሻል የሚማፀኑም አልጠፉም፡፡
ኦሊምፒክን በመሰሉ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ‹‹ለአንድ ለእናቱ›› የሆነው አትሌቲክስ መሆኑ የሚካድ ቀርቶ ለአፍታም ተከራካሪ እንደማይኖር ይታወቃል፡፡ ከሰሞኑ የተፈጠረውን እሰጥ አገባ የሚያደምጡና የሚከታተሉም ይህንኑ እውነታ በመረዳት ይመስላል የሚመለከተው አካል ለጉዳዩ የመፍትሔ አቅጣጫ ሊያስቀምጥለት ይገባል ሲሉ የሚማፀኑት፡፡
የሪዮ ኦሊምፒክ በወራት ሳይሆን በሳምንታት የሚቆጠር ዕድሜ በቀረበት በአሁኑ ወቅት አትሌቲክሱን በበላይነት በሚያስተዳድረው አካልና አሁን በመሮጥ ላይ የሚገኙና በቀድሞዎቹ አትሌቶች መካከል ከፍተኛ የሆነ አለመጣጣም እንዳለ ይስተዋላል፡፡ ሁለቱም አካላት ስፖርቱን በሚመለከት በየፊናቸው ማለት ያለባቸውን እያሉ ናቸው፡፡ በኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ ገብረ እግዚአብሔር ገብረማርያምና በሌሎችም የቀድሞ አትሌቶች የሚመራው አካል በወቅታዊ የአትሌቲክስ ሁኔታና የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጉዳይ ላይ ግንቦት 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም በተጠራው የምክክር መድረክ አቋሙን ይፋ አድርጓል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በበኩሉ፣ ሰኔ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በብሔራዊ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በሁለቱ አካላት መካከል ለተፈጠረው አለመግባባት በምክንያትነት የሚቀርበውን የብሔራዊ አትሌቶች ምርጫን መነሻ በማድረግና በአጠቃላይ የተቋሙን እንቅስቃሴና ወቅታዊ አቋም አስመልክቶ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡
ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ በርካታ የአገር ውስጥ ጋዜጠኞች በተገኙበት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ አለባቸው ንጉሴ፣ የአትሌቲክስ ስፖርት በተለይም በአሁኑ ወቅት ስፖርቱ ከደረሰበት ደረጃና አሠራር አኳያ ተቋሙ ከነበሩበት በርካታ ክፍተቶችና ችግሮች መላቀቅ ይችል ዘንድ ይህንኑ የሚያጠና አካል በመመደብ እየተንቀሳቀሰ ስለመሆኑ፣ በጥናት ቡድኑ በተለይ ሥልጠናና ውድድር እንዲሁም ከምልመላና አትሌቶች ምርጫ ጋር የተያያዙ እጅግ ውስብስብ የአሠራር ክፍተቶች እንደነበሩና በአትሌቶች የውጭ ጉዞ ሽፋን የተለያዩ የቤት እመቤቶች ሳይቀር በፌዴሬሽኑ ማኅተም በመጠቀም ከፍተኛ የሆነ ሕገወጥ ሥራ ሲከናወን መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ጉዳዮች በሕግ አግባብ ክትትል እየተደረገባቸው ስለመሆኑ፣ በአትሌቶችና በማናጀሮቻቸው መካከል በተለይ ከገንዘብ ክፍያ ጋር የተያያዙ መሠረታዊ ችግሮች እንደነበሩ፣ ከንብረት አስተዳደርና አጠቃቀም እንዲሁም ከጽሕፈት ቤት የፋይናንስና ግዥ ጋር የተገናኙ ክፍተቶች እንደነበሩና ሌሎችንም በማካተት ሰፋ ያለ ሪፖርት በሚመስል መልኩ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
እንደ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ከሆነ፣ በተቋሙ ውስጥ ያሉትንና የቆዩትን የተበሻሉ አሠራሮች ለማስተካከልና ለመለወጥ በነበረው ሒደት አሁን ከአትሌቶች ምርጫ ጋር ተያይዞ እየቀረበ ካለው ባልተናነሰ የአመለካከት ፍጭቶች ሲከሰቱ ቆይተዋል፡፡ ፌዴሬሽኑ በአመለካከቶቹ ሳይስማማ መቆየቱን ያከሉት አቶ አለባቸው፣ አሁን ምርጫ ምክንያት ተደርጎ በፌዴሬሽኑ ላይ የተጀመረው ተቃውሞና የስም ማጥፋት ዘመቻ የዚህ ነፀብራቅ መሆኑን ጭምር አስረድተዋል፡፡
የአትሌቶቹን ጥያቄ አስመልክቶ አቶ አለባቸው ሲናገሩ፣ ‹‹የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከእነዚህ የአገሪቱ ብርቅና ድንቅ አትሌቶች ጋር ቀርቶ ጉዳዩ ይመለከተናል ከሚሉ ከማናቸውም ጋር አብሮ ለመሥራት ዝግጁ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ወደፊትም ቢሆን አትሌቶቹ ባላቸው ነፃ ማኅበራቸው አማካይነት ከተቋሙ ጋር ተቀራርበው የማይሠሩበት ምክንያት እንደማይኖር እምነታቸው መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡
ግንቦት 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም በተከናወነው የምክክር መድረክ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ሲናገር እንደተደመጠው ከሆነ፣ እሱን ጨምሮ በሙያው ያሳለፉ አትሌቶች ወደ ፌዴሬሽኑ ገብተው የሙያ ድርሻቸውን መወጣት የሚችሉበት አንዳችም ቀዳዳ የለም፡፡ ይህንኑ የአትሌቶቹን ቅሬታ በተመለከተም አቶ አለባቸው ሲናገሩ ‹‹ይህ አሁን በሥልጣን ላይ የሚገኘው የፌዴሬሽኑ አሠራር እንዴትና በምን አግባብ ወደ ኃላፊነት እንደመጣ አትሌቶቹም የተቋሙን ደንብና ሥርዓት በተከተለ መልኩ መቃወምና መተቸት መብታቸው ነው፡፡ ነገር ግን አሁን እየሆነና እየተሰማ ያለው ከዚህ ደንብና ሥርዓት ባፈነገጠ መልኩ ነው፡፡ እንዲህም ሆኖ አሁንም ሆነ ወደፊት ለምን ትቃወሙናላችሁ? ለምን ከኃላፊነት ልቀቁ ትሉናላችሁ? የሚል አንዳችም መከራከሪያ አናቀርብም፤›› ብለዋል፡፡ ተቋሙ የሚተዳደረው በደንብና ሕግ በመሆኑ ያ ደግሞ ለአትሌቶቹም ሆነ ለፌዴሬሽኑ አመራሮች እኩል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለተቃውሞም ሆነ ለድጋፍ ገዥ የሚሆነው መተዳደሪያ ደንቡ ስለመሆኑም አክለዋል፡፡
ምርጫውን አስመልክቶ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ከ250 በላይ አትሌቶችን በብሔራዊ ቡድን መልምሎ የአሠልጣኞች ቅጥርም ፈጽሞ ሥልጠና ሲሰጥ ስለመቆየቱም አስረድተዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ተቋሙ ለአትሌቶችም ሆነ ለአሠልጣኞች ምልመላ እየተከተለ ባለው መስፈርት ግልጽ ማስታወቂያ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሳይቀር ግልጽ ተደርጎ መከናወን መቻሉንም አስረድተዋል፡፡ ይህ ከአጭር እስከ ረዥም ዕርቀት መሆኑን ያከሉት አቶ አለባቸው፣ ለማራቶን ተወዳዳሪዎች በመስፈርቱ መሠረት ቅድሚያ ያገኙት አትሌቶች ስለመመረጣቸውም ተናግረዋል፡፡ ይህም እ.ኤ.አ. ከነሐሴ 22 ቀን 2015 እስከ ሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያቶች በደረጃ አንድ በተቀመጠ ማራቶን ወይም በደረጃ ሁለት፣ ሁለት ማራቶኖች የተሻለ ደረጃና ሰዓት ላለው (ላላት) ከመቶ በተሰጠው ነጥብ መሠረት መሆኑን ጭምር ተብራርቷል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አለኝ የሚለውን የምርጫ መስፈርት በተመለከተ ወቅቱንና ጊዜውን ጠብቆ የተዘጋጀ አለመሆኑ ተቋሙን በዋናነት ከሚያስወቅሰውና ከሚያስተቸው ይጠቀሳል፡፡ ይህንኑ አቶ አለባቸው፣ መዘግየት ስህተት እንደሆነ አምነው በዕለቱ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ ምክንያት ያሉትንም ሲያብራሩ፣ ‹‹እንዳለመታደል ሆኖ በፌዴሬሽኑ አቅሙም ብቃቱም ኖሮት በራሱ የሚወስንና በራሱ የሚተማመን የባለሙያተኞች እጥረት አለ፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሚገባበት አሠራር ጠባብ በሆነ ነበር፤›› ብለዋል፡፡ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ክፍሉ ተወካይ የሆኑት አቶ አሰፋ በቀለ መምረጫ መስፈርቱን አስመልክቶ ማስረጃውን ከማሳየታቸው በተጨማሪ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶ/ር መለሰ ኃይሌ መስፈርቱ መጠነኛ የቁጥር ስህተት ሊኖር እንደሚችልና በተለይ በማራቶን የማገገሚያ ጊዜያትን ግምት ውስጥ በማስገባት ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት መዘጋጀት መቻሉን አክለዋል፡፡ ይሁንና ዶ/ር መሰለ ከምሕንድስና ሙያቸው በተጓዳኝ ከአትሌቲክሱ ጋር የሚያገናኛቸው ምንም ዓይነት የሙያ ቁርኝት እንደሌላቸው በመግለጽ የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢ መሆን አይገባቸውም ሲሉ የሚተቹዋቸው አሉ፡፡ ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ማብራሪያ በኋላ በርካታ በተለይ ከምርጫና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር የተገናኙ ክፍተቶች የቀድሞና የአሁን አትሌቶች የሚያነሷቸውን የተመለከቱ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡
ከተነሱት ጥያቄዎች በዋናነት በአቶ አለባቸውን ንጉሴ ይቅርታ የተጠየቀበት የመስፈርት መዘግየት ተጠያቂነቱን የሚወስደው ማን ነው? በርካታ የቀድሞና የአሁን አትሌቶች በምርጫ፣ በሥልጠናና በአሠራር ዙሪያ ከፌዴሬሽኑ ጋር ለመወያየት ለሚያቀርቡት ጥያቄ ተገቢው ምላሽ እንደማይሰጣቸው ሲናገሩ በተደጋጋሚ ይደመጣል፡፡ ከዚህ አኳያ ፌዴሬሽኑ የአትሌቶቹን ጥያቄ ያልተቀበለበት ምክንያት ምንድነው? ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ከሚቃወሙት በርካታ አትሌቶች መካከል በኢትዮጵያ ቀርቶ ዓለም ላይ በታዋቂነታቸውና በተሰሚነታቸው የሚታወቁ ናቸው፡፡ ጥያቄያቸውም ለአገሪቱ የአትሌቲክስ ስፖርት መለወጥ እንጂ የጎንዮሽ ፍላጎት የሌላቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ታዲያ እውነታው ይኼ ከሆነ ፌዴሬሽኑ የእነዚህን አትሌቶች ሐሳብና አስተያየት በግብዓትነት መጠቀም ያልቻለበት ምክንያት ምንድነው? የሚሉት ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ፡፡ የቀነኒሳ በቀለ በምርጫ አለመካተት የተመለከቱ ጥያቄዎችም ነበሩበት፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫው ከተገኙት የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ውስጥ ለቀረቡት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ቅድሚያውን የወሰዱት ዶ/ር መለሰ ኃይሌ ቀነኒሳ በቀለ በምርጫው ሊካተት ያልቻለው አንዱና ዋናው ምክንያት በሦስት ማራቶኖች የማይዋዥቅ ውጤት ከሚለው በተጨማሪ አትሌቱ በውድድር ዓመቱ ሁለት ማራቶኖችን ብቻ መሮጡ ይኽም መስፈርቱ የሚጠይቀውን የሚያሟላ እንዳልሆነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሙያተኞችን በተመለከተ ለተነሱት ጥያቄዎች ሌላው ማብራሪያ የሰጡት ዶ/ር በዛብህ ወልዱ ነበሩ፡፡ እንደ ዶክተሩ ማብራሪያ የአገሪቱ ታዋቂ አትሌቶች ለሚያነሱት ጥያቄ ተገቢውን ክብር እንደሚሰጡ ገለጸው፣ ብዙ ጊዜ ግን መልስ የማያገኙለት አስተያየት በአትሌቲክሱም ሆነ በተቀረው ስፖርት በሙያው ያሳለፉ ባለሙያተኞች ለምን የአመራርነት ሚና አይኖራቸውም እየተባለ የሚነገረው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የዓለም አቀፉን ፌዴሬሽን ሳይቀር እንዲያስተዳድሩ የተደረጉት እንግሊዛዊው ሰባስቲያን ኮ እና ሌሎችም በምሳሌነት የሚጠቀሱት ቀድሞ አትሌቶች እንደነበሩ ነው የሚሉት ዶክተሩ፣ እንደሚነገረው ‹‹አትሌቶች ብቻ የሚመስሉን ካለን እንዳንሳሳት፤›› በማለት ሰባሰቲያን ኮ ‹‹አትሌት ብቻ ሳይሆን ምሁርም ነው፤›› በማለት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአትሌትነታቸው በተጨማሪ ተቋምን ለመምራት የአካዴሚክ ዕውቀት ሊኖራቸው እንደሚገባ ጭምር ጠንከር ያለ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ከተጠያቂነት ጋር ተያይዞ ለቀረቡት ጥያቄዎች የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ተመስገን ጥላሁን በበኩላቸው፣ እንደ ተቋም አመራር ተጠያቂነት ተነጥሎ ወደ አንድ አካል ላይ ብቻ የሚሄድ እንዳልሆነ ገልጸው፣ ተጠያቂው ይቅርታ የጠየቀው አካል መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አቶ ተመስገን፣ አትሌቶች ለሚያቀርቡት የአመራርነት ብቃትን በተመለከተ ሲገልጹም በተቋሙ ሕግና ደንብ መሠረት ይህ አመራር ለምንና እንዴት እንደተቀመጠ እንዲሁም ያስቀመጠው አካል ባስቀመጠው አቅጣጫና ዕቅድ መሠረት ምን ያህሉን አከናውኗል? ብሎ የሚጠይቅበት አግባብም አብሮ የተቀመጠ በመሆኑ እሳቸውን ጨምሮ አመራሩ እንዲህና እንዲያ ብሎ ለማስረዳት ቦታው እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ እንደ አመራር የአትሌቲክሱ ዋና የሥልጣን አካል የሆነው ጠቅላላ ጉባዔ ባስቀመጠው የዕቅድ አቅጣጫ መሠረት የተሰጠውን ኃላፊነት እየተወጣ መሆኑን ሳያስረዱ ግን አላለፉም፡፡
ባለፈው ዓመት በአዲስ መልክ የተዋቀረው የኢትዮጵያ አትሌቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ስለሽ ስሕን በበኩሉ፣ በእሱ ሊቀመንበርነት እየተመራ ያለው የአትሌቶች ማኅበር ውክልናውን ለሰጠው ለአትሌቶች መብት እየቆመ አይደለም በሚል ወቀሳና ትችት ይቀርብበታል፡፡ ግንቦት 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም የቀድሞና የአሁን አትሌቶች ባደረጉት የውይይት መድረክ ማኅበሩ እንደማይወክላቸው በግልጽ የተናገሩ አሉ፡፡ ፌዴሬሽኑ በአትሌቶች ላይ የሚያደርሰውን የአሠራር ክፍተት አስመልክቶ ወቀሳውን የሚያቀርቡት አትሌቶች በጉዳዩ ዙሪያ ከማኅበሩ አመራሮች ጋር ለመወያየት ጥያቄ ቢያቀርቡም ሰሚ ማጣታቸው፣ በዚህም ምክንያት ማኅበሩ ላይ ያላቸው እምነት መሸርሸሩንም ይፋ ያደረጉ ነበሩ፡፡
ይህንኑ አስመልክቶ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት፣ ‹‹ማኅበሩ ሕጋዊ ነው አይደለም?›› በሚለው ክርክር ውስጥ መግባት እንደማይፈልግ በመግለጽ ማብራሪያ ለመስጠት የሞከረው አትሌት ስለሽ፣ አትሌቶች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች የማኅበሩም መሆናቸው፣ ሆኖም የሪዮ ኦሊምፒክ ከቀረው ጊዜ አኳያ ጉዳዩ ለጊዜው እንዲቆይና የሁሉም የትኩረት አቅጣጫ በሪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅት ዙሪያ እንዲሆን ማኅበሩና በማኅበሩ ላይ ተቃውሞ ያላቸው አትሌቶች ሚያዝያ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ በቃለ ጉባዔ ተስማምተው መለያየታቸውን አስረድቷል፡፡ አትሌቶች በቀጣይ የአመራርነት ሚና ይኖራቸው ዘንድ ማኅበሩ አበክሮ እየሠራበት ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ አለባቸው ንገሴ በበኩላቸው፣ ሌሎች የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የሰጡዋቸው ማብራሪያዎች እንደተጠበቁ በማንኛውም መመዘኛ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ሕግና ሥርዓትን ተከትለው የሚመጡ አትሌቲክሱን ለማሳደግ እስከሆነ ድረስ ለማናቸውም አስተያየቶችና ጥቆማዎች የፌዴሬሽኑ በሩ ክፍት መሆኑን አስተድተዋል፡፡ ከምርጫና በተለይ የቀነኒሳ በቀለን ጉዳይ አስመልክቶ አቶ አለባቸው፣ አትሌቱ እሳቸውን ጨምሮ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመካበትና ሲመካበት የቆየ መሆኑን ገልጸው፣ ሆኖም የሪዮ ኦሊምፒክን ምርጫ ተከትሎ ግን ለምርጫው የተቀመጠው መስፈርት ሊያስመርጠው አለመቻሉን ነው ያስረዱት፡፡ ፕሬዚዳንቱ ሲቀጥሉም ‹‹የሚኖረን ምርጫ የተፈጠረው ችግር እንዳይከሰትና ፌዴሬሽኑ የፈለገውን አትሌት መርጦ ወደ ሪዮ ለማምራት መስፈርት አለማውጣት፣ ወይም ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አትሌት በወቅታዊ አቅሙና ብቃቱ መስተናገድ ይችል ዘንድ መስፈርት አውጥቶ በመስፈርቱ መሠረት መሄድ ነው፤›› ብለው በእሳቸውና በፌዴሬሽኑ እምነት ‹‹መስፈርት›› የሚለውን መምረጣቸውን ተናግረዋል፡፡
የአትሌቶችን የአመራርነት ጉዳይ በተመለከተ ደግሞ ይኼ ጉዳይ አሁን ባለው በፌዴሬሽኑ አመራርም ሆነ በአትሌቶች ፍላጎቱ ብቻ የሚወሰን እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ፌዴሬሽኑ ለዚህ ራሱን የቻለ ሥርዓትና ደንብ እንዳለው ያንን ተከትሎ መሄድ የማናችንም የግዴታ ውዴታ መሆኑን ጭምር ተናግረዋል፡፡