በታከለ ታደሰ
የዚህ ጽሑፍ መነሻ በሪፖርተር ጋዜጣ መስከረም 10 ቀን 2011 ዓ.ም. የቀረበው ‘ቋንቋ የማን ነው?’ የሚለው የአሰፋ አደፍርስ (ዶ/ር) ጽሑፍ ነው፡፡ መነሻ ሊሆን የቻለውም በቀረበው ጥያቄ ርዕስ ሥር አንድ አጭር መጽሐፍ የጻፍኩት እኔ ስለሆነኩ ነው፡፡ ከዚች ‘ቋንቋ የማን ነው?’ አጭር ጽሑፍ ጋር የተቀራረበች አንድ ሌላ አጭር መጽሐፍ ‘የቋንቋ አጠቃቀም በኢትዮጵያ’ በሚል ርዕስ ጽፌም በ2010 ዓ.ም. ታትሞ ወጥቷል፡፡ ሁለቱንም ብታነቧቸውና ኢትዮጵያዊ ምሁራን ሁሉ በቀረበው ሐሳብ ላይ ብትነጋገሩበት፣ ብትወያዩበትና ለግንዛቤ ሐሳብ መጨበጫ መሠረት ብታደርጓቸውና ለውሳኔ ብታቀርቧቸው የምሁራንን በአገራችን በቋንቋ አጠቃቀም ለይ ያላቸውን አቋም ለመግለጽ ይጠቅማል እላለሁ፡፡ ለዚሁም ይረዳ ዘንድ በዚች አጭር መጽሐፍ ውስጥ ቋንቋ ምን እንደሆነና የማን እንደሆነ የደረስኩበትን ልንገራችሁ፡፡ ልክ አይደለህም የሚል ምሁር ካለ ግን ከአዕምሮው በሚፈልቅ አስተሳሰብ እንጂ፣ ከስሜት መንጭቶ በሚፈነቅል ሚዛን እንዳይለካው አደራ እላለሁ፡፡
ይህንን ‘ቋንቋ የማን ነው?’ ጥያቄ ያነሳሁት ሕወሓት (የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር) አትዮጵያን በሥሩ ካደረገ ጀምሮ የአፍ መፍቻ መነጋገሪያቸው አማርኛ ያልሆኑ ሁሉ አማራዎች አፋችንን ዘግተው እንዳንናገር አደረጉን፣ አፈኑን፣ ጨቆኑን የሚል ነጋሪት ጎስሞ በድፍን ኢትዮጵያ አሠራጭቶ በአማርኛ አፍ ያልፈቱ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚያንፀባርቁትን እሮሮና ምሬት ሰምቼ ነው፡፡ እንደምገምተው ይህንን አስተሳሰብ ለሌሎቹ ቋንቋ ተናጋሪዎች ሁሉ ያስጨበጣቸው ሕወሓት ነው እላለሁ፡፡ ነገር ግን ከመነሻው መታወቅ ያለበት ቋንቋ በተፈጥሮም ሆነ በሕግ ማንም የኔ ነው ብሎ መከራከር አይችልም፡፡
ለምሳሌ የኢትዮጵያ መንግሥት ኦሮሚኛ ኢትዮጵውያን ሁሉ አንዲማሩትና ሁላችንም በኦሮሚኛ ብቻ መናገር፣ መማርና ሥራን ሁሉ ማከናወን አለብን፣ ማዳበርም አለብን ብሎ አዋጅ ቢያውጅ ኦሮሞዎች ተደራጅተው በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ እኛ ሳንፈቅዳላችሁ በእኛ ቋንቋ መጠቀም አትችሉም ብለው የሕግ ጥያቄ ማቅረብ ይችላሉ? በኦሮሚኛ ስለተጠቀምን ኪራይስ ሊጠይቁ ይችላሉ? በኦሮሚኛ አፋቸውን ያልፈቱ ኢትዮጵያውያንስ ቢሆኑ እኛ አዕምሮአችን ኦሮሚኛን ለማወቅ፣ ለመማርም ሆነ ለመረዳት ፈጽሞ አይችልም፡፡ ኦሮሚኛንም ለመናገርም ሆነ ለማወቅ አልተፈጠርንም ብለው ሊከራከሩና ለዚህም ማረጋገጫ ማቅረብ ይችላሉ? እንዲህ ዓይነት ክርክርም ሆነ አስተሳሰብ ሊመላለስ የሚችለው በመኃይም አዕምሮ ውስጥ ብቻ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ታዲያ አማርኛስ ለኢትዮጵያውያን ለሁላችንም በመግባቢያና በማቀራረቢያ፣ በመማሪያና አገር በማሰተዳደር መሣሪያነቱ ብንጠቀምበት ምን ጉዳት አለው? ይህ ቢሆንም የማንንም ኢትዮጵያውያን ማንነት በምንም መንገድ ሊያጠፋ፣ ሊጎዳ ወይም ሊያዋርድ አይችልም፡፡
ስለቋንቋ ምንነት ጠለቅ ብሎ ለማወቅ ለመሆኑ ቋንቋ ከምንና ከምን የተፈጠረ ነው? በአጭሩ ቋንቋ በመጀመርያ ምንም ቋንቋ ያልነበራቸው ሰዎች ለመጀመርያ ጊዜ አንድ ቋንቋ አንድ ቦታ ብቻ የፈጠሩት ከድምፀ ነገርና ከነገረ ነገር ነው፡፡ እጅግ በጣም ብዙ ዓይነት የቋንቋ ድምፀ ነገሮች እየተፈጠሩ ሄደው ብዙ ዓይነት ቋንቋዎች ተፈጠሩ፡፡ የቋንቋ ድምፆች ግን ከሰው አንደበት የሚፈልቁ ናቸው፡፡ ነገረ ነገርስ? ጠቅላላ ፍጥረታት ሁሉ በዓይን የማይታዩትን ጨምሮ ነገረ ነገሮች ናቸው፡፡ ለምሳሌ እኔ ነገረ ነገር ነኝ፡፡ ታከለ የሚለው ቃል እኔን የያዘ ድምፀ ነገር ነው፡፡ ልክ ውኃ ወይም ሌላ የፈሳሽ ዓይነት ብርጭቆ ውስጥ ወይም ሌላ የፈሳሽ መያዣ ውስጥ ቢጨመር እንደሚይዘው ሁሉ፣ ታከለ የሚለው ድምፀ ነገር እኔን ይዟል ማለት ነው፡፡ ነገረ ነገር የያዘ ድምፀ ነገር ቃል ይባላል፡፡ ነገረ ነገር ያልያዘ ድምፀ ነገር ቃል አይሆንም፣ ለምሳሌ ፐደም፡፡ እንግዲህ ድምፀ ነገር እንጂ ነገረ ነገር ይህንንም ያህል ጎልቶ ሊያለያየን የሚችል አይደለም፡፡ ለምሳሌ ስልቻና ቀልቀሎ፡፡ ነገረ ነገሩ አንድ ነው፡፡
ሌላው ወሳኙ ጥያቄ ቋንቋ ምንድነው? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ቀጥታ መልሱ ቋንቋ መሣሪያ ነው የሚለው ነው፡፡ ለምሳሌ ቋንቋ እንማርበታለን፣ እንወያይበታለን፣ የአገርን አስተዳደር እናከናውንበታለን፣ ጦርነት በሚገጥመን ጊዜ ጠላትን የሚያርበደብድ ወሬ እንነዛበታለን፣ እናስፈራራበታለን፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ልሳነ ብዙ አገሮች ሕወሓት እንዳደረገው ቋንቋን መሣሪያ በማድረግ ሕዝቡን አለያይተን ማበጣበጥና ማተራመስ እንችላለን፡፡ በተቃራኒው ከ90 ቋንቋዎች ውስጥ አንዱን ቋንቋ መርጠን ወይም አሁን በተግባር ላይ ያለውን ጥቅሙንና ጉዳቱን በጥሞና አመዛዝነን ጠቅላላው ሕዝብ እንድንነጋገርበትና ወሳኝ የሆኑ ተግባራትን እንዲያከናውንባቸው በማድረግ ሕዝቡን ማቀራረብ እንችላለን፡፡ እንዴት? በመጀመርያ መታወቅ ያለበት ኢትዮጵያን እጅግ በጣም ያተራመሳት የኢትዮጵያውያን ምሁራን ምሁር የተባሉበትን ዕውቀት ያካበቱት ከምዕራባውያን ምሁራንና ተመራማሪዎች አዕምሮ በፈለቁ አስተሳሰቦች በመሆኑ፣ እነዚያን አስተሳሰቦች ከኢትዮጵያውያን ነባር ምሁራን አገር በቀል ከሆኑ ሐሳቦችና ባህላችን ጋር አጣጥሞ ለመጠቀም ባለመቻላቸው ነው እላለሁ፡፡ በትንሹ ለማስረዳት ያህል የሚከተሉትን አስተሳሰቦች እንዴት ወደ አገር አስገብተው እንደተጠቀሙቧቸው እንመልከት፡፡
ኮሙዩኒዝም የተቀዳው ከማርክስና ከኤንግልስ አዕምሮ ነው፡፡ ብሔር ብሔረሰብ የተባሉት ቃላት የተሸከሙት ነገረ ነገሮች ከእስታሊን ጭንቅላት የወጡ ናቸው፡፡ ምሁራኑ ማሰብ የነበረባቸው እጅግ በጣም የጠለቁ የኦርቶዶክስና የእስልምና ሃይማኖኖቶች እምነት ለረዥም ጊዜ በአዕምሮው ውስጥ ባሰፈነና በተጨማሪም ባህሉ በዳበረ ሕዝብ ላይ የኮሙዩኒዝም አስተሳሰብ ማስፈን፣ በአዲስ ነጭ ልብስ ላይ ጥቁር ድሪቶ መለጠፍ እንደ ማለት መሆኑን አለመረዳት ነው፡፡ በሌላም በኩል ሥልጣን ለመሻማት በሚደረገው ትንቅንቅ አገር አንደምትጠፋ አውቆ፣ ይህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ‘ለማንም አይጠቅምም’ ያሉትን መጀመርያውንና መጨረሻውን አውዳሚ መድረሻ አለማወቅና አለመረዳት ነው፡፡ እጅግ በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ በኮሙዩኒዝም ርዕዮተ ዓለም የተጠመቁ የአብዮቱ ወጣት ምሁራንና የጦሩ ሠራዊት ለሥልጣን ብለው ተራርደው መተላለቃቸው ነው፡፡ የተመሩትም በጋለ ስሜት እንጂ በመጠቀ የአዕምሮ ችሎታ አልነበረም፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ የአዕምሮ ችሎታን በመንግሥት አመራር ደረጃ ለመጠቀም የጀመሩት ብዙ ሕዝብ ‹እግዚአብሔር ከሰማይ ያወረደልን መሪ› ብሎ እምነት የጣለባቸው፣ እጅግ በጣም የተከበሩ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና አጋራቸው አቶ ለማ መገርሳ ብቻ ናቸው፡፡ እሳቸውም 95 በመቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኋላቸው ሆኖ የሚደግፋቸው ስለሆነ፣ ምንም ሳይጨነቁ በአሸናፊነት እንደሚወጡ ሙሉ እምነት አለኝ፡፡
ነገር ግን የመላ ኢትዮጵያውያን የሆነ ባህላችንንና አስተሳሰባችንን አሽቀንጥሮ የጣለ ስግብግብ የወገን ትውልድ ተፈጥሮ አቅል እያሳጣን ነውና እንጠንቀቅ፡፡ ከአሁን ወዲያ እንዲህ ዓይነት የዘር መርዝ የተጠናወታቸውን ቡድኖች ማስተገሻ እየሰጡ አደብ እንዲገዙ ማድረግ ይበጃል እላለሁ፡፡ እስኪ ደግሞ ብሔር ብሔረሰብ የሚሉት ድምፀ ነገሮች ወዳዘሉት ነገረ ነገሮች እንሂድ፡፡ ነገረ ነገሮቹን በሚገባ ባለመረዳት በአገራችን ላይ በለጠፉት ምጡቅ ኢትዮጵያውያን ሊቃነ ሊቃውንት ዘመናዊ ምሁራን ምክንያት፣ አገራችንን በመበጥበጥ ላይ ያሉትን ነገረ ነገሮች ከነባር አገራዊ ምሁራን አስተሳሰብ ጋር እናወዳድራቸው፡፡
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በጻፉት የግዕዝና የአማርኛ መዝገበ ቃላት ላይ የብሔርን ነገረ ነገር ሲገልጹ፣ ብሔር የሚለው ድምፀ ነገር የያዘው ከአንድ ትንሽ ቦታ እስከ ጠቅላላ ፍጥረታት ያለውን ነገረ ነገርን ነው፡፡ እነዚህ ነገረ ነገሮች ግልጽ ሊሆኑ የሚችሉት በምሳሌ ነው፡፡ ተስፋ ገብረ ሥላሴ ዘብሔረ ቡልጋ ሲል ብሔር የሚያመላክተው ቡልጋ የምትባለውን ቦታ ነው፡፡ ሌላም ስም ጠርቶ ዘብሔረ ዘጌ የሚልም ጽሑፍ አለ፡፡ ይኼም የሚያመለክተው ዘጌ የተባለችውን ትንሽ ቦታ ነው፡፡ አሁን ደግሞ እስኪ እግዚአብሔር በሚለው ድምፀ ነገር ውስጥ ያሉትን ነገረ ነገሮች እንተንትናቸው፡፡ እዚህ ቃል ውስጥ ሁለት ቃላት አሉ እግዚእና ብሔር፡፡ እግዚእ የሚለው ቃል ጌታ ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ ብሔር ማለት ጠቅላላ ፈጥረታት (The Entire Universe) ማለት ነው፡፡
ዘመናዊ ምሁራኑ በአገራችን ለመጀመርያ ጊዜ ብሔር የሚለውን ቃል የእንግሊዝኛውን ‹‹Nation›› የሚለውን ነገረ ነገር እንዲይዝ ተደርጎ ነበር ሊጠቀሙበት የጀመሩት፡፡ ኮሙኒዩዝም ወደ አገራችን ሲገባ ደግሞ ነገረ ነገሩ ግልጽ ባልሆነ ሁሉም እንደፈለገው በድምፀ ነገሩ ውስጥ መጫን ጀመረ፡፡ ለማናቸውም ብሔር የሚለው ቃል ወደ መሬት ነገረ ነገር ያደላል እንጂ ወደ ሕዝብ አያደላም፡፡ እግዚአብሔር የሚለው ቃል ይህንኑ ያመለክታል፡፡ ለምሳሌ አማራ ብሔር አይደለም፡፡ በአማርኛ አፋቸውን የፈቱ የኢትዮጵያ ዜጎች ናቸው፡፡ ሌሎችም በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች ብሔሮችም ብሔረሶቦችም አይደሉም፡፡ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች በአፍ መፍቻነት የሚናገሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ናቸው እንጂ፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያውያንን ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝቦች እያሉ መጥራት አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ብዙ ዕውቀት የሌለው ነው ብሎ በማደናገር የአስተሳሰብ ጥራት ሳይሆን፣ የማደናገሪያና የኢትዮጵያን ሕዝብ በማታለል የመጨቆኛ መሣሪያዎች ናቸው፡፡
ብሔር ብሔረሰብ የሚሉት ቃላት የፖለቲካ ቃላት ናቸው፡፡ ፖለቲካም ሥልጣን የመጨበጫ ሥነ ዕውቀት ነው፡፡ እነዚህ ከውጭ በተሸመተ ዕውቀት የዘመኑ ኢትዮጵያውያን ምጡቅ ምሁራን እነዚህ የአሁኑ ብሔረስቦች በተለያዩ በታወቁ ቋንቋዎች አፋቸውን የፈቱ፣ ኢትዮጵያውያን እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ ትምህርታቸውን በአማርኛ ሲማሩ ምንም የባዕድነት ስሜት ሳይፈጠርባቸው ደስ ብሏቸው ሲማሩ የነበሩትን እናንተ ብሔረሰቦች ናችሁ እያሉ ንቃት ሰጥተው አነቋቸው፡፡ እነዚህ ምሁራን የነቁ ብሔረሰቦችን ወደ ብሔርነት አሸጋግረው እነሱ የብሔሮቹ ገዥዎች ለመሆን ለምን ፈለጉ? እነዚያንም ብሔሮች ከአሜሪካና ከሩሲያ የበለጠ እንዲሆኑ ፈለጉ፡፡ ከደንቆሮና ኋላቀሮች ጋር መደንቆር አልፈለጉም፡፡ ጨዋታውም ይኸው ነው፡፡ ግን መሰላቸው እንጂ የህልም እንጀራ መሆኑን አላወቁም፡፡ ተታለዋል፡፡ አያዋጣም፡፡ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተምህሮ “ኪሳራ ነው ለማንም አይበጅም”፡፡
ስለዚህ ኢትዮጵያ ብሔር ናት፡፡ በውስጧም የሚኖሩ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች አፋቸውን የፈቱ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ ሕዝብ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች አይደሉም፡፡ እነዚህ የመበታተኛ ቃላት ናቸው፡፡ እረኛ የሌለው ሕዝብ የማድረጊያ፡፡ ጆሮ ያለው ይስማ፡፡ ጀግናው ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) “እንደመር” ብለዋል፡፡ ምን ማለት ነው? ምንም ዓይነት አንድ ሺሕ ትርጉም ልትሰጡት ትችላላችሁ፡፡ ለእኔ ግን እንደመር ማለት በመጀመርያ ሁላችንም እከሌ ከእከሌ ሳይባል ከኢትዮጵያ ላይ የሚበቃንን መሬት ቆርሰን የወደድነውን የባንዲራ ዓይነት ሰቅለን፣ ነፃ ወጥተን፣ ነፃነታችንን አስከብረንና ራሳችንን ችለን እንኖራለን ማለታችንን እርግፍ አድርገን ጥለን ቂም አዝለን ሳይሆን፣ በንፁህ ልብ እውነተኛ ኢትዮጵያውያን ሆንን እንኑር ማለት ነው፡፡
አሁን አሁን ኢትዮጵያ እውነተኛ ምሁራን መሪዎች እያገኘት ይመስለኛል፡፡ ለምን ቢሉ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ሁለተኛው ጀግናዬ የግንቦት 7 ድርጅት ማናቸውም ሌላ ድርጅት (ኦነግ፣ ኦብነግ፣ አርዱፍ፣ ወዘተ.) ያላዳች ማቅማማት ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ ኢትዮጵያን አገሩ እንደሆነች ከተቀበለ፣ ያለ ምንም ችግር ከእኔ ድርጅት ጋር ተቀላቅሎ በነፃነት መታገል ይችላል ብለዋል፡፡ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ነፃ አውጪዎች የምመክረው ከዚህ ወዲያ መንፈራገጥ ለመላላጥ ነው እላለሁ፡፡ የሚበጀው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን (ዶ/ር) እና የብርሃኑ ነጋን (ፕሮፌሰር) ምክር መቀበልና ወደፊት መሄድ ነው፡፡ ነገር ቢበዛ በአህያ አይጫንም ይባላል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡