– አንድ ወር በአቡዳቢ ኢንተርፖል ቁጥጥር ሥር ቆይተዋል
ከባድ ተሽከርካሪ አስመጣለሁ በሚል ከ140 በላይ ከሚሆኑ ሰዎች 25 እና 50 በመቶ ቅድመ ክፍያ በመቀበል ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ሰብስበው የተሰወሩት የዙና ትሬዲንግ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘሪሁን ጌታሰው ተይዘው ሐሙስ ነሐሴ 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ከዱባይ መግባታቸውን ፌዴራል ፖሊስ ለሪፖርተር አስታወቀ፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ኢንተርፖል ዳይሬክቶሬት የዓለም አቀፍ ወንጀለኞች ክትትልና ኤክስትራዲሽን አፈጻጸም ማስተባበሪያ ኃላፊ ኢንስፔክተር ሻምበል አሰፋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከሁለት ወር በፊት ከአዲስ አበባ ፖሊስ የክስ ቻርጁ ከደረሳቸው ጀምሮ ለዓለም አቀፉ ኢንተርፖል አሳውቀው ተጠርጣሪው በወቅቱ ዱባይ እንደሚገኙና ወደየትኛውም አገር ቢንቀሳቀሱ እንዲያዙ ዓለም አቀፍ የእስር ማዘዣ አውጥተው ሲንቀሳቀሱ ነበር፡፡ በዚህም የእስር ማዘዣው ለ190 አገሮች ተበትኖ ነበር፡፡
በወቅቱ ወንጀለኛው ዱባይ መሆናቸውን ከኢምግሬሽን ያረጋገጠው ፌዴራል ፖሊስ ለአቡዳቢ ኢንተርፖል ደብዳቤ ጽፎ ተጠርጣሪው ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ እንዳይወጡና እንዲያዙ ማድረጉን ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል፡፡ የተለያዩ የማጣራት ሥራዎች እስኪሠሩ ተጠርጣሪው ለአንድ ወር ያህልም በአቡዳቢ ኢንተርፖል ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የገለጹት ኢንስፔክተር ሻምበል፣ የተጠርጣሪው ግለሰብ ጉዳይ በፌዴራል መንግሥት ሊታይ እንደሚችልና ተጠርጣሪው በአሁኑ ወቅት የሚገኙት በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
የዙና ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ባለቤት አቶ ዘሪሁን የተለያዩ ተሽከርካሪዎችንና የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችን ከ60 እስከ 75 ቀናት ውስጥ በማቅረብ ከደንበኞች በነፍስ ወከፍ ከ300 እስከ 750 ሺሕ ብር መቀበላቸው ቀደም ሲል መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የአንድ ሲኖትራክ ዋጋ 1.4 ሚሊዮን ብር በመሆኑ አብዛኞቹ ደንበኞች 50 በመቶ ክፍያ መፈጸማቸውን ገልጸው ነበር፡፡
ኩባንያው በገባው ውል መሠረት በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ተሽከርካሪዎችና ማሽኖችን ለደንበኞች ማስረከብ አልቻለም፡፡ በመጨረሻም አቶ ዘሪሁን ሲኖትራኮችንና ማሽኖችን ለማምጣት በሚል ከአገር ወጥተው በመቅረታቸው ደንበኞቹ ጉዳዩን ለፖሊስ ማመልከታቸውም ይታወሳል፡፡