በአሰፋ አደፍርስ
አባት፣ እናት፣ አያት፣ ቅድመ አያትና ቅም አያት የተወለዱባት፣ ለነፃነቷ የተዋጉላትና የሞቱላት አገር የአገሬው አንጡራ ንብረት፣ የማትለውጥና የማትሻር ነች። ይህ እንደ ኢትዮጵያ እንግሊዝ፣ ፈረንሣይ፣ ጣሊያን፣ እስፔን፣ ጃፓንና የመሳሰሉትን ሲመለከት፣ አዲሲቷን የ242 ዓመቷን ወጣት አሜሪካን አያጠቃልልም። አሜሪካ እ.ኤ.አ. በጁላይ 4 ቀን 1776 ራሷን አገር ብላ ስትጀምር ከነባሮቹ የአውሮፓ፣ እስያና ከታላቋ ኢትዮጵያ በተለየ መንገድ ጀመረችና የሁሉም አገር ሆነች። የአሜሪካ ዋና ባለቤት ኢንዲያኖችን (Native Americans) ወግታ አገራቸውን በእንግሊዝ ስም ከነጠቀች በኋላ ከእናቷ ከእንግሊዝም ተለይታ አገር ስትፈጥር፣ ባካሄደችው ጦርነት ጓዶቿን (ፈረንሣይንና ደቾችን) አሸንፋ ግማሹን በግዥ፣ ግማሹን በጉልበት አስቀርታ ራሷን አቋቁማ ታላቅ አገር ለመሆን በቃች።
አሁን ማንም ሰው አሜሪካዊ ለመሆን ከፈለገ ሕግ ብላ ያወጣቻቸውን መሥፈርቶች አሟልቶ በተመደበው መሥሪያ ቤት ተፈትኖ ካለፈ በኋላ፣ በታላቅ ክብር ቃለ መሃላ ፈጽሞ የዜግነት የምስክር ወረቀት ተሰጥቶ ከዚያች ደቂቃ ጀምሮ የአሜሪካዊነት ዜግነቱን ያገኛል፡፡ ማንኛውም አሜሪካዊ የሚሠራውን እንደ ዕውቀቱ የመሥራት መብት ጭምር ይኖረዋል። ግን በአገሩ ባለመወለዱ ፕሬዚዳንት መሆን አይችልም። ይሁን እንጂ እዚያ የተወለደ እትብቱ እዚያው የተቀበረ ለፕሬዚዳንትነት መወዳደርና ከአሸነፈ ለሹመቱ ሕግ ይፈቅድለታል። በተረፈ በማንኛውም ሥራ ተወዳድሮ ሰው ሊሠራ የሚገባውን ሁሉ ችሎታው እስከፈቀደለት ድረስ ይሳተፋል፡፡ ይህንንም ስል መንገዱ ጥርጊያ ነው ማለቴ እንዳልሆነ ተገንዘቡልኝ። በተለይ ጥቁር ከሆነ ሁልጊዜ ችሎታው ጥያቄ ውስጥ ስለሚወድቅ እጅግ ብቁ ሆኖ መገኘት አለበት። አሜሪካም ሆነች ካናዳ ሬድ ኢንዲያንስ ተብለው (Native Americans) የሚታወቁት ዝሪያዎች አገር ነበሩ። ዛሬ የእኛ ነበሩና በእኛ ስም ይጠሩ፣ የእኛ አንጡራ ንብረት ነበሩ ባይ የለባቸውም። ለልማትና ለቴክኖሎጂ መሻሻል እሽቅድድም እንጂ አላስካ የሩሲያ ነበረች፡፡ አሁን ግን አሜሪካ ሆና ቀርታለች፡፡ ታላቋ ሩሲያ የእኔ ነበረችና በአነስተኛ ዋጋ ነውና የሸጥኩላችሁ ትመለስልኝ ብላ አታውቅም። እንዲያው ብዙዎቻችን የማናውቀውን የሰዎችን ችሎታ ለመፈታተን ሳይሆን፣ እንዲያው ለማስታወስ ያህል ዳህራን የተባለች የሳዑዲ ግዛት በማን እጅና የማን ንብረት ነች? ይህችን የዘመኑ ሰዎች ቢመልሱልኝ በእውነት አዋቂነታቸውን ከማኅደሬ አኖርላቸዋለሁ፡፡ አደንቀውም ይሆናል። ሜክሲኮ አሪዞና፣ ካሊፎርኒያና ቴክሳስ ንብረት አካልና የሜክሲኮ ነበሩ፡፡ ግን ጥንት የእኛ ነበሩና ሜክሲኮ ብቻ መኖር አለባቸው፣ የጥቅም ተካፋይ ሜክሲኮውያን ብቻ ይሁኑ የሚል ጥያቄ እንኳን ሊነሳ አይታሰብም። ይሁን እንጂ ሥልጣን ላይ ለመውጣት ውድድር አለ፡፡ በውድድሩም ተወዳድሮ ካሸነፈ ሜክሲኳዊ ሆነ ኢትዮጵያዊ ሊሳተፍ ሊሾምና ሊመራ ቢችልም፣ ኢትዮጵያዊ ወይም ሜክሲኳዊ ነኝ ብሎ ሳይሆን፣ አሜሪካዊ በመሆን ብቻ ነው።
ዛሬ በኢትዮጵያ የማየውና የምሰማው እጅግ የተለየና ታሪክን የሳተ ሁኔታ ነው። አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና የኦሮሞ አንጡራ ንብረት ነች ሲባል እሰማለሁ፡፡ ይህ መሠረት ያለው ታሪክን የተከተለ ወይስ የጊዜውን ፖለቲካ የተከተለ ነው? ኢትዮጵያ የሁሉም ነች። የወላይታው፣ የሐዲያው፣ የከፋው፣ የሹሮው፣ የበኔሾው፣ የኮቶው፣ የአማራው፣ የኦሮሞው፣ የሲዳማው፣ የሶማሌው፣ የትግሬው፣ የጉራጌው፣ የመንጃው፣ የጋምቤላው፣ የቤንሻንጉሉ. . . ነች። አልፎ ተርፎ የመላው የአፍሪካ መሰባሰቢያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ በመሆኗ፣ ልንኮራና ባቋቋሙት ታላቁ መሪያችን መኩራት ይገባናል፡፡ እንደ እህል ዘር ቆጥረን ሳይሆን የእኔ ብቻ የሚል አስተሳሰብ ቢገታና ለአንድነታችን ብንቆም ታላቅነታችንን ለዓለም እናሳያለን። ኢትዮጵያ የኢትዮጵያዊያን እንጂ የአንድ ጎሳ ልትሆን አይቻልም። ለዚህ አንድ ምሳሌ ዋሽንግተን ዲሲን መጥቀስ ይቻላል። የአሜሪካ ዋና ከተማ ፊላዴልፊያ– ፔልሰልቬኒያ እንዲሆን ከተመረጠች በኋላ፣ አንድ ጠቅላይ ግዛት ዋና ከተማ ካደረግን አድልኦ ሊኖር ይችልና ፍትሕ እንዲጓደል መንገድ መስጠት እንዳይሆን ተመካክረው ከተማዋ ከቬርጂኒያ ግማሽ ከሜሪላንድ ግማሽ በመውሰድ የአሜሪካ ዋና ከተማ ዋሽንግተን ዲሲ ለመሆን በቃች። የመጀመሪያውም ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዋሽንግተን ዲሲ በተሠራው ኋይት ሃውስ ሳይገቡ፣ በዚያ በፊላዴልፊያ ፔንሰልቬኒያ የተሰጣቸውን የስምንት ዓመታት ጊዜያቸውን ፈጽመው ከወጡ በኋላ፣ ቀጣዩ ፕሬዚዳንት ጆን አዳምስ ለሁለት ወራት ያህል ቆይተው ወደ አዲሱ ዋሽንግተን ነጩ ቤት በመግባት የመጀመሪያው የነጭ ቤት መራቂ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነዋል።
ዋሽንግተንም ከሁለት ግዛቶች የተውጣጣች ዋና ከተማ በመሆኗ፣ የዋሽንግተን ነዋሪ በፌዴራል መንግሥት ወይም በኮንግረስና በሴኔት ውስጥ አይመረጥም። ለምን ቢባል አድልኦ እንዳይኖር (Federal Neutral City) ታስቦ ሲሆን፣ አሁን አሁን ሕዝቡ ግብር ከፋይነት ያለውክልና (Taxation Without Representation) በማለት ቅሬታውን ይገልጻል። ይሁን እንጂ ነባሩ ውሳኔ አልተሻረም። እኛ ግን በልተንና ሕዝባችንን አብልተን ማደር ሳንችል፣ ባረጀና ባፈጀ አስተሳሰብ የወገን መለዮ እየፈጠርን ከታሪክ የማይገናኝ ምንም መሠረት የሌለው አሉባልታ ይዘናል፡፡ ሕዝባችንን ግራ በማጋባት ከውጭ በሚሰጠን ድጎማ ራሳችንና ቤተሰባችንን በማሽሞንሞን፣ በሌላው ወገናችን ላይ ለመጫወትና የየራሳችንን ዝና ለማራመድ እየተተኮረ ስለሆነ ይህ ድርጊት መቆም አለበት።
አሜሪካን ስንመለከት ሁሉ ሠርቶ አገሩን ለማሳደግ እንጂ የተወሳሰበ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ የሚል አባዜ የለም። ይህ ቢሆን ኖሮ የቴክሳሱ ካሊፎርኒያ ሄዶ በዜግነቱ ኮርቶ ሊሠራ አይችልም ማለት ነው፡፡ የሚችጋኑ ቬርጂኒያ፣ የአትላንታው ሜሪላንድ ሠርቶ መኖር አይችልም ማለት ነው። አሁን በእኛ አገር ዴሞክራሲ እየተባለ ሲነገር እንሰማለን፡፡ በዕውን ዴሞክራሲን አውቀን ነው ወይስ ለይስሙላ? እኔ ተወልጄ ያደግኩት ናዝሬት (አዳማ) አካባቢ ሆኖ ዛሬ በስንት ዘመኔ አዳማ ብሄድ እንደ ውጪ ሰው ታየሁ፡፡ ይባስ ብሎም ፍትሕ ተጓደለብኝ። ይህ ነው ዴሞክራሲ? ትርጉሙም የሚታወቁት አይመስለኝም። በፖለቲካ መስክ ተሠለፍን የሚሉ ሁሉ ያለፈው ይበቃል ብለው በኅብረት ቢነሱ ነው የሚሻለው። ለመሆኑ ታሪካችንን ከመሠረቱ እናውቅ ይሆን? ካወቅን በ14ኛ ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ምን ነበረች? የማንስ ነበረች? የግራኝ መሐመድን አመጣጥና ሕልፈት እናውቅ ይሆን? የግራኝ መሐመድ በኢትዮጵያ ላይ ያመጣውን ለውጥ እናውቃለን? ካወቅን ወደ ልቦናችን እንመለስ ነበር።
እንዲያው ‘ሁሉ ቃልቻ ማን ይሸከም ስልቻ’ ሆነና ታሪኩን ከመሠረቱ ቢያጠኑት የተሻለ ነው። አናጋሪዎችና መሰሎቻቸውን ላስታውስ የምፈልገው የመቶ ዓመታት ታሪክ እያሉ የሚለቁትን የመለያየት ዘመቻ አቁመው፣ ኦሮሞ የኢትዮጵያ አንጡራ ልጅ እንጂ በመቶ ዓመት የሚወሰን ያለመሆኑን ተገንዝበው ወደ ልቦናቸው ይመለሱ፡፡ ኢትዮጵያን የማልማትና ሌሎች ወደ ደረሱበት ደረጃ እንድንደርስ ቢሰብኩ የተሻለ የዜግነት ግዴታቸውን ይወጡታል ብዬ እገምታለሁ። ኢትዮጵያ ውስጥ በተደረጉ የነፃነት ትግሎችና ጦርነቶች የኦሮሞ ጀግኖች ያልተካፈሉበት አለ ብለው ያምናሉ? ካመኑ ጀግኖቹ ተገደው ነው ወይስ አገር ወይም ሞት ብለው ይሆን? ይኼንን ይመልሱልኝ፡፡ የኦሮሞን ኢትዮጵያዊ አለመሆንና የመቶ ዓመታት ታሪክ መሆኑን ያስረዱን። ፖለቲካ ብዙም አስቸጋሪ ጉዳይ ባይመስልም ማጠፊያ ሐረጉ ግን ከባድ ነው፣ ይታሰብበት፡፡ አሜሪካ እንዴት ለማች ብለን የልማት ፈለጓን ብንከተል እንጂ፣ ሌሎች ሊያጠፉን የሚፈልጉትን አቅጣጫ በመያዝ መሣሪያቸው ባንሆንና ባንራወጥ መልካም ነው አስቡበት። የኢትዮጵያ ብዙ ሳይንቲስቶች፣ ኢኮኖሚስቶች፣ መሐንዲሶች፣ ሐኪሞች፣ ጥሩ ጥሩ ነጋዴዎች፣ መልካም የሥነ አዕምሮ ተመራማሪዎች፣ የነቁ የበቁ ትክክለኛ ጠበቆችና የመሳሰሉት ምሁራን አገራቸው ይግቡ፡፡ አገራቸውን ከችግርና ከመከራ ይታደጉ፡፡ ወጣት ሴት ሕፃን ተሸክማ ስትለምን፣ ሕፃናት ልጆች ትምህርት ቤት ከመሄድ ፈንታ በየመንገዱ ሲለምኑ ይኼንን ችግር ማስወገድ እንዳይቻሉ አንዳንዶች በሚረጩት መርዝ ያልነበረን ሁኔታ እየፈጠሩ ምሁራን ተመልሰው አገራቸውን እንዳያለሙ የሚያደርጉትን ፕሮፓጋንዳ በመሸሽ፣ ወደ ኋላ እያሉ የሰው አገር አገልጋይ ሆነው ቀርተዋል። ይልቅ ለመከፋፈል የሚደረገው ሙከራ እጅግ የዘቀጠና የወረደ ስለሆነ፣ ይህ ጉዳይ በተቻለ መጠን ተወግዶ ለጋራ አገራችን አብረንና ተባብረን ለመሥራት፣ ሌሎች ወደ ደረሱበት ለመድረስ ብንነሳ የተሻለ ይሆናል።
ፖለቲከኞች ቀደም ሲል በነበረው የተመሰቃቀለ የአስተዳደር ብልሹነት በመቆርቆር መነሳታቸው የሚደነቅ ሲሆን፣ አሁን ግን ወገንን ለማለያየት የሚደረገው ሩጫ ይጎዳል እንጂ ስለማይጠቅም ወደ አንድነት ወደ አገር ልማት መመለሱ የተሻለ ነው፣ ሁላችንም ልብ እንግዛ፡፡ ሌሎቻችን ደግሞ የሦስት ሺሕ ዘመን እየቆጠርን መኖር ዛሬ በ21ኛ ክፍለ ዘመን ስለማይቻል ከሕልም ሩጫ እንጠንቀቅ። ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ ተደርጎ አያውቅም የሚል እሮሮ እየሰማሁ ነው። የዓለም መሪዎች በምርጫ አይደለም የጀመሩት፣ ግን ሕዝቡ እየነቃ መጣና እንደነ አሜሪካ በተለይም እንደ ጆርጅ ዋሽንግተን፣ እንደ ጀፈርሰንና ሃሚልተን ዓይነቶቹ ተፈጠሩና ዛሬ ላለንበት የምርጫ ዘመን ደረስን፡፡ ዓለም በምርጫ የተጀመረች አስመስለን ራሳችንን አናሞኝ።
ትናትና አባቴ እየገረፈ ሥነ ሥርዓት አስይዞ አሳድጎኝ፣ ዛሬ በተራዬ ልጆቼን በሠለጠነው መንገድ በጥሩም ይሁን በጋጠወጥነት ስለማሳድግ አባቴ በነበረው ዕውቀቱ ጥሩ መስሎት ያደረገውን ዛሬ እንደኔ ለምን አላደረገም ብዬ ልወቅሰው አልችልም፡፡ ጊዜውና ሁኔታው በፈቀደው አድርጓልና። አሁንም የመምረጥና የመመረጥ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ፣ የምንመረጠው በችሎታ ወይስ በዘር? በሃይማኖትና በመሳሰሉት? ይኼ ካልተስተካከል ታጥቦ ጭቃ እንዳይሆን እንጠንቀቅ። የምንመረጠው በንፁህ ልቦና አገርን ለመርዳትና ለማገልገል መሆኑን ተገንዝበን ከተወዳደርን መልካም ይሆናል። እንዲያው እከሌ ተሹመው ስለነበረ እንቶኔን እንተካው በሚል ሁኔታ ከሆነ ከንቱ ነው። ለዚህ ቀላል ምሳሌ መሆን የሚችለው ለማ መገርሳንና ዓብይ አህመድን ማየት ነው። ባደረጉትና ባሳዩት ቀና አመለካከትና በተራመዱት ዕርምጃ ኢትዮጵያዊ ዳር ከዳር ልጆቻችን፣ ወንድሞቻችንና ወገኖቻችን ብሎ በዓለም አካባቢ እንደተቀበላቸው ሲታይ፣ ኢትዮጵያዊ ምን ያህል አስተዋይና ወገንተኛ እንዳልሆነ የሚያሳይ መስታወት ነው። መሪ እንደ ጠማውና እንደ ናፈቀውም ታይቷል።
ይኼ ከሆነ ለአገር አንድነት፣ ለነፃነትና ለኅብረት መነሳት እንጂ ለመከፋፈል ሩጫው ከምን የመጣ አባዜ ነው? ተሳስተንም ወደ ስህተት እንዳንመራቸው እንጠንቀቅ። ዛሬ ልጆቻችን የሚበሉት አጥተው በየመንገዱ ሲለምኑ፣ ሕፃን ተሸክማ በየመንገዱ ለልጄ የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ እያለች ስትንከራተት እያየን ያንን እንዴት ተረባርበን እናስወግድ በማለት ፈንታ፣ ጥንት የጀርመን ሚሲዮኖች ባስተማሩን ከታሪክ የራቀ የመለያየት ተንኮላቸውን እውነት አስመስለን ይዘን አገርን አናፍርስ፡፡ ሌሎች በመፍረስ ላይ ላሉ አገሮች ምሳሌ ባንሆንና ወደ ልቦናችን ብንመለስ የተሻለ ይሆናል፡፡ ተረጋግተን የአገራችንን ታሪክ ከመሠረቱ ብናጠና ወደ መሠረታችን ብንመለስ መልካም ይሆናል። በዚህ ጉዳይ መወያየት የሚሻ ካለ በኢሜይል አድራሻዬ ልንገናኝ እንችላለን፡፡ መልካም ንባብ!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡