Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያን የቡና አምራችን በዓለም ገበያ ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ ተስፋዎች 

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከፍተኛ የግብይት ድርሻ የያዘው የቡና ምርት፣ በአፍሪካ እንኳ ለሚሊዮኖች መተዳደሪያና የገቢ ምንጭ በመሆን የበርካታ ቤተሰቦችን የዕለት ኑሮ ለመምራት አስችሏል፡፡ ይሁንና ከሚመረተው አብዛኛው ቡና፣ ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚለውም በዚያው መጠን ከፍተኛ በመሆኑ በዓለም ገበያ ሊገኝ ይችል የነበረውን ገቢ አነስተኛ ሲያደርገው ይታያል፡፡ ለአብነትም በአፍሪካ ከ11 ሚሊዮን ኬሻ (ኬሻ 60 ኪሎ ግራም ይመዝናል) በላይ ቡና ከሁለት ዓመት በፊት ተመርቶ ለፍጆታ የዋለ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከ3.7 ሚሊዮን ኬሻ በላይ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተጠጣ የቡና መጠን እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ከእነዚህ መረጃዎች መካከል ሰሞኑን ይፋ የተደረገው የተመድ ሪፖርት ይጠቀሳል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጀት የንግድና የልማት ጉባዔ፣ ‹‹ኮሞዲቲስ አት  ግላንስ›› በተሰኘው ልዩ ዕትሙ በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ላይ ያነጣጠረ የቡና ግብይት ላይ የተመረኮዘ ሪፖርት ከቀናት በፊት ይፋ አድርጓል፡፡ ሪፖርቱ ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ስለመሆኗ በይፋ ዕውቅና በመስጠት በተለይም የአረቢካ ቡና የሚባለውንና ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለውን የቡና ዝርያ ለዓለም ያስተዋወቀችው ኢትዮጵያ ስለመሆኗ በመዛግብት የተደገፈ ማስረጃ እንዳለ በመጥቀስ አስፍሯል፡፡ የኢትዮጵያ አራቢካ ቡና እ.ኤ.አ. ከ500 ዓመታት እስከ 1,500 ዓመታት በፊት ከኢትዮጵያ ወደ የመን ማቅናቱን የሚጠቁመውና ተመድ ዋቢ ያደረገው የቡና ታሪክ፣ ከዚያም ወደ ምዕራብ እስያ ብሎም ወደ አውሮፓ በተለይም ወደ ኔዘርላንድስ እ.ኤ.አ. በ1616 እንዲሁም ወደ ህንድ በ1660 በማቅናት፣ ወደ ኢንዶኔዥያም በ1690 ጀምሮ እንደተስፋፋ ሪፖርቱ አውስቷል፡፡ ሮቡስታ የሚባለው የቡና ዓይነትም ከመካከኛው አፍሪካ ወደ ፈረንሣይ እ.ኤ.አ. በ1890ዎቹ ከዚያም ወደ አሜሪካና ወደ እስያ በ1900 መጀመሪያ እንደተስፋፋ ያትታል፡፡ 

በጽሑፍ የሠፈሩ መረጃዎችን ዋቢ እንዳደረገ የሚጠቅሰው ተመድ፣ የኢትዮጵያ አራቢካ ቡና ወደ የመን የተስፋፋው የምዕራብ እስያ አምራቾችም ሆኑ የሂንዱ ነጋዴዎች ስለቡና ከማወቃቸው ቀድሞ እንደነበር አስፍሯል፡፡ በፍጥነት ወደ ዓለም የተዳረሰው የኢትዮጵያ ቡና፣ ዕውቅናና ተፈላጊነቱ እያየለ ቀስ በቀስ ወደ መካ መዲና፣ ካይሮ፣ ከዚያም ወደ ኢስታንቡል ማቅናቱም በታሪክ ተመዝግቦለታል፡፡ ወደ የመን ከሄደው የኢትዮጵያ ቡና በመነሳት የመኖች በ18ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ገደማ ከ12 ሺሕ እስከ 15 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ቡና ማምረት ስለመቻላቸውም ተመዝግቦ ይገኛል፡፡

እንዲህ የተዛመተው የኢትዮጵያ ቡና ለኢትዮጵያውያን አሁንም ቢሆን ባለውለታነቱን ቢያረጋግጥም፣ ካለው ሰፊ ሀብትና ተፈላጊነት አኳያ ግን አምራቾችን በተለይ ብዙም ተጠቃሚ እንዳላደረጋቸው ይታያል፡፡ ከ20 እስከ 25 ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ በቡናና ከቡና ጋር በተያያዘ እንቅስቃሴ ተጠቃሚ በሆነባት ኢትዮጵያ ውስጥ ቡና አንድ ሦስተኛውን የወጪ ንግድ ገቢ በማስገኘት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ይህም ማለት አገሪቱ ከምታስገባው የሦስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ የወጪ ንግድ ገቢ ውስጥ፣ ከቡና ወደ 900 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ዓመታዊ ገቢ እየተገኘ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ በዚህም የአገሪቱን 40 በመቶ የወጪ ንግድ ሸቀጥ ድርሻ ቡና ስለመያዙ ተመድ አስፍሯል፡፡ ይሁንና የወርቅ፣ የአበባ፣ የጨርቃ ጨርቅና የቆዳ ውጤቶች የወጪ ንግድ ድርሻ እየጨመረ በመምጣቱ የቡና የወጪ ንግድ ድርሻ እየቀነሰ መምጣቱ ይታወቃል፡፡ ምንም እንኳ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሥነ ምኅዳር ለቡና ምርት የተመቸ እንደሆነ ቢነገርም፣ ዋና ዋና ቡና አብቃይ ከሚባሉት አካባቢዎች ማለትም ሐረር፣ ሲዳማ፣ ይርጋ ጨፌ፣ ሊሙ፣ ጅማ፣ በበቃ ቴፒ፣ ጊምቢ ለቀምቴ በብዛት የሚታወቁና የንግድ ምልክት ያገኙ የቡና ዝርያዎች መገኛ አካባቢዎች ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ከሚመረተው ቡና ውስጥ አሥር በመቶው የጫካ ቡና እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህም በደን ውስጥ የሚበቅልና በአብዛኛው የተናጠል ባለቤትነት የሌለው የወል ቡና ሊባል የሚችል ነው፡፡ ይህ የቡና ምርት ኢትዮጵያን በዓለም ብቸኛዋ የጫና ቡና አምራች የሚል ስያሜ ያተረፈላት ሲሆን፣ ከፊል የጫካ ቡና ወይም በተወሰነ ደረጃ ገበሬዎች ክብካቤ የሚያደርጉለት ቡናም የኢትዮጵያ የቡና ምርትና አመራረት ጠባይ መገለጫ ነው፡፡ ይህ ቡና 35 በመቶውን አጠቃላይ የቡና ምርት ይዘት እንደሚሸፍን ይታመናል፡፡ በአነስተኛ ገበሬዎች ማሳ የሚመረተው ሌላኛው ቡና 45 በመቶውን የአገሪቱን የቡና ምርት መጠን ሲሸፍን፣ በሰፋፊ እርሻዎች የሚመረተው የቡና መጠን ከጠቅላላው የቡና ምርት ውስጥ የአሥር በመቶ ድርሻ እንደሚይዝ ይታመናል፡፡

ከ90 በመቶ በላይ የቡና ምርት በአነስተኛ ገበሬዎች፣ በአብዛኛው ከአንድ ሔክታር ያነሰ የመሬት ይዞታ ባላቸው አምራቾች የሚመረት በመሆኑም አገሪቱ በቡና ምርትና አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ እንዳደረገ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

የዓለም ዋና ዋና ቡና ገዥ ከሆኑት አምስት ትልልቅ ኩባንያዎች አንዱ የሆነው ስታር ባክስ፣ ለኢትዮጵያ ቡናዎች ዕውቅናና የንግድ ምልክት በመስጠት የኢትዮጵያን የቡና ባለቤትነት መብት ላለማክበር ከተከራከረባቸው ምክንያቶች አንዱና ዋናው የአገሪቱ የቡና ምርት እምነት የሚጣልበት ባለመሆኑ እንደሆነ ኃላፊዎች ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡ በአብዛኛው በአነስተኛ ገበሬዎች ማሳ የሚመረተው ቡና ከአገሪቱ ፍጆታ አልፎ ለዓለም ገበያ በሚበቃ መጠን ልክ እነ ብራዚል፣ ኮሎምቢያና ቬትናም እንደሚያመርቱት ከፍተኛ የቡና ምርት መጠን ለዓለም ገበያ ማቅረብ አለመቻሏ ኢትዮጵያን ተጎጂ እንዳደረጋት ስታር ባክስ ሲከራከር ቆይቷል፡፡ ይህ መከራከሪያው እውነትነት የሚኖረው ደግሞ በርካታ የቡና እርሻዎች የቡና ዋጋ አላዋጣ በሚልበት ወቅት ወደ ሌሎች ሰብሎች እንዲቀየሩ ሲደረግ መለያየቱ ነው፡፡ በርካታ የቡና ማሳያዎች በዚህ ወቅት አዋጭ በሆኑ የሰብል ምርቶች ማለትም በቅባት እህሎች አለያም እንደ ጫት ባሉ ምርቶች ሲተኩ መታዘብ ተችሏል፡፡

መንግሥት ለቡና ዘርፍ በተለይም ግብይቱን በተመለከተ ይታዩበት የነበሩ ችግሮችን ለማስተካከል በርካታ ዕርምጃዎች ሲወስድ ቢቆይም፣ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ ዋጋ ወሳኝ ለመሆን በርካታ ምዕራፎች ይቀሩታል፡፡ ባለሙያዎችም ሆኑ የተመድ ሪፖርት የሚጠቅሱት አገሪቱ የቡና ምርቷን ለማሻሻል የቡና እርሻዎችን ማስፋፋት እንደሚገባት ነው፡፡ በተለይም ሰፋፊ የቡና እርሻዎች አሁን ከሚገኙበት የአሥር በመቶ ድርሻ ቢያንስ እስከ 30 በመቶ ከፍ እንዲሉ ማድረግ ለአገሪቱ የቡና ምርትም ሆነ የወጪ ንግድ ድርሻ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ሐሳባቸውን ያሠፈሩ አሉ፡፡    

ይህም ሆኖ ኢትዮጵያ ከዓለም ዋና ዋና የቡና አምራች አገሮች ዘንድ በአሥረኛ ደረጃ ላይ ተመድባለች፡፡ ከ590 ሺሕ ሔክታር ያላነሰ መሬትም ለቡና ተክል ስለማዋሏ መረጃዎች ይመሰክራሉ፡፡ 50 አገሮችን የሚያዳርሰው የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ፣ በጥራት ችግሮችም ስሞታ ይቀርብበታል፡፡ በአብዛኛው የኢትዮጵያን የቡና ጥራት እየተፈታተኑ እንደሚገኙ ከሚነገርላቸው መካከል ተባይና የቡና ተክል በሽታ፣ የአየር ጠባይ መለዋወጥ፣ የግብርና ክህሎትና ዕውቀት ውስንነት ብሎም በቡና የምርት ሰንሰለት ውስጥ የሚሳተፉ አካላት የሚታይባቸው አስተዳደራዊና ተቋማዊ ችግሮች ለቡና ጥራት ዝቅተኛ መሆን ተወቃሽ ናቸው፡፡ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ እንደ ሐረር ያሉ አካባቢዎች ቡና አብቃይነታቸው ከነጭራሹ ሊያከትም የሚችልባቸው ለውጦች እየታዩ ስለመሆኑ ሮያል ሶሳይቲ የተሰኘው የእንግሊዝ የሳይንስ ጥናትና ምርምር ተቋም ከሁለት ዓመት በፊት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ 

ከተፈጥሮና ከበሽታ ችግሮች ባሻገርም ለኢትዮጵያ የቡና ጥራት መዳከም ጣት ሲቀሰርባቸው ከቆዩ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አንዱ ነው፡፡ በተመድ ሪፖርትም ምርት ገበያው ከምሥረታው ጀምሮ ከመንግሥት እርሻዎች፣ ከትልልቅ የግል እርሻዎችና የኅብረት ሥራ ማኅበራት ውጭ ያሉ ላኪዎች በቀጥታ ለዓለም ገበያ እንዳይሸጡ የሚከለከል አሠራር በመዘርጋት ላኪዎች በግብይት ማዕከሉ በኩል እንዲስተናገዱ ማስገደዱ አነስተኛ አምራቾች ከተጠቃሚዎች ጋር በቀጥታ ግብይት የሚፈጽሙበትን ዕድል በማሳጣት ጭምር ከጥራት ባሻገር የግብይት ችግር ማስከተሉ ሲያስተቸው ቆይቷል፡፡ ሆኖም ይህ አሠራር ማሻሻያ ተደርጎበት ካለፈው ዓመት ጀምሮ ላኪዎች በቀጥታ መላክ የሚችሉበት አሠራር መዘርጋቱ ይታወሳል፡፡

ምንም እንኳ ኢትዮጵያ እንደ ቡና መገኛነቷ በየቀኑ ከ500 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ከሚጠጣው ቡና የምታገኘው ተጠቃሚነት ዝቅተኛ መሆኑ ሲዘገብ ቢቆይም፣ ለኢትዮጵያ ቡና በመልካም አጋጣሚነት ከሚጠቀሱ ጉዳዮች መካከል የልዩ ጣዕም (ስፔሻሊቲ) ቡናዎች ተፈላጊነት እየጨመረ መምጣት ኢትዮጵያን በተለየ መንገድ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋት ይታሰባል፡፡ ኢትዮጵያ ካላት ተፈጥሯዊ የቡና አብቃይነት ስጦታ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የልዩ ጣዕም ቡናዎች መገኛ መሆኗ ሲሆን፣ በተመድ ሪፖርት መሠረት ሁለት ሦስተኛው የአገሪቱ የቡና ዝርያዎች በልዩ ጣዕም ቡና ለመመደብ የሚያበቃቸው ተፈጥሯዊ ይዘት አላቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ቡና የተፈጥሮ ወይም ‹‹ኦርጋኒክ›› ደረጃን የሚያሟላ ከመሆኑም ባሻገር ከ90 በመቶው የአገሪቱ ቡና ዝርያዎች በተፈጥሮ ቡናነት የሚመደቡ በመሆናቸው ለኢትዮጵያ ቡና ሰፊ የገበያ ዕድሎች እንዳሉ ተመድ አስፍሯል፡፡ በዓለም የቡና ገበያ ውስጥ ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ሊያደርጋት የሚችለው ሌላው መልካም አጋጣሚ በታሪክ ኢትዮጵያ የቡና መገኛ መሆኗ፣ ‹‹ኮፊ›› የሚለው የቡና መጠሪያ ምንጩም የኢትዮጵያ የከፋ አካባቢ መሆኑ በራሱ አዳዲስ ገበያዎችን ለማዳረስ ምቹ ዕድል ከሚሰጧት መካከል ይመደባሉ፡፡

ይህም ሆኖ በዓለም የቡና ግብይት ሰንሰለት ውስጥ ከ28 ሺሕ በላይ የቡና መደብሮችን በመክፈት የተንሰራፋውን ስታር ባክስን ጨምሮ፣ የዓለምን 40 በመቶ የቡና ንግድ የተቆጣጠሩት አምስት ዋና ዋና ኩባንያዎች መሆናቸው ግን እንደ ኢትዮጵያ ላሉና 70 በመቶውን የዓለምን የቡና ምርት ለሚያቀርቡ አነስተኛ ገበሬዎች የእኩል ተጠቃሚነት ጉዳይ ተራራን የመግፋት ያህል ከባድ እንደሚሆን ይታመናል፡፡ ይህንን አባባል የሚያጠናክረው እውነታ በዋቢነት በተመድ ሪፖርት ቀርቧል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2011 ወደ ውጭ የተላኩት የኢትዮጵያ የልዩ ጣዕም ቡናዎች (ይርጋ ጨፌ፣ ሲዳማና ሐረር ቡናዎች) የነበራቸውን የእሴት ሰንሰለትና የግብይት ሒደት በሚያስቃኘው ትንታኔ መሠረት ለኢትዮጵያ ገበሬዎች ሲደርሳቸው የቆየው አማካይ ጥቅል ገቢ 2.8 በመቶ እንደነበር ያሳያል፡፡ የላኪዎች የትርፍ ህዳግ 1.96 በመቶ፣ የትራንስፖርትና የቡና ማቀነባበሪያ ወጪ 20 በመቶ፣ የቡና መፈልፈያና የወጪ ንግድ ወጪዎች 0.5 በመቶ ሲሆን፣ የቸርቻሪ ነጋዴዎች የትርፍ ህዳግ በአንፃሩ 48 በመቶ ሲሆን፣ ቡና ቆልተው የሚያዘጋጁ ኩባንያዎች የትርፍ ህዳግም 15 በመቶ ገደማ ሆኗል፡፡ በመሆኑም በየመደብሩና በየሱፐር ማርኬቱ ቡና የሚቸረችሩ ኩባንያዎች ከፍተኛ የቡና ጥቅም አጋባሾች  በመሆን የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች