Tuesday, March 5, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

‹‹ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ…››

በአሁኑ ወቅት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ተቀምጧል፡፡ ይኼ ስብሰባ በአገሪቷ ላይ ነጥረው የወጡት ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ እንዲበጅላቸው መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ ስለሆነም ኢሕአዴግ ይህን ስብሰባ በአግባቡ ከተጠቀመበት ሕዝቡ በመንግሥትና በፓርቲው ላይ ያለው እመነት እንዲጠናከር የሚረዳ መድረክ ነው፡፡

ሕዝብ ከመንግሥት ብዙ ይጠብቃል፡፡ በመልካም አስተዳደር ችግር ክፉኛ እየተማረረ ነው፡፡ በተለያዩ የመንግሥት ደረጃ ላይ የሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሕዝብን ከማገልገል ይልቅ ለራሳቸው ጥቅም ሲሯሯጡ ይታያሉ፡፡ በመሆኑም በርካታ ባለሥልጣናት ከጥቃቅን እስከ ትላልቅ ጉቦ ካልተቀበሉ በስተቀር ሕዝቡን በቀና መንፈስ ማገልገል ካቆሙ ሰነባበቱ፡፡ በእነዚህ የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ የማያዳግም ዕርምጃ መውሰድ የሚገባው ኢሕአዴግ ግን፣ በዚህ ረገድ በጣም መጓተትና መንቀራፈፍ ይታይበታል፡፡ ይህ ደግሞ የሕዝብን ትዕግሥት እያሟጠጠ ነው፡፡ ስለዚህ ሕዝብን እያማረሩና እያንገሸገሹ ያሉ ማናቸውም የመንግሥት ባለሥልጣናትና ኃላፊዎች ላይ የማያዳግም ዕርምጃ መወሰድ አለበት ብለን እናምናለን፡፡

የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ ከግምገማ ባለፈ ቁርጠኛ የሆነ ዕርምጃ መወሰድ አለበት፡፡ ሕዝቡም ይህን ማየት ይፈልጋል፡፡ ያኔ ሕዝብ መንግሥት ላይ ያለው እምነት ይጨምራል፡፡ ስለዚህም መንግሥት ለምናነሳቸው ሦስት ነጥቦች ከበፊቱ በበለጠ መልኩ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ በፍጥነት ወደ ዕርምጃ መግባት እንዳለበት እናምናለን፡፡

  1. የመልካም አስተዳደር ችግር

ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ 25 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ኢሕአዴግ በተደጋጋሚ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዳሉ ቢያምንም፣ በተጨባጭ ግን ምንም ዓይነት መፍትሔ ማግኘት አልቻለም፡፡ ይህ በሕዝብ ዓይን ሲታይ ትልቅ ውድቀት ነው፡፡ አሁንም ኢሕአዴግ ራሱን መፈተሽ አለበት፡፡ በተለያዩ ደረጃዎች ላይ የሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናት ዋነኛ ሥራቸው ሕዝብን ማጉላላትና መበደል እስኪመስል ድረስ፣ ሕዝቡን በመልካም አስተዳደር ችግሮች ሲያሰቃዩት ይታያሉ፡፡ በመሆኑም ሕዝብን አገለግላለሁ የሚል መንግሥት እንደነዚህ ዓይነት ባለሥልጣኖችን ከውስጡ እስካልነቀለ ድረስ፣ ሕዝብን ማገልገል የህልም እንጀራ ነው የሚሆነው፡፡ በመሆኑም ኢሕአዴግ በዚህ አቅጣጫ ሥር ነቀል ለውጥ ማምጣት አለበት እንላለን፡፡  

በተደጋጋሚ ኢሕአዴግ በአንድ ምሽት ለውጥ አይመጣም ቢልም፣ በ25 ዓመታት ውስጥ ግን ከ9,125 ምሽቶች በላይ ማለፋቸውን መዘንጋት የለበትም፡፡ ይህ በጣም አፋጣኝ የሆነ መፍትሔ ይሻል፡፡ በዚህ ላይ ኢሕአዴግ ቀንና ሌሊት መሥራት አለበት እንላለን፡፡ 

  1. ሙስና

አገሪቷን ወደኋላ እየጐተቱ ካሉና በጣም መሠረታዊ ችግሮች ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ ዋነኛው ሙስና ነው፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ሠራተኞች ቀላል በማይባል መልኩ በሙስና መዘፈቃቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ይህንንም ኢሕአዴግ ሕዝቡም ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ የሚያስተዛዝበው ግን ሙስናን ለማጥፋት አፋጣኝ የሆኑ ዕርምጃዎች አለመወሰዳቸው ነው፡፡

ሙሰኛ የሆነ ባለሥልጣንን ያለምንም ርህራኄ ለፍርድ አለማቅረብ ትልቁ ውድቀት ነው፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ ሙሰኛ ባለሥልጣናት ፍርድ ቤትና ማረሚያ ቤት መመላለስ ሲገባቸው፣ በተቃራኒው ከተማ ውስጥ በማን አለብኝነት ሲንፈላሰሱ ይታያሉ፡፡ ይህን ሕዝብ ያያል ደግሞም ይታዘባል፡፡

ኢሕአዴግ ይህን ችግር የማስተካከልና መፍትሔ የመስጠት ትልቅ አገራዊ ኃላፊነት በጫንቃው ላይ መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሙሰኞች እየፈረጠሙና እየደለቡ በሄዱ ቁጥር፣ ጫንቃውን ሰብረው ይጥሉታል፡፡ ይህም ለፓርቲውም ሆነ ለሕዝብና ለአገር ትልቅ ኪሳራ ያስከትላል፡፡ ምንም እንኳን ኢሕአዴግ ሙሰኞች በአንድ ሌሊት ማጥፋት አይቻልም ቢልም፣ በተገላቢጦሽ ሙሰኞች በአንድ ሌሊት ሲከብሩ ይስተዋላል፡፡ ስለዚህ ይህንን አንገብጋቢ ጉዳይ ያለምንም ዕረፍት ዘላቂ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል፡፡  

  1. ብቃት ማነስ

ኢሕአዴግ ከበፊት ጀምሮ የሚለው አንድ ብሂል አለው፡፡ ‹‹የመንግሥት ሹመት በፓርቲ ታማኝነት›› የሚል፡፡ ይህ ደግሞ አገርን እያጠፋ ያለ አመለካከት ነው፡፡ የመንግሥት ሥልጣንና ኃላፊነት ላይ የሚቀመጡ ሰዎች ከሙያዊ ብቃት ይልቅ የኢሕአዴግን የፖለቲካ አመለካከት መቀበላቸው በቂ ነው፡፡ በመሆኑም የመንግሥት ሥልጣን ላይ የሚቀመጡ ሰዎች በብሔር ተዋጽኦ፣ በኮታ፣ ለፓርቲው ባላቸው ታማኝነትና በተመሳሳይ ውኃ በማያነሱ መሥፈርቶች ነው፡፡ ይህ ደግሞ በመንግሥት ሆነ በሕዝብና በአገር ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳለው እየታየ ነው፡፡

ዓለም በአሁኑ ወቅት የደረሰችበት ደረጃ ለማንም ሚስጥር አይደለም፡፡ ስኬትን ባስመዘገቡ በርካታ አገሮች የሚታየው ደግሞ ብቃትን ያማከለ ሹመት ነው፡፡ ኢሕአዴግ ይህ ሊሰርጽበት ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ ብቃት የሌላቸው ሰዎች ሥልጣን ላይ መቀመጣቸው ብቃት ያላቸውና አገርን ማገልገል የሚፈልጉ ግለሰቦችን ተስፋ ያስቆርጣል፤ እንዲያውም ያርቃል፡፡ ስለዚህ በዚህ ምክንያት ሊደርስ የሚችለው ኪሳራ ለመታደግ፣ መንግሥት ሳይውል ሳያድር ብቃት የሌላቸውን የመንግሥት ባለሥልጣናትና ኃላፊዎች በፍጥነት ከሥልጣናቸው ማንሳት አለበት እንላለን፡፡

በአጠቃላይ የኢሕአዴግ የቤት ሥራዎች ቀላል የማይባሉ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህ ጥያቄ ደግሞ የ90 ሚሊዮን ሕዝብ ጥያቄ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በአንድ ምሽት አይቀየርም የሚለው አባባል ተፍቆ፣ ትናንት ነበር ማለቅ የነበረበት በሚለው መተካት አለበት፡፡ ኢሕአዴግ ከምንም በላይ ሊፈራው የሚገባው ሕዝብ ነው እንጂ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ኃላፊዎችን አይደለም፡፡ ምክንያቱም መንግሥትን የሾመው ሕዝብ እንደመሆኑ መጠን፣ መልሶ የማውረዱም አቅሙ ስላለው ኢሕአዴግ ቆም ብሎ ሕዝብን ማዳመጥ አለበት፡፡

እንግዲህ ‹‹ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ›› የሚለውን አባባል ኢሕአዴግ ሊረሳው አይገባም፡፡ ከረሳው ግን ተረቱ እንደሚለው ድንጋይ ነው ብለው አውጥተው ይጥሉሃልና ጠንቀቅ ማለቱ ይበጃል፡፡

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...

ምርጫ ቦርድ ፓርላማው ያፀደቀለትን 304 ሚሊዮን ብር አለማግኘቱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ሰኔ 2016 ዓ.ም. በአራት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሰብዓዊ ቀውስና በውድመት የታጀቡ ግጭቶች በአስቸኳይ ይቁሙ!

በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ተጀምሮ አማራና አፋር ክልሎችን ያዳረሰው የሁለት ዓመቱ አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ቢገታም፣ ከነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል የተጀመረው...

ታላቁ የዓድዋ ድል ሲዘከር የጀግኖቹ የሞራል ልዕልና አይዘንጋ!

የታላቁ ዓድዋ ድል 128ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሲዘከር፣ ለአገርና ለሕዝብ ክብር የሚመጥኑ ተግባራት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በዓድዋ ከወራሪው ኮሎኒያሊስት ኃይል ጋር ተፋልመው ከትውልድ ወደ...

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...