Sunday, September 24, 2023

የኤርትራ መሪዎች የእጃቸውን ያገኙ ይሆን?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ የሚሠሩ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በኤርትራ ላይ በርከት ያሉ ሪፖርቶች ሲያወጡ ቆይተዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አጣሪ ቡድን ባለፈው ዓመት ያወጣው 484 ገጽ ሪፖርት ግን ከሁሉም የላቀና በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያንን በመጠየቅና በማጥናት ተጠናክሮ የወጣ ሲሆን፣ ኤርትራ ውስጥ የሚፈጸም የሰብዓዊ መብት ጥቃት፣ አፈናና ግድያን በዝርዝር ያጋለጠም ነበር፡፡

አስመራ ላይ የከተመው መንግሥት፣ ኤርትራን ከኢትዮጵያ አስገንጥሎ መምራት ከጀመረ ባለፈው ግንቦት ወር ላይ ሩብ ክፍለ ዘመን የሥልጣን ዕድሜ ሞላው፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ‹‹በወርቅ ኢዮቤልዩ ያገናኘን›› በማለት ሌላ ሩብ ዘመን ለመግዛት ተመኝተዋል፡፡ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት የሚባል ነገር አይታወቅም፣ ከመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ውጪ ተቃዋሚ ብሎ ነገር የለም፣ የፕሬስ ነፃነትም ስሙ አይነሳም፡፡

ይኼም ብቻ ሳይሆን፣ የኤርትራ መንግሥት ሥልጣን ላይ ከወጣ ጊዜ ጀምሮ ከጎረቤት አገሮች በሙሉ የተናከሰ ሲሆን፣ እያንዳንዱ የኤርትራዊ ወጣት ወታደራዊ ግዳጅ እንዲፈጽም ይገደዳል፡፡ ከዚህም ለማምለጥ ሕይወቱ መንገድ ላይ የሚቀር ቁጥር ስፍር የለውም፡፡

መንግሥት ላይ ጥያቄ ያነሳ የትኛውም ዜጋ፣ ለእስርና ለግድያ የሚዳረግ መሆኑን በየቀኑ የሚወጡ ሪፖርቶች ሲያመለክቱ ነበር፡፡ ቡድን 15 በመባል የሚታወቁት የፓርላማ አባላትን ጨምሮ መንግሥት ላይ ጥያቄ ያነሱ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች ለእስር የተዳረጉ ሲሆን፣ በሕይወት ይኑሩ አይኑሩ የገቡበት አይታወቅም፡፡

ፍራንስ 24 በቅርቡ በሠራው ዘጋቢ ፊልም ‹‹ትንሿ ኤርትራ ወደ ትልቅ እስር ቤት ተለውጣለች›› ያለውን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በኤርትራ ዜጎች ላይ የሚፈጸም ግፍና በዓለም ላይ እየተበተኑ ስላሉት ኤርትራውያን ወጣቶች ያልዘገቡበት ወቅት የለም፡፡

ተመድ የአስመራ መንግሥት በአፍሪካ ቀንድ በተለይ ደግሞ በሶማሊያ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ አሸባሪ ቡድኖች በመደገፍና በቀጣናው ሽብርተኝነትን በማስፋፋት ምክንያት ሁለት ጊዜ ማዕቀብ ቢጥልም፣ በፕሬዚዳንት ኢሳያስ ላይም ሆነ እሳቸው በሚመሩት መንግሥት ላይ ያስከተለው የባህሪ ለውጥ እስከዚህም ነው፡፡

ለዓለም አቀፍ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት

ሰሞኑን የተመድ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያወጣው ሪፖርት ግን ከዚህ ቀደም ከወጡ መግለጫዎችና ባዶ ማሳሰቢያዎች ለየት ያለ ይመስላል፡፡ ቀደም ሲል ሁለት ጊዜ በአስመራ መንግሥት ላይ ማዕቀብ የጣለው የፀጥታው ምክር ቤት በዋናነት የጦር መሳሪያ ዝውውር ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ተግባራዊነቱም እስከዚህም ነው ተብሎ ይተቻል፡፡

ሰሞኑን የወጣው ሪፖርት፤ በኤርትራ ውስጥ ‹‹በሰብዓዊነት ላይ የተቃጣ ወንጀል›› ስለመፈጸሙ አሳማኝ ምክንያቶች የተገኙ ስለመሆኑ የሚያትት ሲሆን፣ ፈጻሚዎችም በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ፊት ቀርበው እንዲጠየቁ የሚያሳስብ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንዲጠየቁ ጥያቄ የቀረበባቸው በአገሪቱ በከፍተኛ የሥልጣን ቦታ የሚገኙት የፖለቲካና ወታደራዊ መሪዎች ሲሆኑ፣ ባርነትን፣ ሕገወጥ እስራትን፣ ተገዶ መሰወርን፣ ማሰቃየትን፣ አስገድዶ መድፈርንና መግደልን ጨምሮ የተለያዩ   ወንጀሎችንና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንደፈጸሙም ተዘርዝሯል፡፡

በብዙዎች አፍሪካዊቷ ሰሜን ኮርያ እየተባለች የምትጠራው ኤርትራ፣ ወጣቶችን በማስገደድ ወታደራዊ ግልጋሎት እንዲሰጡ ከሚያስገድዱ ጥቂት አገሮች መካከል አንዷ ነች፡፡ የመንግሥት ባህሪ በየቀኑ በርካታ ወጣቶች ከኤርትራ ድንበር እየሸሹ እንዲኮበልሉ ምክንያት ሆኗል ሲልም ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡

ፕሬዚዳንት ኢሳያስን በአካል ከሚያውቋቸው መካከል የሚካተተው አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ዳን ኮሎኔል በኤርትራ ላይ በርከት ያሉ መጽሐፍትን ያበረከተ ሲሆን፣ የኮሚሽኑን ግኝት እውነታነትን ሲያረጋግጥ፣ ‹‹በአገራቸው ራሳቸውን እንዳይገልጹ የታፈኑ የኤርትራ ወጣቶች፣ በእግር ጣቶቻቸው እንዲመርጡ እየተገደዱ ናቸው፤››  ብሏዋል፡፡

ሮይተርስ እንደዘገበው ባለፈው ዓመት ብቻ አውሮፓ ውስጥ 47 ሺሕ ኤርትራውያን የፖለቲካ ጥገኝነት የጠየቁ ሲሆን፣ በጦርነት እየታመሰች ካለችው ሶርያ በመቀጠል ኤርትር ያስቀምጣታል፡፡ እስካሁን አንድ አራተኛ ኤርትራውያን ለስደት መዳረጋቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ባለፈው ዓመት የወጣው ሪፖርት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ይኼው ባለ 94 ገጽ ሪፖርት፣ በኤርትራ ዜጎች ላይ የተፈጸመ ‹‹በሰብዓዊነት ላይ የተቃጣ ወንጀል›› [Crimes Against Humanity] በዋናነት በእስር ቤቶች፣ በወታደራዊ ካምፖችና ሌሎች ማዕከላት ላይ የተፈጸመ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

‹‹ኤርትራ በፈላጭ ቆራጭ መንግሥት የምትተዳደር ነች፡፡ ገለልተኛ ፍርድ ቤት፣ ብሔራዊ ፓርላማ ሆነ ማናቸውም ዓይነት ዴሞክራሲያዊ ተቋም ብሎ ነገር የላትም፡፡ ይህ የሕግና የአስተዳደር ዕጦት ፈጥሯል፡፡ ባለፈው ሩብ ዓመት በሰብዓዊነት ላይ ለተቃጣው ጥቃት በር ከፍተዋል፡፡ ዛሬም ወንጀሉ በመፈጸም ላይ ይገኛል፤›› ሲሉ የኮሚሽኑ አጣሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሚስተር ማይክ ስሚዝ ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም በአገሪቱ ሕግና ፍትሕ የሚከታተል ፍርድ ቤት ብሎ ነገር ስለሌለ እስከዛሬ ይኼ ሁሉ ወንጀል የፈጸሙና ያስፈጸሙ ግለሰቦች ተጠያቂ የሚሆኑበት ሥርዓት ያልተበጀ በመሆኑ በዓለም አቀፍ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲጠየቁ ሪፖርቱ ያሳስባል፡፡

ኮሚሽኑ በዚህ የተጠረጠሩ መሪዎች ከአገር አገር እንዳይንቀሳቀሱም ማዕቀብ እንዲጣልባቸውም የሚጠይቅ ሲሆን፣ የሰበሰቡት ገንዘብም እንዳይንቀሳቀስ (እንዲታገድ) ያሳስባል፡፡

ሚስተር ማይክ ሪፖርቱን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ለኤርትራ ሕዝብ ፍትሕ ለማረጋገጥ አስፈላጊ የተባለው መረጃና ማስረጃ ለፍርድ ቤት ለማቅረብ ኮሚሽኑ ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

አጣሪ ኮሚቴው ወደ ኤርትራ መጓዝ ስላልተፈቀደለት መግባት ያልቻለ ሲሆን፣ በ13 የውጭ አገሮች የሚገኙ 833 ኤርትራውያን በማነጋገር ላይ ተመርኩዞ የተጠናከረ ሪፖርት ነው፡፡ እንዲሁም በመጀመርያው ሪፖርቱ ከ160 በላይ ደብዳቤዎች ደርሰውታል፡፡

ሁለተኛው ሪፖርቱ ሲያጠናክር ግን ከ45 ሺሕ በላይ ደብዳቤዎች የደረሱት ሲሆን፣ ከሞላ ጎደል በኤርትራ መንግሥት በተደራጁ ቡድኖችና አቀንቃኞች የተዘጋጁ መሆናቸው በተለያዩ መንገዶች ማረጋገጡንም ኮሚቴው አብራርተዋል፡፡ ፈረሙ የተባሉ ሰዎች ፊርማና ምንነት ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት ጥቂቶች ለማጭበርበርና ሪፖርቱን ውድቅ ለማድረግ የተሞከረ ሴራ አካል እንደነበሩም በግልጽ አስፍሯል፡፡  

የኤርትራ መንግሥት በወጣው ሪፖርት መደናገጡ እየተነገረ ሲሆን፣ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጠው ምላሽ፣ ‹‹በኤርትራ ላይ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካና ባልበለፀጉ አገሮች ላይ የተቃጣ ጥቃት›› በማለት ሪፖርቱን ውድቅ አድርጎታል፡፡ እንዲሁም፣ የኤርትራ ባለሥልጣናት ቢቢሲን ጨምሮ ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እንደተናገሩት፣ የሪፖርቱ ግኝት አንዳች ማስረጃ የሌለውና በበላ ልበልሃ የተሰበሰበ መረጃ ነው፡፡

የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ አንዴም ሁለቴም ማዕቀብ ቢጥልም፣ የኤርትራ መንግሥት ይህንን በመጣስ የመን ላይ እየተሰባሰበ ላለው የዓረብ አገሮች ጥምረት ወታደራዊ ኃይል መስጠቱና የቀይ ባህር ዞን ነፃ የበረራ አገልግሎቶች መፍቀዱን ይታወሳል፡፡

በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች ይህንን ከማዕቀቡ መንፈስ የሚጻረር ሆኖ ሳለ ተመድ ምንም ዕርምጃ አለመውሰዱ ሲተቹ የነበሩ ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ ለቡድኑ በሰጠው ድጋፍ ምክንያት ያገኘው ገንዘብና የወደብ የ30 ዓመት ኪራይ እንደ ጠላት የምትታየው ኢትዮጵያውያን ለማተራመስ ጥቅም ላይ ሊያውለው ይችላል ተብሎ ተሰግቶ ነበር፡፡

ዓለም አቀፍ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት (ICC) በአፍሪካ ላይ በዘር ማጥፋት ወንጀል ላይ፣ በሰብዓዊነት ላይ የሚቃጣ ወንጀልንና የጅምላ ጭፍጨፋ አስፈጽሟል በሚላቸው የኬንያና የሱዳን መሪዎች ላይ የእስር ማዘዣ ቆርጦ የነበረ ሲሆን፣ አፍሪካ ኅብረት በተደጋጋሚ ድርጊቱን መቃወሙ ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ ፍርድ ቤቱን በመቃወም ግንባር ቀደም የምትጠቀስ ሲሆን፣ በኤርትራ መንግሥት ላይ ሊመሠረት የታሰበው ክስ ላይ ምን ዓይነት አቋም እንደምትወስድ ለማወቅ ብዙዎች በጉጉት የሚጠብቁት ነው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -