ከጥቅምት 11 እስከ 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ለሁለት ቀናት የተሰጠው የከፍተኛ አመራሮች ስትራቴጂካዊ የአመራር ሥልጠና ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ሃያዎቹን ካቢኔ ለሚመሩ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ ኃላፊዎች የ100 ቀናት ተቀዳሚ ስትራቴጂካዊ ተግባራትን አሳውቀዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍፁም አረጋ እንዳስታወቁት፣ ከፍተኛ አመራሮቹ በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ አስተማማኝና ተቋማዊ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ለዚህም የማያቋርጥ ትምህርትና የአፈጻጸም ብቃትን ልማድ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ተነግሯቸዋል፡፡ የ100 ቀናት ኃላፊነታቸውም ትኩረት ዓላማ ያለው አፈጻጸምና ውጤታማነት መሆን እንዳለበት፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መብራራቱን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ የአደረጃጀት ለውጥ የተካሄደባቸው ተቋማት በፍጥነት ለሠራተኞቻቸው ገለጻና የተግባር ሥልጠና በመስጠት ሥራ እንዲጀምሩ፣ የቢሮና የንብረት ርክክብ በፍጥነት እንዲከናወን፣ በየደረጃው የሚገኙ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ተልዕኮአቸውን ለመወጣት የሚያስችላቸው ሥልጠና ተሰጥቶ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማስቻል እንደሚገባ ለአመራሮቹ ገለጻ ተደርጓል፡፡ ተቋማቱ የአገርን ሰላምና ደኅንነት ከማረጋገጥ ጀምሮ ግጭቶችን ማስወገድና ብሔራዊ መግባባት መፍጠር፣ ከአገሮች ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና ወዳጅነትን ማጠናከር፣ የአገር የሀብት ምንጮችን ማሳደግና ብድር የመክፈል አቅምን ማጎልበት፣ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር፣ የሕግ የበላይነትን ማስፈን፣ የሕግና የፍትሕ ተቋማትን በማጠናከር ሕጎችን ማሻሻል፣ የግብርና ምርታማነትን ማሻሻልና ማዘመን፣ የአገሪቱን ሉዓላዊነት ማስከበርና የባህር ኃይል ማደራጀት፣ ወዘተ. ትኩረት እንዲሰጥባቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ መስጠቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሳምንት ሃያ ሚኒስትሮችና ኃላፊዎች ያሉት ካቢኔ በፓርላማ ማፀደቃቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ አሥር የሴት ሚኒስትሮች ተሹመዋል፡፡ በምሥሉ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጠቅላይ ሚኒስትር አዳራሽ ለካቢኔ ሚኒስትሮች ማብራሪያ ሲሰጡ ይታያሉ፡፡