በብሩክ አብዱ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን በፓርላማ ሲሰየሙ የተናገሩት ንግግር ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ትኩረት የሳበ ነበር፡፡ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት በብጥብጥ ስትታመስ የቆየችው አገር አዲስ ምዕራፍ ትጀምራለች የሚል ተስፋ በርካቶች እንዲሰንቁ ያደረገ ክስተትም ነበር፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሥልጣን እንዲለቁ ካደረጋቸው የሦስት ዓመታት ብጥብጥ ጀምሮ፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ስለአፍሪካ የሚከታተሉ ባለሙያዎች ዓይናቸውን ኢትዮጵያ ላይ ተክለው፣ ምን ሊከሰት እንደሚችል በጥሞና ሲከታተሉ እንደነበር ታይቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በበዓለ ሲመታቸው ወቅት በፓርላማ በአገሪቱ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ለውጦችን ለማምጣት ቁርጠኝነታቸውን ያሳዩበትን ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ እነዚህንም ለውጦች እጅግ አጭር በሚባል ጊዜ ውስጥ በተግባር ለማሳየት በርካታ ዕርምጃዎችን ወስደዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ሁናቴ እየተከታተሉ በተለያዩ መንገዶች ሐሳቦቻቸውን የሚገልጹ በዋናነት በአገሪቱ እየተካሄደ ስላለው ለውጥ፣ ፈተናዎችና የወደፊት አመላካቾችንና የሚጠበቁ ጉዳዮችን የሚመለከቱ አስተያየቶቻቸውን በተለያዩ ጊዜያት ሲሰጡ የተስተዋሉ ባለሙያዎች በርካቶች ናቸው፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መሪነት እየተካሄደ ስላለው ለውጥ
በመጋቢት ወር ወደ ሥልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር በመጀመርያዎቹ ሁለት ወራት ውስጥ ያከናወኗቸው ተግባራት፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ለኢትዮጵያ አዎንታዊ ምልከታዎች እንዲንፀባረቁ ያደረጉ ነበሩ፡፡
ለሮያል ዩናይትድ ሰርቪስስ ኢንስቲትዩት (ሩሲ) አስተያየት የጻፉት የሰላምና ደኅንነት ፕሮፌሰር የሆኑት አን ፊትዝ ጄራልድ ከመጋቢት ወር ጀምሮ ኢትዮጵያ ለየት ማለቷን፣ የኢንተርኔትና የማኅበራዊ ድረ ገጾች መከፈትና በአዲስ አበባ በካፌዎችና በምግብ ቤቶች ውስጥ የሚነፍሰው ንፋስ መልካም እንደሆነ አስፍረዋል፡፡ ይህም ይላሉ ጸሐፊዋ፣ አገሪቷን ለረዥም ጊዜ በመምራት ላይ ካለው ኢሕአዴግ ውስጥ የወጣ አዲስ መሪ በመምጣቱ ምክንያት ነው፡፡
በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን እንደመጡ የወሰዷቸው የካቢኔ ማዋቀርና እስረኞችን የመፍታት ዕርምጃዎች፣ በክልል ከተሞች እየተዘዋወሩ ንግግሮችንና ውይይቶችን በማድረግ ከክልል መንግሥታት ጋር ያላቸው ግንኙነት እንዲጠናከር ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውንና ይህም በርካቶችን ማስደሰቱን ያወሳሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል የገቧቸው ለወጣቶች ሥራ መፍጠር፣ የደኅንነትና የፍትሕ ዘርፍ ማሻሻያዎችን ማድረግ፣ ግልጽ የሆነና ብዝኃነትን የሚያስተናግድ ፖለቲካዊ ሥርዓት ማምጣት፣ ሙያዊ ብቃት ያላቸው የሲቪል ማኅበራትን ማጠናከርና ተዓማኒነት ያለው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዕውን ለማድረግ ቁርጠኝነት ማሳየታቸው ከፍተኛ ተቀባይነትን ያስገኙላቸው እንደሆኑ፣ ነገር ግን እነዚህን ጉዳዮች እንደሚያሳኩ ማመላከቻዎችን ግልጽ ማድረግ ላይ ፈተናዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይጠቁማሉ፡፡
በተመሳሳይ ለሲኤንኤን የጻፉት አወል አሎ የአገሪቱን ፖለቲካ ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ረገድና በሕዝብ ውስጥ ያለን እምነት ከመመለስ አኳያ በአገሪቱ የተደረጉ ለውጦች መኖራቸውን በመጥቀስ በተለይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ መደረጉ፣ በመንግሥት ይዞታ ሥር ያሉ ግዙፍ የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል እንዲዘዋወሩ መወሰኑና ከኤርትራ ጋር የነበረውን ጦርነት በይፋ ለማብቃት የአልጄርሱ ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲፈጻም መወሰኑ ዋነኞቹ ናቸው ሲሉ ያወሳሉ፡፡ በአገሪቱ የተደረገውን ለውጥም አስደናቂ ሲሉ ይገልጹታል፡፡
ስለኢትዮጵያ ተከታታይ አስተያየታቸውን ለኦፕን ዴሞክራሲ ድረ ገጽ የጻፉት ሬኔ ሌፎርት፣ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ በኢትዮጵያ አመራር ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ብዙ ነገሮች መቀያየራቸውን ያወሳሉ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የሚመራው መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ የተወሰዱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችና የሊበራል ባህርይ ያላቸው ለውጦች፣ የብዙኃን ኢትዮጵያውያንን አንገብጋቢ ጥያቄዎች የመለሱ ናቸው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
በነሐሴ ወር ‹‹የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ›› በማለት 19 ገጾች ያሉት ጽሑፍ በዓለም የሰላም ፋውንዴሽን አማካይነት ለንባብ ያበቁት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ባለሙያው አሌክስ ዲ ዋል በተመሳሳይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ የኢትዮያን የፖለቲካ ምኅዳር ለመቀየር ፈጣን ዕርምጃዎች መውሰዳቸውን ይጠቅሳሉ፡፡
ምንም እንኳን እነዚህ ባለሙያዎችና ጸሐፊዎች በኢትዮጵያ የሚታዩ ለውጦችን በአዎንታዊ ጎኑ የተመለከቱ ቢሆንም፣ በለውጦቹ ውስጥ የሚታዩ ሥጋቶችንና ፈተናዎችን ሳያነሱ አላለፉም፡፡
የሩሲ አስተያየት ዓምድ ላይ በጻፉት ጽሑፍ ላይ አን ፊትዝ ጄራልድ እንደጠቀሱት፣ የኢትዮጵያ ትልቁ ሥጋት የሆነው ኢኮኖሚው ቢሆንም፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚታዩ የፖለቲካና ብሔር ተኮር ክፍፍሎች ሌላ ፈተናን ሊደቅኑ የሚችሉ ናቸው፡፡
እንደ ጄራልድ ምልከታ የኢትዮጵያ ለውጥ ሦስት ፈተናዎች የተደቀኑበት ሲሆን፣ ለውጦቹን ተመዛኝ ማድረግና በግንባሩ ውስጥ ያለውን ልዩነት አሸንፎ ወጥቶ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ንቁ ተሳታፊ ማድረግም አንዱ ፈተና እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
በተመሳሳይ ለሲኤንኤን የጻፉት አወል አሎ እንደሚገልጹት፣ መንግሥት በኢኮኖሚው ላይ የያዘው ፖሊሲን በብቃት የማስፈጻም እክል ሊገጥመው ስለሚችል በተለይ ወደ ግል የሚተላለፉ ድርጅቶችን በተመለከተ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡
አሌክስ ዲ ዋል በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ለውጥ ላይ ጥያቄዎችን ያነሳሉ፡፡ የመጀመርያው ዕውን በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ለውጥ አጀንዳ ከአገሪቱ የመነጨ ነው? ወይስ ከሌላ ሥፍራ የመጣ ነው? በማለት ጥያቄ አቅርበው ለዚህም የአሜሪካንና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስን ይጠቅሳሉ፡፡
በመቀጠልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትኛውን የለውጥ ጎዳና ነው እየተከተሉ ያሉት ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ዕውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ለኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ የሆነ ዓላማ አላቸው ወይ የሚሉት ዲ ዋል፣ በለውጡ ውስጥ በሚከናወኑ ጉዳዮች ላይ ጠቅላላ እውነታዎችን ማገናዘብ ቢያስፈልግም፣ ኢትዮጵያን ለየሚመለከቱ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ልዩ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ሲሉም ያትታሉ፡፡
ሌላው ደግሞ ኢትዮጵያ አሁንም የልማታዊ መንግሥትን አቅጣጫ እየተከተለች ነው ወይ የሚለው ጥያቄ ሲሆን፣ በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ካሉ የግል ባለሀብቶች ተፅዕኖ ነፃ የሆነ መንግሥትና ኢትዮጵያ አሁን የደረሰችበት ታሪካዊ የሒደት ደረጃ ምንድነው የሚሉ ምልከታዎች የሚሰጡት ምላሾች፣ የመንግሥትን አቅጣጫ የሚያመላክቱ ናቸው ይላሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ለውጦቹን ተቋማዊ ማድረግ ላይ ፈተናዎች እንዳሉና ዘለቄታዊ እንደሚሆኑም አስተማማኝ ሁኔታ እንደሌለ ያወሳሉ፡፡
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ለውጥ ላይ ጥያቄያቸውን የሚያነሱት ሬኔ ሌፎርት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጀንዳቸውን ባላቸው ከፍተኛ ተቀባይነትና በጥቂት ታማኞች በመከበብ ብቻ ሊያሳኩ እንደሚችሉ ያምናሉ ሲል ይተቻሉ፡፡ ለውጡንም ከተቋማት በተላቀቀ መንገድ ማሳካት እችላለሁ ብለው ያስባሉ ሲሉ ያሰምራሉ፡፡
ሁለተኛው ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተከታታይ የወሰዷቸው የለውጥ ዕርምጃዎች በአገሪቱ መልካም የሚባል ነፋስ እንዲነፍስ ያደረገ ቢሆንም፣ እነዚህ የለውጥ ዕርምጃዎች ለሚያመጧቸው ውጤቶች በቂ ዝግጅት ሳይደረግና ውጤታቸውን ለመቆጣጠርም ብቁ ሳይኮን የተከናወኑ ናቸው ሲሉ ይተቻሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በአገሪቱ እየታየ ያለው ሰፋ ያለ ሕገወጥነት ትልቅ ፈተና እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ይህም መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም. የደመወዝ ጥያቄ አለን በማለት ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የተመሙት የመከላከያ ሠራዊት አባላት አካሄድ ጎልቶ የታየ መሆኑን በማውሳት፣ ሕገወጥነትና ሥርዓተ አልበኝነት ጥግ መድረሱን አመላካች ክስተት ነው ይላሉ፡፡
በአገሪቱ እየተስተዋሉ ያሉ በርካታ ግጭቶች በወሰንና በመሬት ይገባኛል ምክንያት የሚነሱ ሲሆኑ፣ አንዳንዴም በአካባቢ አመራሮች የሚቀሰቀሱና ለግል ጥቅሞች የሚቀለበሱ እንደሆኑ ሌፎርት ይተነትናሉ፡፡ ነገር ግን የእነዚህ ግጭቶች ዋነኛው መንስዔ የፀጥታ አስከባሪዎች በሚያሳዩት ቸልተኝነትና እስቲ የት እንደሚደርስ እንየው በሚል አስተሳሰብ የሚባባሱ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
በአገሪቱ እየተስተዋሉ ስላሉ የፀጥታ ችግሮች በሽግግር ወቅት እየተፈጠሩ ያሉ ናቸው በሚል በቸልታ ሊታዩ እንደማይገባ፣ ለሩሲ በጻፉት ጽሑፍ ያላካተቱት ፕሮፌሰር ጄራልድ ያስረዳሉ፡፡ በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ ባሉ ግጭቶችና ከግብፅ ጋር በዓባይ ውኃ ተጠቃሚነት ምክንያት ያለው ክርክር ለረዥም ጊዜ ተቀባይነት አግኝቶ የቆየው አካባቢያዊ ኃያላንን ሊፈታተን የሚችል ዲፕሎማሲያዊ ተግዳሮት ሊሆን እንደሚችል ይጠቅሳሉ፡፡
‹‹የፖለቲካው ጫጉላ አሁን አልቋልና አዲስ አበባ ያለው መንግሥት ከፊቱ ትልቅ የሚወጣው ተራራ ይጠብቀዋል፤›› ሲሉም የፈተናዎቹን ትልቅነት ያስገነዝባሉ፡፡
የትጥቅ ግጭቶች ሥፍራና ሁነት መረጃ ፕሮጀከት (The Armed Conflict Location and Event Data Project (ACLED)) በቅርቡ ባወጣው መረጃ መሠረት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ፣ በእሳቸው የሥልጣን ዘመን ከበፊቶቹ ጋር ሲነፃፀር የግጭቶች ቁጥር መጨመሩን በመግለጽ፣ በኦሮሚያ ክልል ሠልፎችና አመፆች ቢቀንሱም ለረዥም ጊዜ የቆዩ ግጭቶች መቀስቀሳቸውንና የእርስ በርስ ግጭቶች መበራከታቸውን ያመለክታል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወደ ሥልጣን መምጣት አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋትን ፈጥሯል ቢባልም፣ የግጭቶችና አመፆች ቁጥር በስምንት በመቶ መጨመራቸውን በማሳየት፣ ከስድስት ወራት በፊት 388 የነበረው የግጭቶች ቁጥር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመጡ በኋላ ባሉ ስድስት ወራት 420 መድረሳቸውን ይገልጻል፡፡
በሰኔ ወር የተስተዋለው አመፅ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተገናኘ እንደሆነ የሚገልጸው መረጃው፣ በፀጥታ ኃይሉና በሠልፈኞች መካከል የነበሩ ግጭቶች ግን በ56 በመቶ መቀነሳቸውን ያመለክታል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በብዛት ይስተዋሉ የነበሩ ብጥብጦች ሥፍራ መቀየራቸውን መረጃው ያሳያል፡፡ በዚህም ምክንያት ከአዲስ አበባ ዙሪያና ከኦሮሚያ ክልል ምዕራባዊ አካባቢ ብጥብጦች ርቀዋል፡፡ ግጭቶችና ብጥብጦችን ወደ ሶማሌ ክልል ከፍ ብለው መታየታቸውንም መረጃው ያመላክታል፡፡
ነገር ግን በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የአፋኝ ሕጎች ማሻሻያ ሒደት በአገሪቱ የሚስተዋሉ ብጥብጦችንም ሆነ ሥርዓተ አልበኝነትን ሊያስወግድ የሚችል ዕድል ሊፈጥር እንደሚችል፣ በኢትዮጵያ ኢንሳይት ድረ ገጽ ላይ አስተያየቱን ያሰፈረው ዊሊያም ዴቪሰን ይገልጻል፡፡ ይኼም ለነፃና ገለልተኛ ምርጫ ሜዳውን የሚያመቻች ዕርምጃ እንደሆነ ያስረዳል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተሸጋገረች እንደሆነች የሚናገሩት አሌክስ ዲ ዋል፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ውይይቶች በብዛት የተበታተኑ፣ ጽንፍ የያዙ፣ ትችትና ብሔር ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው ይላሉ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ እየተወሰዱ ያሉት የማሻሻያ ዕርምጃዎች፣ ያልታሰበ የፖለቲካ ገበያን በኢትዮጵያ ውስጥ ሊፈጥሩ ይችላሉ ሲሉ ያመላክታሉ፡፡
ምንም እንኳን ትችቶችና ሥጋቶችን ያንፀባረቁ አስተያየት ሰጪዎች ቢኖሩም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያዋቀሩት አዲስ ካቢኔ ግማሽ ያህሉ በሴቶች የተደራጀ በመሆኑ ዓለም አቀፍ አድናቆትን ያስገኘ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝን ጨምሮ በርካቶች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ካቢኔ ሴቶችን አሳታፊ ስላደረገ አድናቆታቸው ሲቸሩ ተስተውለዋል፡፡