Wednesday, March 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዕጩ ተወዳዳሪዎች ሚስጥር የሆኑበት የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫ ነገ ይካሄዳል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱን የንግድ ኅብረተሰብ በመወከልና ከሌሎች መሰል ተቋማት አንፃር በጥንካሬው የሚገለጸው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ነገ ጥቅምት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ አዳዲስ አመራሮችን የሚሰይምበት ምርጫ ያካሂዳል፡፡

በዚህ ምርጫ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ በፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩትን አቶ ኤልያስ ገነቲ በአዲስ ተመራጭ ይተካሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የምክትል ፕሬዚዳንትነት ቦታው በአዲስ ተመራጭ ይተካል አይተካም? የሚለው አነጋጋሪ ቢሆንም፣ ከምክትል ፕሬዚዳንቱ ውጪ እስካሁን ሲያገለግሉ በነበሩት የቦርድ አባላት ምትክ አዳዲስ የቦርድ አባላት ለማካተት ምርጫ ይካሄዳል፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ ለሪፖርተር እንዳስታወቀው፣ በድጋሚ መመረጥ የማይችሉት ፕሬዚዳንቱ እንጂ ምክትል ፕሬዚዳንቱ አይደሉም፡፡

ከምርጫው ቀደም ብሎ የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫውን ለማስፈጸም ያግዛሉ ያላቸውን ኮሚቴዎች ማዋቀሩንና ወደ ሥራ መግባታቸው መገለጹም አይዘነጋም፡፡ በተለይ ንግድ ምክር ቤቱን በፕሬዚዳንትነትና በቦርድ አባልነት የሚያገለግሉ ዕጩዎችን በመመዘን ተወዳዳሪዎችን የመለየት ሥራ የተሰጠው የምርጫ አመቻች ኮሚቴ፣ ከንግድ ኅብረተሰቡ የተጠቆሙትን የመጨረሻ ተወዳዳሪዎች መርጦ ያጠናቀቀ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይሁንና ነገ ጥቅምት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. የሚካሄደው ምርጫ ላይ ለፕሬዚዳንትነት እነማን ተጠቆሙ? የቦርድ አባል ሆኖ ለማገልገል እነማን ተለዩ? የሚለው ግን ሚስጥር እንዲሆን መደረጉ እያነጋገረ ነው፡፡

የንግድ ኅብረተሰቡን የሚመሩትን ዕጩዎች ቀድሞ በማወቅ ለምርጫው መዘጋጀት ሲገባ ንግድ ምክር ቤቱ ዕጩዎቹን ሚስጥር ማድረጉ አግባብ እንዳልሆነ ያነጋገርናቸው የንግዱ ኅብረተሰብ አባላት እየገለጹ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን እንደሚተጋ ቢያስታውቅም፣ የዕጩዎችን ማንነት ቀድሞ ባለማሳወቁ ግን የምርጫውን ዴሞክራሲያዊነት ይጋፋል የሚል አስተያየትም ያክላሉ፡፡

እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ከዚህም ቀደም ሲተገበር እንደነበር ያወሱት እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች፣ ዕጩዎችን የመመዘንና ለውድድር እንዲቀርቡ የማድረግ ኃላፊነት የተሰጠው የምርጫ አመቻቺ ኮሚቴም ሆነ የንግድ ምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ዕጩ ተወዳዳሪዎችን ቀድሞ ለማሳወቅ አለመፈለጉ ግልጽ አይደለም ብለዋል፡፡ በዘንድሮው ምርጫ ዴሞክራሲያዊነትን ሊያጎሉ የሚችሉ እንዲህ ያሉ አሠራሮች ይተገበራሉ ብለው ጠብቀው እንደነበር የገለጹት አስተያየት ሰጪዎች፣ አሁንም በተመሳሳይ መንገድ ምርጫውን ለማካሄድ መዘጋጀቱ ላይ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡

የዕጩ ተወዳዳሪዎቹ ማንነት ቀድሞ ቢገለጽ የንግድ ኅብረተሰቡ ሊመርጠው የሚችለውን መለየትና አስተያየት ለመስጠት ያስችላል የሚል እምነት እንዳላቸው በማመልከትም፣ ዕጩዎችን ቀድሞ ለማሳወቅ ፈቃደኛ ያለመሆናቸው የምርጫ ሒደቱን አሁንም ጥርጣሬ ላይ ሊጥለው ይችላል ይላሉ፡፡ አንድ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ነው ከተባለ አንዱ መገለጫ ተወዳዳሪዎችን ቀድሞ በማሳወቅ አስተያየት እንዲሰጥባቸው ማድረግ ነው በማለትም ተናግረዋል፡፡ እንደውም እያንዳንዱ ተወዳዳሪ ለንግድ ምክር ቤቱ ምን እንደሚሠራ ጭምር መከራከር ሲኖርበት፣ ጭራሽ ማንነታቸው ከምርጫው በፊት አይገለጽም መባሉ አግባብ አይደለም ተብሏል፡፡ ከዚህ ቀደም ምክር ቤቱን ለመምራት በተደረጉ ምርጫዎች በተለይ በፕሬዚዳንትነትና በምክትል ፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩ ዕጩዎች ቀድመው ራሳቸውን በማስተዋወቅ ያደርጉ የነበረው ውድድር ጠንካራ መሪ ለማግኘት ዕድል የሰጠ መሆኑን በማስታወስ፣ አሁንም እንዲሁ መደረግ እንደነበረበት ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ተመራጮችን በተመለከተ እየተነሳ ያለውን አስተያየት ተከትሎ ሪፖርተር መረጃ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡

ሆኖም ለዚህ ምርጫ ተጠቋሚዎችን በመሰብሰብ ለውድድር የሚያበቃውን መሥፈርት መሟላት አለመሟላቱን የመለየት ኃላፊነት የተሰጠው የምርጫ አመቻች ኮሚቴ አንድ አባል ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኮሚቴው በተሰጠው መመርያ መሠረት የዕጩዎችን ማንነት መግለጽ የማይችል መሆኑን ነው፡፡ ‹‹በተሰጠን ኃላፊነት መሠረት የዕጩዎችን ማንነት ይፋ የምናደርገው ምርጫው በሚካሄድበት ዕለት ለጠቅላላ ጉባዔው  ብቻ ነው፤›› በማለትም የዕጩዎችን ማንነት ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የምርጫ አመቻች ኮሚቴው ለፕሬዚዳንትነትና ቦርድ አባልነት የሚወዳደሩ ዕጩዎችን ለይቶ የያዘ መሆኑ ግን ተረጋግጧል፡፡

እስካሁን በፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ኤልያስ ገነቲ መጀመርያ የተመረጡት ታኅሰስ 10 ቀን 2006 ዓ.ም. ነበር፡፡ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡ ደግሞ አቶ ታደሰ መሸሻ (ከዘርፍ ማኅበራት በቀጥታ የተወከሉ ነበር) በቦርድ አባልነት ደግሞ ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ (አትሌት)፣ አቶ ሞላ ዘገየ፣ አቶ አፈወርቅ ዮሐንስ፣ አቶ ገሠሠ ተሾመ፣ አቶ ኃይሌ አሰግዴ፣ አቶ ሁንልኝ ጥጋቡ፣ አቶ ፍሰሃ ሻንቆ፣ አቶ ፋሲካው ሲሳይና አቶ ያረጋል ገሠሠ ነበሩ፡፡ ሆኖም ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴና አቶ ኃይሌ አሰግዴ ከቦርድ አባልነታቸው በፈቃዳቸው ለቀዋል፡፡

ታኅሳስ 10 ቀን 2006 ዓ.ም. የተመረጡት እነዚህ የንግድ ምክር ቤቱ አመራሮች ወደ አመራር የመጡበት ሒደት የምክር ቤቱን ሕገ ደንብ ያከበረ አይደለም የሚል  ክስ ቀርቦባቸው፣ ምርጫውና በዕለቱ የተላለፈው የጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ እንዲሻርና ድጋሚ እንዲካሄድ በፍርድ ቤት ተወስኗል፡፡ በዚህ የፍርድ ቤት ውሳኔ መሠረት ንግድ ምክር ቤቱ ድጋሚ ምርጫው እስኪያካሂድ በባለአደራ ቦርድ እንዲመራ እንዲደረግ መደረጉ አይዘነጋም፡፡ ባለአደራ ቦርዱም በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሠረት ምርጫው ሲካሄድ አቶ ኤልያስ ድጋሚ ተመርጠው እስካሁን ቆይተው ነበር፡፡ ከቀድሞ የቦርዱ አባሎቻቸው የተወሰኑትን ይዘው ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች