Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየበጀት ዲሲፕሊን አለን?

የበጀት ዲሲፕሊን አለን?

ቀን:

በበሪሁን ተሻለ

ሰኔ የአገራችን የበጀት ካሌንደር የመጨረሻ ወር ነው፡፡ እንዲህ ያለ ልዩ ልዩ ዓይነት ድግስ የሚታይበት ወር ግን ገና በርበሬ መቀንጠስ የሚጀመርበት፣ በርበሬ ቀንጥሱ የሚባልበት ጊዜ አይደለም፡፡

የ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት አንድ አሥራ ሁለት ጊዜ ያህል ስለበጀት ቢያወሳም አብዛኞቹ ምናልባትም ሁሉም የተናጥል መሥሪያ ቤቶችን (ለምሳሌ ፍርድ ቤት፣ ኦዲተር ጄኔራል ወዘተ) የሚመለከቱ፣ እግረ መንገዳዊ ፋይዳ ያላቸው እንጂ የመንግሥት ገንዘብን አሰባሰብ፣ አስተዳደር፣ የበጀት ዓመትን አወሳሰን ጉዳዬ ብለው የሚደነግጉ አይደሉም፡፡ በዚህ ረገድ ብቸኛው ድንጋጌ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር ውስጥ የተካተተው ዓመታዊ በጀት የማዘጋጀት፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማቅረብ፣ ሲፀድቅም ተግባራዊነቱን የማረጋገጥ ሥራ ነው፡፡ በተወካዮች ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባርም ውስጥ ‹‹ለፌዴራል መንግሥት በተከለለው የገቢ ምንጭ ክልል ግብርና ታክስ ይጥላል፡፡ የፌዴራል መንግሥት በጀት ያፀድቃል፤›› ተብሏል፡፡

የአንድ ሕገ መንግሥት ‹‹የመንግሥት ገንዘብ›› ሽፋን ግን ከዚህ በላይ ነው፡፡ የአገራችን የ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት የበጀት ነክ ጉዳዮች ድንጋጌ ይህን ያህል መላ ያጣው (በምዕራፍ አሥራ አንድ የሕገ መንግሥት ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች ውስጥ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር ከተሰነቀረው የፋይናንስ ጉዳይ በስተቀር) ራሱን የቻለ ምዕራፍ ወይም ክፍል ያልተሰጠው ለምን እንደሆነ መናገር በጣም ከባድ ነው፡፡

የበጀትንና የበጀት ዓመትን ወሳኝና የመርህ ድንጋጌዎችን በመወሰን ረገድ የ1948ቱን ሕገ መንግሥት የሚወዳደረው የለም፡፡ ይህ ደግሞ መነሳት ያለበት ስለታሪክ ብቻ ሳይሆን በዚያው ሕገ መንግሥት መሠረት የተዘረጋው የበጀት ዓመት ሥርዓት አሁንም ሥራ ላይ ያለ በመሆኑ ነው፡፡

የ‹‹መንግሥት ገንዘብ››ን የሚመለከቱ መሠረታዊ ድንጋጌዎች በተጠቀሰው የቀድሞው ሕገ መንግሥት ተፍታትተው የተጻፉት ዓይነት ናቸው፡፡ በሕግ ካልሆነ በስተቀር ታክስ ቀረጥ ግብር ኤክሳይ ቀረጥ አይጣልም፣ አይጨመርም፣ አይቀነስም ወይም አይፋቅም፡፡ በሕግ ካልተፈቀደ በቀር በሕግ የተወሰነውን ማንኛውንም ታክስ ቀረጥ ግብር ወይም ኤክሳይስ ቀረጥ ከመክፈል የሚያስቀር ነገር የለም ማለት ዛሬም አለ፡፡ መኖር አለበት፡፡ ይህንን መጣስ አይቻልም፡፡ የሚቸግረንና የሚያስቸግረን የዚህን ሕግ ቦታና ከፍታ መለየትና ይኸኛው ነው ማለት ይሆናል፡፡ በተለይም የሕዝብን ልብ የረታ የመታመን ብቃቱን የገነባ ፍርድ ቤት በሌለበት አገር የዚህ ችግር ስፋትና ክፋት ወደር የሌለው ነው፡፡

ማንኛውም የመንግሥት ገቢ ገንዘብ በሕግ እንደተፈቀደው ካልሆነ በስተቀር ወጭ አይሆንም ማለትም የአገር ሕግ የሆነው ከብዙ ጊዜ በፊት ነው፡፡ ይህን የአገር ሕግ፣ አሁን ኦዲተር ጄኔራል ፓርላማ እየቀረበ ‹‹ሰበር ዜና›› አድርጎ ሲያቀርበው እንደምንሰማው መሆን አልነበረበትም፡፡

የበጀቱ ዓመት በልዩ ሕግ ይወሰናል የሚል ሕገ መንግሥት የለም ተብሎ የበጀቱን ዓመት ከዚህ ዓይነት ልዩ ሕግ ባነሰ ‹‹ደንብ›› ወይም ‹‹መመርያ›› እወስናለሁ ማለት አይቻልም፡፡ ደግነቱ ኢትዮጵያ የበጀት ዓመቱን በልዩ ሕግ የወሰነችበት ሕግ አሁንም ሥራ ላይ ነው፡፡ ይህም ሕግ የበጀት ዓመት አዋጅ ቁጥር 162/51 ነው፡፡ በዚህ መሠረት የበጀት ዓመቱ ከሐምሌ 1 ቀን ጀምሮ እስከሚቀጥለው ዓመት ሰኔ 30 ቀን ድረስ ያለው የአንድ ዓመት ጊዜ ነው፡፡ በዚህ መልክ የተቋቋመው የኢትዮጵያ የመጀመርያው የበጀት ዓመት እስከ ሰኔ 30 ቀን 1952 ዓ.ም. የተዘረጋው የበጀት ዓመት ነበር፡፡ ስለሆነም አሁን በዚህ ወር የሚጠናቀቀው የበጀት ዓመት 57ኛው የበጀት ዓመት ነው፡፡

የበጀት ዓመቱ በሕግ ከሚወሰነው ጉዳይ ጋር የተቆራኙ ሁለት ሌሎች ወሳኝ ጉዳዮች አሉ፡፡ አንደኛው የበጀት ዓመቱ ሊከተለው የሚገባ የጊዜ ሰሌዳ ነው፡፡ የጊዜ ሰሌዳው ዋነኛው መዋቅር፣ ዋልታና ማገሩ የሚገነባውም እንደፈቀደና እንዳሻ፣ በየዓመቱም አይደለም፡፡ የ1948ቱ ሕገ መንግሥት የዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ ፓርላማው በበጀቱ ላይ ድምፅ መስጠቱን እጅግ ቢያንስ አዲሱ የበጀት ዓመት ከሚጀምርበት ከአንድ ወር በፊት መጨረስ አለበት ይል ነበር፡፡ የመንግሥት የበጀት ዲሲፕሊን የሚነሳው ከእንዲህ ያለ የጥበብ መጀመሪያ ነው፡፡ ዛሬ ለገንዘብና ለኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ያልተተወ በሕገ መንግሥት ደረጃ ቀርቶ ራሱን የገንዘብ ሚኒስቴርን ከዚያም በላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤትን ጭምር እንኳን የሚገዛ በአዋጅ የተነደፈና የተቋቋመ የበጀት የጊዜ ሰሌዳ የለንም፡፡

የቀድሞውና በእሱ ላይ መገንባት የነበረበት ሕገ መንግሥት ግን ፓርላማው በበጀቱ ላይ ድምፅ መስጠቱን እጅግ ቢያንስ አዲሱ የበጀት ዓመት ከሚጀምርበት ከአንድ ወር በፊት ማለትም ከግንቦት 30 በፊት መጨረስ አለበት ይላል፡፡ በዚህ ሕግ መሠረት የታወጀው የበጀት ዓመት አዋጅም ለመጪው ዓመት በሥራ ላይ የሚውለው በጀት እጅግ በዛ ጉዳይ ከመጋቢት 15 ቀን በፊት ለምክር ቤቱ መቃረብ እንዳለበት ይደነግግ ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በሕገ መንግሥት ደረጃ የተደነገገ ሌላም የጊዜ ሰንጠረዥና ‹‹ፌርማታዎች›› ነበር፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 120 (1948ቱ) እያንዳንዱ የበጀት ዓመት በተፈጸመ በአራት ወር ውስጥ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የዚያውኑ የተፈጸመውን ዓመት የገቢና የወጪ ሙሉ ራፖር ለንጉሠ ነገሥቱና ለፓርላማው ያቀርባል፣ ራፖሩም ወዲያውኑ ለዋናው ኦዲተር ይላካል፡፡ ኦዲተሩም በራፖሩ ላይ ያለውን አስተያየት በሦስት ወር ውስጥ ለንጉሠ ነገሥቱና ለፓርላማው ያቀርባል ይል ነበር፡፡ ይህን የደነገገው የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት በፈረሰ ከ42 ዓመት በኋላ በዚህ ሕገ መንግሥት የተጠቀሰው ድንጋጌ መሳቅና መሳለቅ ያለብን ድንጋጌው የቢሻኝ ድንጋጌ በመሆኑ እንጂ የማያስፈልግ በመሆኑ አይደለም፡፡

እንዲህ እንደዛሬው በየዓመቱና የሚጠብቀውና የሚከተለው የጊዜ ሰሌዳና ፌርማታ ስለመኖሩ ሳያውቅ የዋናውን ኦዲተር ራሱን እንኳን ብርቅና ድንቅ የአገር ዜና ተሽክሞ መስማት ከመጀመራችን ከ15 ዓመታት በፊት ከመንግሥት ከራሱ የምንሰማው ሪፖርት የየዓመቱ የመንግሥት ሒሳብ በወቅቱ የማይዘጋ መሆኑን ነበር፡፡ ያልተዘጋ የሁለት ዓመት ያህል የመንግሥት ሒሳብ መኖሩን ሁሉ ሰምተናል፡፡ መንግሥት ተራ ነጋዴ ወይም የበጎ አድራጎት ድርጀት ወይም ማኅበር ቢሆን ሒሳቡን ሳይዘጋ ያልተዘጋ የሁለት ዓመት በላይ ሒሳብ ይዞ ፈቃዱን የሚያድስለት ማን ይኖራል?

አሁን መንግሥት ሒሳቡን ስለመዝጋቱና አለመዝጋቱ የምንሰማው ሪፖርት ግልጽ ባይሆንም አንድ ነገር ግን ግልጽና እውነት ነው፡፡ መንግሥት የሚከተለውና ከእሱ በላይ የሆነ የሥልጣን አካል ያወጣው የበጀት የጊዜ ሰሌዳ ሕግ የለውም፡፡ ከመንግሥት ከራሱ በላይ የሆነ የሥልጣን አካል ስንል ከሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ ከመስተዳድሩ በላይ የሆነ የሥልጣን አካል ስለዚህም የተወካዮች ምክር ቤት ያወጣው አዋጅ ማለታችን ነው፡፡

ትልቁ ይህን የሚመለከተው በተወካዮች ምክር ቤት የወጣ ሕግ የፌዴራል መንግሥት የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 648/2001 ነው፡፡ ወይም ከእሱ በፊት የነበረውና የተሻረው አቻ ሕግ ነው፡፡ ወይም ከእሱ በፊት የነበረውና የተሻረው አቻ ሕግ ነው፡፡ ይህ ሕግ ጥብቅ የጊዜ ሰሌዳ አያቋቁምም፡፡ እንዲያውም የሚያቋቁመው የጊዜ ሰሌዳ የለውም፡፡ እንዲያውም በጀት ስለሚፀድቅና ስለማሳወቅ የሚደነግገው በአዋጁ የበጀት ክፍል ውስጥ የሚገኘው ድንጋጌ የገንዘብ ሚኒስትሩ ለተከታዩ የበጀት ዓመት የሚያስፈልገውን በጀት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀርባል፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተደግፎ ስለተላከው በጀት ማብራሪያ ይሰጣል፡፡ እንዲሁም የዓመቱ በጀት እስከ ሰኔ 30 ቀን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የክልል መንግሥታት እስከ ሐምሌ 7 ቀን እንዲያውቁት ይደረጋል፡፡ በተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው በጀት በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ይወጣል ይላል፡፡

እንደወትሮው ዛሬም የበጀት ዓመቱ ከሐምሌ 1 ቀን እስከ ሰኔ 30 ያለው ጊዜ ነው፡፡ ይህም በዚሁ በራሱ በፌዴራል መንግሥት የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ ትርጓሜ ሥር (አንቀጽ 2/10) ተደንግጓል፡፡ ለመጪው ዓመት በሥራ ላይ የሚውለው በጀት እጅግ ቢዘገይ ከመጋቢት 15 ቀን በፊት ከምክር ቤቱ መቅረብ አለበት ከሚለው ከመጀመሪያው የአገር የበጀት ዓመት አዋጅ ግን በጣም ያንሳል፡፡ ፓርላማውም በበጀቱ ላይ ድምፅ መስጠቱን እጅግ ቢያንስ አዲሱ የበጀት ዓመት ከሚጀምርበት ከአንድ ወር በፊት መጨረስ አለበት ከሚለው ከሕገ መንግሥታዊው ድንጋጌም ጋር ጭራሽ የሚነጻጸር አይደለም፡፡

አሁን ሥራ ላይ ያለው የበጀት የጊዜ ሰሌዳን የሚመለከተው ሕግ እንዳመቸ እንዳይጣስ ነባራዊ አስገዳጅነት የሌለበት የቢሻን ውሳኔ ብቻ እንዳይሆን የሚያስገድድ፣ ከታች እንዳያፈስ ከላይ እንዳይተነፍስ አድርጐ የሚቋጠር መጠበቂያ የለውም፡፡ እንዲያውም በአዋጅ ደረጃ የወጣው ሕግ ራሱ (የመንግሥት የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ) የዓመቱ በጀት እስከ ሰኔ 30 ቀን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የክልል መንግሥታት እስከ ሐምሌ 7 ቀን እንዲያውቁት ይደረጋል በማለት ሐምሌ 1 ቀን የሚጀመረው አዲሱ የበጀት ዓመት በዚህ መሠረት እንኳን የአንድ ሳምንት ‹‹ሥራ ማቆም›› ዕረፍት ውስጥ እንዲገባ ያደርጋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው በጀት በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ የሚወጣው ከሰኔ 30 ቀን በኋላ ነው ማለት ራሱ የበጀት ሕግ ለአገርና ለሕዝብ የማስታወቅ የመንግሥት ተግባሩን ያስተጓጉላል፡፡

ከዚህ ቀደም በሕገ መንግሥት ደረጃና ከገንዘብ ሚኒስቴር በላይ፣ በዚህም ሳይወሰን ከአገሪቱ ከፍተኛ የአስፈጻሚና የአስተዳደር የሥልጣን አካል (ማለትም ከሚኒስትሮች ምክር ቤት) በላይ የሆነ የሥልጣን አካል በሚያወጣው ሕግ ይወሰን የነበረው የበጀት የጊዜ ሰሌዳ ዛሬ በዝርዝር ተወስኗል የተባለው የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው የፌዴራል መንግሥት የበጀት አስተዳደር መመርያ መሠረት ነው፡፡ ይህ መመርያ መመርያ ቁጥር 3/2003 ይባላል፡፡ ከታህሳስ 1/2003 ዓ.ም. ጀምሮ የፀና እና ከዚህ በፊት ወጥቶ የነበረውን የ1996 ዓ.ም. የፋይናንስ የጊዜ ሰሌዳ መመርያ የሻረ መመርያ ነው፡፡

በዚህ መመርያ መሠረት

  • የገንዘብ ሚኒስቴር የተከታታይ ሦስት ዓመታት የማከም ኢኮኖሚና የፊስካል ማዕቀፍ በየዓመቱ እስከ ጥቅምት 15 ያዘጋጃል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤትም በሚኒስቴሩ ተዘጋጅቶ የቀረበውን የማክሮ ኢኮኖሚና ፊስካል ማዕቀፍ በመመርመር እስከ ጥቅምት 30 ባለው ጊዜ ያፀድቃል (አንቀጽ 8/1)
  • የፌዴሬሽን ምክር ቤት የብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታትንና የከተማ አስተዳደሮችን የበጀት ድጋፍ ማከፋፈያ ቀመርን በማፅደቅ ወይም ነባሩ የሚቀጥል መሆኑን በመግለጽ እስከ ህዳር 20 ባለው ጊዜ ውስጥ ለሚኒስቴሩ ያስታውቃል፡፡
  • በፌዴሬሽን ምክር ቤት በፀደቀው የበጀት ድጋፍ ቀመር መሠረትም ሚኒስቴሩ ዓመታዊ ጠቋሚ የበጀት ደጋፍ ለብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታትና የከተማ አስተዳደሮች እስከ ህዳር 30 ያዘጋጃል፣ ያስታውቃል፡፡
  • የገንዘብ ሚኒስቴር የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለሚቀጥለው የበጀት ዓመት የሚያስፈልጋቸውን መደበኛና ካፒታል ወጪዎች በጀት አዘጋጅተው እንዲያቀርቡ የበጀት ጥሪ እስከ ጥር 30 ያቀርባል፡፡
  • በዚሁ መመርያ መሠረት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለበጀት ጥሪው መልስ ‹‹አስፈላጊ የሆኑ ዝርዝር የስሌት አሠራሮችንና ደጋፊ ማስረጃዎችን በማያያዝ እስከ መጋቢት 30 ባለው ጊዜ ውስጥ ለሚኒስቴሩ ማቅረብ አለባቸው›› (አንቀጽ 7/2/ሐ) ቢባልም ‹‹ሚኒስቴሩ የተጠቃለለውን በጀት እንዲደግፍ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እስከ መጋቢት 30 ቀን ያቀርባል›› ብሎ መመርያው ይደነግጋል፡፡ (አንቀጽ 6/4/00/)
  • የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚኒስትሩ የቀረበውን በጀት በመመርመር የደገፈው በጀት እንዲፀድቅ እስከ ግንቦት 30 ቀን ድረስ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀርባል፡፡ (አንቀጽ 8/2)
  • የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበውን የተደገፈ በጀት በመመርመር እስከ ሰኔ 30 ባለው ጊዜ ውስጥ ያፀድቃል፡፡ (አንቀጽ 9)  

የኢትዮጵያ የበጀት የጊዜ ሰሌዳና በጀትም የሚጠይቀው ጥብቅ ዲሲፕሊን የሚገዛው በዚህ መመርያ መሠረት ነው፡፡ መጀመሪያ ነገር የገንዘብና የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሌላው ቢቀር በፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ላይ ግዴታ የሚያቋቁም ሕግ ማውጣት ይችላል ወይ? የገንዘብ ሚኒስቴርን እስከ ጥር 30 የበጀት ጥሪ ታቀርባለህ፣ የጠቀለልከውን የበጀት ጥያቄ ደግሞ እስከ መጋቢት 30 ቀን ድረስ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ታቀርባለህ ብሎ አስገዳጅነት ያለው ሕግ የማውጣት ሥልጣንስ ለራሱ ለገንዘብ ሚኒስቴር የሚሰጥ ነወይ? ሥርዓት የመዘርጋት ተቋም የመገንባት ሙከራችንና ተሞክሯችንን የሚያጋልጡ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ሕግና ደንብ እንዳመቸ የሚጣሉና የሚነሱበትን አሠራርና ተግባር በሕግ አወጣጥ ውስጥም ጭምር መድገምና መልሶ መላልሶ መደጋገም እንደሚቻል የሚያሳይ ከሕግ በላይ የመሆን ‹‹አዲስ›› ዘዴና ሥልት ነው፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ ባለገንዘብ መንግሥት ነው፡፡ የትልቅነቱና የግዙፍነቱን መጠን አፍታተውና አብጠርጥረው፣ ከአገር አጠቃላይ ምርትና ሀብት ጋር አነጣጥረው ቢነግሩን የሚያምርባቸው ባለሙያዎች ናቸው፡፡ በእኔ በኩል መንግሥት ትልቁና ግዙፉ ቀጣሪ፣ እጅግ ግዙፉ ሸማች፣ ገዢና ገንዘብ አንቀሳቃሽ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ሲሉ እሰማለሁ፡፡ የዚህ ሁሉ የገንዘብ ምንጭ ደግሞ ሲሆን በብቸኝነት አለዚያም በዋነኛነት የአገር ውስጥ ገቢ ነው፡፡ ገቢ ማለት ደግሞ ታክስ ነው፡፡

ዕድሜ ለበጀት አዋጆች እንጂ እነሱ ባቋቋሙት ወግ መሠረት መንግሥት በገንዘብ ላይ ያለው ሥልጣን ወሰን የሌለው፣ ያሻውን የሚያደርግ፣ ያሻውን ያህል የሚያገኝ አይደለም፡፡ አሁን ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. የሚጠናቀቀውን የበጀት አዋጅ ሕግ ለምሳሌ እንመልከት፡፡ አንቀጽ አንድ የአዋጁን አጭር ርዕስ ይደነግጋል፡፡ የ2008 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት የበጀት አዋጅ ተብሎ እንደሚጠቀስ ይገልጻል፡፡ (ምንም እንኳን ለሕግ ቴክኒሺያኖቻችን የሕጐች አጭር ርዕስ ከረጅም ርዕሳቸው የተለየ መሆኑ ከቀረና ከተረሳ ዘመናት ቢቆጠሩም፡፡) አንቀጽ 2 ጠቅላላ የተፈቀደ በጀት ይላል፡፡ ይህ ራሱ መንግሥት በገንዘብ የሚያዘው በገቢም ሆነ በወጪ ረገድ በፈቃድ መሆኑን ያሳያል፡፡ ከተረሳ፣ የተፈቀደ በጀት ማለት ትርጉሙ ከነተበ ቆየ እንጂ እናም ከሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በሚፈጸመው በአንድ የበጀት ዓመት ጊዜ ውስጥ የፌዴራሉ መንግሥት ከሚያገኘው ገቢና ከሌላ ገንዘብ ላይ ከዚህ ጋር በተያያዘው ሰንጠረዥ ውስጥ ለተጠቀሱት ሥራዎችና አገልግሎቶች 223.3 ቢሊዮን ብር ለፌዴራል መንግሥት ወጪ ሆኖ እንዲከፈል በዚህ አዋጅ ተፈቅዷል ይላል፡፡

መነሻችን ላይ የጠቀስነው በሕግ ካልሆነ በቀር ታክስ፣ ቀረጥ፣ ግብር፣ ወዘተ አይጣልም፡፡ በሕግ ካልተፈቀደ በቀር በሕግ የተወሰነውን ማናቸውንም ታክስ ቀረጥ ግብር  ከመክፈል የሚያስቀር የለም ማለት በመንግሥት ገንዘብ ምንም ላይ ገደብ ማበጀት ነው፡፡ ማንኛውም የመንግሥት ገቢ ገንዘብ በሕግ እንደተፈቀደው ካልሆነ በቀር ወጪ አይሆንም ማለትም ትርጉሙ ይኸው ነው፡፡

ይህ ሁሉ ተፈጻሚ እንዲሆን ደግሞ የበጀት፣ የጊዜ ሰሌዳ ግልጽ ሆኖና ሁሉንም የመንግሥት የሥልጣን አካላት በሚገዛ ልክና መልኩ በሕግ መወሰን አለበት፡፡ ይህንን በማክበር ብቻ የማይወሰነው የመንግሥት የበጀት ዲሲፕሊንም በሕግ የተወሰነ፣ በተግባር የሚገለጽ፣ አገር የሚያውቀው ፀሐይ የሞቀው መሆን አለበት፡፡

አዳላጭ መንገድ ላይ ወድቀን ኋላቀር ከሆንባቸው ይልቁንም የኋሊት ጉዞ ከተያያዝንባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱና ትልቁ ይህ ጉዳይ ነው፡፡ ዘመናዊ የመንግሥት የገንዘብ አስተዳደርን ሀ ብለን ስንጀምር ያቋቋምነው አሠራር እያንዳንዱ የበጀት ዓመት በተፈጸመ በአራት ወር ጊዜ ውስጥ የዓመቱን የገቢና የወጪ ራፖር ለፓርላማ ማቅረብ ይህንን ራፖርም ለአደጋ ጊዜ ማቅረብ ሴክተሩም በሪፖርቱ ላይ ያለውን ነፃ አስተያየት በወር ጊዜ ውስጥ ለፓርላማ ማቅረብ ነው፡፡ ከእያንዳንዱ ነጋዴ ወይም በሕግ የሰውነት መብቱ ከተሰጠው ተቋም የሚጠበቅ ዓመታዊ ሒሳብ የመዝጋት በውጭ ኦዲተር የማስመርመር ሪፖርት የማቅረብ ግዴታ መንግሥት ላይ ሲመጣ መጠናከር እንጂ መቅረትም ሆነ መላላት በሌላ ማሳወቂያ መተካት የለበትም፡፡

የመንግሥትን ሒሳብ የሚገዛው አሁን ሥራ ላይ ያለው ሕግ ቀድሞ ስንጀምር ካቋቋምነው ከሕገ መንግሥታዊ ከፍታውና አቅሙ ወርዶ በመንግሥት የፋይናንስ አስተዳደር አዋጁና ደንቡ (አዋጅ አንቀጽ 59 እና ደንብ ቁጥር 190/2003 አንቀጽ 58) የተወሰነ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን የተወሰነውም ተልከስክሶና ተበጣጥሶ ነው፡፡ ስለሆነም የመንግሥትን የሒሳብ ሪፖርትና አፈጻጸም ሙሉ ሥዕል አያሳይም፡፡

በየዓመቱ መዝገብ ባለመያዝ የሒሳብ ሪፖርት ባለማቅረብ ወዘተ ቀምሶ ቃሉን የሚያየው የንግድም መዝጋትን የገቢና የወጪ ሙሉ ሪፖርት ማቅረብን በዚህም ላይ የነፃና የገለልተኛ ኦዲተር አስተያየት ሳይፈሩ መስማትን ከመንግሥት መማር አለበት፡፡ የመንግሥትን የዚህን ግዴታ መወጣት የሌሎች ግዴታ መወጣት ቅድመ ሁኔታ ነው አላልንም፡፡ መንግሥት ግን በነጋዴውና ይህ ግዴታ ባለበት ሰው ብቻ ሳይሆን በተራው ዜጋና በተማሪው ልብ ውስጥ ሁሉ ተጎዝጉዞ መቀመጥ የሚችለው ይህንን ሲያደርግና የበጀት ዲሲፕሊኑን ሲያከብር እንዲሁም ለዚህም በሁሉም መስክ ሲተጋ ነው፡፡

ኢትዮጵያን ግፍ ያስቆጠረው የወታደራዊው መንግሥት የተወገደው፣ የኢሕአዴግ መንግሥትም ሥልጣን የያዘው በ1982/83 የበጀት ዓመት መጨረሻ ላይ ነበር፡፡ ከሐምሌ 1 ቀን 1983 ዓ.ም. ጀምሮ ሰኔ 30 ቀን 1984 ዓ.ም. የተፈጸመው፣ የ1984 የበጀት አዋጅ በኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት የተወካዮች ምክር ቤት የታወጀው ጳጉሜን 2 ቀን 1984 ዓ.ም. ነው፡፡ የ1984 ዓ.ም. የበጀት ዓመት አልቆ ሐምሌና ነሐሴ አልፎ ጳጉሜን ውስጥ ነው፡፡ የበጀት ዓመቱ ካለቀ በኋላ ነው፡፡ ከሐምሌ 1 ቀን 1984 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን 1985 ዓ.ም. የሚዘረጋው የ1985 ዓ.ም. የበጀት አዋጅም በሽግግር መንግሥቱ የተወካዮች ምክር ቤት የታወጀው የ1984 ዓ.ም. በጀት በታወጀበት ወቅት ጳጉሜን 4 ቀን 1984 ዓ.ም. ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ከአገር ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የ1984 እና የ1985 ዓ.ም. የሁለት ተከታታይ ዓመታት የበጀት አዋጆች አንድ ላይ ታወጁ፡፡ አዋጅ ቁጥር 26/1984 እና አዋጅ ቁጥር 27/1984 የሚል ተከታታይ ቁጥርም ተሰጣቸው፡፡

ይህ ራሱ ያስገርማል፡፡ ያም ሆኖ ግን ይገባል፡፡ በጀማሪነትም በሌላ ሌላ ምክንያትም ይብራራል፡፡ አብራርተውም ያስረዱታል፡፡ የማይገባውና መረዳት የሚያዳግተው ግን አገር የተቋቋመ የበጀት የጊዜ ሰሌዳዋንና በመንግሥት ላይ መጫን የጀመረችውን የበጀት ዲሲፕሊን ያላንዳች በቂ ማብራሪያና የፖሊሲ ምክንያት ያጣችበት ሁኔታ ነው፡፡

የተወካዮች ምክር ቤት ለምን ሥራውን በሚያጠናቅቅበት ወቅት፣ የበጀቱም ዓመት በሚዘጋው ዕለት በጀቱን የሚያፀድቅበት የመጨረሻው ቀን ይሆናል፡፡ ለመጪው ዓመት በሥራ ላይ የሚውለው በጀት ቀድሞ እንደነበረው እጅግ ቢዘገይ ከመጋቢት 15 በፊት ለምክር ቤቱ ለምን አይቀርብም? ምክር ቤቱ ለምን አዲሱ የበጀት ዓመት ከሚጀምርበት ከአንድ ወር በፊት መጨረስ አይችልም? (ፓርላማው የቀረበለትን የበጀት የሕግ ሐሳብ ሳይቀበለው የቀረ እንደሆነና አዲሱ የበጀት ዓመት ከመጀመሩ በፊት ሕግ ሆኖ ያልታወጀ እንደሆነ አዲሱ የበጀት ሕግ እስኪታወጅ ድረስ የዚያው የቀድሞው ዓመት በጀት ሲሠራበት ይቆያል ወይም ሌላ አሠራር እንደተጠበቀ ሆኖ) ሐምሌ ከገባ በኋላ የፀደቀውን በጀት ማስታወቅና ያልታወጀ የሳምንት በአሠራር ደግሞ ከዚያም በላይ የሥራ ማቆም (የሥራ መፍታት) ፈቃድ በይፋ ማቋቋም አይደለም ወይ?    

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...