Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊመንግሥት መዝናኛ ላይ የሚያተኩሩ ፕሮግራሞችን እንደማይፈልግ ብሮድካስት ባለሥልጣን አስታወቀ

መንግሥት መዝናኛ ላይ የሚያተኩሩ ፕሮግራሞችን እንደማይፈልግ ብሮድካስት ባለሥልጣን አስታወቀ

ቀን:

– በቅርቡ የሳተላይት ቴሌቪዥን ፍቃድ ሲሰጥም የፕሮግራሞች አገራዊ ፋይዳ ከግምት ይገባል

መንግሥት መዝናኛ ላይ ብቻ የሚያተኩሩ የሬዲዮም ሆነ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን እንደማይፈልግና በዚህ ረገድ ሥርጭት ውስጥ ከገቡ፣ በመግባት ላይ ካሉ ሬዲዮና የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ብሮድካስት ባለሥልጣን ገለጸ፡፡

የሚቀርቡ ፕሮግራሞች ይዘት ለማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካ ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያደርጉና ከመዝናኛ ባሻገር የሚሄዱ እንዲሆኑ ባለሥልጣኑ ከሬዲዮ ጣቢያዎች በተለይም ከአዳዲሶቹ ጋርና ከውጭ በሳተላይት ከሚተላለፉ ቴሌቪዥኖች ጋር እየተነጋገረ እንደሆነ የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ልዑል ገብሩ  ነሐሴ 2 ቀን 2008 ዓ.ም. መግለጫ በሰጡበት ወቅት ገልጸዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ከሁለት ወር በፊት በአገር ውስጥ ፍቃድ አግኝተው በሳተላይት የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ማሰራጨት የሚፈልጉ ተቋማት እንዲያመለክቱ ማስታወቁንና በዚህም 27 ፍላጎት ቢያሳዩም እስካሁን ፕሮፖዛል ያስገቡት ሦስት (ፋና ብሮድካስቲንግ፣ ዋልታና ድምፀ ወያኔ ትግራይ) ብቻ መሆናቸውን አቶ ልዑል ተናግረዋል፡፡ ቀሪዎቹ እስከ ሰኔ መጨረሻ ፕሮፖዛላቸውን ያስገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ፤ በምዘናውም የፕሮግራሞች ይዘት አገራዊ ፋይዳ ዋነኛ መስፈርት እንደሚሆን አቶ ልዑል ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የገንዘብ አቅም፣ የአመራር ብቃትና የሰው ኃይል ሌሎች የመመዘኛ መስፈርቶች ይሆናሉ፡፡

ባለሥልጣኑ ለምን ያህል በሳተላይት ቴሌቪዥን ለሚያሰራጩ ጣቢያዎች ፍቃድ መስጠት እንደሚያስብ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ልዑል፣ ‹‹መንግሥት መጨረሻ ላይ ይወስናል፡፡ ብቃት ያላቸውና መስፈርቶችን ለሚያሟሉ ፍቃድ ይሰጣል፤›› የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡

ባለሥልጣኑ እስካሁን በአማርኛ በሳተላይት ለሚተላለፉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ፍቃድ ባይሰጥም ዋልታ ስርጭት መጀመሩን በሚመለከት ለቀረባቸው ጥያቄ ሲመልሱ ‹‹በውይይት ወደ ሕጋዊ ሥርዓቱ ተመልሶ እንዲሠራ እየተነጋገርን ነው፤›› ብለዋል አቶ ልዑል፡፡

ከውጭ አገር በአማርኛ በሳተላይት የሚያስተላለፉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ፍቃድ ያወጡት ከተቋቋሙበት ከውጭ አገር ቢሆንም፣ ተጠያቂ የሚሆኑበት ነገር እስካስተላለፉ ድረስ ኃላፊነት የሚወስዱበት መንገድ መኖሩን ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ምንም እንኳን ፍቃድ ያገኙት ከተቋቋሙበት አገር ቢሆንም ለፕሮግራሞቻቸው የብቃት ማረጋገጫ የሚሰጠው ባለሥልጣኑ በመሆኑ፣ ፕሮግራሙን ለማስተላለፍ የብቃት ማረጋገጫ የወሰደው አካል ተጠያቂ የሚሆንበት አሠራር አለ፤›› ብለዋል፡፡

የአየር ሰዓት ገዝተው የተለያዩ ፕሮግራሞችን የሚያስተላልፉ አካላትን ሳይሆን ዋናውን ቴሌቪዥን ጣቢያ የሚያስጠይቅ ነገር ሲተላለፍ ደግሞ ጣቢያው የንግድ ፍቃድና ቢሮ እዚህ ስላለው እንደ ሁኔታው የወንጀል ሕግ፣ የሽብር ሕግና ሌሎችንም ሕጎች መሠረት በማድረግ ኃላፊነት እንዲወስድ እንደሚደረግ አቶ ልዑል ያስረዳሉ፡፡

ባለሥልጣኑ ከውጭ አገር በሳተላይት ለሚተላለፉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ፍቃድ አይሰጥም አይከለክልም ማለት መቆጣጠር የሚችልበት ምንም ዓይነት መንገድ የለም ማለት እንዳልሆነና ይልቁንም ከጣቢያዎቹ ጋር እንደሚነጋገርና እንደሚመካከር ጠቁመዋል፡፡

ከመንግሥት በቂ መረጃ አለማግኘትን ጨምሮ የግሉ ሚዲያ የተለያዩ ችግሮች እንዳሉበት ስለዚህም ለግሉ ሚዲያ ድጋፍ ለማድረግ መታሰቡ በመግለጫው ላይ ተጠቁሟል፡፡ በዚህ ረገድ ከታሰቡ ነገሮች መካከል የግሉ የኅትመት ሚዲያ በተሻለ የመንግሥት መረጃ የሚያገኝበትን መንገድ ማመቻቸትና የመንግሥት ማስታወቂያዎችን በፍትሐዊነት እንዲያገኝ ማድረግ እንደሚጠቀሱ አቶ ልዑል ገልጸዋል፡፡ በቅርቡ አሥር የሬዲዮ ጣቢያ ፍቃዶች እንደሚሰጡም ተጠቁሟል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...