‹‹የመከላከያ ሠራዊታችን ቀጣይ ዕርምጃም በኤርትራ መንግሥት ቀጣይ እንቅስቃሴ የሚወሰን መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ የኤርትራ መንግሥት ካለው ባሕሪ አንፃር ጉዳዩን ከማባባስ የማይቆጠብ ከሆነ፣ የመከላከያ ሠራዊታችን ተመጣጣኝና አስተማሪ ቅጣት በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል ይሆናል፡፡››
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት፣ የኤርትራ መንግሥት ትንኮሳን
አስመልክቶ ሰኔ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. ከሰጠው መግለጫ የተወሰደ፡፡ ጽሕፈት ቤቱ በመግለጫው እንዳመለከተው፣ የኤርትራ መንግሥት እሑድ ሰኔ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠዋት፣ በጾረና ግንባር ጥቃት ለመሰንዘር በመሞከሩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በወሰደው የአጸፋ ዕርምጃ፣ የኤርትራ ጦር ጥቃት የማድረስ አቅም በከፍተኛ ሁኔታ እንዲዳከም ተደርጓል፡፡ ኤርትራ ከሩብ ክፍለ ዘመን በፊት ከኢትዮጵያ ተገንጥላ ሉአላዊ አገር ከሆነች ከሰባት ዓመት ቆይታ በኋላ፣ ሁለቱ አገሮች ከ1990 ዓ.ም. እስከ 1992 ዓ.ም. ድረስ በድንበር ሰበብ ከባድ ጦርነት አካሂደው እንደነበር ይታወሳል። በጦርነቱም የ70 ሺዎችን ሕይወት መቅጠፉ ይነገራል።