Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የሻንጣ ሌቦች ስልታቸውን በመቀያየር ተጓዦችን የሚዘርፉበት መንገድ ተባብሷል ተባለ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ከውጭ ወደ አገር ቤት የሚመጡ መንገደኞችን በመጠባበቅ የትራንስፖርት አገልግሎት ወይም ትብብር ለመስጠት በማስመሰል የተጓዦችን ሻንጣና ሌሎች ንብረቶችን የሚዘርፉ ሌቦች ለመቆጣጠር ጥረት ቢደረግም፣ ዘራፊዎች በየጊዜው ስልታቸውን እየቀያየሩ መምጣታቸው አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የኢትዮጵያ የኤርፖርቶች ድርጅት ገለጸ፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ኃላፊዎች እንዳሉት ከሆነ፣ በኤርፖርት አካባቢ የትራንስፖርት አገልግሎት በሕጋዊ መንገድ ተደራጅተው የሚሠሩት የታክሲ ማኅበራት በተባራሪ ሌቦች የተነሳ ስማቸው መጥፋቱ እንደሚያሳስባቸው ለድርጅቱ እየገለጹ ነው፡፡

የሻንጣ ሌቦች በተለይ ከዓረብ አገሮች ተመላሽ ሴት ተጓዦች ላይ በዋነኛነት በማነጣጠር የስርቆት ወንጀሉን እየፈጸሙ ሲሆን፣ ለዚህ የስርቆት መባባስ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ ጉዳዮች መካከል ወንጀለኞቹ ከተያዙ በኋላ የሚተላለፍባቸው የሕግ ቅጣት አነስተኛ መሆን ተጠቃሽ እንደሆነ ምንጮች ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጀት የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ወንድም ተክሉ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ድርጅታቸው ከታክሲ ማኅበራት፣ ከፀጥታ ተቋማትና ከሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ጋር በየጊዜው እየተመካከሩ የሌቦችን መንገድ ለመዝጋት ቢሞክሩም፣ በየጊዜው ስልታቸውን እየቀያየሩ ዘረፋውን ቀጥለዋል፡፡

በተለይ በከተማ ውስጥ ብቻ አገልግሎት መስጠት የሚጠበቅባቸው ባለታክሲዎች ኤርፖርት ድረስ በመምጣት ተጓዦችን በአነስተኛ ዋጋ እንደሚያደርሱዋቸው በማግባባት እንዲሁም ስልክ በማስደወል የሚተባበሩ በመምሰል እየዘረፉ መሆኑን አቶ ወንድም አስረድተዋል፡፡

በመደበኛነት የታክሲ ትራንስፖርቱን አገልግሎት መስጠቱ ሥራም የሚከናወነው በባለ ቢጫ ታክሲዎች ቢሆንም፣ ዋጋቸው ከመደበኛ ታክሲዎች ታሪፍ ከፍ ያለ በመሆኑ ተጓዦች ለዋጋ ቅናሽ ሲሉ የከተማ ታክሲዎችን በሚመርጡባቸው ጊዜ ለዝርፊያው እንደሚጋለጡ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

ለዚሁም በቅርቡ በተደረገ የጋራ ምክክር ጉባዔ ላይ የታክሲ ማኅበራትም ሆኑ ባለንብረቶቹ የዋጋ ማስተካከያ ለማድረግ ፍላጎት ማሳየታቸው፣ ችግሩን ለመቅረፍ ከሚረዱ መፍትሔዎች አንዱ ሊሆን እንደሚችል አቶ ወንድም ገልጸዋል፡፡

ተደራጅተው ከኤርፖርቶች ድርጅት ዕውቅና አግኝተው በጋራ እንደሚሠሩ የሚናገሩ ባለታክሲዎች በበኩላቸው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከከተማ በሚመጡ ተባራሪ ታክሲዎችና በግብረ አበሮቻቸው የሚፈጸሙ ዝርፊያ የእነሱንም ስም እያጠፋው መሆኑ አሳስቧቸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ ወንጀሉን ከምንጩ አድርቀናል ብሏል፡፡  የፖሊስ ኮሚሽንና የከባድ ወንጀል መርማሪ የሆኑት ኮማንደር ዓለማየሁ አያልቄ በአካባቢው ሲዘርፉ የኖሩት ሕገወጦች በአብዛኛው ማረሚያ ቤት እንደሆኑና ዋና ምንጫቸውን ማድረቃቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም አብዛኛው ዘራፊዎች ከመያዛቸው ባሻገር የዘረፏቸው ዕቃዎችና ንብረቶቻቸው በሕግ ተወርሰው በኤግዚቢትነት መያዛቸውን አመልክተዋል፡፡

መርማሪው ይህን ይበሉ እንጂ ሪፖርተር በአውሮፕላን ማረፊያው አካባቢ በመዘዋወር ያናገራቸው የታክሲ አሽከርካሪዎችና በዚያው አካባቢ በሥራ ላይ የሚገኙ ታዛቢዎች እንደገለጹት፣ ከዓረብ አካባቢ በሚመጡ ሴቶች ላይ የሚፈጸመው ዝርፊያ እየተለመደ መምጣቱንና ሌሎችም የራሳቸውን ኔትወርክ ዘርግተው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ ዋና መርማሪው ግን አለ የተባለውን ኔትወርክ መኖሩን የሚያሳይ ነገር እስካሁን አለማየታቸውን ገልጸው፣ ሊኖር የሚችል ከሆነም ዕለት ከዕለት የፀጥታ ኃይሎች እንደሚከታተሉት ጠቁመዋል፡፡

ሰኔ 3 ቀን 2008 ዓ.ም. ረፋድ ላይ መገናኛ አካባቢ ዝርፊያ ተፈጽሞባት ስታለቅስ አግኝቶ ሪፖርተር ያነጋገራት ወጣት ሴት ስሟን መጥቀስ ባትፈልግም፣ ቅዳሜ ጠዋት ለአራት ዓመታት በሳዑዲ ዓረቢያ በቤት ሠራተኝነት ስታገለግል ቆይታ መምጣቷን ገልጻለች፡፡ ከአውሮፕላን ወጥታ ሻንጣዋን በመያዝ የምትጠብቀውን ዘመዶቿን በመፈለግ ላይ እንዳለች አንድ ወጣት ጠጋ ብሎ ምን ልርዳሽ ብሎ እንዳነጋገራትና ዝርፊያውን የመፈጸም ሒደቱ እንደተጀመረ አመልክታለች፡፡

የሚቀበላትን ሰው እየፈለገች መሆኑን ስትነግረው ስልክ ልደውልልሽ በማለት ሊተባበራት እንደሚፈልግ ከገለጸላት በኋላ የስልክ ቁጥሩን መዝግቦ በተንቀሳቃሽ ስልኩ ደውሎ ያገናኛታል፡፡ ነገር ግን ደውሎ ያገናኛት ሰው መኪና እንደላከላትና አሽከርካሪውም ወደ ቤት እንደሚያመጣት ይነግራታል፡፡ የተነገራት አሽከርካሪም ወዲያው ከደረሰ በኋላ ሁለት ትላልቅ ሻንጣዎቿን በመጫን የመኪናውን ሞተር አስነስቶ ወሰደኝ በማለት ትገልጻለች፡፡

ነገር ግን ይኼው አሽከርካሪ ከዓረብ ተመላሽ መንገደኞች ካርድ መቁረጥ እንዳለባቸው እንደነገራትና ከዚያም መገናኛ አካባቢ ወደሚገኘው የውልና ማስረጃ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ወስዷት ሰልፍ እንድትሰለፍ፣ ከዚያም እንደሚጠብቃትና ቆርጣ እንድትመጣ ይነግራታል፡፡ ነገር ግን ከደቂቃዎች በኋላ እንደተሰወረባት በእንባ እየታጠበች ስልክ በመደወል እንደተባበራት በገለጸችው ሰውና በአሽከርካሪው ሙሉ ዕቃዋን መሰረቁን ገልጻለች፡፡

ተጎጂዋ ለሪፖርተር እንደገለጸችው በሁለቱ ሻንጣዎች ውስጥ በርከት ያሉ አልባሳት፣ ጫማዎች፣ አራት ስማርት ፎን የሞባይል ቀፎዎችና ከ2,700 ሪያል (15,650 ብር) በላይ ገንዘብ ጨምሮ መዘረፉንና ባዶ መቅረቷን አስረድታለች፡፡

ስልክ በማስደወል ሊተባበሩ የሚችሉ በማስመሰል ተጓዦችን የሚዘርፉ ሌቦች በተደጋጋሚ ማስተዋላቸውን ያረጋገጡት የኤርፖርቶች ድርጅት ኃላፊው ነገሩን ለመቅረፍ ተጓዦች ከአውሮፕላን እንደወጡ ነፃ የስልክ አገልግሎትና ሲም ካርድ በቀጥታ በግዢ የሚያገኙበትን መንገድ ለማቅረብ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች