ሰሞኑን የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በከፍተኛ አመራሩ ላይ ጠንካራ ግምገማ ማካሄዱ ተሰማ፡፡
በአገሪቱ የሚታዩት የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰባቸው መጥተው ገዢው የኢሕአዴግ ፓርቲ ላይ ጥያቄ እያስነሱ ይገኛሉ፡፡ ላለፉት 25 ዓመታትም በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ የበላይነትን የተጐናፀፈው ኢሕአዴግ፣ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ቁረጠኝነት አይታይበትም ተብሎ የሰላ ትችት እየቀረበበት ይገኛል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት በከፍተኛ አመራሩ ላይ ጠንከር ያለ ግምገማ ያካሄደው የኢሕአዴግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ በተለይ በመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ በሙስናና ከአቅም ማነስ ጋር በተያያዙ አጀንዳዎች ላይ መወያየቱን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በዚህ ግምገማ በመንግሥትና በፓርቲው አመራር ውስጥ የአቅም ማነስ ችግር እየታየ መሆኑ በስብሰባው ተገልጿል፡፡ በመሆኑም ያለብቃት የመንግሥትን ሥልጣን የያዙ ሹመኞች መኖራቸው በግልጽ በስብሰባው ተነስቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ሹመኞች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን በአግባቡ መምራት አለመቻላቸው ተወስቷል፡፡ ምንጮች እንደገለጹት፣ በስብሰባው ላይ ግለሰቦች በግልጽ በስም እየተጠሩ ጠንከር ያለ ግምገማ ተደርጐባቸዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ የሀብት ምዝገባ ከተካሄደ በኋላ ከገቢያቸው በላይ ሀብት ያላቸው ባለሥልጣናት ላይ ዕርምጃ ይወሰዳል ተብሎ ቢጠበቅም፣ ይህ ሳይሆን መቅረቱ በስብሰባው ላይ ተነስቷል፡፡ በርካታ የመንግሥት ባለሥልጣናት ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ባለቤት ከመሆናቸው ባሻገር፣ ከገቢያቸው በላይ ሀብት ማፍራታቸው በስብሰባው ተገልጿል፡፡ ይህም ጉዳይ ለመልካም አስተዳደር ችግሩ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑ ተገልጾ፣ በእነዚህ ባለሥልጣናት ላይ ዕርምጃ መወሰድ አለበት ተብሏል፡፡
ከዚህ የከፍተኛ አመራሩ ግምገማ በኋላ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ግምገማዎች በተለየ ፓርቲው በባለሥልጣናት ላይ ዕርምጃ ይወስዳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮች ተናግረዋል፡፡
ከወራት በፊት በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ከፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃይል ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በተሠራው ጥናት መነሻነት ከፍተኛ የፓርቲው አመራሮች መወያየታቸው ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት አመራሮች በነበሩበት በዚህ ስብሰባ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አስመልክቶ አመራሮቹ በግልጽ ሲተቻቹ በቴሌቪዥን መተላለፉም ይታወሳል፡፡ ምንም እንኳን በዚያ ስብሰባ አመራሮቹ በግልጽ ሲተቻቹ መታየቱ በሕዝብ ዘንድ አድናቆት የተቸረው ቢሆንም፣ ከውይይቱ በኋላ ስለሚመጣው ለውጥ ግን ብዙዎች ጥርጣሬ ነበራቸው፡፡ ከስብሰባውም በኋላ በአገሪቱ የተንሰራፋውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ በመንግሥት በኩል የተጠበቀውን ያህል ለውጥ አለመታየቱ ሲያስታቸው ቆይቷል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት በተካሄደው ጠንካራ ግምገማ ግን ባለሥልጣናት በግልጽ በስም እየተጠሩ በአቅም ማነስና ምንጩ ባልታወቀ ሀብት የተገመገሙ ሲሆን፣ በቀጣይ ዕርምጃዎች ይወሰድባቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮች ተናግረዋል፡፡