የትግራይ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት ባካሄደው 13ኛ መደበኛ ጉባዔ፣ ከዚህ ቀደም በፌዴራል መንግሥት ሚኒስትርና ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ያገለገሉ ባለሥልጣናትን በተለያዩ ዘርፎች የክልሉ ኃላፊ እንዲሆኑ ሹመታቸውን አፀደቀ፡፡
በዚህም መሠረት ጥቅምት 10 ቀን 2011 ዓ.ም. መደበኛ ጉባዔ ያደረገው የክልሉ ምክር ቤት ከዚህ ቀደም የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር የነበሩትና በቅርቡ በአቶ አህመድ ሽዴ የተተኩት አብርሃም ተከስተን (ዶ/ር)፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አድርጎ ሾሟል፡፡
በተጨማሪም የትራንስፖርት ሚኒስትር ደኤታ የነበሩት አቶ አርዓያ ግርማይ፣ የመቀሌ ከተማ ከንቲባ ሆነው መሾማቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ቀደም ሲል የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ነበሩ፡፡
በተመሳሳይ ከዚህ ቀደም የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ፣ ከዚያም የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ቴዎድሮስ ገብረ እግዚአብሔርን የውኃ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አድርጎ ሾሟል፡፡
ምክር ቤቱ ከ18 የክልሉ ቢሮዎች ለዘጠኙ አዳዲስ ኃላፊዎችን ሹመት ሲያፀድቅ፣ ከእነዚህም ውስጥ አምስቱ ሴቶች ናቸው፡፡ ይህም የክልሉን ሴት የቢሮ ኃላፊዎች ቁጥር ሰባት አድርሶታል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የደኅንነት አማካሪ ሆነው መሾማቸው ተሰምቷል፡፡ በተመሳሳይ ምክር ቤቱ የዞን አስተዳዳሪዎችን ሹመት አፅድቋል፡፡