በዘንድሮ የአይኤኤፍ የዓለም ምርጥ አትሌቶች ዕጩ ውስጥ በሁለቱም ጾታ የኢትዮጵያውያን ስም አልተጠቀሰም፡፡ ጥቅምት 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ድምፅ መስጠት የሚቻልበት ጊዜን ያበሰረው አዘጋጁ አካል ይፋ ካደረግናቸው አሥር ሴት አትሌቶችን ውስጥ የኢትዮጵያውያኑ ስም የለበትም፡፡
ስማቸው ከተጠቀሱት አሥር እንስቶች ውስጥ ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሲፋን ሀሰን በቀዳሚነት ተጠቅሳለች፡፡ አትሌቷ በአኅጉራዊ ውድድር ላይ በ3,000 ሜትር ያስመዘገበችው ውጤት፣ በአውሮፓ የ5,000 ሜትር ክብረ ወሰን ባለቤትና ግማሽ ማራቶን አሸናፊ መሆኗ ተመራጭ አድርጓታል፡፡ ሲፋን ትውልደ ኢትዮጵያዊት ስትሆን ለኔዘርላንድ በመሮጥ ላይ ትገኛለች፡፡ በተለይ አትሌቷ በመካከለኛ ርቀት ላይ የምታደርጋቸው ውድድሮች ላይ ለኢትዮጵያውያን ፈታኝ ስትሆን ይታያል፡፡
የዓለም አቀፍ ምርጥ የአትሌቲክስ ሽልማትን ማሸነፍ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በ1990 ዓ.ም. ፈር ቀዳጅ ሲሆን በ1996 እና 1997 ዓ.ም. ቀነኒሳ በቀለ ከአሸነፈ በኋላ በወንዶቹ ስሙ የተነሳ የለም፡፡
በሴቶች መሠረት ደፋር በ1999 ዓ.ም.፣ ገንዘቤ ዲባባ በ2007 ዓ.ም. እንዲሁም አልማዝ አያና በ2008 ዓ.ም. አሸናፊ መሆን ችለዋል፡፡ አልማዝ አያና ዓምና ለፍጻሜው ታጭታ እንደነበር ይታወሳል፡፡