Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርከሚፈለገው ግብ ለመድረስ ምን መደረግ አለበት?

ከሚፈለገው ግብ ለመድረስ ምን መደረግ አለበት?

ቀን:

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

‹‹ብዙዎቻችን የኅብረተሰቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውህደት እንመኛለን፡፡ ነገር ግን አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ መናኛ ግጭቶችን ለማናርና በዚህ ችግር ተጠቃሚ ለመሆን የሚፈልጉ ኃይሎች አንድነትን ለመሸርሸርና ውህደቱን ለማደፍረስ ይጥራሉ፡፡ ከአንድ ይልቅ ለሁለትና ለሦስት የተከፈለ ልብ እንዲኖረንም ይወተውቱናል፤›› ኤልተን ትሩብለድ የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊዲክሌሬሽን ኦፍ ፍሪደምበሚል ርዕሰ ባሳተሙት መጽሐፋቸው እንደገለጹት።

በእርግጥም አንድነትን የመበተንና ውህደትን የመሸርሸር ችግር ሊወገድ የሚቻለው ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ነፃ የሆነ አስተሳሰብ ያለ አንዳች ገደብ በሕዝብ ዘንድ የተናኘና የሰረፀ እንደሆነ ነው፡፡ ያለ አንዳች ጥርጥር፣ ‹‹የእኔን አመለካከት አንጂ የሌላውን አትመኑ፣ የእኔን ድርጅት አምልኩ፣ የሌላው ሁሉ ፋይዳ ቢስ ነው፤›› የሚሉ ግለኛ አስተሳሰቦች ሲወገዱ የተሻለ ዘመን ይመጣል፡፡

በደርግ ዘመን የሶሻሊስት ሥርዓት፣ ‹‹ሰዎች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እኩልነታቸውን ሊያረጋግጡ የሚችሉት የወዛደር መደብ በአሸናፊነት የወጣ እንደሆነ ነው፤›› የሚል ፕሮፓጋንዳ፣ ባለፉት 27 ዓመታት ደግሞአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ የተነሳ መለስተኛ ሶሻሊስታዊ ሥርዓት አመለካከት ይሠራጭ ስለነበረ ዛሬ፣ ‹‹ሌሎች መደቦች ጭምር በነፃ የሚንቀሳቀሱበት ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ይኑር፤›› ብንል ድሮውንምፓርቲያችን ያሸንፋልበሚል አጉል አመለካከት ተጀቡነን የኖርን ነንና በነፃ ገበያ ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እናምጣ ቢባል እንዲህ በቀላሉ የሚኖር አይሆንም፡፡

ዳሩ ግን ለተፋጠነ ዕድገት ከነፃ ገበያ ሥርዓት የተሻለ እንዳልተገኘ ሕይወት ራሷ እየመሰከረች ነው፡፡ ነፃ ገበያ ደግሞ ከነፃ የፖለቲካ ሥርዓት ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ያንተ ድርጅት ድርጅቴ ሥልጣን በያዘበት አካባቢ ዝር እንዳይልየሚያሰኝ ሳይሆን፣ እንዲያውም የተቀናቃኝ ድርጅቶቸ በአካባቢው መኖር ለእኔ ህልውና ዋስትና ነው የሚያሰኝ ነው፡፡ ነጋዴው ከነጋዴው፣ ምሁሩ ከምሁሩ፣ ገበሬው ከገበሬው፣ ፖለቲከኛው ከፖለቲከኛው በነፃ ካልተወዳደረ፣ ካልተቸና በዚህ ሒደት የተሻለ አመለካከት መንጭቶ ለዕድገት በር ካልተከፈተ፣ መጨረሻው አማራጭ በሌለው አምባገነናዊ መንገድ መጓዝና ለፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ መዳረግ ይሆናል፡፡

ኤልተን ትሩብለድ በግልጽ እንዳሰፈሩት ደግሞ፣ነፃ ኅብረተሰብ የሚባለው ሁሉም ነው፡፡ ደሃም ሆነ ሀብታም፣ ገጠሬም ሆነ ከተሜ፣ የተማረውም ሆነ ያልተማረው፣ ባለሥልጣኑም ሆነ የሌለው፣ የፓርቲ አባሉም ሆነ ሌጣው፣. . . ሁሉም በአገሩ ተጠቃሚ መሆኑ የተረጋገጠና መብቱ የተጠበቀለት እንደሆነ ነው፡፡ ነገሩን በትክክል ስናስቀምጠውም መንግሥት የሚኖረው ለግለሰቦች እንጂ ግለሰቦች ለመንግሥት ሲሉ አይኖሩም፡፡ ፓርቲ ለምኖ፣ አሳምኖ፣ ተወዳድሮ፣ ዓላማውንና ግቡን ተቀባይነት ባለው መንገድ አሳውቆና አሳምኖ ሕዝብን ለማገልገል የሚታትር እንጂ፣ በሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ መጥፎ ተግባር ይፈጽማል ተብሎ አይገመትም። ዴሞክራሲ በሰፈነበት ሥርዓት መንግሥት የእያንዳንዱ ግለሰብ ጠበቃ ሲሆን፣ የማንኛውም ሥርዓት ዴሞክራሲያዊነት የሚለካውም መንግሥት ለዚያ ግለሰብ መብት መጠበቅ በሚያደርገው አስተዋጽኦ ነው፡፡ ይሁንና በብዙዎቹ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች መንግሥት የሕዝብ መሆኑ ይቀርና ግለሰቦች የመንግሥትን ፈቃድ ካላገኙ በስተቀር፣ ልዩ ልዩ ተፅዕኖ ሲደረግባቸው ይታያል፡፡ ለምሳሌ በደርግ ኢሕዲሪ ሥርዓት የፓርቲ፣ የወጣቶች፣ የሴቶች፣ የገበሬዎች፣ የሠራተኞች ማኅበራት፣ ወዘተ. አባል ለሆኑ ግለሰቦች ቅድሚያ አገልግሎት ይሰጥ ነበር፡፡ ከእነሱም የሚፈለገው የፖለቲካ ድጋፍ ሁሉ ይገኝ ነበር፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት የታየው የዚያ ግልባጭ ነው። እዚህ ላይ አንድ ኦሮሚኛ የሚናገር የቅርብ ወዳጄ እንደነገረኝ ሴትየዋ ኡኡታ ትሰማና ወደ ውጭ ሮጣ ትወጣለች። ወጥታም አንዳች መጥፎ ነገር ታይና ወደ ቤቷጉዲ ሰዲ፣ ጉዲ ሰዲእያለች ተመለሰች። ትርጉሙጉዱ ሁለት ነውማለት ነው። በዚህ ጊዜ ቁና ቁና እየተነፈሰ የጠበቃት ባሏተኮ ነመ ኬኛአለና መለሰላት። ትርጉሙአንዱ ጉድ የእኛ ነውማለት ነውና ነገሮችተኮ ነመ ኬኛእንዳይሆኑ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

በሌላ በኩል ደግም በደርግ ሥርዓትም ሆነ ራሱ እንዳመነው በኢሕአዴግ ሥርዓት፣ በማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለመሳተፍ የማይፈልግ በግድ እንዲሳተፍ ተደርጓል፡፡ በመሠረቱ በግድ አባል የሆኑ ግለሰቦች ድሮውን በሁኔታዎች አስገዳጅነት እንጂ ወደው ስላልሆነ፣  ለሥርዓቱ መቦርቦር ብሎም መውደቅ አስተዋጽኦ የማይታበል ሀቅ ነው።ከውጭ ይልቅ ውስጥ ሆኖ መታገልይሏልም ይኸው ነው። በዚህ ረገድ ባለፉት አርባ ዓመታት ኢሕአዴግና ሻዕቢያ ከሁሉም የበለጠ ተጠቅመውበታልና እንግዳ ነገር አይሆንም።

ያም ሆነ ይህ  ሰዎች ነፃ ሆነው የመረጡትን ለራሳቸው ብሎም ለኅብረተሰቡ ጠቀሜታ ሥራ እንዲያከናውኑ ዕድሉ ካልተሰጣቸው በስተቀር የመንግሥት ወዳጅ መስለው ቢቀርቡ እንኳን፣ ያለ ውዴታቸው እንዲሠሩ ከተደረገ ለውድቀት የሚዳረጉ መሆናቸውን ነው፡፡

የደርግ ኢሕድሪ መንግሥትንም ሆነ ያለፉት 27 ዓመታት የኢሕአዴግን ስህተትና ውድቀት በምንተችበት ጊዜ፣ የዚያ ሥርዓት ቅሪት ዛሬ አለ ወይስ የለም? ብለን መጠየቁ ተገቢ ይሆናል፡፡ ይሁንና መልሱአለቢሆን ደግሞ ነፃ አስተሳሰብ፣ ነፃ አመለካከት፣ ነፃ እምነት፣ በአጠቃላይ የዴሞክራሲ ምንነት ስለገባንና አምባገነን ሥርዓትን የሙጥኝ ብለን በመያዛችን ነው ወይስ ዴሞክራቶች የሆንን መስሎን አምባገነንነትን እያራመድን ነው? የሚሉትን መለየት ይኖርብናል፡፡ ዴሞክራቶች የሆንን መስሎን አምባገነን አመለካከትን እያራመድን ከሆነ፣ የሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ነፃነት ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳትና የተረዳነውን ደግሞ ያለማመንታት በተግባር ለማዋል ወኔው ሊኖረን ይገባል፡፡

በዚህ ጸሐፊ በተደጋጋሚ የሚጠቀሱት ዊሊያም ዳግላስ የተባሉ አሜሪካዊ የሕግ ሰውየሕዝብ ነፃነትበሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ አንድመንግሥት ሥርዓት (በሩሲያም ሆነ በቻይና እንደሚታየው) ሐሳብን በነፃ የመግለጽ ነፃነት በተወሰነ ደረጃ ሊኖር ይችላል፡፡ በፋብሪካዎች፣ በእርሻዎችና በተለያዩ ማኅበራዊ ኑሮ አገልግሎቶች ላይ ምን ዓይነት ፖሊሲ መንደፍ እንደሚኖርበት እጅግ በሰፋ ሁኔታ ሊከራከሩበት ይችሉ ይሆናል፡፡ በዚህ ሒደት የመንግሥትን ሥልጣን ይዞ የሚያራምድ ድርጅት ለመቃወም እስካልተቻለ ድረስ፣ የፈለገው ልዩነትና መጨቃጨቅ ቢኖር ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት አለ ብሎ መናገረ አስቸጋሪ ይሆናል ብለዋል፡፡

እንዲያው ለነገሩ፣ እንዲያው ለጨዋታው፣ በአንዲት ሉዓላዊት አገርአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጎዳና፣ በኅብረ ብሔራዊነት ድልድይ አድርገን ወደ 17ኛው ክፍለ ዘመን ዘመነ መሳፍንት የተመለስን መሆናችንን ልብ ብለነዋል? በክልሎች መካከል ያለውን አደገኛ ፍጥጫናይሞክረኛአዝማሚያ ወደነዋል?  ባንወደውምእንግዲያው የወደድነው አስመስሎናል። ወይስ የአቶ መንግሥቱ ለማሹሚያድራማ እየተሠራ ነው? ይሆናል ወይም አይሆንም። ነገሩ ግን ይመስላል።

ስለዚህ ምን መደረግ አለበት? አሜሪካዊው ፕሬዚዳንት ጀፈርሰን፣ ‹‹በበኩሌ የሕዝብ ጥሩ ስሜት ከሁሉም የተሻለ መሣሪያ መሆኑን ራሴን አሳምኛለሁ፡፡ እርግጥ  ሕዝብን ለተወሰነ ጊዜ ከትክክለኛው መንገድ አውጥቶ መሳሳት ይቻል ይሆናል። ዳሩ ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ራሱን ያርማል፡፡ ሕዝብ እንዳይሳሳት ለማድረግ ደግሞ የራሱን ጉዳይ አሳምሮ በፕሬስ ውጤቶች እንዲያውቅ ማድረግ ነው፡፡ የመንግሥታችን ዋና መሠረቱ የሕዝብ አስተያየት እንደ መሆኑ መጠን ይኼንን መብቱን ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡ በዚህም ምክንያት ጋዜጣ ከሌለው መንግሥትና መንግሥት ከሌላው ጋዜጣ ምረጥ ብባል ሁለተኛውን አስቀድማለሁ፤›› ሲሉ የሕዝብን አመለካከትና ስሜት አጢኖ መጓዝ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

የሕዝብን ስሜት አጢኖ መጓዝ ማለት ደግሞ ባለው መንግሥት ወይም በምሥራቅ አውሮፓ በነበሩ ኮሙዩኒስት አገሮች 70 ዓመታት እንደተደረገው፣ በእኛም አገር ባለፉት 40 ዓመታት ሲደረግ እንደነበረው፣ መንግሥት እንደዚህ ያለ ፖሊሲ አውጥቷልና እንዴት ተግባራዊ ልናደርገው ይገባናል ብሎ ጨርሶ የማያውቀውን ሐሳብ ለመድረክ በማቅረብ፣ ተስማምቻለሁ ብሎ ከስብሰባ እንዲበተንና በኋላ በጉዳዩ ላይ ሳቅና ስላቃ እንዲያካሂድ ማድረግ አይደለም፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ ፖሊሲው የሕዝቡን ፍላጎት እንዲከተል ከሱ ከራሱ የመነጨ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ለመሆኑ በቢፒአርና በካይዘን ስንት በገንዘብ፣ በጊዜ፣ በዕውቀት፣ የሚለካ ሀብት ባከነ? እርግጥ ነው ሁለቱም በሚጠቅሙበት ቦታና ወቅት ሊጠቅሙ ይችላሉ። በእኛ ግን ራሱ ባለሥልጣኑ ሐሳቡን ተረድቶ በሐሳቡ ተመርቶ ያልተገበረው ስለሆነ፣ የታለመለትን ውጤት አስገኝቷል ማለት ያስቸግራል።ከውጤት ተኮር ሥራ!” አለ አንዱ በአሠራሩ የበሸቀ ሰው።                                                                                                                                                                                 

በመሠረቱ በሀቅ ይህች አገር በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንድትጓዝ ከተፈለገ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሕዝብ ቀርቶ አንድ ግለሰብ እንኳ የሚያመነጨውን ሐሳብ እንደምን በሥራ ላይ  ሊተረጉመው እንደሚችል ማብራሪያ መጠየቅ፣ ማብራሪያውንም ከተጨባጭ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ እንዲያቀርብ ማበረታታትና አስፈላጊም ከሆነ እገዛ ማድረግ አለመታወቁ ሁኔታዎችን አስቸጋሪ እንዳደረጋቸው ልብ ልንለው የሚገባን ዓብይ ጉዳይ ነው። ወይም ‹‹የአንተ አቋም ከእኔ አቋም ጋር የሚቃረን በመሆኑ የምታመነጨውን ሐሳብ ምን ያህል እውነት ቢሆን አልቀበልህም፤›› ሊሉት አይገባም፡፡ ለምሳሌ አንድ ሐሳብ ቀርቦ ከሕዝብ መካከል አንድ ሰው ቢቃወምና የዚያ ሰው ሐሳብ ምን እንደሆነ በውል ሳይጤን ቢቀር፣ ነገር ግን የዚያ ግለሰብ ሐሳብ ትክክል ሆኖ ቢገኝ መንግሥትን ብሎም ሕዝብን መጉዳቱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ የመንግሥት ባለሥልጣናትሥልጣን ወንበር ላይ የሚቀመጡት ሕዝብን ለማገልገል እንጂ በሕዝብ ለመገልገል ባለመሆኑ፣ የሚመሯቸው ሰዎች ጥሩ ሐሳብ ቢያፈልቁም ባያፈልቁም መብታቸውን ማክበርና ማስከበር ይኖርባቸዋል፡፡

በመሠረቱ የፖለቲካ መሪዎች ሐሳባቸውን ሕዝብ እንዲቀበላቸው የተለየ ጥረት ቢያደርጉ መልካም ነው። ከሕዝብ አስተያየት በመነሳት ለመሥራት ቢነሱ ያም የሕዝብ አስተያየት እንደምን በተግባር ላይ ሊውል እንደሚችል አዎንታዊም ሆነ አሉታዊም ሐሳብ ቢሰጣቸው ይጠቅማቸዋል። ሁሉንም እኔና ቡድኔ ብቻ እንሥራው ብሎ ማስቸገር ግን የትም አያደርስም።  

ይኼንን የሚመለከት አንድ ምሳሌ ላቅርብ የቀድሞው  የደርግ መንግሥት ባለሥልጣንናት  በአጭር ጊዜ ለውጥ ለማምጣት ይፈልጉናየኮሙዩኒስት መንደርለማቋቋም ይፈልጋሉ። ለዚህም አርሲ ክፍለ ሀገር ትመረጣለች። ለነገሩ ቆቃ አካባቢም ነበር፡፡ ይኼንንም ሐሳባቸውን በተግባር ለማዋል ከአዲስ አበባ ሳይቀር ባሕር ዛፍ እየተቆረጠ መንደሮች ወደሚሠሩበት ሥፍራ ይጓዛል፡፡ ወጣቱ፣ ወንድ፣ ሴቱ ዘመተ። እያንዳንዳቸው 500 ቤተሰብ የሚይዙ መንደሮችም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተሠሩ፡፡ የአካባቢው ገበሬዎችም የለመዱትና የሞቀ ቤታቸውን አፍርሰው ወደዱም ጠሉም በእነዚያ መንደሮች ጎጆ እየተሰጣቸው ገቡ፡፡ ያለመዱትን መልመድ መቻል ነበረባቸው፡፡ እነዚህን መንደሮች የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መንግሥቱ ይለ ማርያም እየተዘዋወሩ ሲጎበኙ፣ ‹‹ማድረጋችን ካልቀረ በቆርቆሮ ቢሠሩ መልካም ነው፡፡ ለሌሎችም አርዓያ ሊሆን ይችል ነበር፤›› አሉ፡፡ ስሜታቸውን ተከትለው በጭፍን ይጓዙ የነበሩ ሌሎች ባለሥልጣናትምይበልአሉና መንደሮች ሁሉም እንደገና ፈርሰው ባለአራት ማዕዘን ቆርቆሮ ቤት ሆኑ። መኝታና ሳሎን ቤት ተለየላቸው፡፡ ከከብቱ ጋር ማደር ለለመደ ገበሬ ግን አዲሱ ኑሮ ፈጽሞ የሚስማማው አልሆነም፡፡ ዱብ ዕዳ ሆነበት፣ ቅሬታውንም በይፋ አሳወቀ፡፡

በመሠረቱ እንዲህ ያለው ችግር የተከሰተው በአገራችን ብቻ አይደለም፡፡ የሊቢያ መሪ የነበሩት ሙአመር ጋዳፊም ሕዝባቸው የበሮዊን ኑሮውን ትቶ ቀለብ እየተሰፈረለት በፎቅ ቤት በነፃ እንዲኖር ፈልገው ነበር፡፡ ዳሩ ግን ፍላጎት ብቻውን ውጤት ሊያስገኝ ባለመቻሉ የፈለጉት ሳይሆን ቀረ፡፡ ለታይታ የተደረጉ እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ዋጋ ያላቸውን መኪናዎች አላስፈላጊ በሆኑና መንገድ በሌለባቸው የትውልድ ቦታዎቻቸው ጭምር ያስገቧቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ድልድይ ባልተሠራበት ወንዝ ለዚያውም በክረምት እንዲያቋርጡ በማድረግ ለጎርፍ የተዳረጉ አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ምናልባት የሚፈጽሙት ስህተት ከቀና መንፈስ የመነጨ እንኳን ቢሆን ሥር መሠረቱ ሲታይ፣ ለታይታ ሲባል የተከናወነ ስለሚሆን ውጤቱ አይሰምርም፡፡ ለታይታ የሚደረግ ነገር ሁሉ ይጎዳል።

ሌላው ትኩረት ሊሰጥበት የሚገባው ጉዳይ ሰዎች በጎሳቸው፣ በሃይማኖታቸው፣ በቋንቋቸው በፖለቲካዊ አመለካከታቸው፣ ሳይለዩ የመኖር መብት ያላቸው መሆኑ ነው። አብረው እንዲኖሩ የሚያደርጋቸውም በጋራ የሚካፈሉት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ትውልዳዊ ትስስራቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ሥፍራ እንዳይኖሩ የሚከለከል ሕግም አልወጣም። አካባቢዎቻችን ለምን በቋንቋ መከለል እንዳለባቸው ያልገባው አነስተኛም ሆነ ታላቅ ባለሥልጣንም ጠይቆ መረዳት እንጂ፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት በሚያደናቅፍ መንገድ በመተርጎም እጅግ በጣም አደገኛ ዕርምጃ መውሰድ አይኖርበትም፡፡ እንደ ቋንቋም ሁሉ ፖለቲካዊ አመለካከትርዕዮተ ዓለማዊ ግንዛቤ፣ እምነት፣ ወዘተ. የግለሰቦችን መሠረታዊ መብት በማይነካ መንገድ መንቀሳቀሱን መከታተል ተገቢ ነው፡፡

ስለዚህም ባለሥልጣናት በተለይም ዴሞክራሲያዊ አመለካከት ያላቸው የፖለቲካ ባለሥልጣናት ለሰዎች ሁለንተናዊ ነፃነት፣ እኩልነትና በወንድማማችነት አብሮ ለመኖር ሲሉ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ መሆን ሲገባው በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የራሳቸው ጎሳ ወይም ብሔረሰብ ወይም ብሔር ጎልቶ እንዲታይ ከሞከሩ ሁከት በተሞላበት ዘመን ለመኖር ይገደዳሉ፡፡ የብዙዎቹ የዓለማችን የፖለቲካ ባለሥልጣናት ውድቀትም ከጠባብ አመለካከታቸው ጋር የተያያዘ እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡

እነዚህ ላይ በድሮ ጊዜ ክፉ  አምባገነን ባለሥልጣናት የሚቀናቀኗቸውን፣ ግድፈታቸውን የሚነቅፉባቸውን፣  የማያምኑበትን ሥራ እንዲሠሩ ቢጠይቋቸው አይሆንም የሚሏቸውን ግለሰቦችንም ሆነ ቡድኖችን በልዩ ልዩ መንገዶች ያጠቁ እንደበር ይታወቃል፡፡ ይኼን ጥጋበኛ እሰርልኝ፣ ግረፍልኝ፣ ቅጣልኝ ማለትም የተለመደ ነበር፡፡ ሕግና ደንብ ቢኖርም የሚያገለግለው ለባለሥልጣናቱ ስለነበር በዚህ ረገድ ሕዝብ ሲበደል ቆይቷል፡፡

ዛሬ ዜጎችን ቀደም ሲል በነበረው መንገድ ማጥቃት ባይቻልም፣ በሕግ እያስታከኩ ወይ ወንጀል እንዲሠሩ እየገፋፉ ወይም የሕጉን ትርጉም እያጣመሙ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ተግባር ማከናወን የማይሞከርበት ሁኔታ የለም። ሁላችንም የአሮጌው ሥርዓት ውጤቶች እንደ መሆናችን መጠን ችግሩን ደረጃ በደረጃ ለማስወገድ ጥረት ካልተደረገ በስተቀር፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አጭርና ቀጥተኛ መንገድ አይገኝለትም፡፡ መንግሥት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እገነባለሁ ሲልም የቀድሞ ፀረ ዴሞክራሲ አመለካከቶችን እያስወገድኩ፣ በዚህ ሒደት የሚከሰቱትን ስህተቶች እያረምኩ እጓዛለሁ ከማለት ውጪ ሊሆን አይችልም፡፡

ዋናው ቁም ነገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት ታጥቀው የተነሱ ኃይሎች በሥልጣን ላይ ሆኑም አልሆኑም ሕዝብ በተወካዮቹ አማካይነት የሥልጣኑ ተካፋይ ተቆጣጣሪ፣ ቢያሻው ነቃፊ በሚፈልገው ሰው የመመራት የማይፈልገውን ደግሞ ከሥልጣን በማስወገድ ወሳኝ ሚና ያለው መሆኑን ማመኑ ላይ ነው፡፡

ስለዚህም የአሁኖቹም ሆነ የወደፊቱ ባለሥልጣናት ..አ. 1874-1950 የነበረው ደብልዩ ማኬንዜንግ፣ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ማለት በአነስተኛው ትንታኔ የተሰበሰበ የሕዝብ አስተያየት ነው፡፡ አነስተኛውንም ወይም ምንም አስተያየት የማይቀበል ግን በሩቅም ይሁን በቅርብ  ወደ ፈላጭ ቆራጭነት የሚቀየር ይሆናል ብለው ነበር፡፡  1882-1945 (..አ.) የነበሩት አሜሪካዊው ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ደላኖ ሩዝቬልት ታሪክ እንደሚያረጋግጠው አምባገነንነት ሊመሠረት የሚችለው ከጠንካራና በታማኝነቱ ውጤታማ ከሆነ መንግሥት ሳይሆን፣ ከደካማና ተስፋ ቢስ ከሆነ መንግሥት ነው፡፡ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ከሥጋትና ከረሃብ የሚያድናቸውን መንግሥት ካቋቋሙ ውጤታማ ይሆናሉ፡፡ ካላቋቋሙ ግን አይሆኑም፡፡ አንድና ትክክለኛ የሆነ የማይለወጥ የነፃነት መንገድ ሊኖር የሚችለው የሕዝብ ፍላጎት የሚረዳ ጠንካራ የሆነ መንግሥትና መብቱን ያረጋገጠ ማንኛውም መረጃ ያለው ሕዝብ ነው በማለት ያስቀመጡትን መርህ ማጤን ተገቢ ነው፡፡

1842-1910 (..አ.) የነበረው ዊልያም ጀምስ አገር ከሌሎች የበለጠችና ቅድስት ልትባል የምትችለው እያንዳንዱን ቀን በጥቅም ላይ የሚያውል፣ ያለምንም ተፅዕኖ ተግባሩን የሚያከናውን ገንቢ አስተያየትና ተቃውሞ የሚያቀርብ፣ ተግባሩን ለሚደግፈው ድምፁን የሚሰጥ፣ ብልፅግናን በፍጥነት ለማምጣት የሚጥር. . . ሕዝብ ሲሆን ነው ሲል ያሰፈረው ወርቅ አስተሳሰብም የዕለት ተዕለት መመርያችን አድርገን ልንወስደው ይገባል፡፡

ስለዚህ የባለሥልጣኖቻችን እምነት ሕዝብን በማስተባበር ማሠራት፣ ረሃብንና እርዛትን ለማስወገድ የሚልበትን ዘዴ ረጋ ብሎ በመቀየስ አስተሳሰቦችን በነፃ እንዲገልጽ ሁኔታዎችን በማመቻቸት፣ ዴሞክራሲን ከቃል ይልቅ በተግባር እንዲተረጉም በማድረግ ላይ እንዲመሠረት የዘመኑ ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡ የአሁኑ የውጥረት ጊዜ ታላቅ ትዕግሥትና ጥበብን የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህን ጊዜ ለማለፍ ቢቻልም፣ የዚህ ዘመን ባለሥልጣናት በእርግጥም ታላላቅ ሰዎች ነበሩ ማለት እንዲቻል ጠንክሮ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡

ከአዘጋጁ፡– ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡                                                                             

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...