Monday, September 25, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከማጠናቀቂያ ጊዜያቸው ዘግይተው የተመረቁት የአዲስ አበባ መንገዶች

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን እስከ 2008 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ አስመርቃቸዋለሁ ካላቸው ግንባታቸው የተጠናቀቁ መንገዶች ውስጥ ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸውን ሰባት መንገዶች ባለፈው ረቡዕ በይፋ አስመርቋል፡፡

ባለሥልጣኑ በራሱ አቅምና በሌሎች የአገር ውስጥ ተቋራጮች ተገንብተው ከተመረቁት መንገዶች ውስጥ ከደጃች ውቤ ሰፈር-በአቡነ ጴጥሮስ አደባባይ፣ አውቶብስ ተራ ልደታ፣ ከአቃቂ ዋና መንገድ – ቂሊንጦ – ጥሩነሽ ቤጂንግ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ከአስኮ አዲሱ ሰፈር ፊሊጶስ ድልድይ መቃረቢያ መንገድ ይገኙባቸዋል፡፡

ከመስቀል ፍላወር ጐርጐሪዎስ ቦሌ ሚካኤል አደባባይ፣ ከሦስት ቁጥር ማዞሪያ ተዘንአ ሆስፒታል ታቦት ማደሪያ፣ ከየረር ሆቴል ኮተቤ ካራ መንገድና ከቅዱስ ዮሴፍ አደባባይ ካዲስኮ ደብረ ዘይት መንገድ ድረስ ያሉት መንገዶች በእዚሁ ዕለት ተመርቀዋል፡፡

በአጠቃላይ 16 ኪሎ ሜትር ርዝመት ካላቸው ከእነዚህ መንገዶች ውስጥ ከደጃች ውቤ፣ አቡነ ጴጥሮስ፣ አውቶቡስተራ ፣ አብነት ልደታ ድረስ ያለውን መንገድ በሁለት ተከፍሎ እንዲገነቡ የተደረጉት አሰርና እንይ የተባሉ አገር በቀል ኮንትራክተሮች ናቸው፡፡ በሁለት ተከፍለው ከተገነቡት መንገዶች በአሰር ኮንስትራክሽን የተሠራው መንገድ ጥር 2006 ዓ.ም. የተጀመረ ሲሆን፣ ጥር 2008 ዓ.ም. የተጠናቀቀ ነው፡፡ በአሰር ኮንስትራክሽን የተሠራው 2.4 ኪሎ ሜትር መንገድ የተገነባበት ዋጋም 507 ሚሊዮን ብር ነው፡፡

በእንይ ኮንስትራክሽን የተገነባው 2.5 ኪሎ ሜትር መንገድ የሚሸፍነው ሁለተኛውን የፕሮጀክቱ ክፍል ሲሆን፣ የጠየቀው ወጪም 355.5 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ግንባታው ጥር 2007 ዓ.ም. ተጀምሮ የካቲት 2008 ዓ.ም. ተጠናቋል ተብሏል፡፡ ከአስኮ አዲሱ ሰፈር ፊሊጶስ ድልድይ ድረስ ያለው ፕሮጀክትም በሁለት ተከፍሎ በአፍሮ ፅዮን ኮንስትራክሽንና በባለሥልጣኑ እንደተገነቡ ተገልጿል፡፡ እንደ አዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን መረጃ ከሆነ፣ ከአቃቂ ዋና መንገድ ቂሊንጦ ድረስ ያለውን የመንገድ ፕሮጀክት እሸቱ ለማ ኮንስትራክሽን፣ ከመስቀል ፍላወር እስከ ሚካኤል አደባባይ ያለውን ደግሞ በሃዚ ኮንስትራክሽን ገንብቶታል፡፡ ቀሪዎቹ አራት ፕሮጀክቶች በባለሥልጣኑ የራስ ኃይል የተሠሩ ናቸው፡፡ ከሰባቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል በተለይ አምስቱ ፕሮጀክቶች ከተያዘላቸው የግንባታ ጊዜ እጅግ ዘግይተው የተጠናቀቁ ናቸው፡፡ ባለሥልጣኑ በራስ ኃይል ገነባኋቸው ያላቸው መንገዶች ጭምር ዘግይተው የተጠናቀቁ ስለመሆናቸው ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

በተለይ ከመስቀል ፍላወር ጐርጐሪዎስ ቦሌ ሚካኤል አደባባይ የሚደርሰው 1.45 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ ለዚህ በአስረጅነት የሚቀርብ ነው፡፡ የዚህን ፕሮጀክት ግንባታ ለመጀመር የታቀደው ከ10 ዓመታት በፊት ነው፡፡ የጨረታው አሸናፊ የሆነው ሃዚ ኮንስትራክሽን ሥራውን ተረክቦ ወደ ግንባታ የገባውም በጥር 2000 ዓ.ም. ነው፡፡

ሆኖም መንገዱ ግንባታ የተጠናቀቀው በጥር 2008 ዓ.ም. ነው ተብሏል፡፡ 1.4 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመገንባት ይህን ያህል ዓመት መቆጠሩ አስገራሚ ቢሆንም ባለፈው ረቡዕ ለምረቃ በቅቷል፡፡ ከ197 ሚሊዮን ብር በላይ የፈጀው ይህ መንገድ፣ በወቅቱ ባለመጠናቀቁ ለካንትራክተሩ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ሲሰጠው ቆይቷል፡፡

በቀድሞው የከተማዋ ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ ዘመን የግንባታ ሥራው የተጀመረው ይህ መንገድ የኮንትራት ውሉ ሲፈረም ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ ውለታ የተፈጸመበት ነበር፡፡ ሆኖም ይህ ሊሆን አልቻለም፡፡ አሁን ተጠናቆ ይመረቅ እንጂ በዚህ በግንባታ ሒደት ወቅት በርካታ ችግሮች ታይተዋል፡፡ ከግንባታ ጥራት ጋር በተያያዘም ኩባንያው ሲተች እንደነበር ይታወሳል፡፡ የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ፈቃደ ኃይሌ ይህ  ፕሮጀክቱ መዘግየቱን ያምናሉ፡፡

ይህ ፕሮጀክት ብቻም ሳይሆን ሁሉም ፕሮጀክቶች ዘግይተዋል ብለዋል፡፡ ለፕሮጀክቶቹ መዘግየት ምክንያት የሆኑት ደግሞ የተለያዩ እክሎች ናቸው፡፡ የመስቀል ፍላወር ጐርጐርዮስ ቦሌ ሚካኤል አደባባይ መንገድ ዲዛይን ሁለቴ መቀየሩ አንዱ ምክንያት ነበር፡፡ በግንባታ ላይ እንዳለ የፕሮጀክቱ አንዱ አካል የሆነው ድልድይ በግንባታ በጐርፍ መወሰዱ ግንባታው ከታሰበለት ጊዜ በላይ እንዲወስድ አድርጓል፡፡ እንደ ሌሎች ፕሮጀክቶች ሁሉ የወሰን ማክበር ችግር መከሰቱ ለግንባታው ዘግይቶ መጠናቀቅ ምክንያት ሆነው እንደሚቀርቡ ኢንጂነር ፍቃደ ይገልጻሉ፡፡

በተመሳሳይ በባለሥልጣኑ በራስ ኃይል የተገነቡት የረር ሆቴል ካራ መንገድ፣ ቅዱስ ዮሴፍ፣ ቀለበት መንገድ አደባባይ ደብረ ዘይት መንገድ መገንጠያና ከሦስት ቁጥር ማዞሪያ ቀለበት መንገድ መገንጠያ ድረስ ያሉት መንገዶችም መጠናቀቅ ከነበረባቸው ጊዜ ቢያንስ በአንድ ዓመት የዘገዩ ናቸው፡፡ በባለሥልጣኑ በራስ ኃይል የተገነቡም መዘግየታቸው ለምን? ሲባል መልሱ የዲዛይን ለውጥና የወሰን ማስከበር ችግር ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ኢነጂነር ፍቃዱ ይገልጻሉ፡፡

ከሰባቱ ፕሮጀክቶች የተሻለ አፈጻጸም የታየበት የደጃች ውቤ አቡነ ጴጥሮስ መንገድ ነው፡፡ በ168.2 ሚሊዮን ብር ወጪ የወጣበትን የአስኮ አዲሱ ሰፈር ፊሊጶስ ድልድይ ፕሮጀክትን የሠራው መንገድ ግንባታም በተያዘለት ጊዜ የተጠናቀቀ ነው ቢባልም ግንባታውን ለማጠናቀቅ የገጠመው የወሰን ማስከበር ችግር ትልቅ ፈተና እንደነበር ግንባታውን ያካሄደው የአፍሮፂዮን ኮንስትራክሽን ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡

ግንባታውን በፍጥነት ለመፈፀም የገጠመው የወሰን ማስከበር ችግር ተቋቁሞ የወሰን ማስከበሩ ሥራ ከተፈጸመ በኋላ በፍጥነት መገንባት እንደተቻለ ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ መንገድ ሥራ ተጓቷል ተብሎ ከዚህ ቀደም ተቋራጩ ሥራውን እንዳይሠራ ታግዷል የሚል መረጃ የተሠራጨ ቢሆንም በምረቃው ዕለት ግን ከዚህ በተለየ የተከናወነ ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡

ከአፍሮፅዮን የተገኘው መረጃ እንደሚገልጸውም ሥራውን በወቅቱ ማጠናቀቁን የሚገልጽ ነው፡፡ እንደ ድርጅቱ ገለጻ በቦታው ላይ የወሰን ማስከበር ሳይፈጸም ለወራት የቆመ ቢሆንም ይህንን ተቋቁሞ ሥራውን ማጠናቀቅ እንደተቻለ ያመለክታል፡፡

ኢንጂነር ፍቃደ የአስኮው መንገድ መጨረሻ ላይ በፍጥነት በጥሩ አፈጻጸም ተሠርቶ የተፈጸመ ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን ሰባቱም መንገዶች ከተያዘላቸው ጊዜ በላይ የወሰዱት በወሰን ማስከበር ችግርና የዲዛይን ለውጥ ጋር የተያያዘ ነው፡ ከሰባቱ መንገዶች ውስጥ ሥራቸው በ1996 ዓ.ም. የተጀመረ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡ በተለይ ሦስት ቁጥር ማዞሪያ አካባቢ የተገነባው መንገድ ተጨማሪ ሥራዎች የተጨመሩበት በመሆኑ ጅምር ሥራው ከአሥር ዓመታት በላይ የወሰደ ነውም ተብሏል፡፡

ሦስት ኪሎ ሜትሩ ቀርቶ 0.36 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለውን የቅዱስ ዮሴፍ አደባባይ ካዲስኮ መንገድ በወራት መጠናቀቅ የነበረበት ቢሆንም ከዓመት በላይ ፈጅቷል፡፡ ጥቅምት 2007 ዓ.ም. የተጀመረው ይህ ግማሽ ኪሎ ሜትር የማይሞላ መንገድ የተጠናቀቀው ሰኔ 2008 ዓ.ም. ነው፡፡ ግንባታው 9.6 ሚሊዮን ብር ጠይቋል፡፡

የየረር ሆቴል ካራ መንገድ ደግሞ 0.92 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ቢሆንም ግንባታው ከዓመት በላይ ወስዷል 23 ሚሊዮን ብርም ወጥቶበታል፡፡ ከ3 ቁጥር ማዞሪያ ተዘንዓክ ታቦት ማረፊያ ድረስ የሚዘልቀውና 1.4 ኪሎ ሜትር ያለው መንገድ 30 ሚሊዮን ብር የጠየቀ ሲሆን፣ በእጅጉ ዘግይቶ የተጠናቀቀ መንገድ ነው፡፡

ከጥሩነሽ ቤጂንግ ቂሊንጦ ያለው የ3.4 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባት የተጀመረው ህዳር 2005 ዓ.ም. ሲሆን፣ የተጠሃቀቀው ጥር 2008 ዓ.ም. ነው፡፡ 163 ሚሊዮን ብር ፈጅቷል፡፡ የእነዚህ መንገዶች ዋነኛ ችግር የወሰን ማስከበር መሆኑን ኢንጂነር ፍቃደ ይገልጻሉ፡፡ የመስቀል ፍላወር መንገድም በተደጋጋሚ የዲዛይን ለውጥ ምክንያት የቆየ ነው፡፡ በግንባታ ሒደት ቀን ሲጠጠር ለወጪ የሚደረግ ቢሆንም ባለሥልጣኑ እነዚህ ሥራዎች በአብዛኛው በመሥራቱ ተጨማሪ ወጪ ሳይወጣ ቀርቷል፡፡ በኮንስትራክተሮች የተሠሩትም ቢሆኑ ምንም ዓይነት ክሌም ያልቀረበባቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በግንባታው ተሳታፊ የሆኑ ኮንትራክተሮች ግን ለመዘግየቱ ካሳ ይገባን ነበር ይላሉ፡፡

የከተማው የመንገዶች ግንባታ በአብዛኛው በተያዘላቸው ጊዜ የሚያልቁ አልሆኑም፡፡ ለዚህ ዋናው ምክንያት በሥራ ላይ ከሚገኙት ፕሮጀክቶች ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት የወሰን ማስከበር ችግር ያለባቸው በመሆኑ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ቢዘገይም የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተጠናቀቀና ለአገልግሎት እየበቃ ነው ተብሏል፡፡ በቅርቡም 10 መንገዶች ተመርቀው አገልግሎት እንደሚሰጡ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች