Wednesday, October 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያ ተቋርጦ የነበረው የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ድርድር እንዲጀመር ጠየቀች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ላለፉት ስድስት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ድርድር እንዲንቀሳቀስ ኢትዮጵያ ጥያቄ አቀረበች፡፡

የዓለም ባንክ የመረጃና የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር ኪዝ ሮልዌል ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እ.ኤ.አ. በ2012 ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት በድጋሚ እንዲንቀሳቀስ ጥያቄ ቀርቧል፡፡

በዓለም ንግድ ድርጅት የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚመለከተው ኮሚቴ ሊቀመንበር በጡረታ በመሰናበታቸው ኢትዮጵያ ላቀረበችው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ እንዳልተሰጠ የገለጹት ኃላፊው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ እንደሚሰጥና ድርድሩ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እ.ኤ.አ. በ2003 ድርድር ብትጀምርም፣ በ2012 መቋረጡን አስታውሰው፣ በዚህ ሒደት ውስጥ ኢትዮጵያ የባለ ብዙ ወገን ድርድር ጨርሳ ወደ ተናጠል ድርድር መሸጋገሯን ገልጸዋል፡፡

ከዓለም የንግድ ድርጅት አባል አገሮች ጋር የሚደረገው የተናጠል ድርድር ከባድ እንደሆነ ያስረዱት ዳይሬክተሩ፣ ኢትዮጵያ የሸቀጦች ታሪፍ ምጣኔዋን ለድርድር ማቅረቧን አስታውቀዋል፡፡ ለድርድር የቀረበው ታሪፍ እንዲቀንስ አገሮች ጥያቄ ማቅረባቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከባድ የሚባለው ድርድር ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ክፍት እንድታደርግ የሚመለከት መሆኑን፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በዚህ ጉዳይ ላይ እስካሁን ምንም አለማለቷን ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያ ድርድሩ እንዲቀጥል ጥያቄ ማቅረቧን አድንቀዋል፡፡

 ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ድርድር በፍጥነት ማጠናቀቅ እንደሚፈልጉ የሚታወቅ ሲሆን፣ ይህም በመስከረም ወር 2011 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ተገልጿል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪና የዓለም ንግድ ድርጅት ዋና ተደራዳሪ አድርገው አቶ ማሞ ምሕረቱን በቅርቡ መሾማቸው ይታወሳል፡፡ አቶ ማሞ በዓለም ባንክ ለረዥም ዓመታት ያገለገሉ ባለሙያ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች