እነሆ መንገድ። ከስቴዲየም ወደ ሳሪስ ነን። ፀዳል ተጎናፅፋ ሕይወት በብርሃንዋ እያረጠበችው ይኼ መንገድ ይኼ ጎዳና ዛሬም ያስጉዘናል። ‹‹እኔ በቃኝ! በቃኝ! ነው የምልሽ። አለቀ ደቀቀ። ገባሽ አይደል? አዎ! በቃ! በቃኝ! በቃኝ! እንዴ ለምን ብዬ? ገባሽ?!›› አንዲት ጠይም ሎጋ በስልክ እየተነጋገረች ጋቢና ገብታ ሥፍራዋን ታደላድላለች። ‹‹እንዴት እንዴት ነው ነገሩ? ምኑን ነግራት ነው የሚገባት? ሳትናገር?›› ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየሙ አዛውንት በነገረ ሥራው ቁርጥ አምሳያቸው ወደ ሆነው ወጣት ዞረው ያፈጡበታል። ‹‹አባዬ ምናለበት በሰው ጉዳይ ባትገባ? ለምን ዝም አትልም?›› ይላቸዋል፡፡ ልጃቸው መሆኑ ነው። ‹‹ለምንድነው ዝም የምለው? እንዴት ያለ ነገር ነው እናንተ? ነገር ሳይብራራ፣ ሳይተረተር፣ ሳይመተር ‹ገባሽ፣ ገባሽ›፣ ‹ገባህ፣ ገባህ› ተብሎ ንግግር አለ እንዴ? ምን ይላል ይኼ እባካችሁ?›› ብግን ብለዋል አዛውንቱ።
‹‹በቃ! ሰው እንዳሻው የመናገር መብት አለው። አሁን እኮ ዘመኑ ተቀይሯል…›› ከማለቱ ቀልቡን ገፈፉት፡፡ ‹‹ተወኝ አላልኩህም አንተ ልጅ? ተወኝ ብያለሁ! እንዳሻን የመናገር መብታችን የተጠበቀው ወይም ሊጠበቅ የሚገባው እኮ ስለሐሳብ ደንታ ተብሎ ነው። ሐሳብን ምን ይሸከመዋል? ምን ብዬሃለሁ ደጋግሜ?›› ሲያፈጡበት ኃፍረቱ በአኳኋኑ የተገለጠበት ወጣት ‹‹ቋንቋ›› አላቸው። ‹‹አዎ! ቋንቋ ክብር ነው። ጌጥ ነው። ማንነት ነው። ሰው መሆን ነው አየህ። በተጣመመ አነጋገር ሐሳብ ምን ‹እኔ ነኝ› ቢል ግቡን አይመታም። ‹ከአነጋገር ይፈረዳል ከአያያዝ ይቀደዳል› ሲሉ አበው ለዚህ ነው አየህ . . . ›› ብለው ሳይጨርሱ፣ ‹‹ቢሆንም አንድ ሕዝብ እስከ ተግባባበት ድረስ ቋንቋን እንዳሻው መጠቀም መብቱ ነው። ደግሞ በባህሪው ቋንቋ ይወለዳል፣ ያድጋል…›› ብሎ ቢያቋርጣቸው፣ ‹‹ዝም በለኝ ብዬሃለሁ!›› ብለው አዛውንቱ ገነፈሉ። እንደ ቴአትር ተመልካች ተሳፋሪዎች በአባትና በልጅ ትዕይንት ተወስደዋል። ዘመን አካል ገዝቶ በሁለቱ በኩል ሙግት ይዟል። ረቺ የለም። ሙግት ብቻ ሆነ ነገሩ ሁሉ!
ጉዟችን ተጀምሯል። አዛውንቱ እንደ መቆዘም አድርጓቸው ሲያበቃ፣ ‹‹አሁን አንተ የእኔ ልጅ ነህ?›› ብለው ተመለሱ። ወጣቱ ማዶ ማዶ ያያል። ሁላችንም የገዛ ማዷችንን በዓይነ ገመድ እንመትራለን። ‹‹ምን አጠፋሁ? ‹በዛሬ ጊዜ ማንም ሰው ምንም ነገር ሲሉት አይወድም። ምክር እንኳ የተጠላበት ጊዜ ነው፣ አንደበትህን ቆጥብ› የምትለኝ አንተ እኮ ነህ፤›› ወጣቱ አባቱን በቃላቸው ሊያጠምድ ይከሳል። ‹‹ታዲያ የእኔ ቃል ዘለዓለማዊ መሰለህ የማይሻሻለው? ወይስ የእግዜር ቃል ሆነብህ? አሁን እስኪ ይታያችሁ (ወደ ጀርባቸው እየዞሩ) ‹አንድ ሕዝብ› ብሎ የቋንቋ አጠቃቀም አለ? አንድ አንድ ነው። ሕዝብ ሕዝብ ነው። አንድ ሕዝብ ያየኸው የት አገር ነው?›› ብለው ዘወር አሉ፡፡ በዚያ በኩል ንትርኩ ቀጥሏል፡፡
እዚያ … ጋቢና የተሰየመችው ጠይም፣ ‹‹ … እሱን እኮ ነው የምልሽ። ገባሽ አይደል? እኔማ እንደ ምንም ብዬ ይኼን ሱቅ እዘጋና ካልተገላገልኩ ምንም ‹ፒስ› የሚባል አይኖረኝም። በቃ ቁጭ ብዬ በወር ‹ላይክ› አንድ መቶ ሺሕ ብር ካገኘሁ ምን እፈልጋለሁ? ገባሽ?!›› ስትል ሁላችንም ሰማናት። አዛውንቱ የከበዳቸው ይመስል ፀጥ አሉ። ከጀርባ መካከለኛው ረድፍ አጠገቤ የተቀመጠ ቅልስልስ ወጣት፣ ‹‹እ? እ? ጆሮዬ ነው ወይስ ከምሯ ነው?›› ብሎ እንዳማከረችኝ ሁሉ ይጠይቀኛል። ከእኛ ጀርባ፣ ‹‹ጉድ ነው። መቶ ብር በቁጥጥራችን ሥር ማድረግ አቅቶናል፣ እሷ ተቀምጣ መቶ ሺሕ ብር መሸምጠጥ ያምራታል፤› ትላለች አንዲት ወይዘሮ። ‹‹ተቀምጣ ከሆነ የተመኘችው መርቅና ስለሆነ አትፍረዱባት…›› ይላል መጨረሻ ወንበር እግሩን ጎማው ላይ ሰቅሎ በየሰከንዱ የሚያፋሽክ መለሎ። ‹‹ታዲያ ግፍ አትፈራም እንዴ? ሰው አለ የለም አይባልም እንዴ?›› ባለ ሐምራዊ ሻሽ ቀዘባ ከጎኑ ተነሳችበት። ‹‹ቀምሰሽ እይው እንጂ ሌላ ምን ይባላል?›› ብሎ መለሎው ዝም አለ። በገሃድ ዓለም የተሸነፈ በምናብ ከመማለል ውጪ ሌላ ምርጫ የለው ለነገሩ!
ወይዘሮዋ በመስኮት አሻግራ የአገር ባህል ልብስ ቤት ታማትራለች። ‹‹አቤት ጥበቡ እንዴት እንደሚያምር ታየዋለህ ያን ቀሚስ?›› አለች ሳይታወቃት አጠገቧ የተቀመጠውን ጎልማሳ ጎሸም አድርጋ። ‹‹ማማርስ ያምር ነበር። ግን በጣም ሸነሸኑት…›› አላት። ‹‹እንዴት ይታይሃል ከዚህ? እኔስ ዓይኔ ደክሟል መሰል?›› ስትለው፣ ‹‹ልብ ላለው ሰው ጆሮም ዓይን ነበር፤› ብሎ መለሰላት። ‹‹ምነው ‹ነበር … ነበር …› አበዛህ?›› ስትለው ደግሞ፣ ‹‹ነው ከሞተ ቆየ!›› ብሏት ዝርዝር ብር ፍለጋ ኪሱን በረበረ። ወይዘሮዋ መልሱን ነገሬ ሳትል፣ ‹‹ባለፈው ምን የመሰለ የአገር ባህል ቀሚስ ልጄ ከቻይና ይዛልኝ መጥታ … አይጦች ተጫወቱበት። እኔ ቤት ያሉት አይጦች ደግሞ እንዲህ አይምሰሉህ አበዛዛቸው። ቻይናን ዓይተህ አይጦቹን ማየት ነው፤›› ብላ ሐሳብ ይወዝውዘኝ ስትል፣ ‹‹የቻይናን የሕዝብ ብዛት ማለትሽ ነው ወይስ ሰዎቹን?›› ብሎ አያያዛት።
‹‹ኧረ! ምን አደረግኩህ! ሰውን በአምሳሉ ፈጠረ የሚል መጽሐፍ እያነበብኩ አድጌ እንዴት ከአይጥ አመሳስላለሁ? እንዲያው ሌላው ቢቀር ማን ባቀናው መንገድ እንደምጓዝ ይጠፋኛል?›› እያለች ተርበተበተች። ጎልማሳው ቋጠሮውን ሲያጠብቅ፣ ‹‹አፍ ሲያመልጥ ራስ ሲመለጥ አይታወቅም ብዬ ነው እኔማ። ለማንኛውም ቤት ውስጥ አይጥ ሲበዛ ምቀኛ ነው ይባላል፤›› ከማለቱ አጠገቤ የተቀመጠው ወጣት ተጠምዞ፣ ‹‹መንገዱን ሲያጨናንቁትስ?›› ሲለው ‹‹ዘራፊ!›› ብሎ ሲመልስለት፣ ‹‹ካልክስ ኩራታችን፣ ሃይማኖተኝነታችን፣ ታሪካችን፣ አትንኩኝ ባይነታችን የተበጣጠሰው በዋነኝነት በሌላ በማን ይመስልሃል?›› ብሎ ተስተካክሎ ተቀመጠ። ተናጋሪው ሲተነፍስ ሰሚው ለሰማው ይቁነጠነጣል። ሀቁን ሳይውጡ መድኃኒት ቢውጡ ያሽር ይመስል፣ አለባብሶ አርሶ በአረም ለመመለስ ጉንጭ ማልፋቱም ይሰለቻል። ‹‹ለተግባራዊነት መዋጮ እንዳንጠየቅ እንጂ ሌላውስ ሌላ ነው…›› ይላል አንዱ ተሳፋሪ። ምን ይበል ታዲያ?
‹‹እንግዲያው መድኃኒቱን ለምን ከቻይና አናስመጣም?›› መጨረሻ ወንበር በወዲያ ጥግ የተቀመጠ አንዱ ሐሳብ አነሳ። ‹‹የምን መድኃኒት ነው ከቻይና የምናስመጣው?›› ጎልማሳው ጠየቀው። ‹‹በጫማ ጀምረውናል በመድኃኒት ይጨርሱን› ብሎ ነዋ?›› ብሎ ከጎኑ የተቀመጠ ወዳጁ አሾፈ። ‹‹እስኪ ዝም በል ሥራ እኮ ነው የያዝነው፤›› ብሎ ገሰፀውና ‹‹የአይጥ መርዝ ከቻይና ማስመጣት ይቻላል። ለምሳሌ እሳቸው ምን የመሰለ የባህል ቀሚሳቸውንን . . . አስቡት . . . . ከቻይና ድረስ ልጃቸው ይዛ መጥታ እንዳይሆን ያደረጉት በቤታቸው የመሸጉት አይጦች ናቸው። ስለዚህ . . .›› ሲል፣ ‹‹ነው እንዴ? እኔ ደግሞ ለፀረ ሌብነት መድኃኒት ከቻይና ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ እናጣቅስ ያልክ መስሎኝ አገሪቱ ጎለጎታ ስትሆን ታይቶኝ በርግጌ ነበር፤›› አለው ጎልማሳው። ‹‹ያማ የሰብዓዊ መብት አያያዛችንን ያስነቅፍብናል። እንዴ ምን ማለታችሁ ነው?›› ብሎ መለሎው ከእንቅልፉ ነቃ።
‹‹እኔም እኮ እሱን ነው የምለው። እንኳን ይኼ ተጨምሮባት አገሪቱ በሰብዓዊ መብት አያያዝ መወቀስ ልማዷ ነው። ምዕራባውያን ከሚቀየሙን ደግሞ ሌቦች ቢግጡን ምንም አይደል…›› ብሎ ከጎኔ የተቀመጠው ይጠቅሰኛል። ይኼኔ በዝምታ አደብ ገዝተው ተቀምጠው የነበሩት አዛውንት፣ ‹‹ምን ነበር ቅድም ስትይ የሰማሁሽ?›› ብለው አንገታቸውን እስኪያማቸው ተጠማዘው ወይዘሮዋ ላይ አፈጠጡ። ‹‹ምን አልኩ ጋሼ?›› አለች ለራሷ ሲፈጥራት ድንጉጥ ናት እንኳን አፍጠውባት። ‹‹ከቻይና ነው ልጅሽ የአገር ባህል ቀሚስ ይዛ የመጣችው?›› አስታወሷት የከነከናቸውን። ‹‹አዎ! ምነው?›› ብላ መቅለስለስ ስትጀምር፣ ‹‹እሱን ነው አይጥ የበጣጠሰው?›› የሚል ሌላ ማጣሪያ ጥያቄ አቀረቡ። አዛውንቱ ማጣሪያውን በአዎንታ ሲያልፉ፣ ‹‹ደግ አደረጉ!›› ብለው እርፍ። ‹‹ኧረ አይባልም!›› ሲል ልጃቸው ጥፊ ቃጡና ተገለገሉ። ‹‹እኚህን ሰውዬ ስኳር ወይ ደም ግፊት ሳይሆን የሚገድላቸው ገና ያልተነካው የግሎባላይዜሽን ጉድ ነው፤›› ሲሉ የምንሰማቸው መጨረሻ ያሉት የኢትዮ-ቻይና ጀማሪ ነጋዴዎች መሳይ ናቸው። እንዲያው ግን ሸማኔው ዜግነቱን በቃለ መሃላ ባስለወጠባት ምድር ሸማ ሸፈተ ተብሎ እሪ እንቧ የት ሊያደርስ ይሆን? ግራ ቢገባን ነው ለነገሩ!
ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። እነዚያ ጀማሪ መሳይ ነጋዴ ወጣቶች በአይጥ አሳበው በጀመሩት ወሬ፣ ‹‹ከቻይና ማንኛውንም ዓይነት ዕቃ በትዕዛዝ እናስመጣለን! ደውለን እጅ በእጅ እናስረክባለን!›› የሚል ካርድ በትነው ወረዱ። ‹‹ደረሰኝ አላችሁ?›› ብሎ ጎልማሳው ጠይቋቸው ነበር። ‹‹በሚቀጥለው ዙር እስከ ምንገናኝ ለዛሬ ደርሰናል…›› ብለው ያልተጠየቁትን ሲመልሱ፣ አዛውንቱ እንደተለመደው በቋንቋ አጠቃቀማቸው ወረፏቸው። እነሱን ተክተው ጥቂት የተጓዙት ተሳፋሪዎች ፀብ ግን ተበትነንም ከሐሳባችን አልጠፋም። ሲጀምሩ አንደኛው፣ ‹‹ምን ያጋፋሃል? ድንበርህን ብትጠብቅ ይሻልሃል…›› ማለት። ‹‹ማን ያሰመረው ድንበር ነው? ወንበር እኮ ነው…›› ብሎ ያ ማባባስ። ‹‹ምንድነው ሽብሩ?›› ብሎ ቁጥቡ ወያላ ሊገላግላቸው ወደ መጨረሻ ወንበር ሄደ። ‹‹አታየውም እንዴ እግሩን እላዬ ላይ ሰቅሎ?›› ይደነፋል ከሳሽ። ‹‹ወንበሩ ሰፊ ነው ደግሞ እግሩን አልጫነብህም፤›› ብሎ ወያላው ዓይቶ ፈረደ። ‹‹ለምን ይታከከኛል?›› ከሳሽ ነገር ነገር አለው። ‹‹ታክሲ ውስጥ ነው እኮ ያለኸው ወንድም። የግልህ ሊሞዚን አደረግከው?›› ተከሳሽ እያባባሰው ሄደ። ‹‹በቃ ወደ ግዛቴ አትምጣ ማለት አትምጣ ነው፤›› ከሳሽ ደረቅ ቢጤ ይመስላል። ‹‹ፌደራሊዝም ታክሲ ተሳፍሯል እንዴ?›› ትላለች ባለ ሻሿ። መለሎው፣ ‹‹ተይው ሰዓቱ ደርሶ ነው እንዲህ የሚሆነው፤›› እያለ ያዛጋል። ‹‹ታክሲያችን የዘመኑን የፌስቡክ አብዮተኞች አስንቆ የለ እንዴ?›› ይለኛል አጠገቤ የተቀመጠው፡፡ ምን ይበል ታዲያ?
‹‹ሲከር ይበጠሳል ተስማሙ እስኪ?›› ብለው አዛውንቱ መሸምገል ያዙ። ‹‹‘ፈርስት’ እሱ ሥርዓት ይያዝ፤›› አለ ከሳሽ። ‹‹አዛውንቱ ‘ፈርስት’ የሚባል አማርኛ የለም። በቅድሚያ አትልም?›› ብለው እንደለመዱት ሲጦፉ፣ ‹‹አማርኛ አፍ መፍቻ ቋንቋዬ እስካልሆነ ድረስ ‘I don’t care!’” ብሎ ጮኸባቸው። ይኼኔ እንዳቀረቀሩ ቀሩ። ወዲያው መውረጃችን ደርሶ ወያላው ‹‹መጨረሻ›› ሲለን አዛውንቱ ካቀረቀሩበት ቀና ብለው፣ ‹‹በላ ወንበርህን ይዘህ ውረድ፤›› አሉት ድንበር ድንበር ሲል የቆየውን። ይኼኔ አመዱ ቡን። አዛውንቱም፣ ‹‹ጊዜና ታክሲ የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር አንድ ቀን ፈልገን ሳይሆን፣ ሳንፈልግ ከተሳፈርንበት የምቾት ኮርቻ ላይ ማስወረዳቸው ነው። ስንሞት ሁሉ ቀሪ ነው። ስንኖር ግን ከተጋራነው መሬቱ፣ ሳሩ ቅጠሉ፣ እንስሳቱ ሁሉ ለእኛ ነው። እስኪ እንቻቻል፡፡ በድንበር፣ በክልል፣ በቀዬ… ተቀያይመን ስለኖርን በያዝነው ይዞታ አፈር አንቀበር። መሬቱስ ችሎናል ምናለበት እኛ ብንቻቻል?›› እያሉ በልጃቸው ተደግፈው ወረዱ። እየወረዱም፣ ‹‹እስኪ ከሁሉ በፊት ሰው መሆናችንን እናስቀድም፤›› እያሉ ማዝገም ሲጀምሩ እኛም ተከተልናቸው። ‘ሀቅን የመሰለ መድኃኒት እያለ የሐሰት ፈውስ ምን ሊረባ?’ የሚለው አባባል ትዝ አለኝ፡፡ አንዳንዴ መሀል መንገድ ላይ ቆመን ስንቆዝም ሰውና ፍትሐዊነቱ ግራ ያጋባናል፡፡ የዘንድሮም ሰው ነገር ይኼንን ይመስላል፡፡ መልካም ጉዞ!